“Our true nationality is mankind.”H.G.

“ ህልም እልም ” ድሮ ቀረ!!

“ ህልም እልም ” ድሮ ቀረ!!

ብዙ አይነት ህልሞች አሉ። የውን ህልም ምኞት ነው። የፈጠራ ህልም ድርሰት ነው። የወግ ህልም ትዕቢት ነው። ቦሰና የምታየው አይነት የየዋሆች ህልም አለ። የካፌ ቤት ህልም አድማ ነው። ሁሉም ህልም ክፋት የለውም። ማለም መብት ነው። ለራስ ብቻ መቃዠት አይጎዳም። የቅዠትም  መብት መገፈፍ የለበትም። የተሳሳተ ፍቺ ግን አደጋ አለው። ስቶ ያስታል። ያበደው ስለህልም የሰማውን መልሶ እየለፈለፈ ….. ድንገት  ትዝ ሲለው ባለበት አገር መጮህ ክልክል ነው። ስርዓት ጠብቆ መናገር ግን ይቻላል። ስርዓት የማይጠብቁትንም  ህግ ፊት ማቅረብ ቀላል መሆኑ ታወሰው።

                                       የህትመት ቅድመ ምርመራ ጉዳይ ሲገርመን፣ ሰካይፒና ያሆ በመጠቀም መነጋገር  ያስቀጣል የሚል ህግ ተከተለ፣ ብዙ ህጎች አሉ። ወደፊት የሚጨመሩም አሉ። የወጡ ህጎች የሚመለከቱዋቸውና የማይመለከቱዋቸው ተፈጥረዋል። ልዩነቱ በኑሮ ብቻ አይደለም። ህግ የበላይ የሚሆንባቸውና ህግ የሚሰግድላቸው መኖራቸው ነው። ልማታዊው መንግስታችን ይህንን ቢያስብበት መልካም ነው። የህግ የበላይነት ጥያቄ በየቦታው አለ።

ያበደው ያልተከለከሉ ጉዳዮችን አሰላ። “የቀረውና የተፈራው ህልም ማየትና ህልም መፍታት እንዳይከለከል ነው” በማለት አንድ ወዳጁ የነገረው ታወሰው። አዎ! ማን ያውቃል  ፀሃዩ መንግስታችን ለማለም መደራጀትን እንደግዳጅ፣ መጠርነፍን እንደ አማራጭ ሊያውጅ ይችላል። ያበደው ባሰበውና ባሳሰበው ጉዳይ ከት ብሎ ሳቀ። እውነት ነው ማን ያውቃል? እኒህ ባለ ሚጢጢ አይኖች ህልም የሚያሳብቀውን ጅኒም ይሰሩት ይሆናል። ያበደው ቦሰና ሰለነሱ የምትናገረው ትዝ አለው። ግድግዳ በስታ ምናምን ስትቸረችር  ዱቤ ይወስዱ ነበር። አንዱ በተለይ ወዳጇ ነበር። እዳው ሲበዛና ተጨማሪ ሲጠይቃትና  ስትከለክለው  በቻይንኛ አማርኛ ” ማያምን” እያለ ይምል  ነበር ። እነሱ ሲያውቁን፣ እኛ ተረሳሳን!!

የኑሮ ውድነት ቅዠት ውስጥ የጣላቸውን ቤት ይቁጠራቸው። መንገድ ላይ ቆመው የሚያልሙ ለቁጥር ይታክታሉ።ጤነኞችም በሽተኞችም አላሚዎች ሆነዋል። የረሃብ ህልም ቅጥ የለውም። ከዚህም ከዚያም የህልም ፈቺ ችግር አለ። አቶ መለስ ጥሩ ጥሩ ህልም ተርጓሚ ያስፈልጋቸዋል። እሳቸው ሁሉንም ነገር ህልም  በህልም ስላደረጉት ህልም እንደማያዩ ያበደው በሹክታ ሰምቷል።

በወታደራዊው መንግስት ወቅት ያየትን ህልምና ገራፊ እያዩ ዛሬ ድረስ የሚደነብሩ አሉ። ያኔ በዱላ ብዛት በግድ ህልም ይታይ ነበር አሉ። አንድ የሀደሬ ሰፈር ነዋሪ በዛን ዘመን ስለገጠመው የእስር ቤት ታሪክ ሲያወጋ፣ ቦሰና አለቀሰች። ነጠላዋን እየበላች “ አይ ጊዜ ” አለች። “ ታንክ ጓሮ ቀብረናል ” ብሎ ጀጎልን ያስቆፈረ ነበር። ያበደው ባለቤቱ ቦሰናን  “አትነፍርቂ ” ብሎ መቆጣቱን ያስታውሳል።  እንግዲህ ድሮም ዛሬም አሳላሚና አላሚዎች አሉ። ቅብብሎሽ መሆኑ ነው። ለድጋፍም ይታለማል፣ ለተቃውሞም ይታለማል። አገር በሪፖርት፣ በህግ ብዛትና በህልም ቀደመች። የኢትዮጵያንና የወደፊቱን ትውልድ ህልም  መፍታት የሚችሉ ማፈላለግ ግድ ነው። አስተካክሎ የሚፈታ !!

አማኑኤል ሆስፒታልም ሆነው የሚያልሙ አሉ። ያበደው መረጃ ባያሰባስብም የእብዶች ህልም ፍቺ እንደሌለው ሰምቷል። እብዶች የሚፈልጉትን ባደባባይ ስለሚናገሩ ህልምና ህልም ተረጓሚ አይፈልጉም። ሲነጋም ቢሆን ትዝ አይላቸውም። የተጣሉት በውን ከሚያዩት ዓለም ጋር በመሆኑ ከማያውቁት ዓለም ስሜት ጋር ግብ ግብ አይገቡም። ያበደው የረሳቸው ብዙ ጉዳዮች ታወሱት። አንድ ጊዜ ህልም ይሁን ቀልድ ባይታወቅም እንዲህ ሆኗል፤

አንድ እብዶች የሚታከሙበት ቦታ ነበር አሉ። መታከሚያው በረጅም ግምብ ዙሪያው ታጥሯል። እዚሁ ቦታ ለህክምና የሄደ አንድ ሰው ክልሉ ውስጥ እንደገባ ጫጫታ ይሰማል። ጫጫታው ድምጹ እንጂ ከየት ሆነው እነማን እንደሚንጫጩ ለማየት አጥሩ ይከለክላል። ታካሚው ድምፁን ለመስማት ተረጋጋ። ጆሮውን አሾለ። አዳመጠ። አስራ ሶስት፣ አስራ ሶስት፣ አስራ ሶስት…. እያሉ ነበር የሚጮሁት። የእብድ ቀልድ !!

ግራ የተጋባው ታካሚ፣ “ አስራ ሶስት፣ አስራ ሶስት…” እያሉ የሚጮሁትን ለመመልከት ዙሪያውን ሲማትር ቆይቶ አንድ ሽንቁር ቀዳዳ አገኘ። አጮልቆ ባንድ አይኑ በሽንቁሩ ሲመለከት ጩኸቱ ተቀየረ። “ አስራ አራት፣አስራ አራት፣አስራ አራት…” እያሉ መጮህ ጀመሩ !! አሰራ  አምስት፣ አስራ ስድስት፣ …………. ሃያ፣ ሃያ አንድ፣ ሃያ…… ሃምሳ ?  እንዲህ ያለ ነገር ህልም ባይሆንስ? አይን እያጠፉ እንደ ቅርጫት ኳስ ጎል ማሽካካት፤

ሰው በውኑ፣ እያወቀ፣ ሳይተኛ፣ ሳይታመም፣ በማያውቀው ጉዳይ ገብቶ ይፈርዳል። በማያውቀው ጉዳይ ይመሰክራል። ፍጹም መረጃ በሌለው ጉዳይ ሌላውን ይቀባል። ምንም ነገር መሆን ያንድ ሰው መብትና ፍላጎት እንደሆነ የሚዘነጉ አሉ። በእንደዚህ አይነቱ መንገድ  “ አይናቸው የተደነቆለ ” ለማን አቤት ይላሉ? ያበደው ጠየቀ ? መልስ ማግኘት ባይችልም ድርጊቱ አስገረመው።  የሰለጠነ ምድር ላይ በዚህ መሰል ችግር የተጠመዱ ካሉ ያሳዝናሉ።

አዎ!! ብዙ ሊያቀራርቡና ሊያላልሱ የሚችሉ ጉዳዮች አሉ። ግን እንዴት ተደርጎ? መለስና ፓርቲያቸው በሚወቀሱበት ጉዳይ ሳናስበው ተዋናይ የሆን አለን። የፖለቲካ ጨዋታ ዋና አላማ ደጋፊ ማብዛት ሳይሆን ደጋፊ መቀነስ ተደርጎ የተወሰደ ይመስላል። በስድብና በቀድሞ አስተሳሰብ የሚሮጡ አሉ። እጃቸው የገባውን እየገፈተሩ አዲስ የሚናፍቁ አይታጡም። የበረገጉትን የሚሰበስብ ሲመጣ አስቀድሞ “ እገሌ ማን ነው ” ሚል ህልም ቢጤ ይደረስለታል። አዲስ ሃሳብ ብቅ ሲል እድል አይሰጠውም። እድል ታላቅ ነገር ነው። አለመታደል መረገም ነው። የታደላችሁ አመስግኑ!! ያበደው በታደሉ ይቀናል።

አጠገባችን፣ እጎናችን፣ እጉያችን፣ ያልተጠኑ፣ ያልተጎበኙ፣ ያልተዳሰሱ፣ ያልተዘከሩ በርካታ ጉዳዮች አሉ። የካምፕ ህይወት!! ስደት ራሱ፣ አገር አልባ መሆን፣ ማንነትን፣ ባህልን፣ ወግን፣ ወገንን፣ እናትን፣ ልጅን፣ አባትን፣ ጓደኛን ማጣት፣ አብሮ አደግን መክሰር፣ ያበደው እንባው ቀረረ። “ ሰው በቂጣ ብቻ አይኖርም ” ያለው ጌታ ታወሰው። ” አንተን አስፈቅጄ ባልሰደድም እኔንና ወገኖቼን እርዳን። ምድራችንን  …… ” ያበደው ፀሎቱን አቋረጠ። ብዙ ጉድለት። ጎዶሎ ህይወት። ይህ ሁሉ ሳያንስ አለመስማማት። እንደ ሸቀጥ መመዳደብ!! የበሰለ እያለ ለቃሪያው መሻማት፣ መቧቀስ፣….

ብዙ አይነት ህልሞች አሉ። የውን ህልም ምኞት ነው። የፈጠራ ህልም ድርሰት ነው። የወግ ህልም ትዕቢት ነው። ቦሰና የምታየው አይነት የየዋሆች ህልም አለ። የካፌ ቤት ህልም አድማ ነው። ሁሉም ህልም ክፋት የለውም። ማለም መብት ነው። ለራስ ብቻ መቃዠት አይጎዳም። የቅዠትም  መብት መገፈፍ የለበትም። የተሳሳተ ፍቺ ግን አደጋ አለው። ስቶ ያስታል። ያበደው ስለህልም የሰማውን መልሶ እየለፈለፈ ….. ድንገት  ትዝ ሲለው ባለበት አገር መጮህ ክልክል ነው። ስርዓት ጠብቆ መናገር ግን ይቻላል። ስርዓት የማይጠብቁትንም  ህግ ፊት ማቅረብ ቀላል መሆኑ ታወሰው።

በህልም፣ በተስፋ፣ በጉራ፣ በአማላጅነትነት፣ በሰብአዊነት ….. ቆረጣ የሚጫወቱ አሉ። የቆረጣ ነገር ለሚገባቸው ይገባቸዋል። ስካይፒ ኢኮኖሚ ይጎዳል ሲባል ቆረጣ ነው። መረጃ መቀባበልን በህግ ለመዝጋት የተፈጠረ ድርስት ይመስላል። አገራችን በአፋኝ ህጎች እየመራች ነው። ብቻ ላስተዋለ ምልክቱ የመወጣጠር ነው። ከዚያም ከዚህም ውጥረት አይሏል። የአራት ኪሎ  አጉሟል። የአውሮፓን ክረምት መስሏል።

ይህንን አደርጋለሁ፣ ይህንን አደርግልሻለሁ፣ ይህንን እናደርጋለን፣ ይህንን ያደርጉላችሁዋል፣ … ወዘተ በማለት የማይጨበጥ፣ እንደ ጉም የሚተን ተስፋ ከዚህም ከዚያም ይሰማል። ቀናነት ራሱ ህልም ሆኗል። በቀናነት የማይሆን ነገር ይሰብራል። የቁም ህልም ክፉ ነው። እንዲህ ያለ ህልም በዝቷል። እንዲህ እደረጋለሁ፣ እናደረጋለን ማለት ብቻውን አልሰራም። ህልም ነው። እንደውም ቅዠት ነው። ቅዠት ገለባ ነገር ነው። ከሃያ ዓመትና ከሃያ ዐመት በፊት በህልም ኖርን። መንግስቱ ስለ ዳቦ ቅርጫት፣ መለስ ስለ ሶስቴ መብላት  አስረግጠው የነገሩን ህልም ነው። ከህልም ስንነቃ “ዋይ ዋይ”  እያልን ነው። ቅንጅት መንፈስ ነበር……መንፈስ ሆኖ ሆኖ  በብልጠትና በስርዓቱ  ርኩስነት ….. ያበደው ” ህዝብ ምን ተጠቀመ ” ሲል ጠየቀ። ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው!! ያበደው ዘለለ። የሰማቸውንና ያያቸውን ዋቢዎቹን አሰበ።

የራሳቸውን ህልም የሚፈቱ አሉ። ለነዚህ ሰዎች “ህልም እንደፈቺው ነው” የሚለው ተረት አይገባቸውም። ለራሳቸው ያልማሉ። ለራሳቸው  ይፈታሉ። “ ህልም እልም ” ሲሉ አይሰማም። ስላለሙትና ስለፍቺው ለሌሎች ሲናገሩ ፍፁም አዋቂ ሆነው ነው። “ይመስለኛልን” ሰምተው “ይመስለኛል” እያሉ ህልምን በህልም ሲፈቱ የኩራትና የመጀነን ስሜት ይታይባቸዋል። ያበደው ህልምና ፊልም አዘውትሮ ያየው፣ የራሳቸውን ህልም የሚፈቱትን በተመስጦ ለማዳመጥ እድል ያገኘው ሙታክ ውስጥ ነው። ሙታክ የስደተኞች መኖሪያ ካምፕ!! ያበደው አጥወለወለው  ለሙታክ ነዋሪዎች መፍትሄ የሚፈለገው እንዴት ነው?  ሰማዩና ምድሩ የዞረባቸው ምርጥ ምርጥ ልጆች አሉ። ዝም ብለው ውለው፣ ዝም ብለው የሚያድሩ አሉ። ሰው መሸሽ የጀመሩ አሉ። ከዚያም የባሰባቸው ….. እናስ ? አይ ስደት ኩራት? አይ ተሰዶ ትልቅነት? ሰው ብንሆን ከዚህ በላይ ሊያፋቅር የሚችል ምን ይኖራል? ያበደው ያላቸውን የሚያካፍሉ፣ በስጋም በነብስም የሚያረጥቡትን፣ ስራዬ ብለው ወገኖቻቸውን የሚያስቡትን፣ ለተቸገሩ በረው ከተፍ የሚሉትን….. ምርጦች አስታወሰ። ምርጦች በየፈርጁ አሉ። አለም ዥጉርጉር ነች።  ሁሉን አግበስብሳ ትበራለች።

ሙታክ!! ውበት የለቀቀባቸው፣ ውልውል ብለው የሚያብረቀርቁ ማገዶ የማይፈጁ ያሉበትን ያህል፣ እንደ አቦል ቡና ቀደም ቀደም የሚሉትን፣ በብርሃን ፍጥነት ካልበረርን የሚሉትን፣ ቀልጣፋ ነኝ …. የሚሉትን አርግቦ ስም የሚያስለውጥ ገዳም ነው። ኢዮቦች!! ሙታክ ውስጥ ቀኑን በለሊት ተክተው፣ በለሊት እየቆሙ፣ በቀን የሚተኙ ብዙ ናቸው። በተለይ ብዙ የቆዩት ….. ያበደው ማስታወሻውን ከፈተ። ቀንና ለሊትን አደባልቀው ከሚኖሩ ከየአቅጣጫው የሰበሰበውን ተመለከተ። የሌላውን ዓለም  ነዋሪዎችን ህልም በይደር አስቀመጠው። ቦሰና ዛሬ ድረስ “ ህልም እልም ” ትላለች። ህልም እልም ባትልም ህልም ራሱ እልም እንደሚል ቢነገራትም ሊገባት አልቻለም። ዛሬም “አናሎግ” ነች። ያበደው ደክሞታል። አሁን ማረፍ አለበት ሲነጋ ሰንበት  ነው። በሰንበት ዋናው ፋጣሪም እረፉ ብሏል። እንረፍ፤ ቢያንስ ከቀኑ ክፋት እናመልጣለን!! “ብሄር ብሄሮችን ያማከለ አንድነት ይስጠን ” የዘመኑ ለማኞች ምርቃት ነው። የሚሰጣቸውን ስለሚያውቁ ሰጢውን ማስደሰት ግድ ይላል። ሲርብ ችግር ነው። ግን እኮ እውነት ነው። የብሄር ብሄረሰቦች ጉዳይ የታተመበት ጉዳይ ነው። በብሄር ብሄረሰቦች ጉዳይ ህልም እልም ብሎ ነገር እቃ እቃ የመጫወት ያህል ነው። ለምሳሌ ኦሮሞዎች ብዙ ናቸው። በህልም መሆኑ ቀርቶ በውናቸው አስተዳዳሪ ቢሆኑ ጸብ የለም። ቀጥሎ አማራ ነው። ቀጣዩ ….. ተወደደም ተጠላም እውነቱ ይህ ነው። ይህንን ያልተቀበሉ ከዘላለም እንቅልፍ አልነቁም። መለስም ላይጨርሱ ጀምረው ያንጠለተሉት ጉዳይ  ነውና!! ያበደው  የሚያውቃቸው የአዲሱ አንድነት ኬሚስትሪ ያልገባቸው ብዙ ናቸው። ህልም እልም ይሏል ይሄ ነው። ሰላም !!

የህልሙ ርዕስ – የባቄላ እሸት

ህልሙ የታየው – 2011 ግንቦት ወር

ህልሙን ያው – በለጠ / ለስም ጥንቃቄ የተቀየረ ስም/

የህልሙ ይዘት – እውነተኛ  ታሪክ ላይ የተመሰረተ አድቬንቸር

ህልሙ የታየበት ሰዓት – ባገራችን አቆጣጠር  ሊነጋጋ ሲል

ህልሙን የፈታው – ራሱ በለጠ

የህልሙ ተራኪ – ያበደው ………. መልካም ሰንበት ለዛሬ ሳምንት እንገናኝ!!

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0