ሙታክ/ የስደተኞች ካምፕ ማለት ነው በኖሽክ/ ውበት የለቀቀባቸው፣ ውልውል ብለው የሚያብረቀርቁ ማገዶ የማይፈጁ ያሉበትን ያህል፣ እንደ አቦል ቡና ቀደም ቀደም የሚሉትን፣ በብርሃን ፍጥነት ካልበረርን የሚሉትን፣ ቀልጣፋ ነኝ …. የሚሉትን አርግቦ ስም የሚያስለውጥ ጋዳም ነው። ኢዮቦች!!

ሙታክ ውስጥ ሁሉም አይነት ህይወት አለ። የራሱ ዓለም ነው። ከቦታ ወደቦታ ሁኔታው ቢለያይም የቀናቸውና የጨለመባቸው አብረው ያዘገሙበታል። የቀናቸውን እየሸኙ፣ አዲሱን እየተቀበሉ እዛው ወልደውና ከብደው እድሜያቸውን የሚገፉ ጥቂት አይደሉም። ለዛም ወግ ያለበቁ፣ የኑሮ ወጉ ጠፍቶባቸው እድሜያቸውንና ህይወታቸውን እዚያው የሚያጠወለጉ.… በቻ በዙ ነው። የዛኑ ያህል ራሱ የሙታክ ኑሮ በቂ ሆኒላቸው እንደ ስኬት የሚመለከቱም አይታጡም። ፍሪዝ ማድረግ ግብ ከሆነ? ያበደው አጥወለወለው!!

ሙታክ ውስጥ ቀኑን በለሊት ተክተው፣ በለሊት እየቆሙ፣ በቀን የሚተኙ ብዙ ናቸው። በተለይ ብዙ የቆዩት ….. ያበደው ማስታወሻውን ከፈተ። ቀንና ለሊትን አደባልቀው ከሚኖሩ ከየአቅጣጫው የሰበሰበውን ተመለከተ። የሌላውን ዓለም ነዋሪዎችን ህልም በይደር አስቀመጠው። ለዛሬ ይህንን መረጠ።

የህልሙ ርዕስ – የባቄላ እሸት

ህልሙ የታየው – 2011 ግንቦት ወር

ህልሙን ያው – በለጠ / ለስም ጥንቃቄ የተቀየረ ስም/

የህልሙ ይዘት – እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ አድቬንቸር

ህልሙ የታየበት ሰዓት – ባገራችን አቆጣጠር ሊነጋጋ ሲል

ህልሙን የፈታው – ራሱ በለጠ

የህልሙ ተራኪ – ያበደው ………. መልካም ሰንበት

የሙታክ አባል በለጠ ተራራ ሰንጥቆ ማየት ሲጀምር የሚረብሸው አይፈልግም። “ አሻግሬ እያየሁ ነው፣ ተራራውን ሰንጥቄ እየማተርኩ ነው ” ካለ በቃ!! በ2011 ግንቦት ወር ያየውን ህልም “ ቀጥታ እንደ ፊልም አሳየኝ ” በማለት ነው ሚያወራው። በሌ ነብስ ነው። ሴቶችን ይወዳል። መላጣው እስክታብረቀርቅ ስለሚወለውላት የጠቦት ጉበት ትመስላለች። ጠጉር የሚባል እንዲበቅልባት አይፈልግም። በየቀኑ ሙልጭ ያደርጋታል። መልከ መልካም፣ የዋህ፣ የልቡን የሚናገር፣ የተንኮልን አድራሻ የማያውቅ፣ ደግ፣ የስደት ማመልከቻው ውሳኔ ሳይታወቅ ለቀጣይ ህይወቱ ቅቤ አንጥሮ የሚያስቀምጥ፣ ሽሮና በርበሬ የሚከዝን፣ እንጀራ መጋገር ከመውደዱ የተነሳ መጥበሻ ሲመለከት “ ይሄ ለእንጀራ አይሆንም፣ ይሆናል ” እያለ አስተያየት የሚሰጥ ውብ ሰው ነው።አዲስ ሰው ሲመጣ የሚቀበል፣ የሚጋብዝ፣ በፈቃደኝነት የሚነገረውን ሁሉ አስቀድሞ በመንገር መረጃ የሚሰጥ፣ ገጠመኙን ያለ ሃፍረት የሚናገርም “ስደተኛ”

