አቶ መለስ በቅርቡ “ማለፍም አለ” ብለው ነበር

     “ሃይለማርያም ደሳለኝ ህጉን ተከትሎ ቃለ መሃላ በመፈጸም ሹመታቸው እስኪጸድቅ አቶ መለስ ሲሰሩ የነበረውን ስራ ሁሉ ይሰራሉ ”                                                 

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን አስመልክቶ “ ነበሩ ” እያለ መግለጫ ያወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት “ አፍሪካና አለም አንድ ብርሃናቸውን አጡ” ብሏል። ህልፈታቸውን የሚያወጀውም  በሃዘን በተሰበረ ልብ መሆኑን አመልክቷል። ወቅቱ አስቸጋሪ ቢሆንም አቶ መለስ የጀመሩትን ስራዎች ዱካቸውን በመከተል ተግባራዊ እናድርግ ሲል ጥሪውን አስተላልፏል።

በተደጋጋሚ ታላቅ፣ አርቆ አሳቢ፣ መላው ዓለም ብቃታቸውን የመሰከረላቸው፣ ደከመኝ የማያውቁ በማለት አቶ መለስን እያወሳ የተነበበው መግለጫ “ ታላቁ መሪያችን ከጎናችን ቢለዩም ትተውልን የሄዱት ህገ መንግስት ከአለት የጸና ነው ” ካለ በሁወላ ፣ በዚሁ የጸና አለት ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ህዳሴ የማይቀለበስ ነው ሲል አስታውቋል።

“የኢትዮጵያን የተስፋ ሻማ የለኮሱ”  ሲል የመለስን ያለ ጊዜ ማለፍ የጠቆመው የሚኒስትር ምክር ቤት መግለጫ አቶ መለስ ላለፉት ሁለት ወራት ህክምና ሲከታተሉ ቆይተዋል ብሏል። ከህመማቸው በማገገም ላይ እንዳሉ በድንገት መነሻው ኢንፌክሽን ሆኖ ተመልሰው ሆስፒታል መግባታቸውን ተናግሯል። ሆኖም በትላንትናው እለት ከሌሊቱ 5፡40 ህይወታቸው ማለፉን ይፋ አድርጓል። መግለጫው አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን “ ክቡር ” በማለት አቶ መለስን መተካታቸውን አመልክቷል።

ከፊትለፊት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም ወቅቱ በአስተማማኝ እንደሚያልፍ የጠቆመው መግለጫው ህዝብ የተጀመሩትን ስራዎች ለማስቀጠል እጅ ለእጅ እንዲያያዝ አበክሮ ጥሪ አስተላልፏል።

መለስ ላለፉት ሁለት ዓመታት ይታመሙ እንደነበር መግለጫው ጠቅሷል። ይሁን እንጂ አቶ መለስ ህዝባቸውን ስለሚወዱ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ከፍ ብላ እንድትጠራ ያደረጉ፣ አገሮቱን በብቃት የመሩ፣ ታላቅ መንግስት የገነቡ፣ ድህነትን አጥብቀው ለመዋጋት የሚሰሩ ታላቅ ባለራ ዕይ መሪ በመሆናቸው ከጤናቸው ጋር እየታገሉ ሲሰሩ መቆየታቸውን በመግለጫው ጎልቶ ታይቷል።

አቶ መለስ ህይወታቸው አልፏል መረጃ አለኝ በማለት ከወራት በፊት ያስታወቀው ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ የሚመሩት የሽግግር ካውንስል እንደሆነ ይታወቃል። ካውንስሉ ምንጮቹን ጠቅሶ የመለስን ህልፈት በድረ ገጾች ማሰራጨቱን ተከትሎ የመለሰት ህልፈት ታላቅ ወሬ ሆኖ ነበር። ባለፈው ሳምንት ደግሞ አይ ሲ ጂን ምንጮች በመጥቀስ መለስ ህይወታቸው ማለፉን ኢሳት ማስታወቁ አይዘነጋም።

የመለስ መታመምና ህልፈት ይፋ ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ እጅግ ገለልተኛ የሆኑ ክፍሎች የሚሰጡት አስተያየት ቢለያይም አቶ መለስ ታላላቅ ስራ የሰሩትን ያህል በትውልድ የማይረሳ ጥፋት የተመዘገበባቸው መሪ እንደሆኑ ይናገራሉ። አቶ መለስን በብቃታቸው የማያሟቸው አስተያየት ሰጪዎች በቀጣይ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው አቶ መለስ ያበላሹዋቸው በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ይጠቁማሉ።

ኢህአዴግ አንድ ሰው ላይ የተገነባ ድርጅት መሆኑ አደጋ እንዳለው በሃዘኔታ የሚጠቁሙት እኒህ ክፍሎች “ መለስ ተቋም አልገነቡም፤ ይህ ትልቁ ጥፋታቸው ነው” ይላሉ። በዚህም ሳቢያ በአገሪቱ የተሌአዩ እርከኖች ክፍተትና የሃይል መበጣጠስ ሊፈጠር እንደሚችል ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።  የሚኒስትሮች ምክር ቤት በመግለጫው አቶ መለስ በአፍሪካ ታላቅ ተባለ መንግስትና ተቋም የገነቡ መሆናቸውን በኩራት አስታውቋል።
በተያያዘ  አቶ በረከት ሃይለማርያም ደሳለኝ ህጉን ተከትሎ ቃለ መሃላ በመፈጸም ሹመታቸው እስኪጸድቅ አቶ መለስ ሲሰሩ የነበረውን ስራ ሁሉ እንደሚሰሩ አስታወቁ። አቶ መለስ የት አገር ሲታከሙ እንደነበር አሁንም ያልገለጹት አቶ በረከት፣ የቀብር ስነ ስርዓቱ እስኪከናወን ባገሪቱ የብሄራዊ ሃዘን ቀን መታወጁን አስታውቀዋል።ዛሬ ማለዳ ለጋዠጠኞች በሰጡት አጭር መግለጫ በአቶ መለስ ህልፈት ሳቢያ በአገሪቱ የዋጋ ጭማሪ ሊከሰት እንደሚችል ተጠይቀው ” ለውጥ የለም፤ የፖለቲካና የስትራቴጂ ስርዓቱ ይቀጥላል” የሚል መልስ ሰጥተዋል። አቶ መለስ ስለመተካካት ሲናገሩ ቀጣይ ህይወታቸውን በማንበብ እንደሚያሳልፉ ሲናገሩ ማለፍም አለ ማለታቸው ይታወሳል። ፎቶ ሪፖርተር

Share and Enjoy !

0Shares
0

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *