ሰመጉ ከቤንሻንጉል ተፈናቅለው እንዲመለሱ የተደረጉ ዜጎች
በችግር ላይ ናቸው አለ

ባለፈው መጋቢት ወር ከቤንሻንጉል ክልል ከተፈናቀሉ በኋላ እንደገና ወደ ክልሉ ተመልሰው እንዲኖሩ የተደረጉ በሺህ የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጅ ነዋሪዎች በችግር ላይ መሆናቸውን የሰብአዊ መብት ጉባኤ ገለፀ።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ በአሁኑ አጠራሩ የሰብአዊ መብት ጉባኤ “መንግስት ለዜጎች መብቶች መከበር በቂ ጥበቃ ያድርግ (በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ የሚፈፀመው ሕገ-ወጥ መፈናቀል ይቁም)” ሲል ባወጣው 126ኛው ልዩ መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ከቤንሻንጉል ክልል ባሩዳ እና ብሎን ቀበሌ የተፈናቀሉና በኋላም መፈናቀላቸው ስህተት እንደሆነ ተገልጾ የተመለሱ ዜጎች ላይ አሁንም የመብት ጥሰቶችና አስተደደራዊ በደሎች እየተፈፀሙ መሆኑን አመልክቷል።
የሰብአዊ መብት ተመልካች ድርጅቱ በተፈናቃዮቹ ላይ እያደረሱ ነው ካላቸው የመብትና አስተዳደራዊ ጥሰቶች መካከል በአካባቢው አስተዳደር አካላትና በሌሎች የክልሉ ብሔረሰብ አባላት የተነጠቁትን የተለያዩ ንብረቶች ተመላሽ እንዳልተደረገላቸው፣ በአሁኑ ወቅት ከሌሎች ብሔረሰቦች እየተለዩ ማስፈራሪያና ድብደባ እየተፈፀመባቸው እንደሚገኝ፣ ምንም አይነት እገዛና ማቋቋሚያ እንዳልተደረገላቸው እና የእርሻ ግብዓትን ማለትም እንደ ዘር ማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶችን “እናንተ የዚህ (ብሄር) ናችሁ” በማለት እየተከለከሉ ነገር ግን ለሌሎች እየተሰጠ እንደሚገኝና በፌዴራል መንግስት አማካኝነት ቢመለሱም የዞንና የቀበሌ አስተዳደር አካላት “እናንተ ከዚህ ክልል ውጪ ናችሁ” በማለት ልዩ ልዩ አድልዎና መገለል እየተፈፀመባቸው እንደሚገኝ ሰመጉ ማረጋገጡን በመግለጫው አመልክቷል።
ብሎን ወረዳ ውስጥ ከ11 ዓመት በላይ እንደኖሩ የሚያስረዱት ነገር ግን ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁት ተፈናቃይ እንደነገሩን፤ በዚህ ቀበሌ ውስጥ የተለያዩ ብሔሮች ተስማምተው ይኖሩ እንደነበርና ከሰኔ 7 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ የወረዳና የቀበሌ ባለስልጣናት የአማራ ክልል ተወላጆችን ለስብሰባ ጠርተው “የክልል 3 (የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት) ተወላጅ የሆናችሁ ሁሉ ክልሉ በዕዳ ስለሚፈልጋችሁ በአስቸኳይ ለቃችሁ ውጡ” በማለት ለመውጣት እንድንስማማ በግዳጅ ማስፈረም ጀመሩ። “አንፈርምም ወንጀል ከሰራን በሕግ መጠየቅ እንጂ ውጡ ለምን እንባላለን። ለእኛም ይህ አካባቢ አገራችን ነው” በማለት ለማስረዳት ብንሞክርም የተሰጠን ምላሽ “ይህንን ክልል ለቃችሁ ካልወጣችሁ ለህይወታችሁ ዋስትና የላችሁም” በማለት የቀበሌና የወረዳ (ብሎን ወረዳና ባሩዳ ቀበሌ) አመራሮች እንደመለሱላቸው ሰመጉ በመግለጫው ላይ አስረድቷል።
በብሎን ወረዳ ዶቢ ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት አቶ አስማረ አያሌው ቤታቸው በእሳት እንደተቃጠለባቸውና ድብደባ እንደተፈፀመባቸው እንዲሁም ከ60ሺ ብር በላይ መዘረፋቸውን ይህንንም ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ቢያሳውቁም ምንም አይነት ድጋፍ ወይም መፍትሄ እንዳልተሰጣቸውም መግለጫው አያይዞ ጠቅሷል።
መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ሕገወጥ ድርጊቶችን የሚፈፅሙ ግለሰቦችን፣ ቡድኖችን፣ የፀጥታ ኃይሎችን እና ሌሎች ባለስልጣናትን ሕግ ፊት እንዲቀርቡ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅበታል ያለው ልዩ መግለጫው ከሕግ አግባብ ውጪ ለተፈናቀሉ ዜጐች፣ ቤተሰቦች፣ በግፍ ለተደበደቡና ለቆሰሉ እንዲሁም ለሕገወጥ እስራት ለተዳረጉ፣ ንብረታቸውን ያለአግባብ ለተወረሱና ለወደመባቸው ሁሉ መንግስት ተገቢውን ካሳ እንዲከፈላቸው እንዲያደርግ ሲል በመግለጫው አሳስቧል።
(ምንጭ፡-ሰንደቅ ጋዜጣ 8ኛ ዓመት ቁጥር 405 ሰኔ 5/2005) በዘሪሁን ሙሉጌታ

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *