‹‹የተወጣሁት ሃይማኖታዊ ግዴታዬን ነው››

በባህርዳር ከተማ መስቀል አደባባይ በተካሄደው የደመራ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር ከፍተኛ  ተቀባይነትን ያገኙትና የሰሞኑ አገራዊ የመወያያ አጀንዳ የሆኑት የባህርዳር ምዕራብ ጎጃም አዊና  መተከል አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ አብርሃምን የብአዴን ከፍተኛ  አመራሮች ከትናንት በስቲያ አነጋገሯቸው፡፡ ከውስጥ አዋቂ ምንጮች ባገኘነው መረጃ መሰረት፤  የብአዴን ከፍተኛ አመራር ከሆኑት የመንግስት ባለስልጣናት መካከል የፌደራል አርብቶ አደር  ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃንና በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ህላዊ ዮሴፍ ናቸው፤  ጳጳሱን ያነጋገሩዋቸው፡፡ የንግግራቸው አጀንዳም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይና መደረግ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ እንደሆነም ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በባለስልጣናቱና በአቡነ አብርሃም መካከል  የተካሄደውን ውይይት ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ባንችልም፣ ባለስልጣናቱ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ መንግስት ምን ማድረግ እንደሚገባው አባታዊ ምክራቸውን እንዲሰጡ አቡነ አብርሃምን መጠየቃቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በባህርዳር ከተማ መስቀል አደባባይ ላይ በተከናወነው የደመራ በአል ላይ ለምዕምኑ ንግግር ያደረጉት አቡነ አብርሃም፤ ‹‹የምናገረው ፖለቲካ አይደለም፤ እንደዛ ነው የሚል እንደፈለገ ይተርጉመው፡፡ ሁልጊዜም ቢሆን ችግር የሚፈጠረው በመሪ እንጂ በተመሪ አይደለም፤ የህዝቡ ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡ ወታደሩ ከዚህ በኋላ የሰላምን ምላጭ እንጂ የመሳሪያን ምላጭ መሳብ የለበትም። መንግስት የተሸከመው መሳሪያ ከክርስቶስ መስቀል አይበልጥም ‹‹ሲሉ ልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በሥፍራው የደመራን በዓል ለማክበር የተሰበሰበው ምዕመን በጳጳሱ ንግግር

በመደሰት ስሜቱን በእልልታና በጭብጨባ የገለፀላቸው ሲሆን እሳቸውም ‹‹የምናገረው እውነት ነው፤ ጭምብጨባም ሆነ ሙገሳ አያስፈልገውም›› ብለዋል፡፡ የደመራ በዓሉ ሲጠናቀቅም ‹‹በስፍራው የተሰበሰበው ምዕመን፣ በሰላም ወደየቤቱ መግባቱን ሳላረጋግጥ ከዚህ አልሄድም›› በማለት ህዝቡ ወደየቤቱ መሄዱን አረጋግጠው ሄደዋል፡፡ የአቡነ አብርሃም ሃይማኖታዊ ንግግር በማህበራዊ ሚዲያ የመነጋገርያ አጀንዳ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ጳጳሱ በደመራ በዓሉ ላይ ያስተላለፉት መልዕክት የብዙዎችን ስሜት በእጅጉ የነካና ለበርካታ
የሃይማኖት አባቶች ትምህርት ሊሆን የሚችል እንደሆነም አስተያየት ሰጪዎች ጠቁመውናል፡፡
መልዕክቱ ምዕመኑ በቤተክርስቲያኗ ላይ የነበረውን ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በአስገራሚ ሁኔታ የቀየረና ሁሉንም የእምነት ተከታዮች አንድ ያደረገ መሆኑን የገለፁልን የባህር ዳር ከተማ  ነዋሪ የሆኑት አቶ ማስረሻ ተስፋሁን፤ ቤተ ክርስቲያኒቷ ዛሬም ሰው አላት ያሰኘና እውነትን መሰረት ያደረገ መልዕክት ነው ብለዋል፡፡
አቡነ አብርሃም እንደ ሃይማኖት አባትነታቸው ማድረግ የሚገባቸውን ነገር ነው ያደረጉት፤ መገረም
ካለብን የምንገረመው እንደ እሳቸው ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን ሳይጠብቁ  የሃይማኖት አባቶች ነን
ባዮች ነው ያሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ፤ ሁሉም የሃይማኖት አባቶች ለህሊናቸውና ለሃይማኖታቸው አድረው እንዲህ በአደባባይ እውነትን የሚመሰክሩበት ቀን ሩቅ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡ የሃይማኖት አባቶችን የሚናገሩለትና የሚሰብኩለት ክርስቶስ፤ ስለ እውነት ሞቶ ያስተማራቸውን እነሱም በተግባር ሊያሳዩን ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከሰሞኑ የአቡነ አብርሃም ንግግር ጋር በተያያዘ በባህር ዳር ከተማ ዙሪያ ግምገማ መካሄዱንም ምንጮቻችን ጠቁመዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የጠየቅናቸው አቡነ አብርሃም፤ በሰጡት ምላሽ “በወቅቱ የተናገርኩት መናገር ያለብኝን ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ግዴታዬን ነው የተወጣሁት፡፡
ከዚህ በዘለለ ለጋዜጠኞችም ሆነ ለሌላ አካል መግለጫ መስጠት አልፈልግም” ብለዋል፡፡

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ  Addisadmass newspaper

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *