(ክፍል ፪)

በሚኪያስ በቀለ

(ማስገንዘቢያ፤ በዚህ ጽሑፍ ላይ የተገለጹት ቀኖች፣ ወሮች እና ዓመተ ምኅረቶች በሙሉ በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ናቸው፡፡)

የተፋሰስ ውኃ የሕግ መርሖች እና አፈጻጸማቸው

የናይል ተፋሰስ ካለበት የከረመ የውኃ ፖለቲካ ግጭት በተጨማሪ የተፋሰስ ውኃ የሕግ ማዕቀፎች ላይ የተገለጹ መሠረታዊ የሕግ መርሆች ለአፈፃፀም አስቸጋሪ እንደሆኑ የተለያዩ የሕግ ልሒቃን ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህ የተፋሰስ ውኃ የሕግ መርሖች ውስጥ ዋነኞቹ በምክንያዊ እና በዕኩልነት የመጠቀም መርሕ (Reasonable and Equitable utilization) እና ሌሎች ተፋሰሶችን ያለመጉዳት መርሕ (No Harm/Appretiable Harm) ናቸው፡፡

በምክንያዊ እና በእኩሌታ የመጠቀም መርሕ (Reasonable and Equitable utilization) በተባበሩት መንግሥታት በ1997 ላይ በወጣው የዓለም አቀፍ ስምምነት (UN Convention on the Law of the Non-navigational Uses of International Watercourses) አንቀጽ 5 ላይ ተገልጾአል፡፡ እንዲሁም በአዲሱ የናይል ተፋሰስ የሕግ ማዕቀፍ ክፍል 2 አንቀጽ 4 ላይ ተደንግጓል፡፡

ይህ የሕግ መርሕ በዓለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ ከመገለጹ በተጨማሪ እንደ ዓለም አቀፍ የተፋሰስ የውኃ መርሕም ተቀባይነት አግኝቶ በዓለምአቀፉ ፍ/ቤት (ICJ) በሀንጋሪ እና በስሎቫኪያ መካከል በተፈጠረው ክርክር በ1991 ላይ ውሳኔ ተሰጥቶበታል፡፡ በእኩሌታ ላይ የመጠቀም መርሕ ውኃውን በቀጥታ የመከፋፈል ሳይሆን በሕጉ ላይ የተገለጹት ስምንት መዘርዝሮች በአንድ ላይ ተቀላቅለው ካላቸው ውጤት አንጻር ነው፡፡ በማዕቀፉ አንቀጽ 4 ላይ የተገለጹት መዘርዝሮች የተፋሰስ ሀገሮች ካላቸው፡-

መልክአ ምድርያዊ እና የአየር ሁኔታ፣ የማኅበረሰባዊ እና የኢኮኖሚ ፍላጎት፣ በወንዙ ላይ ጥገኝነት ካላቸው ሕዝቦች አንፃር፣ ውሀውን የመጠቀም ችሎታ አንፃር፣ የወንዙን አካባቢያዊ ሁኔታ ከመጠበቅ አንፃር፣ ሃገራቱ ካላቸው ሌላ የውኃ ሀብት አማራጭ አንፃር፣ ሃገራቱ ለወንዙ ከሚያዋጡት የውኃ መጠን አንፃር እና በሃገራቱ ውስጥ ካለው የበረሃ ቦታ አንፃር የሚወሰድ ነው፡፡

ከላይ የተገለጹት መዘርዝሮች አንዳንዶቹ የላይኞዎቹን ተፋሰሶች ሲደግፉ የተቀሩት የታችኞቹን ተፋሰሶች መደገፋቸው ለአፈፃፀም አስቸጋሪ እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡ ዶ/ር ኤሊያስ አንዳዶቹ መዘርዝሮች ከሌላዎቹ በተሻለ ተገቢነት ስላላቸው ለአፈፃፀም እንደሚያስቸግር ይገልጻሉ፡፡ የሕግ ማዕቀፉ አንቀጽ 4(2) ይህንን ጉዳይ ውሳኔ እንዲሰጥበት ለሚቋቋመው ቋሚ ድርጅት ሥልጣን ሰጥቷል፡፡ ፕሮፌሰር ዋትርበሪ በበኩላቸው ለእያንዳንቸው መዘርዝሮች 11.1 በመቶ ግምት በመስጠት የዕኩልነት መጠቀም መርሕ መፈፀም እንደሚችል የፕሪንስተን ዩንቨርሲቲ ያሳተመው Between Unilateralism and Comprehensive Accords: Modest Steps toward Cooperation in International River Basin በሚለው ጽሑፋቸው ላይ ገልጸዋል፡፡

ሌላው ዋነኛ የተፋሰስ ውኃ የሕግ መርሕ ማንኛውም ሀገር ውኃውን ሲጠቀም ሌሎች ተፋሰስ ሃገሮችን ያለመጉዳት መርሕ (Appreciable harm) ነው፡፡ ይህ መርሕ አመጣቱ ማንኛውም ሰው የራሱን ንብረት ሲጠቀም የሌላውን መብት መጉዳት አይችልም ከሚለው የሮማን የንብረት ሕግ መርሕ እንደሆነ ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ፡፡ የተፋሰስ ሀገሮች ውኃውን ሲጠቀሙ ሌሎች ሀገራት ላይ መሠረታዊ ጉዳት ማድረስ እንደሌለባቸው አዲሱ የሕግ ማዕቀፍ በአንቀጽ 5 ላይ ቢደነግግም በተፋሰስ ሀገራቱ ስምምነት ላይ ካልተደረሰበት የሕግ ድንጋጌ ዋነኛው ነው፡፡

ሌሎች ሀገሮችን ያለመጉዳት መርሕ የግርጌ ተፋሰስ ሀገሮች ያላቸውን የቀደመ የመጠቀም መብት (Historic right) ያንፀባርቃል፡፡ ያለመጉዳት መርሕ የተፋሰስ ውኃን መብታቸው እስከሚፈቅድላቸው ወይም ከመብታቸው በላይ የተጠቀሙት ሀገራት ለሚያነሱት ያለመጎዳት ክርክር መፍትሄ እንደይማሰጥ ፕሮፌሰር ታከለ ሶቦካ Between ambivalence and neccessity in the Nile basin: occlusion on the path towards basin wide treaty በሚለው ጽሑፋቸው ላይ ያስረዳሉ፡፡

እንደ ፕሮፌሰሩ አገላለጽ እንደ ግብጽ ያሉ መብታቸው እስከሚፈቅድላቸው ወይም ከመብታቸው በላይ የተጠቀሙትን ሃገሮችን ጉዳት ባለማድረስ መርሕ እየጠበቅናቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ገና ምንም መብታቸውን ያልተጠቀሙ ሀገራትን በዕኩልነት የመጠቀም መርሕ መጥቀም በራሱ መፍትሔ የሚታጣለት ጉዳይ መሆኑ በሁለቱ የሕግ መርሆች መካከል ያለውን ተቃርኖ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን ሀገራቱ ጉዳት ያደረሱት በእኩልታ የመጠቀም መብታቸውን ለማስፈጸም ከሆነ ሌሎች ተፋሰስሶችን መጉዳት ሕገወጥ አይደለም፡፡ ይልቁንም ሀገራቶቹ በጋራ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ እና/ወይም ለመካስ በሚቋቋመው ድርጅታዊ ማዕቀፍ ተመካክረው መስማማት እንዳለባቸው የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያበረታታው የሕግ ማዕቀፍ ይደነግግል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ከሁለቱ መርሆች መካከል ዋነኛው እና የሚቀድመው በእኩልነት እና በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ የመጠቀም መርሕ እንደሆነ የተለያዩ ጽሑፎች ይስማማሉ፡፡ ይልቁንም ሌሎች ሀገሮችን ያለመጉዳት መርሕ በዕኩልነት የመጠቀም መርሕ በሚታሰብበት ጊዜ እንደ አንድ ግብዓት (ከ8ቱ መዘርዝሮች መካከል) ተደርጎ መወሰድ አለበት፡፡

እንደ ፕሮፌሰር ካልፊሽ አገላለጽ ሌሎች ሀገሮችን ያለመጉዳት መርሕ ሁለት ገጽታዎች አሉት፡፡ ለተፋሰስ ሀገሮች የሚገባቸውን የውኃ መጠን በመተመን (ኢኮኖሚያዊ) እና የናይል ተፋሰስን አካባቢያዊ ገጽታ ከመጠበቅ (አካባቢያዊ)፡፡ የአካባቢያዊ ገጽታው ሙሉ ተቀባይነት ሲኖረው የውኃ ድርሻን ከመተመን አንፃር ያለውን ኢኮኖሚያዊ ትርጓሜ ግን ጥያቄ ውስጥ እንደሆነ ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

ዶ/ር ኤሊያስ በበኩላቸው ይህ የሕግ መርሕ የራስጌ ሀገራት በግርጌ ሀገራት ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት ብቻ ሳይሆን የግርጌዎቹ በራስጌ ሀገራት ላይ ከሚያደርሱት ጉዳት አንፃርም መተርጎም እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ “የላይኛዎቹ ሀገራት ውኃውን የመጠቀም መብታቸውን የታችኛዎቹ ሀገራት ካልጠበቁላቸው ወይም ውኃውን መጠቀም ከከለከሏዋቸው ያለመጉዳት መርሕን እንደተቃረኑ” የሕግ ሊቁ በጽሑፋቸው ላይ ያስረዳሉ፡፡

የተፋሰስ ውኃ የሕግ ማዕቀፍ ውኃውን ከመከፋፈል እና/ወይም ከመጠቀም ይልቅ አካባቢያዊ ተግዳሮቶችን በመጠበቅ ዙሪያ የተፋሰስ ሀገራቱን ስምምነት ላይ ያደርሳል፡፡ በናይል ላይ የሚደርሰው ማንኛውም የአካባቢያዊ ተግዳሮት ሁሉንም ተፋሰስ ሀገሮች መጉዳቱ እሙን ነው፡፡ የአፈር መሸርሸር እና የመሬት ሽፋን መውረድ በላይኞቹ ሀገራት፤ ደለል፣ የውኃ ጨዋማነት መጨመር፣ ከፍተኛ ትነት እና ጎርፍ በታችኞቹ ተፋሰስ ሀገሮች ላይ የሚፈጠሩ የናይል አካባቢያዊ ጥቃቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ በሕግ ማዕቀፉ አንቀጽ 8 ላይ በተደነገገው መሠረት የተፋሰስ ሀገራቱ በጋራ ስምምነት ላይ የተመሠረተ የአካባቢያዊ ጥበቃ ማድረጋቸው የናይልን አካባቢያዊ ተግዳሮቶች አስወግደው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትም እንደሚዳርጋቸው ፕሮፌሰር ያቆብ አርሳኖ ይገልጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ ብዛት ያላቸው የኃይል ማመንጫዎችን መሥራት የሚያስችል አካባቢያዊ አቅም ስላላት ግድቦቹን ብትገነባ ለራሷ የኤሌትሪክ ኃያል እና በወቅታዊ ዝናብ ላይ ለተመረኮዙት ገበሬዎቿ የመስኖ ውኃ ከማግኘቷ በተጨማሪ ግብጽና ሱዳን ላይ የሚደርሰውን የደለል እና የጎርፍ አደጋ ተቆጣጥራ የኤሌትሪክ ኃይል ተጠቃሚም ልታደርጋቸው ትችላለች፡፡

እንደ ማጠቃለያ

የናይል ተፋሰስ ሀገራት በተለይም የምስራቅ ናይል ተፋሰስ ሀገራት ካለባቸው የከረመ የውኃ ፖለቲካ ተቃርኖ እና የግርጌ ሀገራት የቀደመ የመጠቀም መብት በመያዛቸው ምክንያት በዕኩልነት ላይ የተመሠረተ የዓለም ዓቀፍ ሕግ ማዕቀፍ ተፋሰሱን ወደ ጋራ ስምምነት ለማምጣት ያለው አስተዋጾ ከሌሎች የዓለም አቀፍ ሕጎች አንፃር ደካማ የሚባል ነው፡፡ ነገር ግን የግርጌ ተፋሰስ ሀገሮች የነበራቸውን የቀደመ የመጠቀም መብት በቀኝ ግዛቶቻቸው እና እራሳቸው በፈረሟቸው ስምምነቶች ከለላ ሰጥተው መጠቀማቸውን በሕግ ማዕቀፍ አግባብነት እንደሌላቸው ለማረጋገጥ፣ ከውኃው የተሻለ የኢኮኖሚ ጥቅም ለማግኘት እና ከአካባቢ ተግዳሮቶች ለመዳን ያለው አማራጭ ሁሉን ያሳተፈ የተፋሰስ የሕግ ማዕቀፍ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ 84 በመቶ የሚሆነውን የአንበሳ ድርሻ ለወንዙ የምታዋጣ እንደመሆኗ እና የናይል የሕግ ማዕቀፉን ለመፈረም የመጀመሪያዋ ሀገር እንደመሆኗ የማጽደቁንም ሥራ ፓርላማዋ ጊዜ ሳይሰጥ መተግበር ይኖርበታል፡፡ (የመለስን ሌጋሲ እናስቀጥላለን ከተባለ አይቀር….) ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ሥራዎችን በናይል ላይ የመሥራት ተፈጥሯዊ መብቷን ተጠቅማ ፕሮጀክቶችን ለማስፈፀም መጣር እና ያላትን የመከራከሪያ አቅም ማሳደግ ይጠበቅባታል፡፡ የሕዳሴው ግድብ ለዚህ ተጠቃሽ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ፕሮጀክት የግርጌ ሀገራትን አይጎዳም ብሎ ከመለማመጥ የመስኖ ሥራም እንደምንሠራና ድርሻችንን የመጠቀም ተፈጥሯዊ መብት እንዳለን በመግለጽ አቋማችንን በግልጽ ማስቀመጥ ይኖርባታል፡፡

የዚህ ትልቅ ግድብ ግንባታ ወጪ 80 ቢሊዮን ብር ከመሆኑ ባሻገር ወጪው ከሀገር ውስጥ ገቢዎች የሚሰበሰብ መሆኑ ሀገሪቷ ካላት ምጣኔ ሀብት አንፃር አደጋ ውስጥ እንዳይከታት ቢታሰብበት አይከፋም፡፡ ከቦንድ ሽያጭ የሚሰበሰቡትን ገንዘቦች በግልጽነት የተለያዩ የኅብረተሰቡን ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ ኦዲት መደረግ እና ለታሰበለት ዓላማ መዋል፣ በብድር መልክ የተወሰዱትን በጊዜው ከነ ወለዳቸው መመለስ ይገባቸዋል፡፡ የዓለም አቀፍ ገንዘብ ድርጅት እና አንዳንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ግንባታው የሃገሪቷን ኢኮኖሚ እና የግል ዘርፉን አደጋ ውስጥ እንዳይጥል እና በየዓመቱ የወር ደሞዙን (በውዴታም ይሁን በግዴታ) የሚለግሰው የመንግሥት ሠራተኛ እንዳይሰላች ጥንቃቄ መወሰድ ይኖርበታል፡፡

የጋና ፕሬዘዳንት የነበሩት ዋኪ ንክሩማም በአባይ ላይ ትልቅ ግድብ ለመሥራት ዜጎቻቸውን በግብር እና መዋጮ አጨናንቀው ለሲአይኤ መፈንቅለ መንግሥት በር እንደከፈተላቸው አቶ ያሬድ ጥበቡ የአባይ ልጆች ቢወራረዱስ ምን ይሻላል? በሚለው ጽሑፈቸው ላይ አስነብበውናል፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥትም የሕዳሴው ግድብ መመስገኛው እንጂ መቀበሪያው እንዳይሆን ጥንቃቄ ቢወስድ የተሻለ ነው፡፡ የግብጽ ፕሬዘዳንት የነበሩት አንዋር አብዱልናስር ከእስራኤል እና ከአሜሪካ ጋር ከነበራቸው ቅራኔ በተጨማሪ ከሩስያ ባገኙት ብድር የአስዋን ኃይል ማመንጫን ማስገንባታቸው በሕዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ምስጋናንና ተደማጭነት እንዲያገኙ እረድቷቸዋል፡፡ አብዱልናስር ግድቡ ሊመረቅ 3 ወር ሲቀረው ሲሞቱ መለስ ዜናዊ የግድቡን መሠረት ድንጋይ ባኖሩ በአንድ ዓመታቸው መንበራቸውን በሞት ተነጥቀዋል (ነፍስ ይማር)፡፡ በጊዜው ያለው የኢትዮጵያ መንግሥትም የአብዱልናስርን ተሞክሮ ወስዶ ግድቡን ፕሮፌሰር አለማየሁ ገ/ማርያም በተደጋጋሚ እንደሚገልጹት ከፖለቲካ መጠቀሚያነት አልፎ አፈፃፀም ላይ ማድረስ ግድ ይላቸዋል፡፡

ናይልን በተመለከተ የተካሄዱ ድርድሮችን፣ ስለ ግድቡ የአጣሪው ኮሚቴ የደረሰባቸውን ውጤቶች እና የመሳሰሉትን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትራችን በግልጽነት ለሕዝቡ የማሳወቅ ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል፡፡ በፍጥነት እየጨመረ የሚገኘው የናይል ተፋሰስ ሀገራት የሕዝብ ቁጥር በተባበሩት መንግሥታት ትንበያ መሠረት በ2017 ዓ.ም 859 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል ይጠበቃል፡፡ የተፋሰስ ሀገራቱ የሕዝብ ቁጥሩ ሲጨመር የውኃ ፍላጎቱ እና እጥረቱም በዚያኑ ያህል እንደሚጨምር ግልጽ ነው፡፡ የተፋሰስ ሀገሮቹ ከዚህ በተጨማሪ ከበፊቱ በተሻለ መረጋጋት ይታይባቸዋል፡፡ ይህም በናይል ላይ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ተረጋግተው ማስፈጸም እንዲችሉ መንገድ ይከፍትላቸዋል፡፡ ታንዛንያ 1 ሚሊዮን እና ኬንያ 3 ሚሊዮን ለሚጠጉ ሕዝቦቻቸው የመጠጥ ውኃ ለማዳረስ የባንቧ መስመር ግንባታዎችን ከማቀድ አልፈው ማስፈጸም ጀምረዋል፡፡ ኢትዮጵያም ሁለት መቶ ሺሕ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት እና 6000 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ የኃይል ማመንጫ ለመሥራት የመሠረት ድንጋይ ጥላለች፡፡

ኡጋንዳም ከቻይና ጋር ተስማምታ የተለያዩ የኃይል ማመንጫዎችን መገንባት ጀምራለች፡፡ የተፋሰስ ሀገራቱ የሚሠሯቸው ፕሮጀክቶች ከሀገራቸው የውኃ እና የኤሌትሪክ ኃይል ፍላጎት አንጻር እንጂ ሌሎች ሀገሮች ላይ የሚያስከትለውን ጉዳትም ሆነ በአካባቢ ላይ የሚያደርሰውን ተግዳሮት ግምት ውስጥ አይከቱም፡፡ የተፋሰስ ሀገራቱ ለየብቻቸው ፕሮጀክቶችን ማስፈፀማቸው በተፋሰስ ሀገራቱ ያለውን ተቃርኖ ያጎላዋል እንጂ ወደ ጋራ ስምምነት አያመጣቸውም፡፡ ስለዚህ የተፋሰስ ሀገራቱ ከወንዙ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘትም ሆነ ከአካባቢያዊ ተግዳሮቶች ለመዳን በጋራ ስምምነት ላይ የተመሰረተ የውኃ አጠቃቀም የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው ፈላስፋ ሔሮዱተስ እንደገለጸው ‹‹ግብጽ የአባይ ስጦታ›› መሆንዋን ተረድታ የግርጌ ሀገራትን በማይጎዳ እና በሚያሳትፍ መልኩ ውኃውን መጠቀም ይኖርባታል፡፡ ግብጽም ኢትዮጵያ በናይል ላይ ሥራዎችን እንዳትሠራ፤ የገንዘብ እርዳታ እንዳታገኝ ከመሯሯጥ እና የተለያዩ ጦርነቶችን ከመደገፍ ይልቅ በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠተ አካሄድ ማጎልበት ይኖርባታል፡፡ በውኃ ላይ መጣላት ማንንም ስለማይጠቅም የቃላት ጦርነት ከመግጠም እና እኔ ብቻ በሚል ኢ-ምክንያታዊ ብሄል ከመጠመድ ተፈጥሮ የሰጠችንን ፀጋ በጋራ እስከምንችለው ድረስ መጠቀም እንደሚኖርብን ይህ ጽሑፍ የሚመለከታቸውን ሁሉ ያስገነዝባል፡፡እያንዳንዷዋን የናይል ጠብታ ከሜዲትራንያን ባሕር ታድጎ “አባይ ዘመድ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል” የሚለውን ተረት፤ ተረት ማድረግ የሁሉም ተፋሰስ ሀገሮች የተናጠል ሳይሆን የጋር ድርሻ ነው፡፡

ጸሐፊውን ለማግኘት በኢሜይል አድራሻቸው mikiyaslaw@gmail.com ይጻፉላቸው፡፡

 source – ዞን ዘጠኝጦማር

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *