በወሬው ደንግጦ፣ ሰው ሲል ‘ወየው ወየው’፣
ሁሉም ሲተራመስ…ወዳጁን ሲጠራ፣ እኔስ ‘እጅጋየሁ’!
***
ትፈቺያለሽ ብለው ቆመው ሲጠብቁ፣
ባንድ ‘ዜ ኮብልለሽ፣ ውሽሞችሽ ሳቁ፤

                ***
አባቴ ሲጠሩስ… ነገር ጠረጠረ፣ ልቤ ፈራ ተባ፣
ከሰማዩ በላይ፣ እንዳለ በዓለ-ንገስ፣ እንዳለ ስብሰባ፤
***
አይደለም በእጅዎ፣ አይደለም ባይንዎ፣
አይደለም በዘውድዎ፣ በካባ በሀውልትዎ፣
  በአንገት መቁጠሪያዎ፣ በግርማ ሞገስዎ፣
  እኔስ ማስታውስዎ፣
__ በየደብሩ ባለው፣ የቁም ስቅ(ዕ)ልዎ!
***
ድጓ ፆመ ድጓ ተሰቅሎ ከቤቴ፣
ላወርደው ብሞክር፣ አጠረ ቁመቴ፣
አወይ አለማወቅ፣ አወይ ሞኝነቴ፣
አዋራጅ ፈልጌ፣ አባቴን ማጣቴ!
/ዮሐንስ ሞላ/

 የአገራችን ነገር አሳሰበኝ። አስደነገጠኝ። ምን እየሆነና ወዴት እያመራን እንደሆነ ሊገባኝ አልቻለም። ከቀን ወደ ቀን የሚሰሙትና የሚከናወኑት ነገሮች ልብ ያውካሉ። ገዢዎቹም ተቃዋሚዎቹም የደነገጡ አይመስልም። አገሪቱ ከታመመች ቆየች። በድሃ ህዝቦች ጉሮሮና ደረት ላይ ሃብትና ንብረት ካፈሩ ስግብግቦች በስተቀር የአገሪቱ ራስምታት ለሁሉም የሚሰማ ነው። በድህነቱ ብቻ ብንታመም መልካም ነበር። አሁን እየባሰበት ያለውና  የልብ ምታችንን የጨመረው  የጎሰኛነትና የዘር ፖለቲካው በሚያስከትለው መዘዝ ላይ የሃይማኖቱ ጣጣ መደረቡ ነው። ጥንት አብረውን የኖሩ ሙስሊም ወንድሞቻችን ባነሱት ጥያቄ ውስጥ እጀ ሰፊዎቹ ጣልቃ ገብተው እንዳያፈራርሱን ያሰጋል።

አፍ እንጂ ጆሮ የነሳው ኢህአዴግ ቢነገር፣ ቢዘከር አልቀበል ብሎ አንድ ብሄር የጎዳና ያጠፋ መስሎት አገሪቱን የከፋ አደጋ ላይ አስቀመጣት። ሁሉም በቋፍ ነው። መሪዎቹ፣ ተመሪዎቹ፣ አጫፋሪዎቹ፣ አጋፋሪዎቹ፣ የከፋቸው፣ በከፋቸው ጥላ ስር የተሸሰጉ ሁሉም  ተፋጠዋል። ይህ ሁሉ ሆኖ ኢህአዴግ ሁሉንም ችግር መፍታትና መቋቋም ስለሚቻልበት ሁኔታ ፍንጭ አይሰጥም። ወይ ችሎበት ስጋቱን አያስወግድም። እንዲሁ በድንብርብር ሲጓዝ ኖረ። አሁንም ያንኑ የእውርና ያለ እኔ አዋቂ የለም የሚል ተረቱን እየተረተ ሊቀጥል ይፈልጋል።

የተረሳና የተቀበረ ታሪክና አፈ ወግ እየለቃቀመ ህዝቡን ደም ሲያቃባ ኖረ። አስከሬን እየጎተተ እናቶች የቆረጠ አንጀታቸውን ሰብስበው ዋይ ዋይ ሲሉ በፊልም እያሳየ ቀደም ግራ ዘመሞቹ የጀመሩትን የጎሳ ዘሩን ዘራብን። የተዘራው ዘር ዛሬ አብቦ መከሩ ከደጅ ነው። የሚያሳዝነው ተቃዋሚ የሚባሉት በደጅ ያለውን የመከራ አበባ እያሸተቱ አብረው 21 ዓመታትን በአጃቢነት ማስቆጠራቸው ነው። ለመታገልና የተሻለ የሚሉትን ስርዓት ለማምጣት ችግሩ ብዙ ቢሆንም የነሱ ዱካ  ለሚከተለው ደጋፊዎቻቸው አስተማማኝ መሪ መሆን አልቻሉም። ተስፋ የሚጣልበት ተቃዋሚ የለም። መንግስትም ተስፋነቱን ማሳየት አልቻለም። ተስፋ ጠፍቶ ሁሉም በየፊናው ይበራል። የበረራው መጨረሻና መድረሻ የት ይሆን? ለሁሉም መኖሪያና መሸሸጊያ የሆነችው አገር፣ እምዬ ኢትዮጵያ ታሳዝናለች። ምስኪን ህዝቦቿን ታቅፋና አቻችላ እንዳትኖር ተፈርዶባት ታምጣለች። ከዚህ በላይ አስጨናቂ ዘመን የለም። የፕሮፌሰር መስፍንን ጽሁፍ ስጋቴን አጎላው። ማን ይሁን የኢትዮጵያ ታዳጊዋ? እርቅና ብሄራዊ አንድነት እየተመኘን በማውጫው ያውጣን ከማለት ውጪ ምን ይባላል። የብሄራዊ ስምምነት ያለህ! መቀመጫ ቀርቶባቸው አገር የሚያድኑ ናፍቀውናል የህዝባቸውና የአገራቸው ምርጦች የት አሉ? አገር ቢፈርስ ህጻናትና ተንኮል የሌለባቸው ምስኪን ዜጎች ያለ በደላቸው ፍርድ እንዲቀበሉ ለምን ይደረጋል? ማን ይድረስላቸው። በፊት ቀልድ የሚመስሉና የምናሽሟጥትባቸው ጉዳዮች እየከረሩ ነው። የከረረ ደግሞ ………… ሌላው የሚያሳዝነው የሚፈራና የሚከበር ሰው የለም። ሁሉ ቦታ ረክሷል። የገሸበው ሁለመናችን ነው። ኢትዮጵያችንን የሚያስብ ሰላም ያስፈልገናል። የተቆፈረውን ጉድጓድ የሚደፍን አንድነት ካልተፈጠረ ዙሪያችንን መከላከልም ……

የያዝነው አቅጣጫ የት ያደርሰናል?

(የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማህበር ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ከቀረበ ጽሑፍ ላይ ተቀንጭቦ ወቅታዊ የሆነው ክፍል ከዚህ በታች ይነበባል)

መስፍን ወልደ-ማርያም 1995 ዓ.ም.

ራዕይ ኢትዮጵያ 2020

           ከተለያየ የትምህርትና የሥራ መስክ የመጡ ቢሆንም ከዚህ በፊት የተናገሩት ሁሉ በአንድ ነገር ላይ ይስማማሉ፡- አሁን በተያዘው መንገድ መቀጠል አንችልም፤ የያዝነው መንገድ ወደ ‹‹ክፉ ዕድል›› ወደ‹‹መዓት›› ወደ‹‹ውድቀት›› የሚያመራ መሆኑ ተገልጾአል፤ ለእኔ የአዘቅቱ መንገድ የሚታየኝ እንደሚከተለው ነው፤ በሸምበቆ አጥር የተለያዩና የሚተራመሱ ጎሣዎችን ጭኖ የሚከንፍ ባቡር ይታየኛል፤ ነጂው መትረየሱን ይዞ ፊቱን አዙሮ የተቀመጠው ወደሚነዳበት አቅጣጫ ሳይሆን ወደተሳፋሪዎቹ ነው፤ ተሳፋራዎቹ የሚያዩት ወደፊት ነው፤ ነጂው የሚያየው ወደኋላ ነው፤ ስለዚህም ነጂው ገደሉን ስለማያይ ይበልጥ የሚያስፈራው የተሳፋሪዎቹ ትርምስ ነው፤ ተሳፋሪዎቹን የሚያስፈራቸው የሚታያቸው መትረየስና ገደል ነው፤ በባሩ ላይ ያሉ ተሳፋሪዎች ሁሉ በባቡሩ ፍጥነት ላይም ሆነ አቅጣጫው ላይ ምንም ዓይነት ቁጥጥር የላቸውም፤ የባቡሩ ነጂ ተሳፋሪዎቹ የሚያዩትን አያይም፤ እንዲነግሩትም አይፈልግም፤ የነጂውና የተሳፋሪዎቹ አስተሳሰብ ለየቅል ነው፤ አይነጋገሩም፤ ተሳፋሪዎች በዝምታ ነጂውም ባለማወቅ ወደማያየው ገደል ውስጥ ለመግባት ቆርጠዋል፤ ባቡሩን አቁም ብለው ቢጮሁ መልሱ መትረየስ መሆኑን ያውቃሉ፤ በዝምታ አብሮ ገደል መግባት ነው፤ በዚህ አጣብቂኝና የፍርሃት ቆፈን ተይዘናል፤ ከተረዳንለት ነጂውም አጣብቂኝና የፍርሃት ቆፈን ውስጥ ነው፤ ነጂውና ተሳፋሪዎች ካልተነጋገሩ ባቡሩም፤ ተሳፋሪዎችም፤ ነጂውም ከገደሉ ማምለጥ አይችሉም።

እንግዲህ መሣሪያ የያዘውም ይፈራል፤ መሣሪያ ያልያዘውም ይፈራል ማለት ነው፤ የሁለቱም ጠላት አለመተማመንና መሣሪያው ነው፤ አለመተማመንን ሳናጠፋ መሣሪያውን ማጥፋት አንችልም፤ ሳንነጋገር አለመተማመንን ማጥፋት አንችልም፤ ልባችን ከቂምና ከበቀል ካልፀዳ ተነጋግረን መግባባት አንችልም፤ ባቡሩ እውር ድንብሩን እየሄደ ገደል የሚገባው ለዚህ ነው።

የባቡሩ ገደል መግባት የአደጋው መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ ይሆናል የሚል ግምት የለኝም፤ አደጋው የጎሣ ትርምስና የቂም መወጫ ሁኔታን ይፈጥራል፤ ለብዙ ምዕተ- ዓመታት ወደኋላ ሄደን ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር እንሰለፋለን፤ የያዝነው መንገድ ወደዚህ እንደሚያመራ ለእኔ ግልጽ ነው፤ ይህንን የሚጠራጠር ትንሽ ያስብበት፤ ለሌሎች የተዘራው የጎሣ መርዝ ባልታሰበበት መንገድ ሄዶ በኤርትራና በትግራይ ተወላጆች መሃከል የከፋ መልኩን ማሳየቱ የሚያሳዝንና የመርዙንም ጠምዛዛነት የሚያመለክት ነው፤ የዚህ ጦስም የትግራይ ተወላጆችንም በመከፋፈል ላይ ነው፤ ኦነግ ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በማቆጥቆጥ ላይ ያለው ጎሠኛነት ጉዳዩን ለሚከታተሉ ሁሉ ግልጽ ነው፤ በጎሠኛነት ተኮትኩተው ያደጉ ልጆች እየደረሱ ነው፤ አንድ ትውልድ ሊሆን ምንም አልቀረውም፤ብዙዎቻችንን የሚያሳስበን ደሀነቱና የችጋሩ ጉዳይ ነው፤ የኢትዮጵያን ህልውና ጉዳይ ባንረሳውም አደጋውን ላለመቀበል አእምሮአችንን የምንጋርደው ይመስለኛል፤ ጭንቅላታችንን አሸዋ ውስጥ ቀብረን የምንፈልገውን መመኘቱ ብቻ አቅጣጫችንን አይለውጠውም፤ እኔ የማውቃትና አገሬ የምላት ኢትዮጵያ አሁንም በከፊል የለችም፤ በያዝነው መንገድ ከቀጠልን ደግሞ ያሁንዋም ኢትዮጵያ 2020 የምትደርስ አይመስለኝም፤ በያዝነው መንገድ ከቀጠልን የብዙ አፍሪካ አገሮች ሁኔታ ውስጥ መግባት የማይቀር ነው፤ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በጥያቄ ምልክት ውስጥ መግባትዋ የሚቀር አይመስለኝም፤ ከዘመነ መሳፍንት የባሰና አስከፊ ሁኔታ እንደሚያጋጥመንና በሆነ ባልሆነው መከሳከሳችን ይቀራል ብዬ አልገምትም።

የወደፊቱ ግጭት ከአሁን በፊት ከለመድነው በጣም የተለየ ይሆናል፤ እስከዛሬ የምናውቀው ግጭት በአፈንጋጭ የማኅበረሰቡ ክፍልና በአገዛዙ መሀከል ነበር፤ ቀደም ሲል እንደተናገርሁት ደርግ ራሱ ባወጣው ‹‹የነቃ የተደራጀና የታጠቀ ያሸንፋል፤›› በሚለው ሕግ ወደቀ፤ ወያኔም ራሱ የጠነሰሰውና ሕጋዊ ያደረገው ጎሠኛነት የሚፈጥረው ግጭት እንደበፊቱ በአገዛዝና በአፈንጋጭ መሀከል ሳይሆን በተለያዩ ጎሣዎችም መሀከል ይሆናል፤ በጎሠኛነት ተኮትኩቶ ያደገ ትውልድ በማኮብኮብ ላይ ነው ብያለሁ፤ ዛሬ በትግራይና በኤርትራ ተወላጆች መሀከል ያለው ስሜት ነገ በሌሎች መሀክል ይከሰታል፤ በተነጠቁት መሬት የተነሳ ወሎና ጎንደር ውስጥ ያለው ንዴት ቀላል አይደለም፤አፋር ተከፍሎና ታፍኖ አይኖርም፤ ኦነግ እየተዋጋ ነው፤ ኦጋዴን ለመገንጠል ይችላል የሚል ማደፋፈርያ ተሰጥቶታል፤ ሌላው በየጎራው እያብላላው ነው፤ የጎሣው ግጭት የሚፈጥረው ትርምስና መተላለቅ ከጀመረ በራሱ ኃይል እየተቀጣጠለ ስለሚስፋፋ ላማቆም አስቸጋሪ ይሆናል፤ ስለዚህም ሰላም ይኖራል ብዬ አልገምትም፤ አዘቅቱ የከፋና የኢትዮጵያ ሕዝብ በታሪኩ አይቶት የማያውቀው ደሀነትና ችጋር ጭካኔን እየወለደ፣ በጎሠኛነት ሞተር እየተነዳ በጥላቻና በቂም እየታወረ ክፋት በገሃድ የሚወጣበት መተላለቅ ነው።

በዚህ መተላለቅ ከአካባቢያችን የሚረዱን አይጠፉም፤ በአለፉት ዓመታት ከሶማልያና ከኤርትራ ጋር የተደረገው መዳማት፤ ከጅቡቲ ጋር የተደረገው አለመግባባት፤ በአንድ በኩል ከአሜሪካ ጋር፣ በሌላ በኩል ከሱዳን ጋር የተደረገው ሽር ጉድ የሚከተሉትን ዓመታት ለኢትዮጵያ የሚመቹ አያደርጓቸውም፤ እኔ እንደምገምተው ሁሉም የተነበየው አዘቅት ወይም አፋፍ ላይ በ1997 መጨረሻ እንደርሳለን፤ አዲስ ኢትዮጵያ የምትወለደው ከኤርትራ እስከቦረና ከጋምቤላ እስከጂጂጋ ሁሉም በአንድ ጊዜና በአንድ ላይ በሚሰማው የጭንቀት ምጥ ይሆናል፤ ሕገ አራዊት የሚያደርሰን እዚህ ነው፤ የሰው ልጅ አእምሮ ውስብስቡን የኑሮ ገመድ ሲገምድና ሲፈታ እኛ ገና ከቀላሉ የማስፈራራትና የጡንቻ ዘዴ አልወጣንም፤ በማስፈራራትና በጭቆና የጨቋኝም የተጨቋኝም አእምሮ ደንዝዞ፤ መንፈስም ታምሞ በደነዘዘ አእምሮና በታመመ መንፈስ ትርጉም ያለው ሥራ ለራሳችንም ሆነ ለማኀበረሰባችን ለማበርከት አንችልም።

እንደምትገምቱት ይህንን መናገር ቀላል ነገር አይደለም፤ እስካሁን ድረስ ሦስት አገዛዞች በውርደት ሲወድቅ አይቻለሁ፤ የሁለቱ አገዛዞች መውደቅ በቅድሚያ ታውቆኝ በአደባባይ ተናግሬ ነበር፤ የአሁኑ አገዛዝ በዓይነቱ የተለየ ነው፤ ራሱንም ለማረም በጊዜ ካልጣረ አወዳደቁም የተለየና አገሪቱንም የሚያጠፋ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ባሕሩ[1] እንዳለው ኢትዮጵያ የተአምር አገር ነች፤ አለቀላት ሲባል ነፍስ ዘርታ ትነሣለች፤ እንደዚያ ከሆነ ደስታው የሁላችንም ነው፤ በተአምር ባምንም እጆቻችንን አጣምረን በመቀመጥ ከአንዣበበው አደጋ እናመልጣለን ብዬ ግን አላስብም።

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *