ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ኢሳያስ ” በሽታ የለብኝም… የለመድኩት ወሬ ነው “

 “ እኛ ተመስገን ብለን አስራ ሁለት ሰዓት ስንተኛ፣ ውሸታሞቹ ሃያ ሶስት ሰዓት ከሃምሳ ዘጠኝ ደቂቃ እንቅልፍ የላቸውም ”

እንደተለመደው በቀላል አለባበስ አደባባይ ወጥተው “ እድለኛ ነኝ፣ በሽታ የለብኝም፣ በሽታው ወሬው ነው ” በማለት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፉወርቂ ሲወራባቸው ለነበረው ሁሉ ምላሽ ሰተዋል። ፕሬዚዳንቱ ለERI – TV ለሰላሳ ደቂቃ በሰጡት  መግለጫ ሞተዋል፣ በጠና ታመዋል፣ አይተርፉም በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ የለመድኩት ወሬ ነው፤ ፊትም አልሰጠሁትም ” በማለት ሲወራባቸው የነበረውን ሁሉ በዜሮ አባዝተውታል።

ኤፕሪል 28/ 2012 በአስመራ አቆጣጠር 8 pm ላይ መግለጫ የሰጡት አቶ ኢሳያስ ይህ ሁሉ ሲወራባቸው ለምን ምላሽ እንዳልሰጡ ለተጠየቁት ሲመልሱ የሰጡት ምላሽ ግልፅ ባይሆንም ባለፈው ሳምንት አገር ቤት እንዳልነበሩ አላስተባበሉም። ስሙን ካልጠቀሱት የሄዱበት አገር ሲመለሱ ጋሽ ባርካን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የፕሮጀክቶች ጉብኝት ላይ ነበሩ። አስራ አራት ሰዓት ያለማቋረጥ ጉዞ እንዳደረጉ ያመለከቱት አቶ ኢሳያስ፣ ረጅም ሰዓታት በድካም መተኛታቸውን አስረድተዋል።

ከዚያም እንቅልፉ ሳይለቃቸው የፕሬስ ፀሃፊያቸው ከሰጠቻቸው ወረቀቶች ላይ ስለሳቸው ሲወራ የነበረውን መመልከት እንደቻሉ ተናግረዋል። “ሞባይል የለኝም፤ ኢንተርኔትም አልጠቀምም ” የሚሉት አቶ ኢሳያስ የተወራውን ሁሉ እንደንፋስ እንደሚቆጥሩት አስምረውበታል። ውሸት በተወራ ቁጥር ቴሌቪዥን ላይ በመውጣት ማስተባበያ መስጠት እንደማይቻል በመጠቆም የተወራባቸውን ክፉ ወሬ ያመከኑት ፕሬዚዳንቱ “ እኛ ተመስገን ብለን አስራ ሁለት ሰዓት ስንተኛ፣ ውሸታሞቹ ሃያ ሶስት ሰዓት ከሃምሳ ዘጠኝ ደቂቃ እንቅልፍ የላቸውም ” ብለዋል።

“ አሁን ” አሉ አቶ ኢሳያስ “ አሁን ውሸቱ ሁሉ አርጅቷል። አልቋል ” የኤርትራ ህዝብም ሆነ በውጪ አገር ያሉት ተረጋግተውና  በየሚሰሙትን ሁሉ እንደማስታወቂያ ባለመቀበል ህይወታቸውን እንዲመሩ ጥሪ አቅርበዋል። እስካሁን ለምን ዘገዩ በሚል ለተጠየቁት ውሸታሞች የሚሉዋቸው  ራሳቸውን እንዲያስተካክሉ እድል ለመስጠት በማሰብ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ስለ እሳቸው መጥፎ ሲወራ አስር ዓመት በላይ መቆየቱን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ መንግስት ቢቀየር ፖለቲካው አንድ አይነት መሆኑን፣ የሚቀየር ነገር ቢኖር የፖለቲካው ገጽ እንደሆነ አመላክተዋል። “ ሁልጊዜ አንድ እብድ ወይም ውሸታም በተናገረ ቁጥር የቴሌቪዥን መስኮት ላይ እየቀረቡ መናገር ቁብ እንደሌለው ደጋግመው ተናግረዋል።

አሜሪካ ውሽጥ ያለ አንድ የሽያጭ ሰራተኛ ለገበያ ለማቅረብ  ያሰበውን እቃ እንዴት እንደሚያስተዋውቅና የተጠቃሚዎችን አዕምሮ በማሳመን  እንዴት እንደሚሸጥላቸው እንደሚያስብ ሁሉ፤ ዝም ብሎ እንደሚነፍስ ንፋስ የተሰየሙት ውሸታሞች የመገናኛ ቴክኖሎጂን በተሳሳተ መንገድ በመጠቀም የስነልቦና ጦርነት ማካሄዳቸውን ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል። በዚሁ መነሻ አሉ የሚባሉት ታላላቅ አገሮች ቴክኖሎጊን ህዝብ ለማስጨነቅ፣ ለመረበሽና ለማደናገር  እንደሚጠቀሙበት አመልክተዋል።

የጠጣርና የፈሳሽ ቸኮሌት ማስታወቂያ በመመልከት የቱ ይጠቅመናል ብለው ሳያስቡ መጎምጀት እንደማይጠቅም አቶ ኢሳያስ የተናገሩት ወደፊት ብዙ ይወራልና የምትሰሙትን ሁሉ አትመኑ የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነበር። ስምንትና ዘጠኝ ታላላቅ አገራት ውስጥ  “ ዴሞክራሲ ተብዬ ”  እንጂ እውነተኛ የሰው ልጆች መብት አንደማይከበርባቸው ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ አገራቱ ከወታደራዊ በጀታቸው በላይ የስለላ በጀታቸው እጅግ የናረ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደሚፈለገው እድገት ባይመዘገብም አሁን ያለው ጅምር አበረታች መሆኑን መላልሰው የጠቀሱት አቶ ኢሳያስ እንዲህ ያለው ወሬ ለምን እንደተወራባቸው፣ ምንጩ ከየት እንደሆነ፣  የሚያወሩት ሰዎች፣ ….የማወቅ ፍላገት እንዳላቸው አቶ ኢሳያስ አልሸሸጉም። አያይዘውም  የወሬው መነሻ ምክንያት ግልፅ እንዳልሆነላቸው ገልፀዋል።

በመግለጫቸው ማንንም በስምም ሆነ በድርጅት ደረጃ ጠርተው ለጉዳዩ ተጠያቂ ሳያደርጉ መግለጫ የሰጡት አቶ ኢሳያስ ህክምና ስለማድረጋቸውም ሆነ፣ አለባቸው ስለተባለው ህመም አንድም የተናገሩት ነገር የለም። የሳቸው መግለጫ እንዳበቃ በኢትዬጵያ መንግስት የሚደገፈውና ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጋር ሰዓት ተጋርቶ ዝግጅት የሚያቀርበው ዳሃይ ኤርትራ በፕሮግራም ለኤርትራ ህዝብ ጥሪ አቅርቧል።

የፕሬዚዳንት ኢሳያስን የጤና መጓደል በተመለከተ “ አጋጣሚውን በመጠቀም አዲሲቷን ኤርትራ ለመመስረት እንነሳ ” ሲል ለወታደሮችና ለህዝቡ ጥሪ አቅርቧል።

በትናንትናው እለት የኤርትራ ጀነራሎች አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ የስራ ክፍፍል ማድረጋቸውንና የፕሬዚዳንቱ ጤንነት የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን ያስታወቀው ከፈረንሳይ የሚተላለፈው ERENA ኢሬና ራዲዮ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አደባባይ ወጥተው መግለጫ ስለመስጠታቸው  ያቀረበው  አስተያየት የለም። ዜናውንም አላስተባበለም።

ኢሬና ራዲዮ ጁላይ 15/2009 ከኤርትራ በተሰደዱ ጋዜጠኞች የተቋቋመና በሪፖርተር ዊዝ አውት ቦርደርስ የሚታገዝ፣ በኤርትራ ያለውን የፕሬስ ነፃነት ለማመጣጠን የሚሰራ ሚዲያ ነው።