(ክፍል ሁለት)

በልዑል ዘሩ

በዚሁ ዓምድ ላይ ባለፈው ሳምንት በተስተናገደው ምልከታዬ በአገሪቱ በገዢው ፓርቲና በመንግሥት ውስጥ ሁለተኛው ፈጣን ተሃድሶ አለመደረጉን አንስቻለሁ፡፡ በተለይ ከስድስትና ከሰባት ዓመታት በፊት ሥር ነቀል ማሻሻያ ማድረግ ሲገባ፣ ለተፈጠረው መጓተት ምክንያት የሚባሉ ትንታኔዎችንም ለጋዜጣ አንባቢያን በሚመች መንገድ ብቻ ሰንዝሬአለሁ፡፡ ያ ባለመሆኑና አገሪቱ በከፍተኛ ብድር ጭምር ያሳየችውን የኢኮኖሚ ዕድገት መጋረጃ በማድረግ ‹‹በተሳክቶልናል›› ስም የተፈጠረው የሥርዓት ብልሽት የጋበዘውን ሕዝባዊ እምቢተኝነትና ጥፋትም በስፋት አንስቻለሁ፡፡ እስከ የአሁኑ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ድረስ በመተንተን ማለት ነው፡፡

በሕዝቡ ቁጣና ፍላጎት ጭምር ተገፍተው ወደ ተሃድሶ የገቡት ገዢው ፓርቲና መንግሥት የጀመሩትን ተሃድሶ (Reform) የሚጠራጠሩ ሰዎችን መከራከሪያም ጠቃቅሻለሁ፡፡ በግሌ ይኼ የሥርዓት መታደስና ወቅቱንና የሕዝቡን የግንዛቤ ደረጃ ከግምት ያስገባ የማሻሻያ ዕርምጃ ጠንካራ አይደለም የምልበትን ምክንያት ለማንሳት እወዳለሁ፡፡ ይኼ በየብሔራዊ ድርጅቱ ደረጃ የማነሳው ክፍተት ‹‹እነማንን ተጠያቂ አደረገ?›› ስል ለመሞገትም እወዳለሁ፡፡

የአማራ ክልልና ብአዴን

ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የ36 ዓመት ዕድሜ ያለው ከሕወሓት ቀጥሎ የዕድሜ ባለፀጋ ድርጅት ነው፡፡ በትጥቅ ትግሉ የ11 ዓመታት፣ አገር በመምራት 25 ዓመታት ዕድሜ ያለው ነው፡፡ ይኼ ድርጅት በአገሪቱ የጋራ አመራር ውስጥ ካለው ድርሻ ባሻገር፣ የአማራ ክልልንም በማስተዳደር ለተገኘው የመሠረተ ልማት የማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ሆነ ለሰላሙ (በተለይ በአማራ ክልል ሽፍታ ለሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች ነፃ መውጣት ድርሻው የጎላ ነበር) አስተዋጽኦው ነበረው፡፡

አሁን የክልሉ ሕዝብም ሆነ ከክልሉ ውጪ ያሉ የአማራ ተወላጆች በድርጅቱ ላይ የሚያነሱበት ጥያቄ ግን በርትቷል፡፡ ተለጣፊና የወከለውን ሕዝብ ጥቅም የማያስከብር አድርገው ይቆጥሩትም ይዘዋል፡፡ ለዚህ አገላለጽ የሚያነሱት መገለጫም አለ፡፡

አንደኛው በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች ‹‹በነፍጠኛ ሥርዓት›› ወይም በገዥ መደቦች ስም የሚደርስባቸውን ዱላ አለመመከቱ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ድርጊቱ ፍትሐዊ እንዳልሆነ በይፋ አለማውገዙ ዋነኛው ድክመቱ እንደነበር በራሱ አባላትና አመራሮች በተሃድሶው መድረክ እየተነሳ ነው፡፡

ለምሳሌ ከ1984 ዓ.ም. ኦነግ የተባለው ጽንፈኛ የፖለቲካ ቡድን በምሥራቅ ሐረርጌ፣ በአርሲና በምሥራቅ ወለጋ የፈጸመው በደል ይጠቀሳል፡፡ በመቀጠልም በተከታታይ ኦሕዴድ በተባለው የገዢው ፓርቲ አባል ድርጅት ካድሬዎችና ጠባብ ብሔርተኞች በምዕራብ ደቡብ ሸዋ፣ በአርሲ፣ በምዕራብ ወለጋ የተፈናቀሉ ሀብታቸው የወደመ የክልሉ ተወላጆች ትንሽ አልነበሩም፡፡ በቅርቡም በደቡብ ክልል ጉራፈርዳ፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የንፁኃን ሕይወት ሳይቀር የጠፋባት ክስተት ትልቅ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ በዚህ ክስተት የተጎዱ ዜጎችን እያሰባሰበ ለማገዝ ይሞክር የነበረው እንኳን መኢአድ የተባለው ተቃዋሚ ድርጅት መሆኑ የብአዴንን ቅቡልነት ጥያቄ ውስጥ ጥሎት እንደነበር በሒስ ተገልጿል፡፡ እንደ አገር ይኼ አካሄድ እንደ ጥፋት የተነሳውም ዘንድሮ ከአማራ ክልል ሌሎች ሲፈናቀሉ ነው፡፡

የብአዴን ግምገማ ላይ ሌላው ተደጋግሞ የተነሳው የመሪዎቹ አስመሳይነትና አድርባይነት ነበር፡፡ በአገሪቱ የሥልጣን እርከን እስከ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደረጃ የደረሱ የድርጅቱ መሪዎች ‹‹ኪራይ ሰብሳቢነት›› የተባውን የሥርዓቱ አደጋ ለመመከት ያደረጉት ጥረት ደካማ ነበር፡፡ ዛሬ ‹‹እነ እገሌ ተጠቀሙ፣ በለፀጉ …››  የሚለው ካድሬ ሁሉ ትናንት ድርጊቱ ሲፈጸም እያወቀ የድርሻውን እየወሰደ አልያም በአድርባይነት ዘርፍ ሲፈጸም በዝምታ እያለፈ እንደነበር ጥርጥር የለውም፡፡

ለእዚህ አንድ ማሳይ የሚሆነው ሁሉም የትምህርት ሚኒስትሮች (ወ/ሮ ገነት ዘውዴ፣ ዶ/ር ስንታየሁ ገብረ ሚካኤልና አቶ ደመቀ መኮንን) የመሩት መሥሪያ ቤት የክልሉን ሕዝብ የሚያስቆጣና ለውዥንብር የሚያጋልጥ መጽሐፍ ሲያሳትም በዝምታ አልፈዋል፡፡ በቅርቡም ‹‹ድክመታችን ነው›› ሲሉ ግለ ሒስ አድርገዋል፡፡ ግን ምን ቅጣት ደረሰባቸው? ለሚለው ጥያቄ መልስ የሚሰጥ የለም፡፡

በቅርቡ በሰሜን ጎንደር ለተነሳው ቀውስ ብአዴን ተጠያቂ ነው፡፡ የቅማንትን የማንነት ጥያቄ በአግባቡ ባለማስተናገድም ሆነ የወልቃይትን (የግጨውን ወሰን ጉዳይ) በወቅቱ መልስ እንዲሰጥ ባለማድረጉ ይወቀሳል፡፡ ከጉዳይም አልፎ ጉዳዩ የሞት ሽረት አጀንዳ ሆኖ በሕዝቡ ውስጥ እንዲብሰከሰክ ከተቃዋሚዎች በላይ ራሳቸው የብአዴን ካድሬዎች መሥራታቸውን ራሱ ኢሕአዴግ በተሃድሶው ማረጋገጡ በቅርቡ ተገልጿል፡፡ ግን ምን ዓይነት ዕርምጃ በእነማን ላይ ተወሰደ? ሌላውስ ምን ተማረ?

በመሠረቱ ብአዴን የተባለው የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ አሁንም ከአንድ አካባቢ ልጆች እጅ ወጥቶ ክልላዊ ገጽታን አልተላበሰም፡፡ በአብዛኛው የሰሜን ወሎና የዋግምራ ‹‹ታጋዮች›› ድርጅቱን ከላይ እስከ ታች መምራታቸው ብቻ ሳይሆን የጎንደር፣ የጎጃምና የሸዋ ፖለቲከኞችን አለማፍራቱ ‹‹ውስጠ ወይራ›› አስመስሎታል፡፡ ድርጅቱ በእነዚህ ዓይነቶቹ ውትፍትፍ አሠራሮቹ ቢተችም ግን የጎላ ሌብነት ውስጥ የተሰማሩ መሪዎች እንደሌሉት ተወሰቷል፡፡ ይኼንን ወደፊትም አስጠብቆ መሄድ አለበት፡፡

በግምገማው እንደተረጋገጠውም ‹‹እገሌ ውስኪ ስላመጣልህ አሾምከው፣ ያቺ ተሿሚ የሚስትህ እህት ወይም ውሽማህ አይደለችም ወይ? ከድርጅት ጽሕፈት ቤቱ እስከ ላይ ያለ ቡድነኝነት….›› ከመነሳት የዘለለ የዘርፍ ጉዳይ አልነበረም፡፡ ‹‹ማሽነሪ ገዝተው ያከራያሉ፣ ሁለትና ሦስት ቦታ ይዘዋል፣ ሕንፃ ሠርተዋል፣ ከፍ ያለ ሀብት አከማችተዋል….›› የተባሉትም ጥቂትና በአዲስ አበባና በፌዴራል መዋቅር ያሉት ባለሥልጣናት ብቻ ናቸው፡፡

ይኼ ሁሉ ድክመት ለቀናት በዘለቀ ተሃድሶ የተነገረበት ድርጅት ግን በሚያስቅና በሚያሳዝን ሁኔታ መሪዎቹን እንኳን አልቀየረም፡፡ የሰሜን ጎንደር ዞን አስተዳዳሪና የጎንደር ከተማ ከንቲባ ከመነሳታቸው በስተቀር ‹‹በመጨረሻ ማስጠንቀቂያ› የታለፉት ሊቀመንበሩና ምክትል ሊቀመንበሩ እንኳን ባሉበት መቀጠላቸው እየተወራ ነው፡፡ ዕውን ይኼ ተሃድሶ ነውን?!

የትግራይ ክልልና ሕወሓት

ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) የኢሕአዴግ እርሾ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከትጥቅ ትግሉ ጀምሮ ተፅዕኖ ፈጣሪ ድርጅት ነው፡፡ ጠንካራ የክልሉ ሕዝብ ድጋፍ ያለው መሆኑም ይታወቃል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን አሁንም ከስያሜው ጀምሮ የነፃ አውጭ ባህሪን መላበሱ በሌላው ወገን ዘወትር ለሐሜትና ለትችት አጋልጦታል፡፡

በዘንድሮው ተሃድሶ በሕወሓት መሪዎችና ካድሬዎች ላይም ሆነ በራሳቸው የተነሱ በርካታ የብልሽት መሣሪያዎች እንዳሉ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ ቀዳሚው የፀረ ዴሞክራሲ ባህሪ መንገሡ ነው፡፡ ማሳያው ክልሉ የማዕከል ውሳኔን ገሸሽ ማድረጉ ብቻ አይደለም፡፡ በወልቃይት ጉዳይም ሆነ በሌሎች የወሰን ጉዳዮች ጫጫታ ሳያስነሱ ሕዝብ ያሳተፈ ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ፣ የክልሉን ሕዝብ ሠልፍ ወደ ማስወጣትና ማስፈራራት መግባትም አገር የሚበትን እንደነበር ተሂሷል፡፡ አንዳንዶች ‹‹ነባር ታጋይ ነኝ›› ማለትን የበላይነት ስሜት መፍጠር እንደ ማድረግም ይቆጥሩታል፡፡

የትግራይ ሕዝብና ታጋዮች አገሪቱ ከፀረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትላቀቅ ታሪክ እንዳልሠሩ አሁን አሁን ብቅ ብቅ እያለ ያለው ትምክህትም አደገኛ ነው፡፡ ‹‹እኛ ታግለን ቤተሰቦቻችን መስዋዕት ሆነው … ›› በሚል ትርፍና እላፊ የመፈለግ ዝንባሌ ያላቸው የተወሰኑ የክልሉ ተወላጆች በሕገወጥ መንገድ በልፅገዋል፡፡ በአዲስ አበባ አንድ አካባቢ በሙሉ ከመያዝና በሕንፃ ከመንቆጥቆጥ አንስቶ በእርሻ፣ በኢንዱስትሪና በንግድ ዘርፍ ለፍቶ ጥሮ ባገኘው ሀብት ከለማው ዜጋ በላይ በፍጥነት ‹‹ቱጃር›› የሆኑ እንዳሉ በስፋት ይነገራል፡፡

ይኼን አስመልክቶ በቅርቡ ለ17 ቀናት በትግራይ ክልል በተካሄደው የከፍተኛ አመራሮች ተሃድሶ ላይ ዝርዝርና አሳዛኝ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡ በተለይ በክልሉ ያለው ነባር ካድሬ በአዲስ አበባና በፌዴራል መዋቅሩ ላይ ያነሳው ሒስ እውነተኛና መፍትሔ አመላካች ነው፡፡ ‹‹… ከድርጅታችን መርህ ውጪ በግል መጠቃቀምና በመንደር ልጅነት እየተሳሳቡ መሿሿም አለ፡፡ በአዲስ አበባ መዋቅር በዚህ ደረጃ ሕወሓት ተፅዕኖ መፍጠሩ ለብልሽትም ዳርጓል፡፡ ከመከላከያ፣ ከደኅንነትም ሆነ ከቢሮክራሲው እየወጡ የበለፀጉ ሙሰኞች ሕወሓትንም ሆነ የትግራይ ሕዝብን ሊወክሉ አይችሉም፡፡ እንዲያውም የአንዳንዶች ስግብግብነት ለዘመናት አብሮን ከኖረው ሕዝብ ጋር እያጋጨን ለፍተው ያገኙ የክልላችን ተወላጆችን ለአደጋ እያጋለጠ ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ ሊወገዝና ሊታረም ይገባል፡፡ መጠየቅ ያለበትም በአብዮታዊነት ተወስኖ መጠየቅ አለበት፤›› ማለታቸው የትልቅነት ማሳያ ነው፡፡

ይኼ በራሱ በሕወሓት ካድሬዎች የተነሳ ‹‹የእንታረም›› ትግል በሌሎቹ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችም መነሳቱ ይነገራል፡፡ በተለይ በመሬት፣ በኮንትሮባንድ፣ በወጪና ገቢ ምርት እንዲሁም በታዳጊ ክልሎች አካባቢ ባለ ቅርምት ጤነኛ የማይመስል ዝንባሌ አለ፡፡ ይኼ ደግሞ ‹‹ሥልጣንን መበልፀጊያ›› የሚያደርጉ ዝንባሌ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶችን የብሔር ሥርዓት የሚያደርጉ የተሳሰተ አስተሳሰብ አስተዋፅኦ አድርጓል በሚል፣ በአሁኑ ተሃድሶ ለመቀየር ጥረት እየተደረገ ይመስላል፡፡ ግን ውጤቱ ምን ይሆናል? ዕርምጃውስ እስከ የት ይደርሳል? የሚለው ወደፊት የሚታይ ይሆናል፡፡ ከዚህኛው ድርጅት ጋር በተያያዘ ተደጋግሞ የሚነሳው የኢንዶውመንት ግዙፍ ሀብት ጉዳይም ዝብርቅርቅ ስሜት እንደፈጠረ ቀጥሏል፡፡

የኦሮሚያ ክልልና ኦሕዴድ

ሰፈውን የኦሮሞ ሕዝብ እየመራ ያለው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ገና ከተቋቋሙበት ጊዜ አንስቶ ፈተና ያልተለየው ነበር፡፡ በተለይ በኦሮሞ ሕዝብ ውስጥ ከፍ ያለ ዕውቅና የነበረው አንጋፋው ኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከነበረው ተገዳዳሪነት አንፃር ድርጅቱም ሰፊ ተቀባይነት አልነበረውም፡፡ በኋላ ላይ ወጣቶችን በማሳተፍ፣ የክልሉን ልማትና ሰላም በማፋጠን የተሻለ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ ግን አይካድም፡፡ በዚያው ልክ በአገሪቱ በርከት ያሉ የኦሮሞ ተቃዋሚ ድርጅቶች የመሠረቱ ፖለቲከኞች ተፅዕኖ ቀላል አልነበረም፡፡

በተሃድሶው በየመድረኩ እንደተነሳው ይኼም ድርጅት የጎሉ ችግሮች የነገሡበት ሆኗል፡፡ ቀዳሚው ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት ነው፡፡ በተለይ ከመሬት ጋር በተያያዘ ክልሉ ያለውን ሰፊና ወሳኝ የከተማ መሬት የመቀራመትና የመቸብቸብ ጉዳይ የተፈቀደ በሚመስል ደረጃ ተፈጽሟል፡፡ አመራሩ ብቻ ሳይሆን ታች ያለው ካድሬ አራትና አምስት መሬት ይዞ በመሸጥ ሀብት ከማፍራቱም በላይ፣ የክልሉ ሕዝብ እንዲማረርም አድርጓል፡፡ አንዳንድ የድርጅቱ ባለሥልጣናትም ከትልልቅ ባለሀብቶች ጀርባ ስማቸው ከመነሳቱ ባሻገር ባለሕንፃና ፋብሪካም ሆነዋል የሚል ጉምጉምታም አለ፡፡ ይኼ ብቻ ሳይሆን የሥራ አስፈጻሚና የፖሊስ ኮሚሽነሮች ቤተሰቦችና ወንድም/እህቶች እንዴት ትልቅ ኮንትራክተርና ባለሀብት ሆኑ? ሲባል መልስ አይገኝም፡፡

ይኼ የከፋ ችግር ዋነኛ የጥቅም ማዕከል ከመሆኑ የተነሳም የአዲስ አበባና የዙሪያዋ የጋራ ማስተር ፕላንን ፉርሽ ያደረገውም ራሱ ኦሕዴድ እንደሆነ በግልጽ ታይቷል፡፡ ማስተር ፕላኑ በጥበብና በሥነ ምግባር ከተመራ ያለው አገራዊ ፋይዳ ተዘንግቶ፣ የኦሮሞን ሕዝብ መሬት የመንጠቅ ጉዳይ አስመስሎ የቀሰቀሰውም ካድሬው ራሱ ነው፡፡ ይኼ ደግሞ ቀደም ሲል አንስቶ በመሬት ካሳ አሻጥርና ቅሸባ የተማረረውን የክልሉ ሕዝብ ‹‹እሳት እንዲጎርስ እሳት እንዲለብስ›› አድርጎታል፡፡

በመሠረቱ በኦሮሚያ ክልል ለደረሰው የሰው ሕይወትና የአገር ሀብት ጥፋት የጽንፈኛው ጃዋር መሐመድና ቢጤዎቹ አሉታዊ ቅስቀሳ ድርሻው የጎላ ቢሆንም፣ የኦሕዴድ ድክመትም ትልቅ ድርሻ ነበረው፡፡ አሁን አገር አቀፍ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገጉና የፌዴራሉ የፀጥታና የደኅንነት ኃይል ወደ ክልሉ በመግባቱ አንፃራዊ ሰላም ቢሰፍንም፣ ኦሮሚያ ግን ለአደጋ ተጋልጣ ነበር፡፡ ለዚህ ጥፋትም የድርጅቱ መሪዎችና የክልሉ አስተዳዳሪዎች ቁጥር አንድ ተጠያቂ እንደሆኑ መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡

ኦሕዴድ ግን ሊቀ መናብርቱን ቢቀይርም ‹‹በፈቃዳቸው እንደለቀቁ›› ገልጾ ነበር፡፡ ምንም እንኳን አዲስ በመሠረተው ካቢኔ የተሻለ ብቃትና ያላቸውና  አዳዲስ ሰዎችን ቢያስገባም በሀብት ‹‹የተንበሸበሹ›› የሚባሉ ሰዎችን አሁንም በተለያዩ ድርጅትና በመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ አስቀምጦ ያለምንም ተጠያቂነት ለመቀጠል መሻቱ ታይቷል፡፡ የቡድንና ሕገወጥ ኔትወርክ ትስስሩ ስለመበጠሱም ሆኖ አደርባይነቱ ስለመሸነፉም የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ነገር ግን በአንፃራዊ ሁኔታ ለውጥ ማሳየቱ ደግሞ በተሻለ ደረጃ ላይ አስቀምጦታል፡፡

ደቡብ ክልልና ደኢሕአዴን

የደቡብ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕአዴን) በአንፃራዊነት አጭር ዕድሜ ያለው ነው፡፡ በትጥቅ ትግል እዚህ ግባ የሚባል ተግባር ባይጠቀስለትም፣ በአገር ግንባታው ሒደት ግን እስከ ጠቅላይ ሚነስትር የደረሱ መሪዎችን ያፈራ፣ በልማትም ሆነ በሰላምና መልካም አስተዳደር የበኩሉን ሚና የተጫወተም ነው፡፡

በአሁኑ ተሃድሶ በደኢሕዴን ውስጥ የሚነሳ ችግርና ድክመት መኖሩ ተለይቷል፡፡ አንደኛው የፓርቲው ፈላጭ ቆራጭ የሚባሉ አንዳንድ ግለሰቦች በሙስና መጠርጠር ጉዳይ ነው፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ክልል የሚነሳው የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ከሌሎቹ አንፃር አነስተኛ ሊባል ቢችልም፣ በሥልጣን ላይ ተቀምጠውም ሆነ ከባለሥልጣናት ተወዳጅተው የበለፀጉ ሰዎች የሞሉበት ነው፡፡

ደኢሕዴን የጠባብነት አዙሪት የሞላበት እንደሆነም ተናግሯል፡፡ እርግጥ 56 ብሔረሰቦችና ማንነት ባለበት ክልል ይኼ መሆኑ የሚጠበቅ ቢሆንም በሌሎች ሕዝቦች ታሪክና ማንነት ላይ ጥላቻ ያሳደሩ ካድሬዎች አሉበት፡፡ በየመንደሩ እየተነሳ ያለው ‹‹የማንነት ጥያቄ›› ምንጩ ይኼው እንደሆነ ይገመታል፡፡

አሁንም የድርጅቱ መሪዎች በኢሕአዴግም ሆነ በአገሪቱ ውስጥ ሥልጣን እየያዙ ከመጡት ቁልፍ ድርሻ አንፃር ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ጠባብነት፣ ትምክህትንም ሆነ የሃይማኖት አክራሪነትን ከማስወገድ አንፃር ድርሻቸው ትልቅ ነው፡፡ ይሁንና በአብዛኛው ከአደርባይነት ጋር በተያያዘ ደፍሮ ብልሹ አመለካከትና ተግባሮችን ያለማስተካከል ችግር ተነስቷል፡፡

በአጠቃላይ በገዢው ፓርቲና በመንግሥት ደረጃ ተሃድሶው መጀመሩ መልካም ነው፡፡ የተሿሚ መቀያየር ወይም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕዝብን ‹‹ፀጥ›› ማድረግ ብቻ ግን ተሃድሶ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እስካሁን ለተፈጸሙ መልካም ተግባሮች የሚመሠገኑ፣ ለጥፋቱም የሚወቀሱና የሚጠየቁ ሰዎች መኖር አለባቸው፡፡ ዴሞክራሲውን ያቀጨጩና ወደ መግደል እያደረሱ ያሉ ግለሰቦች አሠራሮችና አደረጃጀቶች ይፈራርሱ፡፡ የሕዝባችንን አንድነት የሚጎዱና መነጣጠልን የሚያመጡ አስተሳሰቦች ይቀረፉ፡፡ ከሁሉ በላይ ኢፍትሐዊነትን የሚያሰፋት አንዱ ዘራፊ ሌላው ተዘራፊ የሚሆኑባት የአሻጥር በሮች ይዘጉ፡፡ ይኼ ሲሆን ነው ተሃድሶው ከልብ ሊሆን የሚችለው፡፡ የሕዝብንም ቀልብ የሚገዛው እላለሁ፡፡

credit Reporter Amharic

ከአዘጋጁ፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን ኢሜይል አድራሻቸው zerul@yahoo.com. ማግኘት ይቻላል፡፡

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *