በተለያዩ የመንግስት መስሪያ ቢቶችና ተቋማት በአነስተኛ ብልሽትና እንከን የተጣሉ ንብረቶችን የመጠገንና ስራ ላይ የማዋል ልምድ አነስተኛ ነው። ይህ ችግር እጅግ ሰፊና አስተያየት ሲሰጥበት የቆየ ጉዳይ ነው። ዛሬ ፋና ይፋ እንዳደረገው በአዲስ አበባ ብቻ ከሚገኙት የፌደራል መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች ውስጥ 137 የችግሩ ሰለባ መሆናቸው ተጠቁሟል። ተቋማቱ ለሚወገዱ ንብረቶች ከ5ሺህ 500 ሜትር በላይ ሊለማ የሚችል ቦታ በብክነት ይዘዋል።

በዜናው ባይካተትም በተለይ በገጠር ፐሮጀክቶች ውስጥ ውድ ዋጋ የሚያወጡ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች ” አይሰሩም” እየተባሉ ይጣላሉ። አንዳንዶቹ የመንግስት ሃላፊዎች የራሳቸው የግንባታ ማሽን ስላላቸው ከኪራይ ገቢ ለማግኘት ሲባል ይህንን እንደሚፈጽሙ ከበቂ በላይ ጥቆማና ማስረጃ ሲቀርብ ነበር። የራሳቸው ማሽን የሌላቸው ደግሞ ከኪራይ የሚገኝ ኮሚሽን ለማግበስበስ ብህዝብ ንብረት እንደሚቀልዱ ያደባባይ ሚስጢር ነው።

በሙሉ ጉልበቱ የማይሰራው የፌደራሉ የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ላይ ባካሄደው ጥናት ” የፐሮጀክት ሃላፊ መሃንዲሶች የራሳቸውን ማሽን ራሳቸው ሃላፊ ሆነው ለሚሰሩበት ተቋም ያከራያሉ። ራሳቸው ክፍያ ፈቅደው፣ ራሳቸው ከፍያ ይረከባሉ” ሲል ጥናቱ በቀረበበት ወቅት መናገሩ ይታወሳል። እንዲህ ያለው የከፋ ሌብነት መኖሩ ስለሚታወቅ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅሙ ካለው በነካ እጁ ቢዳስሰው ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ።

Related stories   Egypt-Sudan alliance shifting in row with Ethiopia over Nile dam

የፋና ዘገባ እንዲህ ይነበባል።

54 በመቶ ያህሉ የፌደራል የመንግስት መስሪያ ቤቶች ንብረቶችን በወቅቱ ባለማስወገዳቸው ለሃብት ብክነትና ህገ ወጥ ተግባር የተጋለጡ መሆኑን አንድ ጥናት አመለከተ።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተደጋጋሚ ለረጅም ጊዜ የቆዩ ንብረቶች ስለሚወገዱበት ሁኔታ ያሳስባል።

ያን ተከትሎም ባለፉት ጥቂት አመታት ሊወገዱ የሚገባቸው ንብረቶች ለሽያጭ ቀርበው ከ4 መቶ ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማስገኘት ችለዋል።

ይሁን እንጂ ችግሩ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ ተንሰራፍቶ መታየቱን ነው የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ጥቅምት 2009 ባወጣው ጥናቱ ያረጋገጠው።

Related stories   ደመቀ መኮንን በፊንላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሚመራ የአውሮፓ ህብረት ልዑክ ጋር ተወያዩ

ጥናቱ እንደሚያመላክተው ከሆነ በፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶችና የልማት ድርጅቶች በስፋት ተከማችተው ከሚታዩ የሚወገዱ ንብረቶች ውስጥ፥ ተሽከርካሪዎች፣ ኮምፒውተርና ተያያዥነት ያላቸው የኤሌክትሮኒክሰ እቃዎች፣ የቶነር ካርትሬጅና ቁርጥራጭ ብረታ ብረቶች ይገኙበታል።

የመንግስት ግዢና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ይገዙ ዳባ እንደሚሉት፥ በአዲስ አበባና አካባቢዋ በሚገኙ 166 የፌደራል መንግስት መስሪያ ቤቶችና የመንግስት ልማት ድርጅቶች የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል።

የሚወገዱ ንብረት ክምችት ያላቸው መስሪያ ቤቶች 137 ሲሆኑ የተቀሩት ክምችት የሌለባቸው ናቸው፤ ክምችት የሌለባቸው ከተባሉት ውስጥ ደግሞ ስምንቱ ተቋማት አዲስ ናቸው።

የንብረቶቹ ዝርዝር ለመስሪያ ቤቱ የበላይ ሀላፊዎች ለውሳኔ አለመቅረብ፣ ከቀረበ በኋላም ውሳኔ የማይሰጥበት መሆኑና ሌሎች ምክኒያቶች ንብረቶቹ ለረጅም ጊዜ ተከማችተው እንዲቆዩ ምክንያት ተብለው ቀርበዋል።።

በዚህ ሂደት 54 በመቶ ያህሉ የፌደራል የመንግስት መስሪያ ቤቶችና የመንግስት ልማት ድርጅቶች፥ ንብረቶችን በወቅቱ ባለማስወገዳቸው ለሃብት ብክነትና ህገ ወጥ ተግባር የተጋለጡ ናቸው ብለዋል።

Related stories   “ዶላር እናወርዳለን” የውጭ አገር ዜጎችን የዝርፊያ ድራማ ፖሊስ አለሳልሶ ይፋ አደረገው

ከተባሉት 137 ተቋማት 561 ተሽከርካሪዎች፣ 555 ማሽነሪ፣ 10 ሺህ 466 ጎማ፣ ከ72 ሺህ በላይ መለዋወጫዎች፣ በአጠቃላይ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ የተለያዩ ንብረቶች ናቸው አገልግሎት አቁመው የተቀመጡት።

በንብረቶቹ ምክንያትም ከ5 ሺህ 500 በላይ ሜትር ካሬ ቦታ ተይዟል።

ታዲያ እነዚህ ንብረቶች በወቅቱ ባለመወገዳቸው በርካታ ተጽዕኖዎችን ከማሳደርም በተጨማሪ ከፍተኛ ኪሳራ እንደሚያስከትሉም ነው አቶ ይገዙ የተናገሩት።

የተደረገው ጥናትም ንብረቶቹን ወጥ በሆነ ሁኔታ ወይም በተዘረጋ መዋቅር በአፋጣኝ ማስወገድ በሚል የመፍትሄ አቅጣጫ አስቀምጧል።

ከዚህ ውጪ ውስን ቀናትን ለተቋማቱ በመስጠት እንዲወገዱ የሚሉና መሰል የመፍትሄ አቅጣጫዎችም ተቀምጠዋል።

ይሁንና ዳግም ችግሩ እንዳይከሰት ቀድሞ የነበረውን የንብረት አወጋገድ መመሪያ በጥልቀት በማየት ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባም ጥናቱ ጠቁሟል።

አሁን ላይ ጥናቱ ተጠናቆ በዛ መሰረት ወደ እርምጃ መግባት እንዲቻል ለገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር መላኩን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *