“Our true nationality is mankind.”H.G.

“እንደኔ እምነት ይህ ሥርዓት እስካልተየቀረ ድረስ የሚዲያ ነፃነት ይኖራል የሚል ተስፋ የለኝም…”

ሚዲያውና የፖለቲካ ተቃውሞዎች የተገናኙበት ነጥብ

ከጥቂት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ በተደረገው የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ፎረም የኢትዮጵያ ሚዲያ ችግር አጀንዳ ባልሆነባቸው የጎንዮሽ የውይይት መድረኮች ጭምር፣ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ መነጋገሪያ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ስብሰባው ኢትዮጵያ ውስጥ ይደረግ አይደረግ የሚለውም በራሱ ማነጋገሩ

የሚዘነጋ አይደለም፡፡ የስብሰባው አዘጋጅ አፍሪካ ሚዲያ ኢኒሼቲቭ (AMI) ዋና ሥራ አስፈጻሚ አማዱ ማሀታር ባ፣ ‹‹ምንም እንኳ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞን የነበረ ቢሆንም ኢትዮጵያ ተገኝተናል፤›› ብለው ነበር፡፡ ቀዳሚ አጀንዳ ባልሆነበት መድረክ ላይ የኢትዮጵያ ሚዲያ በስሜት የሚያነጋግርና የሚዲያ ፎረሙ በኢትዮጵያ መካሄዱ አነጋጋሪ መሆኑ ስለ አገሪቱ ሚዲያ የሚናገረው ግልጽ ነገር አለ፡፡ ሚዲያው ትልቅ ችግር ውስጥ እንዳለ፡፡

አፋኝ የፕሬስ ሕግ መኖር፣ በጋዜጠኞች ላይ ያነጣጠረ የፀረ ሽብር ሕግ፣ ራስን ሳንሱር ለማድረግ መገደድ፣ የጋዜጠኞች ለእስር መዳረግ፣ የፕሬስ ነፃነትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት አለመረጋገጥ በዋነኝነት በመድረኩ ላይ የተንፀባረቁ ነበሩ፡፡ የሚዲያው ሥነ ምግባር መጣስ፣ የሚዲያው መሣሪያ መሆንና የታማኝነት ጥያቄም እንደ ችግር የተነሱ ነበሩ፡፡ የትኞቹ ችግሮች በመሠረታዊነት በምን ያህል ደረጃ ሚዲያው አሁን ላለበት አጠቃላይ ችግር አስተዋጽኦ አድርገዋል? ወይም የትኞቹ ችግሮች መሠረታዊ አይደሉም? የሚለው አከራካሪ ሊሆን ቢችልም ሚዲያው በተጠቀሱት ችግሮች ሁሉ መተብተቡ አያከራክርም፡፡ በሌላ በኩል የግልና የመንግሥት ሚዲያ ከሚለው ክፍፍል በተጨማሪ የሚዲያውን ችግር በመንግሥት የፕሬስ ፕሮፓጋንዳ ላይ፣ በግሉ ፕሬስ የፖለቲካ አቀንቃኝነት ላይ በማተኮርና መሠረታዊ የጋዜጠኝነት መርህን መሳትን በነፀብራቅነት የሚጠቅሱም አሉ፡፡

‹‹
› ለሚለው ቀደም ሲል የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ለነበረውና አሁን የፋክት መጽሔት ዓምደኛ ለሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ የመንግሥት ሚዲያው ልማታዊ ጋዜጠኝነት በሚለው ነገር ግን በማሞካሸትና በፕሮፓጋንዳ፣ የግሉ ሚዲያ ደግሞ በፖለቲካ አቀንቃኝነት መጠመድን በሚመለከት የሚሰነዘረውን አስተያየት በማንሳት ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፡፡

የመንግሥት ሚዲያውን በሚመለከተው አስተያየት ሲስማማ ስለ ግሉ ሚዲያ የሚባለውን እንደማይቀበል ገልጿል፡፡ ለእሱ የግሉ ሚዲያ ራሱ አንድ ዓይነት ቀለም የለውም፡፡ ትርፍ ተኮር፣ ተራ ጉዳዮችን አጯጯሂ፣ በተወሰነ ሁኔታ ድምፅ ለሌለው ሕዝብ ድምፅ ለመሆን የሚሞክሩ በማለት ያስቀምጣቸዋል፡፡ ‹‹ሦስተኛው ዓይነት የግል ሚዲያዎች ለሕዝብ ድምፅ ለመሆን ሲሉ ከመንግሥት ጋር የሚያደርጉት ግብግብ የሥርዓት ለውጥ ወደመጠየቁ መርቷቸው ይሆናል፡፡ ግን እዚህ ላይ እንዲደርሱ ያደረገው ከመንግሥት ጋር የሚደረገው አባሮሽና መተናነቅ ነው፡፡ ድምፅ የሌላቸው ሰዎች ተገፍተው ተገፍተው የሥርዓት ለውጥ እየጠየቁ ነው፡፡ እናም ነገሩ የዚያ ነፀብራቅ ነው፤›› ይላል፡፡

የሚዛናዊነት ችግር በሚዲያው ጐልቶ እንደሚታይ የሚናገረው ተመስገን ይህም የአገሪቷ የፖለቲካ ሥርዓት ያስከተለው ችግር እንደሆነ ሲያስረዳ፣ ‹‹ሚዲያው ድምፅ ላጡ ድምፅ በመሆን የሥርዓት ለውጥ መጠየቅ ደረጃ ደርሷል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ ከተደረሰ ደግሞ ለጋዜጠኝነት መርህዎች መጨነቅ ያስቸግራል፡፡ የኢትዮጵያ ሚዲያ ለዚህ የሚጨነቅበት ጊዜ ያለፈ ይመስለኛል፡፡ የሚዲያው ችግር የጋዜጠኝነት ፍልስፍናን በመከተል ሳይሆን በሥርዓት ለውጥ የሚፈታ ነው፤›› ይላል፡፡

ባሕሪው ተቀይሮ ሕዝብ መብቱን እንዲጠይቅ፣ እንዲያስከብር፣ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ እንዲታገል መንገር ባንድም ሆነ በሌላ መንገድ የፖለቲካ አቀንቃኝ በመሆኑ ይህ የጋዜጠኝነት ሚዛናዊነትን ጥያቄ ውስጥ ሊከት እንደሚችል፣ አንዳንዴም ሚዛናዊነት ሊደፈጠጥ የሚችልበት አካሄድ እንደሚኖርም ያምናል፡፡ ‹‹የትኛውም ስም ቢሰጠው እንደ አንድ ጋዜጠኛ የማተኩረው የሥርዓት ለውጥን የሚጠይቅ ንቃተ ህሊናን መፍጠር ላይ ነው፤›› በማለት ያስረዳል፡፡

ለጋዜጠኝነት መርህ ተገዥ መሆን የሚቻለው ነፃ ሚዲያ ሲኖርና የሚዲያ ምኅዳሩም ይህን ሲፈቅድ ነው የሚል መከራከሪያ የሚያነሳው ተመስገን፣ የፖለቲካ አቀንቃኝነትን እንደ አቅጣጫ የመረጠው ነገ የጋዜጠኝነት መርህ የሚከበርበት ነፃ ሚዲያ እንዲፈጠር መሆኑን ያስረዳል፡፡ ቀደም ሲል በሦስት ለያይቶ ባስቀመጣቸው የግል ሚዲያዎች በሙሉ የጋዜጠኝነት መርህ እየተተገበረ አለመሆኑን በመጥቀስ፣ ‹‹እኛ ግን ቢያንስ በዚህ መስመር እየሄድን ያለነው ነገ እነዚህ የጋዜጠኝነት መርህዎች እንዲከበሩ ነው፤›› ይላል፡፡

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

ተመስገን በአገሪቱ ሚዲያ ላይ የሚታየውን ችግር በሁለት ከፍሎ መመልከት የሚመርጥ ሲሆን፣ ለመጀመሪያው ችግር ምክንያት የሚያደርገው መንግሥትን ነው፡፡ ሁለተኛው ችግር በራሱ በሚዲያው (የግል) ድክመት የተፈጠረ ነው ብሎ ያምናል፡፡

እሱ እንደሚለው መንግሥት በተለያዩ መንገዶች ሚዲያውን ያፍናል፡፡ ለአፈናው ደግሞ የተለያዩ ሕጎችን ይጠቀማል፡፡ የፕሬስ አዋጁን ጨምሮ የፀረ ሽብር ሕጉና ሌሎችም ያልተጻፉ ሕጎች ሚዲያው (የግል ሚዲያው) ራሱን ሳንሱር እንዲያደርግ ያስገድዳል፡፡ በሕግ ቅድመ ምርመራ ባይኖርም ባልተጻፈ ሕግ ቅድመ ምርመራ በመቀጠሉ፡፡ ‹‹የፍትሕ ጋዜጣ አንድ ዕትም በማተሚያ ቤት ተይዞ ተቃጥሏል›› ይላል፡፡

የማተሚያ ቤቶች አለመኖርና ያሉትም አቅም የተወሰነ በመሆኑ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆን ሌላው ሚዲያ ላይ ጫና ማሳደር የሚያስችል ዘዴ መሆኑን የሚናገረው ተመስገን፣ ከሌሎች አገሮች በተለየ ሁኔታ ስም ማጥፋት በወንጀልና በፍትሐ ብሔር መታየቱ ለግሉ ሚዲያ ከባድ ችግር መሆኑን ይጠቁማል፡፡

የመንግሥት ተቋማት ለግል ሚዲያ ማስታወቂያ አለመስጠትና የባለሥልጣናት በቀጥታ ማስፈራራት፣ በተለያዩ መንገዶች የሚዲያውን አቅም የሚያሳጡና እንቅስቃሴውን ችግር ውስጥ የሚከቱ መሆናቸውንም ያስረዳል፡፡

የአቅም ማነስ፣ በዚህ ምክንያት ሥራዎችን በተፈለገው ሁኔታ መሥራት አለመቻል፣ የባለሙያ እጥረት፣ ራስን ሳንሱር ማድረግ፣ የሙያ ብቃት ማነስ፣ ትርፍ ተኮር መሆን፣ እንዲሁም ለመንግሥት ጫና መንበርከክ የግሉ ሚዲያ ችግር ብሎ የሚያነሳቸው ናቸው፡፡

‹‹ሚዲያ እንደ ቢዝነስ ብቻ ሲታይ ሙያዊ ሥነ ምግባሩ ይጠፋል፡፡ ሥርዓቱ ጉልበተኛና ባለጐራዴ ስለሆነ የሚዘግቡትን እንዲመርጡ፣ ይህን ብዘግብና ቢዘጋብኝስ እያሉ ስሌት በመሥራት ለሕዝብ ያላቸውን ታማኝነት እንዲተው ያደርጋል፡፡ ይህ በግሉ ሚዲያ ላይ የሚታይ ትልቅ ችግር ነው፤›› በማለት ተመስገን ይዘረዝራል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርት ጥራት የወረደ በመሆኑ ጋዜጠኝነት ተምረው ከዩኒቨርሲቲ የሚወጡ ተማሪዎች ብቃት ዝቅተኛ መሆኑን፣ በአሁኑ ወቅት ሚዲያ ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞችንም ‹‹ባለሙያዎች ነን›› ለማለት እንደሚቸገር ይናገራል፡፡

የፕሬስ ካውንስል መቋቋሙን በማስመልከት የካውንስሉ አስፈላጊነት ምንም አጠያያቂ ባይሆንም፣ ፕሬስ ካውንስሉን መምራት ያለባቸው እንዴት ያሉ ጋዜጠኞች ናቸው? የሚለውና የተቋሙ ጥንካሬ በሚገባ ሊጤኑ የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው ለተመስገን፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ተቋሙ ትርጉም አይኖረውም፡፡

‹‹ይኼ መንግሥት ነፃ ተቋም እንዲቋቋም ይፈቅዳል ወይ? መጀመሪያ እዚህ ላይ እኛ መተማመን ይኖርብናል፡፡ ይህ ካውንስል ከመቋቋሙ በፊት መንግሥት ያስቀመጣቸውን አፋኝ ሕጎችን እንዲያነሳ፣ ጋዜጠኞችን በወንጀል መክሰሱን አቁሞ በፍትሐ ብሔር እንዲጠይቅና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥ ያስፈልጋል፤›› በማለት አስረድቷል፡፡

ሉሊት ገብረ ሚካኤል ለአሥር ዓመታት ያህል የዴይሊ ሞኒተር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆና ሠርታለች፡፡ በኢትዮጵያና በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች በተለያዩ ጊዜያት ሚዲያዎችን በማቋቋም እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳትፋለች፡፡ ሜትሮፖሊፓን የተሰኘ ጋዜጣም አሳታሚ ነበረች፡፡

የኢትዮጵያ ሚዲያ ችግር ሲነሳ የመጀመሪያው ነገር የፖለቲካው ምኅዳርና የፖሊሲ ማዕቀፎች ቀዳሚ ነገሮች መሆናቸውን ትናገራለች፡፡ ዝቅተኛ የገንዘብ አቅም፣ የሙያ ብቃት ማነስ፣ የሕዝቡ ለሚዲያ ክፍት አለመሆንና ለሙያው የሚሰጠው ዝቅተኛ ወይም አሉታዊ ግምት በተለያየ ደረጃ የምታስቀምጣቸው ችግሮች ናቸው፡፡ ‹‹ሕዝቡ ከጋዜጠኛና ከጋዜጠኝነት የሚጠብቀው ሀቀኝነት በሚገባ መጤን አለበት፡፡ ሀቀኝነት ማለት መንግሥትን መቃወም ማለት ነው?›› በማለት ጠይቃ ጥያቄው ሙያዊ ታማኝነት ላይ የሚያነጣጥር መሆኑን ትገልጻለች፡፡

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

እሷ እንደምትለው ልማታዊ ጋዜጠኝነት የሚል መጠሪያ ሊሰጠው ቢሞከርም የመንግሥት ሚዲያ እያደረገ ያለው ፕሮፖጋንዳ መሆኑን፣ በሌላ በኩል ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ ሲቪል ማኅበረሰብ ባለመኖሩ የግሉ ሚዲያ የፖለቲካ አቀንቃኝነት ላይ አተኩሯል፡፡ ሲቪል ማኅበራት ባለመኖራቸው የግሉ ሚዲያ ላለፉት ሃያ ዓመታት ለተለያዩ ጉዳዮች በፖለቲካ አቀንቃኝነት ውስጥ ማለፉን ታስረዳለች፡፡

ሲቪል ማኅበራት ለምን አልኖሩም? የግል ሚዲያውስ ለምን የፖለቲካ አቀንቃኝነት ውስጥ ገባ? የሚሉት ጥያቄዎች እንዳሉ፣ ‹‹የሙያ መርህ ሊከበር ይገባል፡፡ አንድ ጋዜጠኛ የፖለቲካ አቀንቃኝ ሆኖ ጋዜጠኛ መሆን አይችልም፡፡ እንደ ግለሰብ ጋዜጠኛ የራሱ አመለካከትና የሚያምንበት አቋም ይኖረዋል፡፡ ነገር ግን ጋዜጠኝነት ሚዛናዊነት፣ እውነተኝነትና አድሎአዊ አለመሆንን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ጋዜጠኛ አመለካከቱንና አቋሙን ከሚሠራው ነገር መለየት መቻል አለበት፡፡ ምክንያቱም የሕዝብ አመኔታ መጣስ የለበትምና፤›› የምትለው ሉሊት፣ የግል ሚዲያው በዚህ ረገድ ራሱን መመልከት እንዳለበት፣ ብሔራዊ ጥቅምና የሕዝብ አመኔታ በማንኛውም ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ ሊወድቁ እንደማይገባ ትገልጻለች፡፡

ሚዲያው የመንግሥትና የግል እየተባለ ከመከፋፈሉ በተጨማሪ፣ በግሉ ሚዲያም ሌላ ልዩነት መኖሩን በማመልከት እውነት ልዩነቶች ቢኖሩ ወይም አሉ ተብሎ ቢታሰብ እንኳ ከሁሉም በላይ ሙያውን፣ አገርንና ሕዝብን መሠረት ማድረግ ይገባል የሚል አቋም አላት፡፡ ‹‹ዘርፉ ለውጭ አገር ኩባንያ የሚተው (Outsource) አይደለም፡፡ ታሪካችን መነገር ያለበት አጀንዳችን መቅረብ ያለበት በእኛ ነው፤›› ትላለች፡፡

ሕዝቡን ማስተማር፣ ባለድርሻ አካላትንና ባለሙያውን ስለጋዜጠኝነት ሙያና ሙያዊ ሥነ ምግባር ማሳወቅ የኢትዮጵያን ሚዲያ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ አቅጣጫ ነው የምትለው ሉሊት፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የሠለጠኑ ተማሪዎችን ማውጣትም ትልቅ ተስፋ የሚጣልበት ነገር መሆኑን ትናገራለች፡፡ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ከሙዚቃና ከመዝናኛ ፕሮግራሞች ይልቅ አስተማሪ ነገር ላይ ሊያተኩሩ ይገባልም ትላለች፡፡

ምንም እንኳ የግሉ ሚዲያ ለተቃዋሚዎች ያደላል አንዳንዴም ከእነሱ በልጦ እነሱን በመተካት በመቃወም መስመር ላይ ይገኛል የሚል አስተያየት በተደጋጋሚ የሚሰነዘር ቢሆንም፣ ተቃዋሚዎችም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ባለው የመንግሥት ሚዲያ ብቻ ሳይሆን በግሉም ላይ የተለያዩ ቅሬታዎችን ያሰማሉ፡፡ እነሱም በተመሳሳይ የግሉ ሚዲያ ራሱ ዥንጉርጉር መሆኑን ይስማማሉ፡፡

የመንግሥት የተለያዩ አፋኝ ሕጎችን ማውጣት፣ በተለያዩ ዘዴዎች ሚዲያውን አቅም ማሳጣትና የፍትሕ ተቋማት ነፃ አለመሆን ሚዲያውን ችግር ውስጥ የከተቱ መሠረታዊ ነገሮች መሆናቸውን የሚናገሩት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ አሥራት ጣሴ፣ የግሉ ሚዲያ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አለመግባባትና በፓርቲዎቹ የውስጥ አሠራር ልዩነቶች እስኪፈጠሩ ድረስ የተንቀሳቀሰበት ጊዜ መኖሩን ያስታውሳሉ፡፡

መረጃን ማፋለስ፣ አሉታዊ ነገሮች ላይ ማተኮር፣ ኢፍትሐዊ በሆነ ሁኔታ ለተወሰኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰፊ ዕድል መስጠት እንደ ችግር ያነሷቸው ናቸው፡፡ ይህን ደግሞ ከሙያ ብቃትና ከህሊና ልዕልና ጋር ያያይዙታል፡፡ ነገር ግን የጋዜጠኝነት ሚዛናዊነት መጠበቅ እንዳለበት ያምናሉ፡፡ እሳቸውም በሚዲያው ላይ የሚታዩ ችግሮች መሠረት መንግሥት መሆኑን፣ ‹‹በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እስካልተመሠረተ ድረስ ከአምባገነን መንግሥት ሥርዓት የሚዲያ ነፃነት ይወለዳል ብዬ አልጠብቅም፤›› በማለት መፍትሔው የሥርዓት ለውጥ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

ሚዲያ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን በመጥቀስ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ደግሞ አንድ ዓይነት ሐሳብና አማራጭ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ በመሆናቸው፣ በዚህ ረገድ የሙያ መርህ መጥፋቱን የሚናገሩት የቀድሞው የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሼ ሰሙ ናቸው፡፡ በሌላ በኩል የግል ሚዲያው ጥሬ መረጃን ከማቅረብ በዘለለ ትንታኔዎችን እየሠራ ባለመሆኑ፣ ለሕዝብ የፖለቲካ አማራጭን ለማሳየትና ግንዛቤ ለመፍጠር የሚያስችል ሥራ እየሠራ ነው ብለው አያምኑም፡፡

Related stories   በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ- ትህነግ “ክብሪት” የተባለ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙ ታወቀ፣

ቢሆንም የግል ሚዲያ ተቋማት በገንዘብ አቅማቸው ደካማ በመሆናቸው ሙያዊ ብቃት ያላቸውን ጋዜጠኞች ለመያዝ እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው የሚናገሩት አቶ ሙሼ፣ ለተቋማቱ አቅመ ደካማ መሆንም ተጠያቂ የሚሆነው መንግሥት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ለእሳቸው ሕዝቡም ቢሆን ባለቤትነት የሚሰማውና በተለያዩ ዘዴዎች የግሉን ሚዲያ የሚያበረታታ አይደለም፡፡

በተወሰነ ሁኔታ የሚታየውን ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ ጋዜጠኝነት የፖለቲካ አቀንቃኝነት ለማለት ቢቸገሩም፣ የግሉ ሚዲያና ተቃዋሚዎች አንድ ነጥብ ላይ መገናኘታቸውን የሚናገሩት አቶ ሙሼ፣ ‹‹ተቃዋሚዎች በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ድምፃቸውን ለማሰማት ቦታ ሲያጡ ፊታቸውን ወደ ግሉ ሚዲያ አዙረዋል፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘወትር በመንግሥት ሚዲያ የሚንፀባርቁት አንድ ዓይነት አመለካከት በመሆኑ፣ አማራጭ ፍለጋና ሚዛን ለመጠበቅ በሚል የተለየ ድምፅ ሲፈልጉ አንድ ነጥብ ላይ ከተቃዋሚዎች ጋር ተገናኙ፤›› ይላሉ፡፡

ለእሳቸው አንድ ጋዜጠኛ በግሉ ፖለቲካ አቀንቃኝነት ውስጥ ቢገባ ብዙም ችግር አይደለም፡፡ ችግር የሚሆነው አንድ የሚዲያ ተቋም የፖለቲካ አቀንቃኝነት ውስጥ ሲገባ ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሚዲያው የተለያዩ ሐሳቦች በሚዛናዊነት የሚቀርቡበት ሳይሆን፣ የአንድ ፖለቲካ አማራጭ ልሳን ስለሚሆን ነው፡፡

ወደኋላ ተመልሰው የግሉ ሚዲያ የተገነባበት መሠረት ጥሩ አለመሆኑን፣ እንዲያውም የግሉ ሚዲያ ፅንፈኛ ሆኖ የፖለቲካ አቋም ያራመደበት ጊዜም እንደነበር በማስታወስ፣ አስተያየታቸው ፅንፈኛ አቋም የያዙ የግል ሚዲያዎችን ከትኩረት ውጪ የሚያደርግ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና የኮሙዩኒኬሽን ድኅረ ምረቃ ፕሮግራም አስተባባሪ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የሚዲያ ፕሮፌሽናሊዝም በመንግሥትና በግል ሚዲያ ፅንፍ መካከል አደጋ ላይ መውደቁን ጠቁመዋል፡፡ ጥናታቸው እንደሚያሳየው፣ የመንግሥት ጋዜጠኞች ራሳቸውን እንደ ጀግና የግል ሚዲያ ጋዜጠኞችን ደግሞ እንደ አፍራሾች የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የግል ጋዜጠኞች በበኩላቸው የመንግሥት ሚዲያ ጋዜጠኞችን ለሆዳቸው ያደሩና የመንግሥት ቃል አቀባይ፣ ራሳቸውን ደግሞ የትክክለኛ መረጃ ብቸኛ ምንጭ አድርገው ይቆጥራሉ፡፡

‹‹ጋዜጠኞች የሚሠሩት ለተመሳሳይ ሙያ ሆኖ እያለ አንድ የሚያደርጋቸው የጋራ ብሔራዊ ምክር ቤት የለም፡፡ ያሉት ማኅበራትም የተበታተኑ ናቸው፡፡ የችግሩ ምንጭ ይኼው ነው፤›› ሲሉ ይደመድማሉ፡፡

እንደ ዶ/ር ነገሪ እምነት፣ በኢትዮጵያ የግል ጋዜጠኝነት በአገሪቱ ያለው የፖለቲካ አለመግባባትና ልዩነት ነፀብራቅ ሲሆን፣ ሲጀመር የፖለቲካ አጀንዳ ይዘው በሚንቀሳቀሱ አካላት ቁጥጥር ሥር የወደቀ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቀላሉ ይስተካከላል ተብሎ አይታሰብም ይላሉ፡፡ በተለይ በ1997 ዓ.ም. የታየው በአብዛኛው የግል ጋዜጦች የሥነ ምግባር ችግር እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ በጋዜጠኝነትና የፖለቲካ አቋም በሚያራምዱ ግለሰቦች መካከል ልዩነት መኖር እግዳለበት የሚናገሩት ዶ/ር ነገሪ፣ ችግሩ ግን አሁንም ድረስ በአገሪቱ እየተንፀባረቀ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የመንግሥትና የግል ሚዲያ ሳይባል በአገሪቱ የሚታየውን የሚዲያ ችግር በተመለከተ ያነጋገርናቸው ሰዎች በመሠረታዊነት ተጠያቂ የሚያደርጉት መንግሥትን ነው፡፡ ሚዲያው ሙያዊ መርሆዎችን ሳይከተል ሲቀርና መስመሩን ስቶ በፖለቲካ አቀንቃኝነት ውስጥ ሲጠመድ በቀዳሚነት ከመንግሥት ውጪ ማንን ተጠያቂ ማድረግ ይቻላል የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ነው፡፡

17 NOVEMBER 2013 WRITTEN BY  

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0