ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የደን ሚኒስቴር ሊቋቋም ነው

ሰሞኑን አንድ የተፈጥሮ ገጽታ የሚያሳይ ፎቶ ፍለጋ ስጎለጉል ደነገጥኩ። አገሪቱ አመድ መስላለች። ጫካ የለም። ተራራው ከዳር እስከዳር እርቃኑን አግጧል። ደን ወድሞ ስለማለቁ አሰብኩ። ጽድ እየገነደሱ፣ ዋንዛ እየገደሉ፣ ኮሶና ቀረረሮ እየጨፈጨፉ አገሪቱን በርብርብ ደን አልባ ሲያደርጉ የከለከለ አልነበረም።አንዳንዴ ባለሙያዎች ሲጮሁ የሚሰማም አልነበረም።

“ኢትዮጵያ ተራራ  አየሩ” ሲባልና ሲዘፈን ሌላ አገር ተራራ ፣ ወንዝና አየር ያለ አይመስለንም ነበር። በዘፈንና በመፈክር እየኮራን ምድረ በዳ ታቅፈን ኖርን። በዘፈንና በቀረርቶ አገር አልምተን ባዶ ቀረን። የመሬት መከላት አሳሳቢ ችግር መሆኑ በተነሳበት የኢህአዴግ ጉባኤ ” ፓፓየና አቡካዶ አልምተናል። ይህ ደን አይደለም?” በማለት ስብሰባው ላይ  የወቅቱ የግብርናና የገጠር ልማት ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሰ አቶ መለስ ቀበል አድርገው ማስተካከያ መስጠታቸውን አስታውሳለሁ። ፓፓዬና አቡካዶ ደን ነው የሚል የግብርና ሚኒስትር ነበረን። ብቻ ሁሉም አልፎ የደን ሚኒስቴር ራሱን ችሎ እንዲቋቋም መደረጉ በራዱ አንድ ርምጃ ነው። ከፋና ብሮድ ካስቲንግ ሰኔ 11 ቀን 2005 የተሰማው ዜና ይህን ይመስላል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን እንዲሁም የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በአዲስ መልክ ሊቋቋሙ ነው ። የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ የፌዴራል የስራ አስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባርን ለመወሰን በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አንዱና ዋነኛው ተልእኮው ከመስኖ ልማት መስፋፋትጋር የተያያዘ በመሆኑ ፥ ስያሜው ይህንኑ እንዲያንጸባርቅ ለማድረግ የውሃ የመስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በሚል እንዲስተካከል መደረጉ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ተብሏል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርም የቤቶች ልማትን ከከተማ ልማት ጋር በተያያዘ መልኩ ብቻ ሳይሆን ገጠሩንም ጨምሮ የቤቶች ልማትን በአጠቃላይ የመከታተልና የመደገፍ ሚና ሊኖረው እንደሚገባ ስለሚታመን  ስያሜውም ሆነ ስልጣንና ተግባሩ ይህን እንዲያካትት መደረጉ አስፈላጊ ሆኗል።

በሌላ በኩል የአካባቢና ደን ሚኒስቴር እንዲቋቋም ውይይት የተደረገበት ረቂቅ አዋጁ ፥ የአገራችን  እድገት በአረንጓዴ መንገድ ማስቀጠል በማስፈለጉ የኢኮኖሚ እድገታችንም ከካርበን ልቀት ነጻ እንዲሆንና የውጭ ኢንቨስትመንትን የበለጠ መሳብ ስለሚያስችል ሚኒስቴሩ እንዲቋቋም አስፈልጓል ብሏል።

በምክር ቤቱ ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ረቂቅ አዋጁ ለዝርዝር እይታ ለህግ ፍትህና አስተደደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

በብርሃኑ ወልደሰማያት