- ዳዲ፡፡
- አቤት፡፡
- ምንድን ነው ያወጣችሁት?
- ምን አወጣን?
- አሁን ጓደኞቼ ደውለው ጠይቂው ብለውኝ ነው፡፡
- ምንድን ነው የምትጠይቂኝ?
- ሰሞኑን ስላወጣችሁት አዋጅ?
- እ… ስለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ?
- ምንድን ነው ዳዲ?
- ምኑ?
- አዋጁ ነዋ፡፡
- አንቺን እሱ አይመለከትሽም፡፡
- ምንድን ነው የሚመለከተኝ?
- እኔ አንቺ ላይ ያወጅኩት አዋጅ፡፡
- የምን አዋጅ ነው ያወጅክብኝ?
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፡፡
- እና እሱ ምንድን ነው?
- ከቤት መውጣት አትችይም!
- ምን?
- መጠጥ ቤት ማምሸት አትችይም!
- ለምን?
- እኔን ጥያቄ መጠየቅ አትችይም!
- እሺ፡፡
- እኔ ሳወራሽ ፊት ለፊት ማየት አትችይም!
- እ…
- መኝታ ቤትሽን በፈለግኩት ሰዓት መበርበር እችላለሁ!
- እ…
- ከመኝታ ቤትሽ የፈለኩትን ዕቃ መውሰድ እችላለሁ!
- እ…
- መኝታ ቤትሽ ውስጥ ያለውን ቲቪ እወስደዋለሁ!
- እ…
- ዲኤስቲቪና ዲሽ ማየት አትችይም!
- እና ምን ልይ?
- ኢቢሲ እሱንም በአንቴና፡፡
- እሺ፡፡
- የመኝታ ቤትሽን ኢንተርኔት አቋርጠዋለሁ!
- እ…
- ሞባይል ስልክሽን እቀማሻለሁ!
- እ…
- ሚኒስከርትና አጫጭር ቁምጣ ማድረግ አትችይም!
- እ…
- ጥፍር ቀለም መቀባት አትችይም!
- እ…
- ከቤት የምትወጪው ልማታዊ ስብሰባ ካለሽ ብቻ ነው!
- እ…
- ከጓደኞችሽ ጋር ተሰብስበሽ እኔን ማማት አትችይም!
- እ…
- ቀሪውን ዝርዝር ሳስታውሰው እነግርሻለሁ፡፡
- ምን አድርጌ ነው ግን ዳዲ?
- በጣም አስቸጋሪ ሆነሻል፡፡
- ማንን አስቸገርኩ?
- እኔን፣ እናትሽንና ወንድሞችሽን፡፡
- ዳዲ እኔ ግን ልጅህ ነኝ፡፡
- ቢሆንም አዋጅ አዋጅ ነው፡፡
- እና ሁሉንም ነገር ተከልክያለሁ?
- እንደዛ ማለት አይቻልም፡፡
- ታዲያ ምንድን ነው የተፈቀደልኝ?
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቢሮ እየሄዱ ነው]
- አንተ ቀስ በል እንጂ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ሆነሃል?
- ምነው ክቡር ሚኒስትር?
- ቀይ መብራት ነው እኮ የጣስከው?
- ታዲያ ምን ችግር አለው?
- እንዴት ችግር የለውም መብራት እየጣስክ?
- ቸኩሉ ተብሏል አይደል እንዴ?
- ማን ነው ያለው?
- አዋጁ ነዋ፡፡
- የትኛው አዋጅ?
- የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፡፡
- ምን?
- ክቡር ሚኒስትር ምን ሆኑ?
- አንተ ምን ሆንክ?
- ዛሬ እንዴት ቁርስ እንደበላሁ ያውቃሉ?
- እንዴት ነው የበላኸው?
- በችኮላ፡፡
- እ…
- ያቺን ኪኒን የምታክል ዳቦ በትኩስ ሻይ አወራርጃት ምላሴ ራሱ አሯል፡፡
- ሰውዬ ጤነኛ ነህ?
- ክቡር ሚኒስትር ጊዜው የችኮላ ነው፡፡
- ማን ነው ያለህ?
- አስረድቶኛል በደንብ፡፡
- ማን ነው ያስረዳህ?
- ሁሌ የማመሽበት መጠጥ ቤት ነዋ፡፡
- ማለት?
- አንድ ሁሉን አዋቂ ጓደኛ አለኝ፡፡
- እሺ፡፡
- እንዲያውም ቅጽል ስሙ ጉግል ነው፡፡
- ለምን?
- በቃ ሁሉን ነገር ያውቃል፡፡
- እሺ፡፡
- እና ስለአዋጁ አስረድቶኛል፡፡
- ምን ብሎ?
- በቃ ሁሉን ነገር በአስቸኳይ ማስፈጸም መሆኑን ነዋ፡፡
- እ…
- እንዲያውም አሁን በአስቸኳይ ከመንጃ ፈቃድ ወደ ማስተርስ መገልበጥ አለብኝ፡፡
- ምን አልክ?
