“Our true nationality is mankind.”H.G.

ጠመዳ ፣ አጥማጅና ተጠማጅ

ጠመዳ ፣ አጥማጅና  ተጠማጅ

የባሻዬ ልጅ ያጫወተኝ ጠመዳ ለወትሮው ከማውቀው የአጥማጅና ተጠማጅ ግንኙነት ተለየብኝ፡፡ ጠመዳው የራሱ ሕግና ደንብ ያለው፣ በተጠማጅና አጥማጅ የጋራ ስምምነት ያለ አንዳች ድምፀ ተአቅቦ የፀደቀ፣ ይግባኝ የማይጠየቅበት፣  አጥማጅ ተጠማጅን በምርኮ ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ የሚሰጥበት፣ ተጠማጅ ለአጥማጅ ፍጹም ታዛዥ የሆነበትና አጥማጅ በምርኮ የሰጠውን ተጠማጅ ያለድርድር መልሶ በእጁ የሚያስገባበት ሥርዓት የሚከናወንበት ነው፡፡  በዚህ ሕግ የሕግ ከለላ የሚሰጣቸውም አሉ፡፡

አምበርብር ምንተስኖት ጠየቀ፡፡ የሰማውን የአጥማጅ ተጠማጅ ሕገ ደንብ ካላየ ማመን እንደሚሳነው ለባሻዬ ልጅ አስታወቀ፡፡ ለ”ጠመዳ ሕግ” ሳያዩ የሚያምኑ ብፁአን ናቸው ብሎ ማለፍ ለደላላው አምበርብር አልዋጥልህ አለው፡፡  የባሻዬ ልጅ ጥያቄዬን ተቀብሎ አጥማጅና ተጠማጅ ወዳለበት ቦታ ወስዶ ትርዒቱን ጋበዘኝ፡፡

ዋቢ ሸበሌ አካባቢ በአንድ ቀጭን መንገድ የባሻዬን ልጅ ተከትዬ ገባሁ፡፡ ጠመዳ መንደር ዘለኩ፡፡ በጠመዳ ቤት ስገባ በቤቱ ዙሪያ ጥግ ተቀምጠው ቅጠል እየበሉ የሚያወሩ ይታያሉ፡፡ በላይ በላይ ትምባሆ ይምጋሉ፡፡ ውሃ ይጎነጫሉ፡፡ ኮካኮላ ያክሉበታል፡፡ የባሻዬ ልጅ ግራ እንዳልጋባ ነገረኝ፡፡ አንድ ጥግ ያዝን፡፡ የባሻዬ ልጅ የምሱን አዞ ተመሳሰለ፡፡

የተሰጠኝን ኮካ እየተጎነጨሁ የጠመዳን ሕግና፣ የጠመዳ ሕግ እንዴት እንደመጣ ተተረከልኝ፡፡  ጫት ሲቅሙ ማውራት እንጂ ማዳመጥ የማይፈልጉ አሉ፡፡ ማውራት ቢፈልጉም አድማጭ ማግኘት የማይችሉ አሉ፡፡ ለማውራት አድማጭ ስለሚያስፈልግ፤  ተናጋሪ አድማጭ ማግኘት አለበት፡፡ በጠመዳ ቤት ውስጥ አጥማጅና ተጠማጅ የተፈጠሩት ለዚህ ነው፡፡

አጥማጅ ባለገንዘብ ነው፤ በገንዘቡ የሚፈልገውን ለማድረግ የሚችል ለተጠማጅ አስፈላጊውን ሁሉ የሚያሟላ ይሆናል፡፡ ይህ የጠመዳ ሕግ የመጀመሪያ አንቀፅ ነው፡፡ ስለ ጠመዳ ህግ አንቀፅ በአንቀፅ እየተከተለ ማብራሪያ ተሰጠኝ፡፡ ፍላጎታቸውን ማሟላት የማይችሉ ፣ ሀራሪስቶች፣ (ባለአራራዎ ች ተጠማጅ ናቸው፡፡ አጥማጅ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልቶ ተጠማጅ ሲይዝ “ምርኮ” አገኘ ይባላል፡፡ “ምርኮ የአጥማጅ ባሪያ ነው” ለሱስ ባሪያ የሚሆኑ ምርኮኞች ናቸው። ባሮች ናቸው። ራሳቸውን የረሱ ሞራለ ቢሶች ናቸው።… ሌላው የሕጉ አካል እንዲህ ይላል፡፡

ተጠማጅ አጥማጅ ሊያሟላለት የሚገባውን ይጠይቃል፡፡ ኮካኮላ፣ ጫት፣ ሲጃራ፣ የመቀመጫ ኪራይ  ይከፈልለታል፡፡ በሌላ አነጋገር ኢንቨስት ይደረግበታል፡፡ አጥማጅ ኢንቨስት ማድረግ ያለበትን ካሟላ በኋላ ተጠማጅ ምርኮ ይሆናል፡፡ ኢንቨስትመንቱ ኮካ፣ ጫትና፣ ሲጃራ በየመካከሉ ትኩስ ነገር ብቻ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ተጠማጆች ብዙ ናቸው። ተጠማጆች በየፈርጁ አሉ። ታላላቅ የሚባሉም ይጠመዳሉ። ለቀፈታቸው ሲሉ ባርነትን በራሳቸው ላይ አውጀው ተዋርደው ለመኖር የሚምሉም አሉ። ውርደት በየፈርጁ፤ “አጥማጅ ማውራት ሲጀምር ምርኮ ማዳመጥ ግዴታው ነው” ይህ የጠመዳ ሕግ አብይ ድንጋጌ ለአጥማጆች ልዩ መብት ይሰጣል፡፡ ምርኮ አጥማጅን መከራከር፣ አጥማጅ በሚያወራው ወሬ ላይ ተጨማሪ የመስጠት፣ አጥማጅ ሲያወራ ቢሳሳት እንኳ ማስተካከያ የመስጠት፣ አድማጭ ቢዋሽ እንኳ ዋሽተሃል በማለት ማስተካከያ የመስጠት መብት የለውም፡፡ ይልቁንም በጠመዳ ሕጉ መሠረት አጥማጅ ሲያወራ ምርኮ የአጥማጅን አይን አይን የማየት፣ ወሬውን እየሰማ ለመሆኑ በግንባሩ ምልክት የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡

አምበርብር ምንተስኖትን ገረመው፡፡ ትርፍ ለሌለው ጉንጭ አልፋ ወሬ ቀኑን ሙሉ ተጨብጦ የምርቃና ስብከት ማዳመጥ፣ ለዕለት ሱስ ሲባል ባሪያ መሆን፡፡ ለአፍታ ሳይተነፍሱ በጫት እብዶች ወሬ ተጠምዶ መዋል፡፡ ሲመሽ ወደ ቤት መሄድ፡፡ ሲነጋ ለመማረክ ወደ ምርኮ መንደር መሮጥ፡፡ ለጫት በመማረክ በሕይወት ዘመን ሁሉ ለልመና እጅ መስጠት፡፡ ያለአንዳች ውጤት በእድሜ መጫወት፣ የሱስ ጡረተኞች፤ “የጠመዳ ሕግ የተጀመረው ጅማ ነው” የባሻዬ ልጅ ያስተዋወቀኝ የቤቱ ባልደረባ መናገር ጀመረ፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ገንዘብ ያላቸው ተማሪዎች ገንዘብ ለሌላቸው ተማሪዎች ጫት እየገዙ አብረው ያጠኑ ነበር፡፡ ከጊዜ በኋላ ተጋባዦች ከጋባዦች በላይ ያጠኑትን ደጋግመው በማውራት ተጠቃሚ መሆናቸው ሲታወቅ የጠመዳ ሕግ ወጣ፡፡ ድሆች ዝም ብለው ገንዘብ ያላቸው ብቻ ተናጋሪ የሚሆኑበት ህገ ቻርተር ተዘጋጀ፤

በአዲሱ ህግ  ተጋባዥ ተማሪ ተጠማጅ ይሁን ተባለ፡፡ ተጠማጅ ተማሪ መናገር ተከለከለ፡፡ አጥማጅ ተማሪዎች ያጠኑትን በየተራ ለተጠማጅ ተማሪዎች ሌክቸር እየሰጡ ትምህርታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ታመነበት፡፡ በዚህ የተስማሙ ተጠማጅ ተማሪዎች በምርኮነት አድማጭ ብቻ እንዲሆኑ ከስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ ህጉ በዚሁ ውል መሰረት ጸና፤ የጠመዳ ህግ ተብሎ ተሰየመ፤ ህጉ ክልል አቋርጦ አዲስ አበባ ገባ። አዲስ አበባ ያሉ የሱስ ባሮች ለጠመዳ ህግ እጅ ሰጡ። ተጠመዱ፣ ተያዙ፣ ተማረኩ፣ በጫት ቤት ስብከት ተነደፉ፤ በጫት ቤት ፖለቲካ ይበለታል። መለስን የሚያጀግኑ፣ መለስ ሊቀ ሊቃውንት የሚያደርጉ፣ ስለመለስ የሚቃኙ፣ ስለመለስ  ለመስበክ አላሙዲንን  በማጀቢያነት የሚያቀርቡ ባለበጀቶች አሉ፣ ውስጥ አዋቂ ሆነው ግለሰብ የሚያመልኩ የጫት ቤት ካድሬዎች ብዙ ናቸው፤ በበጀታቸው ያጠምዱና የተሰጣቸውን መልዕክት ይሰብካሉ፤ ሱሰኞች ስብከቱን ያለማወላወል ይጋታሉ።

ሲወርድ ሲዋረድ አዲስ አበባ የገባው የጠመዳ ሕግ በየጊዜው መሻሻል እየተደረገበት ምርኮን አሳልፎ መስጠት የሚችልበት ደረጃ ተደረሰ፡፡ አጥማጅ የፈለገውን አውርቶ፣  እንደሻው ለፍልፎ ለሽንት ሲወጣ ምርኮውን ለሌላ የማሳለፍ መብት በጠመዳ ሕግ ተደነገገ፡፡  አንዴ የተማረከ ምርኮ በቅብብል በወሬ እንዲደነዝዝ ስለተፈረደበት ለመማረክ ቅድመ ሁኔታው ሊሟላለት እጣ ፈንታውን አስቀድሞ ስለሚያውቅ “ጥሩ ምርኮ” ከመሆን ውጪ ሌላ እጣ የለውም፡፡

ተማራኪዎች አድማጭ ብቻ ስለሆኑ ጭብጥ ይላሉ፡፡ የመወራጨት እድል የላቸውም፡፡ የባሻዬ ልጅ ታሪኩን ሁሉ በማስረጃ አስደግፎ ካጫወተኝ በኋላ ያጠመደኝ መሰለኝ፡፡ የጠመዳን ሕግ ሳያስፈቅደኝ የተገበረብኝ መሰለኝ፡፡ ለምን የጠመዳን ሕግ እንደነገረኝ የገባኝ መጨረሻ ላይ ነው፡፡

የባሻዬ ልጅ እጁን ጠቁሞ አመለከተኝ፡፡ ያመለከተኝ ሰው ምርኮ ነው፡፡ እድሜው በ50ዎቹ ይቆጠራል፡፡ ጫትና ሲጃራ ገዝቶ መጠቀም ካቆመ አሥር ዓመት እንደሚሞላው ተገለፀልኝ፡፡ ለኑሮም ለሞራልም እጁን ሰጥቶ በምርኮ ይተዳደራል፡፡ ከግማሽ ቀን በላይ ሳያወራ ውሎ የሚተነፍሰው የት ሲሄድ እንደሆነ አልሰማሁም፡፡ “ስራ ጠፋ” አትበል፡፡ የባሻዬ ልጅ የመጨረሻ ቃል ነበር፡፡ ከእነዚህ ሁሉ የሱስ ባሮች እንደምሻል በማስረጃ አሳየኝ፡፡ የድለላ ነገር አንዴ ሞቅ፣ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ ስለሆነ እንዳላማርር አሳሰበኝ፡፡

ዘራፍ ምንተስኖት ቀብራራው አልኩ፡፡ በየመንደሩ ጉድ አለ፡፡ ሰርቶ መኖር እየተቻለ ለአራራ ባሪያ መሆንም አለ፡፡ ይህች አገር ስንቱን ተሸክማለች፡፡ ሞራል የገሸበባቸው ጥቂት አይደሉም፡፡ ከ”ዋናው ሕግ” ይልቅ ለመንደር ሕግ እጃቸውን የሰጡ፡፡ ለዓመል ሲሉ የተንበረከኩ፣ ሞራላቸውና ስብዕናቸው የወደቀ….. ደላላው ተራገመ፤

ለጫት፣ ለሺሻ፣ ለትምባሆ በጀት የሚመድቡ አሉ፡፡ የሱስ ባሮችን ገዝተው ቀኑን መሉ ሲተፋባቸው ለመዋል በጀት ይመደባል፡፡ ከጫት በተጨማሪ ረዥም ወሬ ካላወሩ የማይመረቅኑ፣ ሞቅ የማይላቸው ተጨማሪ በጀት ቢመድቡ ምን ይላቸዋል፡፡ ጫትም ወሬም እኩል ሱስ ናቸው፡፡ ወጪ ያስወጣሉ፡፡ የእለት ጉርስ ለመሸፈን ከላይ ታች የሚሉትን ደላላው አምበርብር በዓይነ ህሊናው ደረደራቸው፡፡ ገንዘብ በየቦታው፣ በየደረጃው አቅም አለው፡፡ ተፈጥሮን ያስታል፡፡ በሱስ የታጠሩ ይማረካሉ፣ አልጠግብ ባዮች በጥቅም ታውረው አደራቸውን ይበላሉ፣ በገንዘብ ፍርድ የሚያዛቡ፣ በገንዘብ ነብስ ለማጥፋት የሚስማሙ፣ ህይወት ለመቅጠፍ የሚዋዋሉ …. ቤት ይቁጠራቸው፡፡

በየመስሪያ ቤቱ ስንቶች ሲያወሩ ይኖራሉ? ስንቶች በማዳመጥ ብቻ ሕይወታቸውን ይገፋሉ? በፓርላማ ውስጥስ ስንቶች አስተያየት ይሰጣሉ? ይከራከራሉ? ደላላው አምበርብር በቴሌቪዥን የሚያውቃቸውን ተሰብሳቢዎች ሲያስታውስ ያነሳው ጥያቄ ነው፡፡ ፓርላማ ገብተው ሳያወሩ፣ ሳይተነፍሱ መቀመጫቸው በርጩማ የመሰለባቸው አሉ። ለማዳመጥ ተበጅተው፣ ሳይተነፍሱ አድማቂ ሆነው እድሜያቸውን እየበሉ ያሉ አሉ።

በጫቱ ላይ ርምጃ ይወሰዳል ሲባል የሺሻ የሕጋዊነት መብት ታወጀ፡፡ ሺሻ የትምባሆ ዘር ስለሆነ ነውር እንደሌለው አምበርብር ሲሰማ ገረመው፡፡ ሺሻ ለመሸጥ ፈቃድ የሚሰጠው ተቋም ሺሻን የማምረት እቅድ እንዳለውም ተናግሯል፡፡ በአንድ በኩል ሺሻ ቤቶች ይዘጋሉ፣ በሌላ በኩል ሺሻን በሕጋዊ መንገድ ማስገባት ይፈቀዳል፡፡ ሺሻ በሕጋዊ መንገድ ከገባ የት ሊጨስ ነው? ግልፅ አይደለም፡፡

ደላለው አምበርብር በሰማው ሁሉ ተገርሟል፡፡ የሱስ ባሮች ግን አሳዝነውታል፡፡ የሱስ ባሮችን ለመታደግ በአነስተኛና ጥቃቅን ስራ ፕሮጀክት የሚደራጁበትን መንገድ ለማፈላለግ ወስኗል፡፡ ወደ ምርኮ መንደር ያልዘለቁ እንዳይጠመዱ  የሰበካ አገልግሎት ለመስጠት ወስኗል፡፡ ከሱስ ራቁ፣ ሱስ ባሪያ ያደርጋል፣ ሱስ ራስን ዝቅ ያደርጋል፣ ሞገስ ይቀንሳል፣ ክብር ይጥላል፣ ያዘቅጣል፣ ያዋርዳል፣ ያደናቁራል፣ የማይሆን ቦታ ይጥላል፣ አዋርዶ ይገላል፡፡ ይህ የስብከቱ ይዘት ነው፡፡ ደህና ሁሉ፣ ሰላም፡፡

ከቀድሞ ጽሁፎቼ አንዱ ለማላመጃ ከሪፖርተር ተበድሬ አተመኩት

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0