“Our true nationality is mankind.”H.G.

ኢህአዴግ “Vacation” ላይ ሳይሆን አይቀርም!

ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ የተወሰደ

SATURDAY, 03 MARCH 2012 15:07

 ኤሊያሰ

“የልማት ሠራዊት ስንጠብቅ የሙስና ሠራዊት ተፈጠረ”

የአድዋን በዓል በተመለከተ ከጓደኞቼ ጋር ጨዋታ ተነሳና አንድ ወዳጃችን “ዘንድሮ፤ አድዋ ሳይሆን ባይዶዋ ነው!” አለችን፡፡ (ወይ ግራ መጋባት!) ገብቷችኋል አይደል… ባይዶዋ ያለችው እኮ ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን በሶማሊያ ባይዶዋ ከተማ በአልሸባብ ላይ የተቀዳጀውን ድል ለመጥቀስ ፈልጋ ነው፡፡ እሱስ ባልከፋ ነበር፡፡ ችግሩ ግን… አድዋ ሌላ ባይዶዋ ሌላ! የሚያመሳስላቸው ነገር አለ ከተባለ ምን መሰላችሁ… ሁለቱም የእኛ ድል መሆናቸው ብቻ ነው፡፡ ለማንኛውም ግን እንኳን ለ116ኛ የአድዋ ድል በዓል አደረሰን፡፡ (ጣልያንን አይመለከትም!)ይሄን የአፄ ምኒልክንና የእቴጌ ጣይቱን ዘመን አስደናቂ ድል ሳስብ አንድ ጥያቄ ወደ አዕምሮዬ መጣብኝ፡፡ እኔ የምላችሁ… በምኒልክ ዘመን “ኪራይ ሰብሳቢ” ነበረ እንዴ? መልሱን ወደኋላ ላይ ጠብቁኝ፡፡

ሰሞኑን በኢቴቪ “ፊት ለፊት” የተሰኘ ፕሮግራም ላይ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ፤ የቢፒአርን አሳዛኝ “ሽንፈት” በተመለከተ የሰጡትን ቃለምልልስ ተከታትላችኋል? እንኳንም አመለጣችሁ! (ካመለጣችሁ ማለቴ ነው) እንዴ… ቁጭትና መብሰክሰክ ምን ይጠቅማችኋል? ሃቁን ለመናገር ግን… ይሄን BPRን በተመለከተ አንድ ያልገባኝ ነገር አለ፡፡ BPR ከሽፏል ከተባለ የሥራ ሂደት ኃላፊዎች እስካሁን “ወንበራቸው” ላይ ምን ይሰራሉ? መሰረታዊ የሥራ ሂደት ሳይኖር የሥራ ሂደት ኃላፊዎች ያስፈልጋሉ እንዴ? (የሎጂክ ጥያቄ ነው!)

አቶ ጁነዲን ሳዶ ቢፒአርን የተካውን “የዜጐች ቻርተር” ባለፈው ሰሞን “ሲያስመርቁ” መሰረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ በመንግስታዊ ተቋማት ዓላማውን እንደሳተ ጠቁመው ቢፒአር እንዴት እንደተሰናከለ ሲያብራሩም፤ “አመለካከቱ ያልተቀየረ ሠራተኛ መሰረታዊ የሥራ ሂደቱን ከሰራሁ መምሪያ ኃላፊ እሆናለሁ፤ መኪና ይሰጠኛል፤ ደመወዝ ይጨመርልኛል፤ ጥቅማ ጥቅም አገኛለሁ” ብሎ የሚያስብና ተልእኮውን ወደ ጐን በመተው ለግል ጥቅም የሚሽቀዳደም ነበር” ብለዋል (ወይ ነዶ!) እኔ ግን ምን አሰብኩ መሰላችሁ? “መኪናውም ተሰጥቶት፣ ደመወዙም ተጨምሮለት ቢፒአሩ ግቡን ቢመታ ይሻለን ነበር!” አሁን ግን ቢፒአሩም አልተሳካ፣ ጊዜና ሃብትም በከንቱ ባከኑ! (አናሳዝንም?)

እንግዲህ እንደታዘብኩት ወይም ደግሞ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ እቺን አገር አላላውስ ብለው አንቀው የያዙዋት ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው (ልብ አድርጉ! በጥናት ግን አላረጋገጥኩም!) እኔን ካላመናችሁኝ ግን የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩን በምስክርነት እጠራለሁ፡፡ “ለውጡ መልካምና ብዙ ተስፋ የተጣለበት ቢሆንም፤ መንገዱን በመሳት ለኪራይ ሰብሳቢዎች አገልግሏል” ብለዋል አቶ ጁነዲን ስለ BPR ውልደትና ህልፈት ሲናገሩ፡፡ እናም ጠ/ሚኒስትሩ እንዳሉት ቀንደኛ ጠላቶቻችን ሙሰኞች ወይም ኪራይ ሰብሳቢዎች መሆናቸው መቶ በመቶ ተረጋግጧል፡፡ (ከሽብርተኞችም በላይ!) እናም እኔ ምን አሰብኩ መሰላችሁ? የፀረ-ኪራይ ሰብሳቢነት ዘመቻ ለመጀመር! ከምሬ እኮ ነው… ኪራይ ሰብሳቢዎች እኮ እቺን አገር እያተራመሱዋት ነው፤ ልማትዋንም እያደናቀፉ ናቸው (ይሄም በጥናት አልተረጋገጠም)

ቆይ ግን… የሊዝ አዋጅ ሲወጣ “የከተማ ጫጫታ” የፈጠረው ማነው? ኪራይ ሰብሳቢዎች! መንግስት በሙስና “እንዲጨማለቅ” ያደረገው ማነው? ኪራይ ሰብሳቢዎች! (ወይም የመንግስትና የግል ሌቦች) በ97 ምርጫ ኢህአዴግ ላይ ናዳ ለመልቀቅ አሲረው የከሸፈባቸው እነማን ነበሩ? ኪራይ ሰብሳቢዎች! ቢፒአሩን ያከሸፈውስ? አሁንም ኪራይ ሰብሳቢዎች!

አያችሁ… የልማታዊ መንግስታችንና ፓርቲያችን ቀንደኛ ጠላት ኪራይ ሰብሳቢዎች ናቸው የተባለው ያለምክንያት አይደለም፡፡ በዚህ አካሄዳቸው ደግሞ ቢፒአርን በማክሸፍ ብቻ ይመለሳሉ ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ (ያደቆነ ሰይጣን… ይባል የለ) ስለዚህ ልማት፣ ትራንስፎርሜሽን፣ መካከለኛ ገቢ፣ ባለሁለት ዲጂት የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የዜጐች ቻርተር ወዘተ የሚለውን ለጊዜው እርግፍ አድርገን ትተን ኪራይ ሰብሳቢዎችን በቅድምያ እንዋጋ!! (እዬዬ ሲዳላ ነው አሉ!)

በነገራችን ላይ ስሜታዊ ሆኜ እንዋጋ አልኩ እንጂ እንዴት እንደምንዋጋው ሃባ ሃሳብ የለኝም፡፡ (መዋጋት በሚለው ግን አምናለሁ!)

ለነገሩ ኢህአዴግ እንኳን እፍኝ የማይሞሉ ኪራይ ሰብሳቢዎችን ግዙፉን ደርግ ገርስሶ የለ! (ዛሬ ሳይሆን ከ20 ዓመት በፊት) እናም የውጊያ ስትራቴጂውንም ለእሱ ትቼለታለሁ (ለአውራው ፓርቲያችን!) ደግሞም እኮ ኪራይ ሰብሳቢን የፈጠረው ራሱ ኢህአዴግ ነው (የግል ኪራይ ሰብሳቢዎችን ማለቴ ነው?) ስለዚህ በዚህም በዚያም ብሎ መዋጋትም ይሁን ማጥፋት ያለበት ራሱ ኢህአዴግ ይመስለኛል! (ለኪራይ ሰብሳቢ መቼም ሰላም አስከባሪ ሃይል አንጠራም!!)

የBPR መክሸፍ ያብሰከሰከኝ ሳያንስ ሰሞኑን ደግሞ አገሪቱ በሙስና ሠራዊት ተጥለቅልቃለች የሚል ቃና ያዘለ ወሬ ሰማሁኝና በደም ግፊት ተጥለቀለቅሁ! እናንተ… ኢህአዴግ የልማት ሠራዊት እንጂ የ”ሙስና ሠራዊት” እፈጥራለሁ ብሏል እንዴ? (እኔ በበኩሌ አልሰማሁም!)  “የሙስና ሠራዊት” መፈጠሩን ያወቅሁት መቼ መሰላችሁ? የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት ዓለም አቀፍ ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ (አቦይ) ስብሃት ነጋ፤ ህዝቡ በጠቅላላ በሙሰኞች ላይ እንዲዘምት መጠየቃቸውን ስሰማ ነው (85 ሚ. ህዝብ ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ውስጥ ሊቀጠር ነው እንዴ?) እስቲ አንዲት ገራገር ጥያቄ ልጠይቃችሁ፡- ኢህአዴግን የመረጥነው ምን እሰራላችኋለሁ ብሎን ነው?” (ግራ ገብቶኝ እኮ ነው!)

አቦይ ስብሃት ስለሙስና ከተናገሩት ትንሽ የገረመኝ ምን መሰላችሁ? ሙስናን ከነፍጠኛ ሥርዓት ጋር ማያያዛቸው ነው! “ነፍጠኞች በሰባራ ነፍጥ ነበር ህዝቡን የሚዘርፉት፤ አሁን ደግሞ ወንበር ላይ የተቀመጠ ባለስልጣን ነው ሕዝቡን እየዘረፈ ያለው” ብለዋል – አቦይ ስብሃት፡፡ (የነፍጠኞች ስርዓት ተረት አልሆነም እንዴ?)

አሁን ተፈጠረ ለተባለው የሙስና ሠራዊት ያለፉትን ስርዓቶች ምርር አድርገው የወቀሱት አቦይ ስብሃት፤ ያለፉ ስርዓቶች ሰርቶ መብላትን ሳይሆን፣ ሰርቆና ዘርፎ የመብላት ባህል ትተው መሄዳቸውን፣ ይሄ ደግሞ በህዝቡ ውስጥ ሰርፆ እንደ ባህል እየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡ ቆይ ግን… ደርግን “ያለፈው ሥርዓት” እያልን የምንጠራው ስንት ዓመት በ”አምባገነንነት” ገዝቶን ከሄደ በኋላ ነው? ካልተሳሳትኩ 17 ዓመት ይመስለኛል፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ “ህዝብ እየመረጠው” ስንት ዓመት ገዛን? አሁንም ካልተሳሳትኩ 20 ዓመት አልፎታል!! (ጊዜው እንዴት ይሮጣል ባካችሁ!)

እንግዲህ በደርግ የሥልጣን ዘመን ስሌት ካየነው ኢህአዴግም “ያለፈው ስርዓት” በሚለው ጐራ ለመፈረጅ ደርሷል ማለት ነው! (እንደውም 3 ዓመት አልፎታል እንጂ!) እናም ከዚህ በሁዋላ ጥፋቶቹንና ስህተቶቹን ባለፉ ሥርዓቶች ባያላክክ ይሻለዋል (ትዝብት ላይ እንዳይወድቅ ብዬ ነው) አያችሁ… 17 ዓመት የገዛው ደርግ “ያለፈው ስርዓት” ከተባለ 20 ዓመት የገዛውም ኢህአዴግ ያለፈው ስርዓት መባሉ አይቀርም! (የሎጂክ ጥያቄ ነዋ!)

አቦይ ስብሃት ስለ ሙስና ከተናገሩት ሁሉ አንጀቴን ያራሰኝ የቱ እንደሆነ ታውቃላችሁ? “በኢትዮጵያ በተጨባጭ ያለውን ሙስና ለማጥፋት ፍላጐት እንጂ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ብሎ ነገር የለም፡፡ … ቁርጠኛ ሌባ አለ፤ ቁርጠኛ ተዋጊ ግን የለም፡፡” (ቁርጠኛ መሪስ?!) በነገራችን ላይ አቦይ ስብሃት ፀረሙስና ኮሚሽንንም አልማሩትም፡፡ ኮሚሽኑ በከፍተኛ ሙሰኞች ላይ እየዘመተ አይደለም ሲሉ በደንብ ወቅሰውታል፡፡ እኔ የምለው ግን… አሁን እነዚህ ሁለቱ የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች እንዲህ አብጠልጥለው የሚተቹት የራሳቸውን ፓርቲና መንግስት  ይመስላል? (ግልፅነታቸው አስቀናኝ!) ይሄን ዓይነቱን ትችት የሰነዘሩት እነ “መድረክ” ወይም “ኢዴፓ” አሊያም “አንድነት” ወይም ደግሞ የ97ቱ “ቅንጅት” ቢሆኑ ኖሮ እኮ ብዙም ባልገረመን ነበር፡፡ ተቃዋሚዎች ድሮም ሥራቸው ገዢውን ፓርቲ መተቸት፣ መንቀፍ፣ ማብጠልጠል፣ ማሳጣት፣ ወዘተ ብለን እናልፋቸው ነበር፡፡ ግን ኢህአዴግ ኢህአዴግን እንዲህ አፈር ድሜ ሲያስበላው ብንደነግጥ ወይም “አዋቂ ቤት” ጐራ ብንል ይፈረድብናል?  ሌላው የሚገርመው ደሞ ምን መሰላችሁ? ሁለቱ አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ ባጠቃላይ ኢህአዴግም ሆነ መንግስት ችግር ባጋጠመው ቁጥር አግዙኝ እያለ የሚማጠነው እኛን መሆኑ ነው – (ህዝቡን!!) አቦይ ስብሃት ሙስናን ለማጥፋት ህዝቡ ወሳኝ ሚና እንዳለው ሲገልፁ፤ “ህዝቡ በሙሰኞች ላይ ለመዝመት እምቅ ሃብት ነው፣ መዝመት አለበት” ብለዋል፡፡ አቶ ጁነዲንም ቢፒአር የከሸፈው ህዝቡ ስላልተሳተፈበት ነው ካሉ በኋላ በአዲሱ “የዜጐች ቻርተር” ግን ህዘቡ ቀጥተኛ ተሳታፊ ይሆናል ብለውናል፡፡ (እቺ ዳር ዳር…አሉ!) እውነቱን ልንገራችሁ አይደል…ኢህአዴግ ይሉኝታ ይዞት ነው እንጂ  እቺን አገር ብቻዬን መምራት ስላቃተኝ አግዙኝ እያለን ነው (የግል ግንዛቤዬ ነው!) እኛ በበኩላችን ደስ ይለን ነበር – ኢህአዴግን አገር በመምራት ብናግዘው፡፡ ችግሩ ግን አገር ለመምራት የተመረጠው ኢህአዴግ ነው (ያውም በዝረራ!)፡፡ ስለዚህ ብንፈልግም እንኳ ልንረዳው አንችልም (አልተመረጥንማ!) ይልቅ ተቃዋሚዎችን አግዙኝ ቢል ያዋጣዋል፡፡ እንዴት ቢባል…በ97 ምርጫ ህዝብ ስለመረጣቸው ኢህአዴግን አገር በመምራት ቢያግዙት ችግር የለውም! (የህዝብ ድምፅ ኤክስፓየርድ ያደርጋል እንዴ?) በዚህ ካልተስማማ ግን ህዝብ በመምራት ለታወቀ ዓለም አቀፍ የውጭ ኩባንያ በኮንትራት ይስጠንና በቅጡ እንመራ! (እንደ ኢትዮ – ቴሌኮም)

የመጨረሻ ጥያቄ ላቅርብ – ይሄ ሁሉ ሙስና፣ ይሄ ሁሉ የኑሮ ውድነት፤ ይሄ ሁሉ የዋጋ ግሽበት፣ ይሄ ሁሉ የትራንስፖርት ችግር፣ ይሄ ሁሉ ፍትህ ማጣት ወዘተ የተከሰተው ኢህአዴግ “ቬኬሽን” ወጥቶ ይሆን እንዴ? (የ20 ዓመት ዕረፍት ማለቴ ነው) በሥራ ላይ እያለማ እንዲህ መከራ ስንበላ አስችሎት ዝም አይለንም ነበር!! (ኧረ ከእረፍት ቶሎ ይመለስልን!)

እኔ የምለው ግን ኢህአዴግ እረፍት ሲወጣ ባዶ ቤት (ባዶ አገር) ጥሎ ከሚሄድ ለምን ለተቃዋሚዎች አደራ ሰጥቶ አይሄድም? ወይስ ለአደራም አያምናቸውም? (እንደስልጣኑ!) በነገራችሁ ላይ እኔም “ቬኬሽን” ልወጣ አስቤአለሁ – ቻይናን ለመጐብኘት!!

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0