ምንም አይነት የባንክ አካውንት ሳይኖራት ከ10 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ የያዘ ሀሰተኛ ሰነድ አዘጋጅታ የኢንቨስትመንት ቦታ የወሰደችው ተጠርጣሪ ክስ ተመሰረተባት። በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሰረተባት ተጠርጣሪ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ጉባ ወረዳ ነው 452 ሄክታር መሬት ለእርሻ ልማት የወሰደችው።

ተከሳሿ ፋንታነሽ ግዛው በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ነዋሪ ናት። በክሱ እንደተገለጸው ተከሳሿ የማይገባትን ጥቅም ለማግኘት በኢንቬስተር መልክ ለመሰማራት የሚጠይቀውን መስፈርት በሀሰተኛ ሰነድ አቅርባለች። በዚህም በቤንሻንጉል ጉሙዝ በእርሻ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት የክልሉን መንግስት መሬት እንዲሰጣት ትጠይቃለች።
በክልሉ በኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሰማራት አልሚዎች በቂ ገንዘብ እንዲኖራቸው ስለሚጠየቅም የባንክ ማረጋገጫን ይጠይቃል። ተጠርጣሪ ይህንኑ መሰረት በማድረግ በዳሽን ባንክ አፍሪካ አንድነት ቅርንጫፍ የባንክ አካውንት እንዳላትና የባንክ ስቴትመንት ካፒታሉ በማንኛውም ጊዜ የማይንቀሳቀስ መሆኑን ታስረዳለች።
ይህንኑ በሰነድ ለማስደገፍ የተባሉት መስፈርቶችን ማሟላቷን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችና ያንንም የሚገልጽ የድጋፍ ደብዳቤ አያይዛ ለክልሉ ኢንቨስትመንት ጽህፈት ቤት ማቅረቧን ነው ክሱ የሚያስረዳው። በተገለጸው ባንክና አካውንት ቁጥርም የተቀመጠው የገንዘብ መጠን 10 ሚሊየን 500 ሺህ 80 ብር ሲሆን ይህም ለጠየቀችው ኢንቨስትመንት ፈቃድ ማግኘት የሚያስችላት ነበር።
ተጠርጣሪዋ ክልሉ ለኢንቨስትመንት የሚሰጠውን ትኩረት መነሻ በማድረግ በክልሉ ለመሰማራት ያቀረበችው ጥያቄ ይሁንታ አግኝቶ ፍቃድ ከተሰጣት በኋላ ሀምሌ 6 2007 ዓመተ ምህረት ወደ መተከል ዞን ጉባ ወረዳ ታመራለች። በዚያም የወረዳው የአካባቢ ደንና መሬት አስተዳደር ባለሙያዎች እንዲሁም በባሻታ ቀበሌ ካቢኔ አባላት ፍቃዱ ተጣርቶና በቃለ ጉባኤ ተረጋግጦ 452 ሄክታር መሬት ሊሰጣት መቻሉ በክስ ዝርዝሩ ተገልጿል።
ይህን ተከትሎም ህዳር 8 2008 አመተ ምህረት ከክልሉ መንግስት ጋር በእርሻ ልማት ዘርፍ ለመሰማራት የሚያስችል የስምምነት ውል መዋዋሏም ታውቋል። በዚህ ሂደት ላይ የምትገኘውን ተጠርጣሪ ጉዳዩዋን ሲያጣራ የቆየው የቤንሻንጉል ክልል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ተከሳሿ ያቀረበችው እያንዳንዱ መረጃ ሀሰተኛ መሆኑን እንደደረሳባት ነው በክሱ የተገለጸው።
በተለይ ያቀረበችው አካውንት የራሷ እንዳልሆነና ይልቁንም ከ10 ሚሊየን ብር በላይ እንዳላት የሚገልጽ ሀሰተኛ ሰነድ አዘጋጅታ ማቅረቧን ነው ክሱ የሚያስረዳው። በዚህም በፈጸመችው ሀሰተኛ ሰነድ ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና መገልገል ወንጀል ተጠርጥራ ነው ከሱ የተመሰረተባት።
አቃቢ ህግ ከዘጠኝ በላይ ማስረጃዎችን ያሰባሰበበትን ይህ የክስ መዝገብ ለፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ተዘዋዋሪ ወንጀል ችሎት አቅርቦታል። ክሱን ተከትሎ ተዘዋዋሪ ችሎቱ በዝርዝር ተመልክቶ ተለዋጭ ቀጠሮ የሚሰጥበተ ይሆናል።
መረጃውን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊው አቶ አማረ መኩሪያ አድርሰውናል።
Source FBC by በሀይለኢየሱስ ስዩም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *