“Our true nationality is mankind.”H.G.

በሰበታ 1000 ሰዎች ታስረው ነበር

አዲስ አበባ አጠገብ በምትገኘው የሰበታ ከተማ ባለፈው ወር መጨረሻ በተከሰተ አመፅ እና ግጭት ተሳትፈዋል የተባሉ አንድ ሺህ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው እንደነበር የከተማዋ ከንቲባ ገለጹ፡፡ ከንቲባ አራርሳ መርዳሳ ለዶይቸ ቨለ እንደተናገሩት ታሳሪዎቹ መስከረም 24 እና 25 በሰበታ ከተማ “ረብሻ ላይ የነበሩ፣ ፋብሪካዎች እና መኪናዎችን ያቃጠሉ እና በቡድን ሆነው መንገድ ሲዘጉ ነበሩ” በሚል የተጠረጠሩ ናቸው፡ “ያኔ መኪና እና ፋብሪካ ሲያቃጥሉ አንድ ላይ ያንን ለመመከት ተብሎ ያኔ የተያዙ ናቸው አንድ ሺህው እንጂ ተጠርጣሪ ተብሎ በየቦታው በመረጃ የተያዙ አይደሉም፡፡ እና ወዲያውኑ ተይዘው፣ ተጣርቶ ከዚያ ውስጥ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች ከተለዩ በኋላ ሌሎቹ እንዲለቀቁ የተደረገው ” ይላሉ ከንቲባው፡፡

ከሁለት ሳምንት በፊት በሰበታ ከተማ በነበረው አመጽ 11 ፋብሪካዎች እና 62 ተሸከርካሪዎች መቃጠላቸውን መንግስት ገልጾ ነበር፡፡ በድርጊቱ “ተሳትፈዋል”በሚል በእስር ላይ ከነበሩት ውስጥ “ከግማሽ በላይ የሚሆኑት” በአሁኑ ወቅት እንደተፈቱ የሚናገሩት ከንቲባው የቁጥር መረጃ ግን በእጃቸው ላይ እንደሌለ ያስረዳሉ፡፡ ትክክለኛ ቁጥሩን ማወቅ የሚፈልግ ከፖሊስ ማግኘት እንደሚችል ይናገራሉ፡፡

Related stories   የሲኤንኤን ዘጋቢ ኒማ- በተወነችው ተውኔት ውስጥ ዳግም ሞት የተፈረደባቸው ዜጎች

“መረጃ የተገኘባቸው እና ያልተገኘባቸውን የሚለየው፣ የሚመረምረው ፖሊስ ነው፡፡ ፖሊስ ይህን አጣርቶ ሲጨርስ ለህዝብም ይፋ ያደረጋል፡፡ የሚለቀቁ ሰዎችም እንዲለቀቅ ያደርጋል፡፡ ስለዚህ ይህን ምርመራ እያካሄደ ያለው ፖሊስ ነው፡፡ ስንት ሰው ላይ መረጃ ተገኘ፤ ስንት ላይ አልተገኘም የሚለው የመርማሪ ፖሊስ ጉዳይ ይሆናል” ሲሉ የፖሊስን ሚና ያስረዳሉ፡፡

 በቁጥጥር ስር ከነበሩት ውስጥ ከ40 እስከ 50 የሚሆኑት ብቻ የሰበታ ከተማ ነዋሪ እንደሆኑ እና ቀሪዎቹ ከተለያዩ ቦታዎች የተሰባበሰቡ እንደሆነ ያብራራሉ፡፡ “ሌሎቹ ከየአካባቢው ለጥፋት ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ እና ለስራ ፍለጋ ተብሎ ከገጠርም ከሌሎች የክልል የዞን ከተሞች እዚህ እንደከተማ ተሰብስበው ያሉትና በየፋብሪካው እና በቀን ሰራተኝነት ስራ ላይ የተሳተፉ ናቸው፡፡ ሌሎቹ ደግሞ ስራ ፈላጊዎች ናቸው” ብለዋል ከንቲባው፡፡

Proteste in Äthiopien (Reuters/T. Negeri)

በኢትዮጵያ በየአካባቢው እየተደረጉ ያሉ ተመሳሳይ እስሮችን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይኮንናሉ፡፡ “ህግ እና ስርዓትን ለማስፈን በሚል በጸጥታ ኃይሎች የሚደረጉ መብት ጣሽ እርምጃዎች መረጋጋትን የማምጣት እድላቸው የመነመነ ነው” ሲሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዋች የኢትዮጵያ ተመራማሪ ፌሊክስ ሆርን መተቸታቸውን አሶሴትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ከንቲባ አራርሳ ግን “እስር መፍትሄ የሚሆንበት ጊዜ አለ” ይላሉ፡፡

Related stories   መካከለኛዉ ምሥራቅ ሌላ ዘመን ሌላ ጥፋት

“እስር መፍትሄ የሚሆንበት የማይሆንበት አለ፡፡ ዝም ብለው በተቃውሞ ላይ ለተሳተፉ ሰዎች እስር መፍትሄ አይሆንም፡፡ ጥያቄያቸውን በውይይት መፍታት ነው፡፡ በድርጊታቸው ህግን የጣሱ ከሆነ እርሱን የማስረዳት፣ የማሳመን ነው፡፡ ሌሎች ስራ አጥ ወጣቶችን አሳምኖ ወደ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ነው” የሚሉት ከንቲባው በ“ወንጀል ተሳትፈዋል ላሏቸው ግን እስር ተገቢ” እንደሆነ በአጽንኦት ያነሳሉ፡፡

“በተጨባጭ ተደራጅተው ወንጀል ለፈጸሙ ደግሞ መፍትሄ የሚሆነው በፈጸሙት ወንጀል ልክ በህግ ሲቀጡ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ሰዎች እዚያ ውስጥ የተሳተፉት በሕግ ወይም በእስር መማር ይችላሉ ተብሎ ሳይሆን ወንጀል የፈጸሙት በህግ ይማራሉ፣ ሌሎቹ ግን ተምረው ከዚያ ድርጊት እንዲመለሱ ሂስ ተደራርገው የሚለቀቁ ይሆናል” ይላሉ አቶ አራርሳ፡፡    በኢትዮጵያ ህዝባዊ ተቃውሞ ከተቀሰቀሰበት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ መገደላቸውን እና በሺህዎች  የሚቆጠሩ ሰዎች መታሰራቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡  www.dw.com

Related stories   ኦሮሞ ኦሮሞን አድፍጦ እየገደለ ነው፤ ኦነግ ሸኔ ለስራ የሚጓዙ አምስት ኦሮሞዎችን ገደለ

ተስፋለም ወልደየስ    ,   ኂሩት መለሰ


Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0