• ቤቱ ፈርሶ መሰራት አለበት ፣ ሃይሌ ፍጹም ድጋፍና ነጻነት ያስፈልገዋል!!

የኢትዮጵያ የአትሌቲክስ ፌዴሪሽን በኮታ ውክልና ስለ ስፖርቱ ምንም በማያውቁ የፖለቲካ ሹመኞች ሲመራ ዓመታትን አስቆጥሯል። በነዚህ ዓመታት ውስጥ ፌዴሬሽኑ በሂደት እየቀጨጨና ህዝብ የሚኮራበት ድል እየተመናመን ወደ መክሰም ደረጃ ተቃረበ። እንደ ጎርፍ ተከታትሎ በማሸነፍ ዓለምን ያስደመመው ሩጫ ቀስ በቀስ እየከሰመ መሄዱ ሁሉንም ዜጎች አሳዘነ።
በተለያዩ ወቅቶች አስተያየት ሲሰጥ የማይሰሙት የስፖርቱ መሪዎች ስር ነቀል ርምጃ ከመውሰድ ይልቅ በፖለቲካ ግንኙነት ሲደጋገፉ የምንኮራበት ሩጫ አንገታችንን አስደፋን። እንደ ዱቤ ጅሎ አይነት የቴክኒክ ሃላፊዎች ቤቱን አዝረከረኩት። በአተሌት ምርጫ፣ በውጭ ጉዞ፣ በስልጠናና በዕቅድ ችግሮች የተተበተበው ፌዴሬሽን አዲስ ነገር ከመፍጠር ይልቅ የነበረውን እየበላ ኖረ። በውስን ውጤታማ አትሌቶች ላይ የተመሰረተው ድልም ተነነ።
ከዛሬ 12 ዓመት ግድም ይህ ችግር የገባቸው ነባር አትሌቶች ትግል ጀምረው ነበር። ሃይሌን ሊቀመንበር ያደረጉትና ትግሉን የጀመሩት ገዛሃኝ አበራ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ስለሺ ስህን፣ አሰፋ መዝገቡ፣ አለሙ የመሳሰሉት ይገኙበት ነበር።
በሌላው ጎን አዲሱን ማህበር በመቃወም ዱቤ ጅሎ ከሚመራው ማህበር ጋር የቀጠሉት ህብረት ፈጥረው አዲሱ ማህበር ላይ ጫና ፈጠሩ። በተለይም ሃይሌ ላይ ትኩረት አድርገው ማህበሩን እንዲበትን አስገደዱት። ዝርዝሩን ወደፊት እንመጣበታለን።
ዛሬ አዲስ ነገር ተሰምቷል። ሃይሌ ገብረ ስላሴ አዲስ አበባን ወክሎ በዘጠኝ ድምጽ ፐሬዚዳንት ሆኖ ተመረጧል። ሃይሌ ህልሙን እውን ያደርግ ዘንድ ቁልፉ እጁ ላይ ነው። ከ15 መራጮች 9 ድምጽ አግኝቶ አሸንፏል።እነ ሃይሌ የቆሸሸውን ቤት በድፍረት ማጽዳትና ማስተካከል አለባቸው። ሚዲያው፣ የሚመለከታቸው አካላት፣ የአገሪቱ ባለስልጣንት ሙሉ እገዛ ሊያደርጉላቸው ይገባል። የዛጎል ዝግጅት ክፍል ለአዲሱ አመራር ከወዲሁ መለካሙን ይመኛል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *