ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

“እኔ መሪ ብሆን ከማጣቸው ነገሮች አንዱ ነፃነት የሚባለው ነገር ነው” ሃይሌ

“ፓርረላማ ግቡ” ፣” የጥምር መንግስት መቋቋም አለበት”፣ ” ከእነ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ጋር  ሽምግልና ውስጥ ገብቻለሁ”፣ ” ፓርላማ መግብት እፈልጋለሁ፣ በግል ይሁን በፓርቲ ደረጃ አሁን የወሰንኩት ውሳኔ የለም” ፣ ሃይሌ ላሰራው አዲስ ሆቴል የመገልገያ እቃዎች ለመግዛት ደቡብ አፍሪካ በተጓዘበት ወቅት ለአይን የሚታክት እርሻ ተመልክቶ መመለሱን፣ በተመለከተው እርሻ መማረኩን ከገለጸ በሁዋላ በበነጋው ” ገበሬ መሆን አለብኝ” በማለት ለዜና የሚውል መረጃ ሰጠኝ ፣  ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ በተደጋጋሚ በቃለ ምልልስና በዜና ኃይሌ ገ/ስላሴን አስመልክቶ ቃሉን ማስፈሬን አስታውሳለሁ። ዛሬ  ፓርላማ ለመግባት ፍላጎት እንዳለው ለውጪ የዜና አውታሮች ተናገረ ተብሎ ከየአቅጣጫው የሚወረወረው አስተያየት ሪፖርተር በወጉ የዘከረው ጉዳይ በመሆኑ አዲስነቱ አልታየኝም። ከልምድ እንደማውቀው ሃይሌ ነገ “አናጢ መሆን እፈልጋለሁ” ሊል ይችላል። እናም የሃይሌ ዜና ለኔ ዜና አይደለም።  ዜናው ድሮ ተብሎ አልቋል። አሁን አዲሱ ነገር ሃይሌ ያለውን ለመሆን አመቺ ሁኔታ ተመቻችቶለትና ያሰበውን ሆኖ ስናይ ነው። በዜናው ሃይሌ በግልጽ የቀድሞውን አቋሙን ማስቀመጡ ግን አስገርሞኛል። በውጪ አገር ያሉ ተቃዋሚዎች አገር ቤት ገብተው መታገል አለባቸው ማለቱና እንደ ቱኒዚያና ግብፅ አይነት አመጽ ለማስነሳት የሚመኙትን እንደሚታገላቸው መናገሩ ከዋናው ዜና በላይ ታላቅ ዜና ነው። በወቅቱ ሃይሌ ወደፓለቲካው መንደር ለመግባት ስለመፈለጉ ይፋ ሲሆን አንድ ታዋቂ ምሁር  ” ሃይሌ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መሆን ይገባዋል” በሚል በደብዳቤ ምልክት ልከው እንደነበር አስታውሳለሁ።

አትሌት ኃይሌ በመጪው ምርጫ ፓርላማ መግባት ይፈልጋል

*ወደ ፖለቲካ የምገባው ህዝብ ማገልገል ስለምፈልግ ነው
*ኢትዮጵያን አርቀንና በረጅም ጊዜ የማናይ ከሆነ፣አባይን መገደብ አያስፈልገንም
*በውጭ ሆነው የሚቃወሙ አገራቸው ላይ መታገል አለባቸው ባይ ነኝ

ከጥቂት ዓመታት በፊት ጠ/ሚኒስትር የመሆን ፍላጐት እንዳለው ገልፆ የነበረው አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ፤ ሰሞኑን ከአሶሼትድ ፕሬስ ጋር ባደረገው ቃለምልለስ “የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መሆን እፈልጋለሁ” በማለቱ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በ2007 ዓ.ም በሚደረገው አገራዊ ምርጫ ተወዳድሮ ፓርላማ ለመግባት ያሰበው አትሌቱ፤ ከዚያም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት በመሆን ህዝብን ማገልገል እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡
አትሌት ኃይሌ፤ ከጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ፤ ለምን ወደ ፖለቲካ ሊገባ እንዳሰበ፣ ፕሬዚዳንት ሆኖ ቢመረጥ ለመስራት ስላቀዳቸው ተግባራትና ተያያዥ ጉዳዮች አውግቷል።
እነሆ:- የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከአትሌት ኃይሌ ጋር

ሰሞኑን “ፕሬዚዳንት መሆን እፈልጋለሁ”ማለትህን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ከዘገቡ በኋላ ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?