- ከዚች ኮንዶሚኒየም ቤት ወደ ቪላ በአስቸኳይ መግባት እንዳለብኝ ገብቶኛል፡፡
- መቼም የማታመጣው ነገር የለም፡፡
- ሚስቴንም በአስቸኳይ ውጭ ሄዳ እንድትወልድ ላስደርግ ነው፡፡
- እ…
- እንዲያውም የልጄን ስም ራሱ…
- እ…
- አስቸኳይ ብየዋለሁ፡፡
- አንተ?
- ክቡር ሚኒስትር መቼም እናንተም በአስቸኳይ ትለውጡታላችሁ አይደል?
- ምኑን?
- ዴሞክራሲውን!
[ክቡር ሚኒስትሩ አንድ ሚኒስትር ጋ ደወሉ]
- አቤት ክቡር ሚኒስትር፡፡
- የጀርመኗ ቻንስለር ትመጣለች አይደል?
- አዎን ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ላገኛት እፈልጋለሁ፡፡
- እንዴ ክቡር ሚኒስትር?
- ምነው?
- ጉብኝቷ ከእርስዎ መሥሪያ ቤት ጋር አይገናኝም፡፡
- የንግድ ልዑክ አይመጣም እንዴ?
- ኧረ የቻንስለሯ የጽሕፈት ቤት ሰዎች ናቸው የሚመጡት፡፡
- እንዴት የንግድ ልዑክ አይመጣም?
- እነርሱም እኮ ከእርስዎ መሥሪያ ቤት ጋር አይገናኙም፡፡
- በግሌ ነው የፈለግኳቸው፡፡
- ለምን?
- ጀርመኖች እኮ አሪፍ ዕቃ ነው ያላቸው፡፡
- ማለት?
- አሪፍ አሪፍ ዕቃ ነዋ ያላቸው፡፡
- እና ቢኖራቸውስ?
- ከቻይና ዕቃ ይሻላል ብዬ ነዋ፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር አደብ ይግዙ፡፡
- ምን አደረግኩ?
- በአደባባይ አደረጉት፡፡
- ምኑን?
- ኪራይ ሰብሳቢነቱን፡፡
- ዕቃ ላስመጣ እኮ አይደለም፡፡
- እና ምን ሊያደርጉ ነው?
- ዕቃ አስመጪዎችን ከዕቃ አምራቾች ጋር ላገናኝ፡፡
- ሊደልሉ?
- ድለላ ሳይሆን የኮሚሽን ሥራ ነው፡፡
- ምን?
- የኮሚሽን ሥራ፡፡
- ኧረ ክቡር ሚኒስትር ይህን አሳፋሪ ተግባር ያቁሙ፡፡
- ስማ ሥራዬን ከማንም በላይ ነው የምሠራው?
- ማለት?
- ኮሚሽን ከፍላችሁት ራሱ የሚሠራላችሁ ሰው የታለ?
- እውነት ብሶብዎታል፡፡
- ለማንኛውም የመጣ ቢመጣ አላቆምም፡፡
- ምኑን?
- የኮሚሽን ሥራዬን!
[ክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊያቸውን አስጠሯት]
- ትናንት በጊዜ ለምን ወጣሽ?
- ፈርቼ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድን ነው የፈራሽው?
- ትራንስፖርት የለም ሲሉ ሰምቼ፡፡
- ለምንድን ነው የሌለው?
- ያው በጊዜያዊው ግርግር ነዋ፡፡
- ሥራ ግን እንዳትበድዪ፡፡
- እሺ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ለመሆኑ ቀጠሮ አለኝ?
- ኧረ ምንም የለዎትም፡፡
- ቀኑን ሙሉ?
- ከሰዓት አለዎት፡፡
- ጠዋትስ?
- ከአማካሪዎ ጋር ስለሚወያዩ አስታውሺኝ ብለውኝ ነበር፡፡
- በቃ ጥሪው፡፡
[አማካሪያቸው ቢሮ ገባ]
- አንተ!
[ዝም]
- ስማ እንጂ፡፡
[ዝም]
- እያናገርኩህ እኮ ነው?
[ዝም]
- አንተን አይደል እንዴ?
- ለምን አይተውኝም ክቡር ሚኒስትር?
- በጣም ነው የተናናቅነው፡፡
[ዝም]
- አንተ ሰውዬ፡፡
[ዝም]
- እኔ ጠፋሁ፡፡
[ዝም]
- አውራ፡፡
- አውራ ፓርቲው ምን ሆነ?
- ማን ስለእሱ ጠየቀህ?
- ስለምኑ ነው የጠየቁኝ ታዲያ?
- ለምንድን ነው የማታወራው?
- ፈርቼ፡፡
- ምኑን?
- አዋጁን፡፡
- ለምን ፈራኸው?
[ዝም]
- አንተን እኮ ነው፡፡
[ዝም]
- መልስልኝ እንጂ?
- ምላሼ አንድ ነው?
- ምንድን ነው ምላሽህ?
- ዝምታ!