ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ማህበራዊ ቁርኝትን ያናጋው የኢንተርኔት እገታ

የኢትዮጵያ መንግሥት የስድስት ወራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከደነገገ ወዲህ በተንቀሳቃሽ ስልክ የኢንተርኔት አገልግሎትን ወይም የሞባይል ዳታን ዘግቷል፤ በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችንም አግዷል። ይህ እርምጃ እያንዳንዱን የዋና ከተማ አዲስ አበባ ነዋሪ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ተፅዕኖ ቢያሳድርም በተለይ ደግሞ በኢንተርኔት ግንኙነት እና እንቅስቃሴ ላይ ጥገኛ የሆነዉን የወጣቱን ትዉልድ ሕይወት መንካቱን ጀምስ ጄፈሪ ከአዲስ አበባ የላከዉ ዘገባ ያመለክታል። ለዘገባዉ ካነጋገራቸዉ አብዛኞዎቹ ማንነታቸዉ እንዳይታወቅ በመጠየቃቸዉ ለጥንቃቄ ሲባል ስሞቻቸዉ መለወጡንም ጠቅሷል።

አውዲዮውን ያዳምጡ።04:24

http://www.dw.com/am/
አዲስ አበባ ላይ ሰዎች በየቤቱ የሚያደርጉት ድግስ መንግሥት በደነገገዉ የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት ከዚህ በፊት እንደነበረዉ ያለ አይደለም። መስከረም 28 2009ዓ,ም ተግባራዊ እንደሚሆን በይፋ የተደነገገዉ አዋጅ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል ቀደም ሲል የነበረዉን የተቃዉሞ እንቅስቃሴ እንዳበረደዉ መናገር ይቻላል። ሆኖም ግን አሁንም ኢንተርኔቱ ላይ የተጣለዉ እገዳ፤ የእጅ ስልክ የኢንተርኔት አገልግሎትን እና የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን እንደዘጋ ነዉ። ለምን ያህል ጊዜም እንደተዘጉ እንደሚቆዩ፤ ማንም በእርግጠኝነት የሚያዉቀዉ ነገር የለም። «ማኅበራዊ ሕይወትህ ይጎዳል፤» ትላለች ፋታ ለሌለዉ ማኅበራዊ ሕይወቷ ኢንተርኔትን አዘዉትራ የምትጠቀመዉ በ20ዎቹ አጋማሽ የዕድሜ ክልል የምትገኘዉ ሩት። በነገራችን ላይ በዚህ ዘገባ የተካተቱ ሰዎች ማንነታቸዉ እንዳይታወቅ በመጠየቃቸዉ ለጥንቃቄ ሲባል ስሞቻቸዉ ተለዉጠዋል ይላል ጄምስ ጄፈሪ። እናም እንደ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ነዋሪዎች በርከት ያለ ወጪ ለኢንተርኔት መድባለች፤
«በሞባይሌ ኢንተርኔት መጠቀም በምችልበት ወቅት ወደየትኛዉ ድግስ እንደተጋበዝኩ እና መቼም ግብዣ እንዳለኝ መመልከት እችል ነበር። አሁን ግን ልታገኝ የምትፈልጋቸዉን ሰዎች ሁሉ በየሰዓቱ ማግኘት ስለማይቻል የግድ መደወል ወይም አጭር የጽሑፍ መልዕክት ማለትም SMS መላክ ይኖርብኛል።»

Facebook China Symbolbild (picture-alliance/dpa)

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የመንግሥት ጣልቃ ገብነት መጠነኛ የሚሆንበት ስፍራ ካለ ሰዎች የሚያዘወትሯቸዉ የከተማዉ ማኅበራዊ መስተጋብር የሚደምቅባቸዉ ስፍራዎች ናቸዉ በማለት ሲቀልዱ ይሰማል።
በቦሌ ጎዳና ላይ የሞባይል ካርድ የሚሸጠዉ ወጣት ስለገበያዉ ሲጠየቅ «እንደነገሩ» መሆኑን ይናገራል። በሞባይል የኢንተርኔት አጠቃቀም ላይ የተጣለዉ እገዳ ሰዎች እንደከዚህ በፊቱ እንዲጠቀሙ የሚገፋፋ አለመሆኑንም ያስረዳል። ከዚህ ቀደም ታዳሚዎቻቸዉን በፌስ ቡክ አማካኝነት ይጋብዙ የነበሩት የሙዚቃ ድግስ አስተናጋጅ DJዎች ዛሬ ላይ ምነዉ የሙዚቃ አፍቃሪዎችን የስልክ ቁጥሮች ለክፉ ቀን መዝግበን ይዘን በሆነ ኖሮ ይላሉ። የምግብ ቤቶች ስለአዳዲስ የምግብ ዝርዝሮቻቸዉም ሆነ የዋጋ ቅናሽ በፈለጉት ሰዓት በፌስ ቡክ ገጻቸዉ ላይ መለጠፍ አልቻሉም። በርካታ የንግድ እንቅስቃሴዎች መረጃዎቻቸዉን ለሰዎች ለማድረስ በራሪ ወረቀቶችን ወደመጠቀም ፊታቸዉን አዙረዋል። ቁንጥጫዉ ያልተሰማዉ የለም።
«አንዳንድ የእኔ ጓደኞች በኢንተርኔት የቀጥታ ንግድ ለማካሄድ ብለዉ ሥራቸዉን ትተዋል። አሁን ምን ሊሰማቸዉ እንደሚችል መገመት ትችላለህ።» ትላለች ሩት።
«አሁን ቢያንስ ለሞባይል ስልኬ የሞላሁት ገንዘብ ረዥም ጊዜ ሊያቆየኝ ይችላል።» የምትለዉ ደግሞ የሩት ጓደኛ ትዕግስት ናት። ምሳቸዉን በአንድነት ሊበሉ ሁለቱ ወጣቶች ተገናኝተዋል።
«በሞባይሌ ኢንትርኔት ስጠቀም 100 ብር የሚያቆየኝ  ለተወሰኑ ቀናት ብቻ ነበር።  አሁን ግን ከአራት እስከ አምስት ቀናት ያዘልቀኛል።»
ያም ቢሆን ሁሉም ሰዉ ገንዘቡን እየቆጠበ ነዉ ማለት አይደለም። የኢንተርኔት አገልግሎት የሚሰጡ የንግድ ማዕከላት የተጠቃሚዉ ፍላጎት መጨመሩን አስተዉለዉ ዋጋ በመጨመር አጋጣሚዉ ያወረደላቸዉን ገበያ እየኮመኮሙ ነዉ። ምናልባትም በዚህ ምክንያት ይሆናል ከእያንዳንዷ የሥራ ሰዓት በኋላ በመላ ከተማዉ ዋይ ፋይ ባላቸዉ ሆቴሎች ጥጋጥግ ኢንተርኔት የሚጠቀሙ ማለትም ስማርት ፎን የያዙ በርካታ ወጣቶች አንዳቸዉ በሌላቸዉ ላይ ተደግፈዉ ለረዥም ሰዓታት ስልኮቻቸዉ ላይ አፍጥጠዉ የሚታዩት።
«በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን የኢንተርኔት አገልግሎት አለመኖር ማለት በጣም አስቸጋሪ ጥፋት ነዉ!» ይላል ለዶክትሬት ዲግሪዉ በመሥራት ላይ የሚገኘዉ ሄኖክ።
«ከዩ ቲዩብ ተለያይተናል፤ በኢንተርኔት ተጠቅመህ ከዩ ቲዩብ ትምህርቶችን መከታተል አትችልም። ሊንከዲን ወይም ትዊተር መጠቀም አንችልም። እያንዳንዱ መገናኛ ብዙሃን፣ ሁሉም ታግደዋል።»
ከምንም በላይ ተማሪዉን ያበሳጨዉ መፅሐፍትን እንኳን ከኢንተርኔት አዉርዶ መጠቀም አለመቻሉ ነዉ። ነገር ግን የኢንተርኔት ችግሩ እንዲህ ካለዉ የአቅርቦት መስተጓጎልም ያልፋል።
«ብዙዎቹ ወጣቶች ተስፋ አጥተዋል፤ ተደብረዋልም፤ ስጋትም ገብቷቸዋል፤ ምክንያቱም አንዳች ነገር መናገር ይፈልጋሉ ነገር ግን መንገዱ ተዘግቷል።» የሚለዉ ደግሞ የዩኒቨርሲቲ መምህር የሆነዉ ወጣት ዳዊት ነዉ።

Twitter Logo (Reuters/K. Pempel)

«ጉዳዩ ለጓደኛህ የሆነ ነገር ለማለት ብቻ አይደለም፤ በፖለቲካዉ ዉይይት ዉስጥ ለመሳተፍ ነዉ። በተለይ ደግሞ ገለልተኛ መገናኛ ብዙሃን በሌለባት ኢትዮጵያ ሌሎች ሰዎችም በፌስ ቡክ እንዲወያዩ እና እንዲከራከሩ ትፈልጋለህ።»
በተመሳሳይ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ከሚፈልጓቸዉን መሰሎቻቸዉን የሚያገኙበትን መንገድ እየቀየሱ ነዉ። ከምንም በላይ ስልክ መደወልና መልዕት መላላኩ አሁን እየጨመረ መጥቷል የምትለዉ በሠላሳዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል የምትገኘዉ ትዕግስት እነዚያን ኢንተርኔት ያልነበሩባቸዉን ዘመናት ማስታወስ ግድ ነዉ ትላለች።
«ሰዎች እዚህ አዲስ አበባ ላይ በሩቅ ካሉት ይልቅ ከመሰሎቻቸዉ ጋር መነጋገሩን ጀምረዋል።በኢንተርኔት ላይ የተጣለዉ እገዳ እንደዉም ሰዎችን እያቀራረበ ነዉ።»
እንደ ፌስ ቡክ እና ትዊተር ያሉት የማዕበራዊ መገናኛዎች እና መድረኮች አለመረጋጋቱን ለማባባስ ለቅስቀሳ ዉለዋል የሚለዉ መንግሥት እነሱ ላይ የጣለዉ እገዳ አስፈላጊነዉ ባይ ነዉ። ይህን በሚመለከት ከሕዝቡ የሚሰጠዉ አስተያየትም በጣም የተለያየ ነዉ። እንደ ሄኖክ ያሉት ወጣቶች ገዢዉ ፓርቲ ጠንካራ እጆቹን መጠቀሙን ይተቻሉ።
«መንግሥት ራሱ ምናልባት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚተላለፉትን የተዛቡ መረጃዎች በኢንተርኔት አማካኝነት የራሱን ወገን አስተያየት በማቅረብ ማረም ይችል ነበር። ሆኖም አያደርጉትም።» የሚለዉ ደግሞ የድረ ገጽ ጸሐፊዉ ዳንኤል ብርሃኔ ነዉ። ኢንተርኔት ላይ የተጣለዉ ገደብ አንዳች ማስተካከያ እንዲደረግለት ቢሞግቱም መንግሥት የሚለዉን የሚደግፉም አሉ።
«መንግሥት የወሰደዉ ርምጃ ትክክል ነዉ ብዬ አምናለሁ። ነገር ግን በተወሰነ መልኩ ቢሆን ጥሩ ነበር ባይ ነኝ። የሞባይል ዳታ እና የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑባቸዉ በዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆች አገልግሎቱ መለቀቅ ነበረበት ።» ይላል ለዶክትሬት ዲግሪዉ የሚሠራ ሌላ ተማሪ። ይህ በእንዲህ እንዳለም በመላዋ አዲስ አበባ ኢትዮጵያዉያንም ሆኑ የዉጭ ዜጎች ዓይናቸዉን በኮምፕዩተር እና በስማርት ስልኮቻቸዉ ላይ በማድረግ ለማየት የሚፈልጉት የኢንተርኔት ገጽ ከአሁን አሁን ይከፈታል በሚል ተክለዉ ሰዓቱን እየተመለከቱ መጠባበቅ ይዘዋል።

Related stories   “ጣልያኖችም ሆኑ እንግሊዞች ቅኝ ግዛትን ለማስቀጠል ህዝቡን በዘር መከፋፈልን እንደ አንድ ስልት ይጠቀሙ ነበር” -አቶ ታቦር ገረሱ ዱኪ

ሸዋዬ ለገሠ /ጀምስ ጄፈሪ  አዜብ ታደሰ

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0
Read previous post:
ጠዋት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት የተቀመጡት የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ከቀትር በሁዋላ የስንብት ደብዳቤ ደረሳቸው “ምክንያቱን ግልጽ አልሆነለኘም” አቶ ኢሳያስ ባህረ

  የልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ አቶ ሃይለማርያም በጠሩት ስብሰባ ላይ ከተገኙ በሁዋላ ከሰዓት...

Close