እኔ የምልሽ —- ፕሬዚዳንት እንድሆን ኖሚኔት (አጭታችሁኛል) አድርጋችሁኛል እንዴ? ፕሬዚዳንት የሚመረጠው በገዢው ፓርቲ ኖሚኔት ሲደረግ እና ሁለት ሶስተኛውን የፓርላማና የፌደሬሽን ም/ቤት ይሁንታ ሲያገኝ ነው፡፡ እና ይሄ ነገር ሲደጋገምብኝ —- እንዴት ነው ተጠይቆልኝ ይሆን እንዴ እላለሁ፡፡
ለአሶሽየትድ ፕሬስ በሰጠኸው ቃለ – ምልልስ ላይ ነው ፕሬዚዳንት መሆን እንደምትፈልግ የተናገርከው—
እኔ በእርግጠኝነት የምነግርሽ በ2007 ዓ.ም ፓርላማ እንደምገባ ነው፡፡ ለዚህም ዝግጅት እያደረግሁ ነው፡፡
የት ነው የምትወዳደረው? እዚህ ነው አርሲ?
ኧረ እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ የካ ክፍለከተማ ላይ ነው የምወዳደረው፡፡
ለምርጫ ውድድር የሚጠየቁ መስፈርቶችን እንደምታሟላ አረጋግጠሃል?
በሚገባ! በክ/ከተማው ለመወዳደር ህጉ አምስት አመትና ከዚያ በላይ መኖር አለብሽ ይላል፡፡ እኔ ደግሞ እዚያ ክ/ከተማ ውስጥ 10 ዓመት ኖሬአለሁ፡፡ ምርጫው በሚካሄድበት በ2007 ዓ.ም ደግሞ 12 ዓመት ይሆነኛል ማለት ነው፡፡ እርግጥ በትውልድ ስፍራዬ ሄጄም ብወዳደር እንደማሸንፍ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡
ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን እንደምትፈልግ ተናግረህ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ፕሬዚዳንትነቱ ዞረሃል— የመጀመርያውን እቅድ ለምን ተውከው?
ምን መሰለሽ? በአሁኑ ሰዓት እንኳን እኔ ልጆቼም ሲቪክስ ስለሚማሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ለመመረጥ ምን መደረግ እንዳለበት ያውቃሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን በጣም ረጅም ጊዜ ይወስዳል፡፡ ፓርቲም ማቋቋም ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ፕሬዚዳንት ለመሆን ግን ፓርቲም አያስፈልግም፡፡ ገዢው ፓርቲ ካመነበትና ብቁ ሆነሽ ከተገኘሽ መሆን ይቻላል፡፡ እኔ ደግሞ ለዚህች አገር መስራት አለብኝ ብዬ የማምን ሰው ነኝ፡፡ ገና ጠቅላይ ሚኒስትር እስከምሆን እርጅና ሊጫነኝ ይችላል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ወደ ፕሬዚዳንትነት የዞርኩት፡፡ በነገራችን ላይ ለዚህች አገር ሥራ ለመስራት ጠቅላይ ሚኒስትርም ፕሬዚዳንትም ሆኖ መመረጥ ላያስፈልግ ይችላል፡፡
ፕሬዚዳንት ለመሆን መፈለግህን በተመለከተ ከአገር ውስጥ ሚዲያዎች ይልቅ ለውጭ ሚዲያ በቅድሚያ መንገርህ ቅሬታ የፈጠረ ይመስላል፡፡ አንተ ምን ትላለህ?
የሚገርመው ለአሶሼትድ ፕሬስ ጋዜጠኛ ኢንተርቪው የሰጠሁት በጠቅላላ ጉዳዮች ላይ እንጂ በፕሬዚዳንትነት ላይ አይደለም፡፡ ነገር ግን በጭውውት መሃል “ፕሬዚዳንት ብትሆንስ እንዴት ነው?” በሚል ጥያቄ ሲነሳ፣ ከተሳካ ለምን አልሆንም የሚል ምላሽ ሰጥቻለሁ፡፡ ጋዜጠኛው ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ እሱ የላከላቸው ሙሉ ቃለምልልሱን ነው፡፡ እነሱ ፕሬዚዳንት የምትለዋን ሃሳብ መዘዙና ሲያጐሏት የሁሉም መነጋገሪያ ሆነ፡፡ ከዚያም እነ ሲኤንኤን፣ አልጀዚራ፣ ዘ ጋርዲያን፣ ቢቢሲ ትኩረት ሰጥተው ሲዘግቡት፣ “ይሄን ያህል ትኩረት መሳብና ተጽእኖ መፍጠር እችላለሁ እንዴ” በሚል ግርምት ውስጥ ገባሁ፡፡ “ፕሬዚዳንት መሆን ትፈልጋለህ ወይ” ሲሉኝ “አዎ ለምን አልሆንም” አልኳቸው፡፡ እነሱም ከዚህ ተነስተው ነው “ወደፊት ፕሬዚዳንት ይሆናል” ያሉት፡፡ ስለዚህ ፕሬዚዳንት እሆናለሁ ብዬ፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አስቤበት ለውጭ ሚዲያ ኢንተርቪው አልሰጠሁም፡፡ በዚህ መልኩ የረዱት ካሉ ግን በጣም አዝናለሁ፡፡
የፕሬዚዳንትነት ጥያቄ ቢቀርብልህ ግን ትቀበላለህ?
አሁን ፕሬዚዳንት መሆን የሚጠላ አለ! (ረጅም ሳቅ)
የሚጠላ ሊኖር ይችላል፡፡ መቼም ሁሉም ይፈልጋል አይባልም፡፡
እኔ ግን የሚጠላ ያለ አይመስለኝም—
ስለዚህ እኔም አልጠላም እያልከኝ ነው?
አዎ! ለምን እጠላለሁ — ግን ለምን ትገፋፊኛለሽ? እንደምታውቂው ከዚህ በፊት በፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ ከፍተኛ ፍላጐት እንዳለኝና በ2007 እንደምወዳደር ቆርጫለሁ፡፡ እንደነገርኩሽ ለመወዳደር እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ ፓርላማ መግባቴ የራሴን ሚና ለመጫወት ያግዘኛል፡፡ አሁን ዋናው ትኩረት የሰጠሁት ፓርላማ መግባት ላይ ነው፡፡
በፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎትህ ከምን የመነጨ ነው?
ምን መሰለሽ — ብዙ ጊዜ እንደምንሰማውና እንደምናየው ሁሌ እንተቻለን እንነቅፋለን፡፡ እንደዚያ ከምናደርግ ለምን የምንነቅፈውን ነገር ውስጥ ገብተን ተሳትፈን አናየውም? ብዙ ነገሮች በውጭና በውስጥ ሆነን ስናያቸው ይለያያሉ፡፡ መቃወምም ካለብሽ ውስጥ ገብተሽ ነው፡፡ መንቀፍም ካለብሽ እንደዛው፡፡ ውስጥ ሆነሽ ስትቃወሚ፣ ይሄ ልክ አይደለም ስትይ፣ ልክ ነው ያልሽውን አማራጭ ሃሳብ አብረሽ ታቀርቢያለሽ፡፡ እንደው ዝም ብሎ በደፈናው ይሄ ልክ አይደለም ይባላል፡፡ “እሺ አማራጭ አቅርብ” ሲባል የለም፡፡ ይህ አይነት ነገር ትንሽ ያናድደኛል፡፡ ስለዚህ እኔ ፓርላማ ውስጥ ገብቼ በሌላው አለም ስዞር በፖለቲካው ዘርፍ ያገኘሁትን ተሞክሮ ማካፈልና አማራጭ ሃሳቦችን ማቅረብ፣ ህዝብ ማገልገል ስለምፈልግ ነው፡፡ በፖለቲካ የመሳተፍ ፍላጐቴም ከዚህ የመነጨ ነው፡፡
“በሌላም አለም ስዞር” ስትል—በሩጫው ማለትህ ነው አይደል?
አዎ! እኔ ከመቶ በላይ የአለም አገሮችን አይቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደኔ አለምን የዞሩ ሰዎች ጥቂት ናቸው፡፡ በተለይ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ከኢትዮጵያ ወጥቼ ቤልጂየምን ካየሁ በኋላ፣ ኢትዮጵያ እንድትሆን የምመኘው ነገር አለ፡፡ ስለዚህ ልምዴን ለኢትዮጵያ ህዝብ ማካፈል አለብኝ፡፡
አንተ እንደልብህ መንቀሳቀስ፣ በነፃነት መሮጥ የለመድክ ሰው ነህ፡፡ ፕሬዚዳንት ሲኮን ግን ነፃነት አይኖርም፡፡ እንቅስቃሴህ ሁሉ በጋርድ የታጀበ ነው የሚሆነው፡፡ እንደፈለጉ መሆን የለም፡፡ የምትችለው ይመስልሃል?
እንዲህ አይነት ነገሮች ሲደጋገሙ ያስቁኛል (ረጅም ሳቅ…) ይህንን ጥያቄ ጓደኞቼም ይጠይቁኛል፡፡ በተደጋጋሚ ማለቴ ነው፡፡ “ከእንግዲህ ጫካ ውስጥ ላናይህ ነው” ይላሉ፡፡ ያው በልምምድ ላይ ማለታቸው ነው፡፡ እኔም “የበለጠ የምንሰራው እንደውም ያን ጊዜ ነው” እላቸዋለሁ፡፡ እርግጥ እዛ ደረጃ ላይ ስትደርሺ ያንን ህግና ስርዓት ማወቅ አለብሽ፡፡ ያ ህግና ሥርዓት ደግሞ ለሀይሌ ብቻ ተብሎ የሚደረግ አይደለም፡፡ ቦታው ስለሚያዝ ነው የሚሆነው፡፡ ቦታው ያዛል ስልሽ —– ሃይሌ ገ/ስላሴ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሆኖ የሚደርስበትና እንደ ሃይሌ ገ/ስላሴ እንደራሱ ሆኖ የሚደርስበት ነገር የተለያየ ነው፡፡ እነዚህን ነገሮች የግድ ማወቅ አለብኝ፡፡ የአንድ አገር መሪ ስትሆኚና እንደማንኛውም ሰው ስትሆኚ ይለያያል፡፡
ሰው መሆንና ባለስልጣን መሆን ይለያያል እንደማለት ነው?
አዎ! ለምሳሌ እኔ መሪ ብሆን ከማጣቸው ነገሮች አንዱ ነፃነት የሚባለው ነገር ነው፡፡ እኔ አሁን ሁልጊዜ ግን ሁሉ ነገር እንደሚጠፋ አውቃለሁ፡፡ ስለዚህ ይህን ይህን ሳላስብ ፕሬዚዳንት መሆን እፈልጋለሁ ማለት የማይመስል ነገር ነው፡፡
ሌላው ነገር ፕሬዚዳንትነት የሙሉ ሰዓት ሥራ ነው፡፡ አንተ ደግሞ እጅግ በርካታ ቢዝነሶችን የምታንቀሳቅስ ሰው ነህ፡፡ ይህንንስ እንዴት ታስተናግደዋለህ?
ዋናውና ጠቃሚው ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ በድርጅቴ ስር ከአንድ ሺህ በላይ ሰራተኞች ይተዳደራሉ፡፡ እነዚህንም አስቀድሜ ቦታ ማስያዝ አለብኝ፡፡ ቦታ ማስያዝ አለብኝ ስልሽ — እንደ እኔ ሆኖ ይህን ሃላፊነት ሊሸከም የሚችል ሰው ማዘጋጀት ተገቢ ነው፡፡ እነዚህ እነዚህ ነገሮች ቀድሞ ሊታሰብባቸው እንደሚገባ አይጠፋኝም ማለቴ ነው፡
በእነዚህ ጉዳዮች ላይ አሁን ዝግጁ ነህ?
አሁን ተዘጋጅተሃል ወይ ላልሽው አሁን አልተዘጋጀሁም፡፡ ጊዜ የሚፈልጉ ነገሮች ናቸው፡፡ ስዘጋጅ እነግርሻለሁ፡፡
ፕሬዚዳንት ብትሆን ምን ለውጥ አመጣለሁ ብለህ ታስባለህ? አሁን እንደ ጉድለት የምታያቸውና እሰራቸዋለሁ የምትላቸው ነገሮች ካሉ ብትነግረኝ —-
እኔ እርግጠኛ ሆኜ የምነግርሽ ሥልጣን ባገኝ ብዙ የምሠራቸው ነገሮች እንዳሉ ነው፡፡ ሥልጣኑ የሚኒስትር ይሁን ፕሬዚዳንት በይው— ምንም በይው ግን በርካታ ስራዎችን እንደምሠራ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ቀላል ልምድ ያካበትኩ አይመስለኝም፡፡ የሰሞኑን የእኔን ዜና ዝም ብለሽ ብታይው ይገርምሻል፡፡ ቅድም እንዳልኩሽ —- ይህን ያህል ተደማጭና ተጽእኖ ፈጣሪ ነኝ ወይ እስከማለት ደርሻለሁ፡፡ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የእኔን ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጎት በጣም ትኩረት ሰጥተውት ነበር፣ ስለዚህ ይህንን ነገር ተጠቅሜ የራሴን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብኝ የሚል ፍላጐት አደረብኝ፡፡ እንደ ዲፕሎማትም በይው እንደምንም ሆኜ ማለቴ ነው፡፡
ቀደም ሲል ለአገር ለመስራት የግድ ፕሬዚዳንትም ጠቅላይ ሚኒስትርም መሆን እንደማያስፈልግ ነግረኸኛል፡፡ ታዲያ የምትፈልገውን ነገር ለመስራት ምን የሚያግድህ ነገር አለ?
እውነት ነው የሚያግደኝ ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ነገሮች እየተለወጡ ነው፡፡ ነገር ግን ውስጥ ሆነሽ ነገሮችን ብትመለከቺና ልምድሽን ብታካፍይ የበለጠ ይህቺን አገር መለወጥ ይቻላል ለማለት ነው፡፡ ለዚህም እርግጠኛ ሆኜና አስረግጬ የምነግርሽ በ2007ዓ.ም በየካ ክ/ከተማ እንደምወዳደርና ፓርላማ ለመግባት እንደምጥር ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ብትሆን ምን ምን ሥራዎችን እንደምታከናውን አልነገርከኝም —-
ቅድም እንዳልኩሽ ብዙ ስራዎችን መስራት እንዳለብኝ አስባለሁ፡፡ ለምሳሌ ብዙ በውጭ የሚኖሩ ሰዎች ነገሮች ተስተካክለውላቸው አገራቸው ላይ እንዲኖሩ ማመቻቸት አንድ ሥራ ነው፡፡ መሪ ስትሆኚ የገዢውን ፓርቲ አላማ ነው የምታራምጂው፣ ይሄ ግድ ነው፡፡ የገዢውን ፓርቲ ፕሮግራም ስታራምጂ አብረሽ ተዛማጅ በሆኑ ሥራዎች ላይ ትሳተፊያለሽ፡፡ ግን ፖለቲካውን የማይነኩ ነገር ግን ለዚህች አገር በጣም ጠቃሚ የሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ ሁልጊዜ አገር ስትመሪ መመልከት ያለብሽ፣ የዛሬን፣ የነገን ሳይሆን የሩቁንና የወደፊቱን መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያን አርቀንና በረጅም ጊዜ የማናይ ከሆነ፣ አባይን መገደብ አያስፈልገንም፡፡ ስለዚህ በዚያ ዙሪያ ብዙ ነገሮችን አደርጋለሁ ብዬ አስባለሁ፣ ፓርላማ መግባት አንዱም ጥሩ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት እንኳን ባይኮን ማለት ነው፡፡ ሰሞኑን በፓርላማ ምን ተዓምር እየተሰራ እንደሆነ ለአንቺ አልነግርሽም፡፡ ሌላው በስራ አጥነት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በኤክስፖርት ላይ ብዙ መስራት ይቻላል፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም ኤክስፖርት የምታደርገው በጣም ጥቂት ነው፣ እሱን ማሳደግ ላይ መሠራት አለበት፡፡ ጠቃሚ ያልሆኑ ባህሎቻችን ላይም እንዲሁ፡፡ በእኛ አገር ሰርጋችንም ሀዘናችንም ከአንድ ሳምንት በላይ ይወስዳል፣ ሠርግ ጥሩ ነው? አዎ ጥሩ ነው፣ ግን አንድ ሳምንት ሙሉ ሊወስድ አይገባውም፡፡ ይሄ ወደ ኋላ የሚጐትት ነውና መቅረት አለበት፡፡
ወደ ፖለቲካው የመግባት ፍላጐትህን ባለቤትህ ወ/ሮ አለምን ጨምሮ በርካታ ጓደኞችህና ወዳጆችህ ተቃውመውታል ይባላል፡፡ የአንተ ፍላጐት ደግሞ እየበረታ ነው፡፡ እንዴት ልትቋቋማቸው ነው?
ልክ ነው፡፡ ሚስቴም ልጆቼም፣ ዘመድ ወዳጆቼም ሁሉ አልደገፉትም፡፡ ይሄ ግን መጀመሪያም እዚህ ውሳኔዬ ላይ ስደርስ የምጠብቀው ነገር ነው፡፡ ማንም እንደማይደግፈኝ ማለቴ ነው፣ ለምን እንደሆነ ልንግርሽ? ባለቤቴም ቤተሰቦቼም የእነርሱና የእነርሱ ብቻ እንድሆን እንደሚፈልጉ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር የማረጋግጥልሽ ከበፊት ጀምሮ ወደ ፖለቲካው መግባት ምኞቴ ነበር፡፡
ቤልጂየምን ካየሁ በኋላ ኢትዮጵያ እንድትሆን የምመኘው ነገር አለ፡፡ ድሮ ድሮ አውሮፓ ሄጄ ስመጣ፣ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ህንፃ ቢኖራት፣ እንዲህ አይነት መንገድ ቢኖራት፣ የሚል ምኞት ነበረኝ፣ እሱ እየተሳካልኝ ነው፡፡ ለዚህ ነው በማገኘው ገንዘብ ወዲያውኑ እዚህ እየመጣሁ የምሠራው፡፡ ውጭ ወጥቶ የመስራትና የመኖር አጋጣሚው ስለሌለኝ ግን አይደለም፡፡ እንደነገርኩሽ ያልረገጥኩት አገር የለም፡፡ ዜግነት እንስጥህ ያሉኝ በርካታ አገራት አሉ፣ የሰጡኝም አሉ፣ የተቀበልኳቸውም ያልተቀበልኳቸውም አሉ፡፡ እኔ ግን የማረጋግጥልሽ ኢትዮጵያዊ መሆኔን ነው፡፡ ለምን ብትይ — አማራጭ የለኝም፡፡ ሌላ ምርጫ አላካትትም፡፡ ሰዎች ይህንን ቢረዱልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ተደማጭና ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆንኩ ሰርቼ ማሳየት አለብኝ፡፡ እኔ አገር ጥሎ መጥፋትን ለሰው ማሳየት አልፈልግም፣ አላደርገውም፡፡
ቤተሰቦቼ ፖለቲካ ውስጥ ለምን ገብተህ ትቸገራለህ ይሉኛል፣ ግን የአቅሜን መስራት አለብኝ እላለሁ፡፡ በውጭ ሆነው የሚቃወሙትም እዚሁ አገራቸው ላይ መታገል አለባቸው ባይ ነኝ፡፡ እንደ ግብጽ፣ እንደ ሶሪያ ባለ መንገድ ዴሞክራሲን ለማምጣት ከውጭ የሚመጣ ካለ እኔም እራሴ እዋጋዋለሁ፡፡ እነ ግብጽ ያተረፉት ነገር የለም፡፡ ችግሮች ካሉ ፓርላማ ገብቶ በሰለጠነ መንገድ መከራከር፣ ችግሮችን ማስተካከል የኢትዮጵያዊያን ሃላፊነት ነው፣ ምክንያቱም ሰላም፣ ጥሩ ኑሮ፣ መልካም አስተዳደር እንዲኖር እንፈልጋለን፡፡ እነዚህ ነገሮች ደግሞ ዝም ብለው እንደ ዳቦ የሚታደሉ አይደሉም፡፡ እነዚህን ነገሮች ለማድረግ ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ አድርገን፣ ችግሮቻችንን መፍታት መነጋገር እንጂ አገር ጥሎ ሄዶ እሰው አገር ፖለቲከኛ መሆን አያዋጣም፡፡ ለዚህ ነው የቤተሰቦቼን ተቃውሞ ተቋቁሜ ወደ ፖለቲካው የመግባት ፍላጐቴን ያጠነከርኩት፡፡
ሀይሌ አሁን ሩጫ የሚያቆምበት ዘመን ስለሆነ ላለመረሳት ነው ወደ ፖለቲካው ለመግባት ያሰበው የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ አንተ ምን ትላለህ?

Related stories   አውሮፓ ህብረት - ላለፉት 28 ዓመታት በኢትዮያ ተላላኪ መንግስት እንደነበር ለኢትዮጵያ ህዝብ አመነ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ  http://www.addisadmassnews.com