በሌ ጆሊ ነበር። አሁንም ነው። ወደፊት እቅዱ ትልቁን ትራክ መንዳት ነው። ትራክ ይወዳል። ለትራክ ያለው ፍቅር ይገርማል። በህልሙ ትራክ በበረዶ ላይ እየነዳ ሲሸለም መመልከት ልማዱ ነው። ሰው ካምፕ ሲገባና እጁን ሲሰጥ ቀዘቀዝ ይባላል። በሌ “ ከመቀዝቀዙ ” በፊት ዘናጭ እንደነበር አልፎ አልፎ ጣል የሚያደርጋቸውና የሚጫማቸው ኮቴዎቹ ያሳብቃሉ። ደረተ ሰፊው ጓደኛውን ጨምሮ ከበሌ ጋር ማውራት የማይወድ የለም። በሀሉም ጉዳዮች ገጠመኝ አለው። አንድ ጨዋታ ሲነሳ በሌ ማውራት የሚጀምረው “ እንደውም በዚህ ጉዳይ ገጠመኝ አለኝ ” በማለት ነው። አንድ ገጠመኙ!

ስለ እግር ቀዶ ጥገና ሲወራ በሌ ገጠመኝ አለኝ አለ። ስለ በሌ ገጠመኝ ስለምናውቅ ተያየን። “ አንድ ጊዜ አንድ ልጅ መኪና ገጨውና ጥቁር አንበሳ ወሰድነው። እኔ እየነዳሁ ነው የወሰድኩት። ሃኪሞቹ ህክምና አደረጉለት። ግራ እግሩ ነበር የተጎዳው። በሁዋላ ላይ እንደማይድን ሲረዱ እግሩ መቆረጥ አለበት አሉ። ይገርማል ኦፕሬሽን ያደረገው ሃኪም በስህተት ያልታመመውን ጤነኛ እግሩን ቆረጠው።
እንደማይሆን የለም አሁን ሁለት እግር የለውም ” በሌ በሳቅ ገደለን፣ ሳቅ አነፈረን!! በሌ የስደትን ጥላ ይገፋል። የዓእምሮን ውጥረት ያራግፋል። በሌ “ እንደማይሆን የለም ” የሚለው አባባሉን የትኛውም ቦታ ይጠቀመዋል። እንደማይሆን የለም እግሩን የያዘውን አዞ አስለቅቆ በግንቡ አናት ላይ እየሮጠ ባህር ተሻገረ።

ህልሙ እንዲህ ነው!! በሌ እንደተረከው

በሌ ህልሙን ማውራት ጀመረ። ይገርምሃል እኔ እንደፊልም ነው የሚያሳየኝ። በመጀመሪያ ቀን የባቄላ እሸት ይመስለኛል። የአተርም እሸት ይመስለኛል፣ የበቆሎ እሸትም ይመስለኛል…. ብቻ እሸት ነው። ቀኑ ድምቅ ያለ ብርሃን ነው። ገና መነጋጋቱ ይመስለኛል። የሚያምር ቀን ነበር። ስኒከር አድርጌ እንሳፈፋለሁ። በጣቱ እየጠቆመ፣ ከታች ወደ ካምፕ እየመጣሁ ድልድዩ ጋር ስደርስ አንዲት ሴት መጣችና እሸቱን ሰጠችኝ። ተቀበልኩና ምንም ሳልል ወደ ቤቴ ገባሁ። ቤት ገብቼ በደንብ ስመለከተው የባቄላ እሸት ነው።

ፈገግ እያለ “ እሸት ሃሪፍ ነው ” አለ አንዱ፤ በሌ “ ተው ፣ተው፣ ህልምማ ጥርሳችንን የነቀልንበት ነው ” አለና ፍቺውን አስረዳ።እንደማይሆን የለም የልምዱን ቃል ተነፈሰና ቀጠለ፤ ባቄላ ሽፋን አለው። ልክ ትልቅ መልዕክት እንዳለው ፖስታ ነው። መልዕክቱ ባቄላው ነው። እሸት ፈልቅቀህ ፍሬውን እንደምትበላ ሁሉ ፖስታ ከፍተህ የምታነበው መልዕክት በፍሬው ይመሰላል። ሴትየዋም ፈረንጅ ናት፤ እንግዲህ የስደት ማመልከቻዬ ሰሞኑን መልሱ ይመጣል ማለት ነው ብዬ ፈታሁት። ግን ብዙም ሳይቆይ ነጃሳ ህልም አየሁ። በሌ ቀጠለ፤

እንደማይሆን የለም፣ ይህንን ህልም ያየሁት አልጋ ላይ ተኝቼ እንዳይመስልህ። እንደ ቱሪስት እየተዝናናሁ ነው። በሌ ሳቀና ህልሙን ማውራት ቀጠለ። እንደማይሆን የለም ትልቅ ባህር ነው። መካከሉ በግንብ ተከፍሏል። ከየት ጋር እንደ ጀመርኩት አላውቅም በቀጭን ግንብ አናት ላይ እጓዛለሁ፣ እሄዳለሁ፣ ባህሩ ንጹህ ነው። በግራና ቀኝ ያብረቀርቃል። አንዳንዴ ብርሃኑ ጨረር ይለቃል። ጨረር ከሰማይ ተወርውሮ ባህሩ ላይ ተሰክቶ ውሃውን መብራት አስመስሎታል።በሚደንቀው ብርሃን የሬምቦን ቲ-ሸርት ለብሼ፣ የጂንስ ቁምጣ ለቅቄበት እነጥራለሁ። የግንቡ ርቀት ለአይንህ አያልቅም። የምሄድበት ግንብ ከርዝመቱ የተነሳ ጫፉ ሲባጎ ይመስላል። እሄዳለሁ፣ እሄዳለሁ…. አያልቅም። ወዴት እንደምሄድ አላውቅም። ስሄድ ውዬ ጀንበር ያቆለቆለች ይመስለኛል። የመሸም ይመስለኛል በመጨረሻም ደከመኝ። ቀስ አልኩና በጄ ተደግፌ በጀርባዬ እግሬን ቀጥ አድርጌ እግንቡ አናት ላይ ተኛሁ።

ከግራና ከቀኝ ግንቡ አፍ ድረስ የሞላው ውሃ እየተገጫጨ ያዜማል። ፉጨት የሚመስል ዜማ ያወርዳል። ማዘር ኢንዲያ ላይ ያለው ቸል ቸል … ትዝ አለኝ። ከሩቀ ለሚመለከት በጀርባዬ የተኛሁት ባህሩ ላይ ይመስላል። ብቻ አንዲሁ ሰማይ ሰማዩን እአየሁ፣ የውሃውን ድምጽ እየሰማሁ ስልምልም አደረገኝና አሸለበኝ። ብዙም ሳልተኛ አንድ አዞ እየዋኘ መጣ። አጠገቤ ደርሶ አንድ እግሬን ያዘኝ። ታገልኩት። ከግንቡ ላይ እነዳልወድቅ በመጠንቀቅ ያለኝን ሃይል በማሰባሰብ መንጭቄው ሮጥኩ። ስባንን ሰውነቴ ተዝለፍልፎ ከጂም የወጣሁ እመስል ነበር።

በሌ ፍቺውን አከለ። አየህ አዞ የአጅሬ ምልክት ነው። ስሙን አንጠራውም። መናከሱ ደግሞ አንድ ችግር አለ ማለት ነው። ከችግሩ በሁዋላ መልካም ነገር ስላለ አመለጥኩት። ደሙ ሲሳይ ነው። ግን የረሳሁት ስለት ወይም ስጦታ አለ እነደማለት ነው። ባህር ያው አለንበት አገር ነው። መንገድም እድሜ ነው። መኝታው ሃሰብ ነው። ይህንን ህልም እንዳየሁ ሁሉም ነገር ገባኝ። ለማንም አልተነፈስኩም። የስደተኛነት ማመልከቻዬ በመጀመሪያው የተበላሸ መልስ እንደሚሆን አወኩ። አስቀድሜ እንዳወኩት ሆነ። ደግሞም ሆነ።

የበሌና የቁም አላሚዎች ህልሞች ብዙ ናቸው!!ሰላም ሰንበት!! ህልም እልም!!

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *