ለሁለት ተከታታይ ሳምንታት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ አቶ ልዑል ዘሩ የተባሉ ጸሐፊ ‹‹በተሃድሶው የተንቆረቆሩ ሒሶች ማን ላይ አረፉ?›› ሲሉ የሞገቱትን ሐሳብ አንብቤያለሁ፡፡ በእውነቱ ውስጥ አወቅ በሚመስል ዕይታቸው በየክልሉም ሆነ በፌዴራሉ መንግሥት ደረጃ ‹‹አሉ›› ያሏቸውን ዝርዝር ችግሮች አንስተዋል፡፡ ነገር ግን አሁንም ደፈር ብለው እነገሌ ብለው በዚህኛው ጥፋት ሊወቀሱ ሲገባ ታልፈዋል ወደሚል አቅጣጫ ቢያመለክቱን ኖሮ፣ የእሳቸውም ጽሑፍ ጥልቀት ያገኝ ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡

ያም ሆኖ ጥረታቸውን እያደነቅሁ በእኔም በኩል በተለይ እርሳቸው ያልተመለከቷቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ‹‹የጥልቅ ተሃድሶ›› መድረኮች ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡ እንደሚታወቀው አዲስ አበባ ከተማ በአራቱ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች የሚመራ ሲሆን፣ የተናጠልና ጥምር ኮሚቴ የሚዋኝበት ነው፡፡ በመሆኑም ‹‹የተሃድሶ መድረኮች›› እየተካሄዱ ያሉትም በሁለቱም አደረጃጀቶች ነው ለማለት ይቻላል፡፡

በእኔ እምነት የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ የልማት ተግባራትን ቢያከናውንም፣ በአፈጻጸም ወደኋላ የቀረባቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ (ለምሳሌ የሕዝብ የልማት ተሳትፎ፣ በመልሶ ማልማት ፈጥኖ መገንባት ላይ፣ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ፣ የከተማ ፅዳት፣ ትራንስፖርት…) ከዚህም በላይ በሌሎች ክልሎች እንደታየው ሕዝቡ በቁጣ ገንፍሎ አይውጣ እንጂ ቀላል የማይባል ምሬትና የመልካም አስተዳደር ዕጦት አለ፡፡ በኢፍትሐዊነት፣ በሙስናና ብልሹ አሠራር፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት ማጣት፣ ሥርዓት አልበኝነት… የሚገለጸው ይኸው ሕዝብ የማያረካ ክስተት ያለጥርጥር አሁን ያለው አመራር ውጤት ነው፡፡ ተሃድሶውስ ይህን እንዴት እያየው ይሆን?!

ሙስናና ‹‹አስቂኙ ድራማ›› 

ከዚህ ቀደም ለትምህርት ጉዳይ በውጭ አገር አብሮኝ የቆየ አንድ ወዳጄ፣ ‹‹ከዚህ በኋላ ኢሕአዴግ ሙስናን ታግሎ ሊያሸንፍ አይችልም፤›› በማለት ደጋግሞ ይከራከረኝ ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ማን ማንን ሊጠይቅ ይችላል? የሙስና ጣራውስ እስከ የት ድረስ ተብሎ ይገደባል? መቶ ሺሕ፣ አንድ ሚሊዮን፣ ባዶ መሬት፣ የሚከራይ ማሽን ወይስ ሕንፃ ያለው? እነዚህ የሌሉት ‹‹ከፍተኛ አመራር›› የለም ባይባልም ቁጥሩ ግን እዚህ ግባ አይሆንም ሲል አስደምሞኛል፡፡ የአንዳንዶቹን ሀብትም በሚያውቀው መረጃ ላይ ተመሥርቶ እስከ መግለጽ ይደርስ ነበር፡፡

ለዚህ አባባሉ ጥሩ ማረጋገጫ የሆነኝ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ አባላት (ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች) ግምገማ ‹‹እየተጠናቀቀ ነው›› ተብሎ የተገኘውን ውጤት ስሰማ ነው፡፡ ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚያስረዱት እነኛ በኔትወርክና በቡድንተኝነት የተዘፈቁ፣ የሕዝብ መሬት ያዘረፉና የድርሻቸውን ቅንጥብጣቢ የወሰዱ፣ በኪራይ ሰብሳቢው ባለሀብት ኪስ ውስጥ እንደ መሀረብ ገብተው የሚዞሩ፣ በሐሰት የትምህርት መረጃ ‹‹የሚመሩን›› በማወናበድ የውጭ ጉዞን የውኃ መንገድ ያደረጉ፣ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ፊንፊኔ ዙሪያ ከአንድም ሁለት ሦስት ቤቶች እያሉዋቸው በመንግሥት ቤት የሚኖሩ፣ አንዳንዶቹ በድፍረት ጭምር በሚሠሩበት (በሚመሩት) መሥሪያ ቤት ሳይቀር ጨረታ የሚወዳደር ድርጅት (በሌላ ሰው ስም) ያላቸው ነጋዴዎች ሆነው ሳለ… ‹‹መዋቅሩ ከከፋ ሙስና ነፃ ነው›› ተብሎ ሲደመደም በዓይኔ ማየቴና በጆሮዬ መስማቴ የተሃድሶውን ፉርሽነትና ግድፈት አረጋግጦልኛል፡፡

Related stories   አሳሳቢው የእስራኤልና ፍልስጤም ግጭት

በቅርቡ በስብሰባ ማዕከል አንድ የሕወሓት የተሃድሶ ጉባዔ ላይ ‹‹እንዴት ነው ማዕከላዊ ኮሚቴው ሙስና ውስጥ አልገባም የሚባለው? ለ25 ዓመታት ሁላችንም በበረሃ ታግለን ስንመጣ ከለበስነው ቁምጣ፣ ሸበጥና ክሹፍ በላይ ምን ነበረን? ዕውን ይኼ በደመወዝ ብቻ የተገኘ ነው?›› ያለች ነባር ታጋይ ነበረች፡፡

በእውነቱ የተሃድሶው እንዳይሆን፣ እንዳይሆን መሆን እንጂ አባባሏ ማንንም የሚያስቆጭ ነው፡፡ በየትኛውም ደረጃ ያለ የሥራ መሪ ኑሮ መርቶ፣ ልጅ አስተምሮ (አብልቶ፣ አልብሶ፣ አስጠልሎ)፣ እንደ አቅሙ ዘመድ ረድቶ በደመወዝና በአበል ብቻ ከኖረ በጣም ጠንካራ ነው፡፡ መሬት ላይ ያለው ግን ከዚያ በላይ ነው፡፡ ‹‹አመራሩ ነጋዴ ሆኗል›› እየተባለ ያለው በስሙ በተመዘገበ ንግድ ፈቃድ እንዳልሆነ ጥርጥር የለውም፡፡

በተለያዩ መረጃዎችና በሕዝብ ታዛቢዎች እንደሚደመጠው በእህት፣ በወንድም፣ በጋብቻ ትስስርና በዝምድና የሚፈጠር ሽርክና አለ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ‹‹እንዳይጠረጠር›› ከሌላ ብሔር ነጋዴ ሸሪኮች ጋር ሀብት የማካበት አደገኛ አካሄድም ተንሰራፍቷል፡፡ (አንድ የብአዴን አመራር በአርጎባ ማኅበረሰብ ውስጥ ከሚገኙ ባለሀብቶች ጋር ዱቄት ፋብሪካ እንደ ከፈተው ማለት ነው)፡፡ በአዲስ አበባ ደረጃ በተጨባጭ ወደ ውጭ ሀብት አሸሽቷል የሚባል ሰው ስለመኖሩ ማረጋገጫ የተገኘበት ባይኖርም፣ በሙስና የበለፀገ የለም ብሎ መደምደም ግን ተሃድሶ መቀመጫን ከመላጥና ወገብን ከመቁረጥ ያለፈ ተግባር እንደሌለው ያሳያል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ አመራሮች መሀል የብረትና የግንባታ ቁሳቁስ አስመጪዎች፣ ኮንትራክተሮችና ተቋራጮች የሆኑ የሉም?! (በሪል ስቴት ሽርክና ጭምር የሚታሙ አሉ) የጤና ተቋማት፣ መድኃኒት ቤት፣ ትምህርት ቤት ከፍተው በዘርፉ የወጣን ሕግ እስከ ማዛባት የደረሰው ማን ነው?! ሌላው ይቅር ከገቢያቸው በላይ መኖሪያ፣ ተሽከርካሪ፣ የልጆች ትምህርት… ያላቸው ቡችላ ነጣቂዎች በምን ይወቀሱ!?

ተሃድሶውን ትዝብት ላይ የጣለው ሌላው ጉዳይ ፎቅና ቪላ ለግላቸው ሠርተው ከኃላፊነት የተነሱ ‹‹የወሰዱት የሕዝብ ሀብት የውለታቸው ካሳ ነው›› የተባሉ ይመስል ዝም መባላቸው ነው፡፡ በከተማዋ መሬት ሲቸበቸብ፣ የመንገድና መልሶ ማልማት ካሳ ሲጎርፍ፣ የመንግሥት ግዥ ላይ ‹‹በቴክኒክ ስም›› በመቶ ሚሊዮኖች ወጪ ሲደረግ እነማን ነበሩ? ምን ሠሩ? ማለት አልተቻለም፡፡ በሚያሳዝን ደረጃ ከግምገማዎቹ በፊት የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የደኅንነትና የፖሊስ መረጃ ሳይሰበሰብ፣ ጠንከር ያለ የሕዝብ አስተያየት ሳይቀመር እንደተለመደው በኔትወርክ ‹‹ተሃድሶ›› ተደርጓል፡፡ ውጤቱም ‹‹ነፃ›› የሚል ሆኗል፡፡

አብሮ የበላ፣ የጠጣ፣ በእንካ በንካ የጥቅም ተጋሪ የሆነ፣ በሥራው ሕገወጥ ቡድን የፈለገውን እያደከመና እየመዘበረ በብሔር፣ በመንደር ልጅነት፣ በሃይማኖት ግንኙነት፣ በትምህርት አብሮነት… የቀረበውን ሲሰበስብ የከረመው እየተሞጋገሰ አልፏል፡፡ ያለጥርጥር የአዲስ አበባ ሙስናና የመልካም አስተዳደር ዕጦትም ቅንጣት ያህል ሳትቀነስ ተባብሳ ትቀጥላለች፡፡

ብልሹ አሠራርና ኢፍትሐዊነት

አንድ ሌላ የአስተዳደሩ የቅርብ ሰው እንዳጫወተኝ አንድ ቱባ ባለሥልጣን ድምፁን አጥፍቶና ተደብቆ ከአምስት ዓመት በላይ በመማር የፒኤችዲ ዲግሪ ከውጭ ይዟል፡፡ ይህ ሰውና ባልደረቦቹ ባወጡት ቀጭን ትዕዛዝ ግን በግላቸው በርቀት ወይም በኤክስቴንሽን በአገር ውስጥ ትምህርት የጀመሩ ባለሙያዎችና መካከለኛ አመራሮች ‹‹ሥራ ትበድላለችሁ›› ተብለው ትምህርት አቋርጠዋል ወይም ከሥራ ተባረዋል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ብቻ ከ1,500 በላይ ዝቅትኛ አመራሮች እንዳይማሩ ሲከላከሉ ኖረው ብዙ ውለታ (ለሥርዓቱ) ቢሠሩም ከዲፕሎማ በታች ናቸው ተብሎ ተባርረዋል፡፡

Related stories   ይናገር ደሴ "እየተዶለተብንና እየተቀመመልን ያለው ኢትዮጵያን የመበተን ሴራ ጉዳይ ለእኛ ኢትዮጵያውያን አዲስ ነገር አይደለም"

በከተማዋ የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች አይደለም ተገልጋይን ራሱን ሠራተኛውን የሚያማርሩ አሠራሮች ትንሽ አይደሉም፡፡ በቅጥር፣ በዝውውር፣ በምደባና በሹመት ላይ የሚታየው ደባ ኢሕአዴግን ሰው እንዲጠላ የሚያደርግ ነው፡፡ ቅሬታ ሰሚ፣ የዲሲፕሊን ኮሚቴ፣ የመልካም አስተዳደር ማስተባበሪያ… የሚሉ አወቃቀሮች የይስሙላ ናቸው፡፡ በብዙዎቹ ተቋማትም ከስም ባለፈ ሥራ ሲሠሩም አይታይም፡፡

ከዚህ በመነሳትም መርህና አሠራር ተሸርሽሯል፡፡ በብሔር መሰባሰብና መመዳደብ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያው በቅርቡ በአዲስ አበባ ከላይ እስከ ታች እየገቡ ላሉ የአንድ አካባቢ ተወላጅ አመራሮች እንኳን በኢሕአዴግ ደረጃ አባል ድርጅቱም በማዕከል አውቋቸውና እያረጋገጠ ያመጣቸው አልነበሩም መባሉ ነው፡፡ የግለሰብ መሳሳብ ማለት ይህንኑ ነው፡፡ ዘረፋና መጠቃቀሙም በዚያው እየበረታ ይሄዳል፡፡

በከተማው በሚያሳፍር ደረጃ የመንገድ፣ የቤቶችና ኮንስትራክሽን እንዲሁም የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ግንባታ በድርድር አልያም ‹‹በምርጫ›› ባለጨረታ አልተሰጠም!? ይህስ የኢፍትሐዊነት መገለጫ አይደለም? በሆስፒታሎች፣ በትምህርት ቤቶች ማስፋፊያ፣ በክፍለ ከተማና በወረዳ ጽሕፈት ቤቶች ግንባታ በመቶ ሚሊዮኖች የአስተዳደሩን ሀብት የሚያንቀሳቅሱ ተቋራጮች እንዴትና በማን ተመረጡ?! ዕውን አሠራሩ ግልጽነትና ተጠያቂነት አለው? በግንባታ ወቅት ለተፈጠረ የጥራት መጓደልና ‹‹አሻጥር›› (ለምሳሌ ዘውዲቱ ሆስፒታል፣ ምኒሊክ ሆስፒታል) ማን ተጠየቀ? ምንስ ዕርምጃ ተወሰደ? እነዚህ ሁሉ የብልሹ አሠራር ውጥንቅጦች በአፍ ካራቲስቶች ታልፈዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የአገልግሎት አሰጣጥና ብልሹ አሠራር መንሰራፋት ምክንያት እያለቀሰ ያለ ሕዝብ አለ፡፡ ጉዳያቸው ከወራት አልፎ ለዓመታት እየተንከባለለ ተስፋ የቆረጡም ብዙዎች ናቸው፡፡ በመልሶ ማልማትና በተለይ ‹‹በሕገወጥ ግንባታ›› ስም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የጎዳና ተዳዳሪ እስከመሆን የደረሱም አሉ፡፡ ከዚህም በላይ በየጊዜው በሚደርስባቸው ጫናና ማስፈራሪያ ይዞታቸውን በወረደ ዋጋ እየሸጡ ወደ ዳር የወጡ (አንዳንዶቹም ደብዛቸው የጠፋ) አሉ፡፡ ይኼን ከብልሹ አሠራርና ኢፍትሐዊነት ውጪ ማን ያደርገዋል? እንዲያው ሌላው ይቅር በቅርቦቹ የሐና ማርያምና የቦሌ ወረገኑ 30 ሺሕ ሰዎች መፈናቀል የሚጠየቅ ሰው ጠፋ!? አሳፋሪ ነው፡፡

አቅም አልባ አመራሮችና አዲስ አበባ

በከተማ አስተዳደሩ ብቻ ሳይሆን በአገር ደረጃም ስም ከሌላቸው (አንዳንዶቹም ሕጋዊ ዕውቅና የላቸውም) የውጭ አገር ኮሌጆች ዲግሪ መግዛት ተለምዷል፡፡ የአገር ውስጥ የርቀት ትምህርት ቤቶች የከተፋ አካሄድም ጋዋን ለብሰው የተነሱትን ፎቶ በትልቅ ፍሬም ለመስቀል እየረዳ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ማወናበድ ግን ብቃትና ተወዳዳሪነትን አያመጣም፡፡ የሕዝብ አገልጋይነትና ቁርጠኛ አመራርንም አይፈጥርም፡፡

Related stories   ወደ ድርደር ? ከታንክ ወደ አህያ የወረደው ትህንግ በማን ሊወከል?

በአዲስ አበባ ደረጃ በርከት ያሉ የብቃት ችግር ያለባቸው ‹‹የሥራ መሪዎች›› እንዳሉ ተደጋግሞ ይታያል፡፡ የተነገረን ደግሞ በማነብነብ፣ ‹‹ሕዝብ ምን ይለኛል›› ሳይሉ ያለ ይሉኝታ በመዘላበድ ‹‹አዋቂ መሪ›› የሚመስሉት ሁሉ አቅማቸው ደካማ ነው፡፡ ይህንን በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ደረጃ በጥልቀት መፈተሽ ተገቢ ይሆናል፡፡ ባልሠለጠኑበት ሙያና ባልጨበጡት ዕውቀት ውስጥ ገብተው ሴክተር ለመምራት (ኮንስትራክሽን፣ ትምህርት፣ ጤና፣ ዲዛይን) የሚንቦጫረቁም ትንሽ አይደሉም፡፡

ይህ እየታወቀ ግን በአሁኑ ‹‹መሬት አንቀጥቅጥ!›› ተሃድሶ አመራሩ የብቃት ችግር እንደሌለበት ተደምድሟል፡፡ ችግሩ የአመለካከትና የቁርጠኝነት እንጂ የሚያሠራ አቅም ማጣት አይደለም ተብሏል አሉ፡፡ የዚህ መደምደሚያ ዓላማ ደግሞ የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሚያ ክልል የወሰዱትን የአመራር ሽግሽግ በጎ ዕርምጃ ያህል እንኳን ላለመነካካት ነው፡፡ እነዚያን የለውጥ ቀበኞች፣ አንዳንድ ቡድኖችና አቅመ ቢሶች በመድረኩ ላይ እግር እንዲዘረጉ ለማድረግም ነው፡፡

በመሠረቱ አዲስ አበባ የሸገር ልጆች ከተማ ብቻ አይደለችም፡፡ የመላው የአገሪቱ ሕዝቦች የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማዕከልም ነች፡፡ ከዚያም አልፎ የአፍሪካ መዲና፣ ከ120 በላይ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቦች መገኛ፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትም መሰብሰቢያ ነች፡፡ በዚህ ላይ ፈጣን ለውጥ የጀመረች እንደመሆኗ ወደ ሚትሮፖሊታን ደረጃ ለመድረስ ሰፊ ሥራ ይጠብቃታል፡፡ ይህን እውነታ ተገንዝቦ በላቀ ኃላፊነት የሚሸከም፣ ተወዳዳሪና ብቃት ያለው አመራር ሊኖራት ይገባል መባሉም ለዚሁ ነው፡፡

አሁን በተያዘው መንገድ በኢሕአዴግ ‹‹አባልነት›› ታፔላም ሆነ በብሔር ተዋጽኦ ስም (ነባሩን ከተሜ እየገፉ) የገጠር ካድሬ በመኮልኮል የከተማዋን ትራንስፎርሜሽን ማረጋገጥ አይደለም ችግሮቿንም መቅረፍ ያዳግታል፡፡ አዲስ አበባ እኮ አሁንም የሞቱ ወንዞች የሞሉባትና በቆሻሻ ክምሮች የተዋጠች ነች፡፡ ለሕፃናትና አረጋውያን መዝናኛ፣ ለወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያ ዕጦት ያደቀቃት፣ እየተሻሻለ ቢመጣም የአረንጓዴ ልማቷ ያልተሟላ ከተማ ነች፡፡ ነዋሪዎችን መላወሻ የሚያሳጣ የትራንስፖርት እጥረት፣ ኑሮን የሚያማርር የመኖሪያ ቤት እጥረት (የኪራይ ዋጋ ማሻቀብ)፣ የመጠጥ ውኃ አለመዳረስ፣ ያልተሟላ አገልግሎት አሰጣጥ ከፍተኛ ሥራ የሚፈልጉ ናቸው፡፡

መዲናዋ ያላትን ተስፋ ያህል የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ በሱስና አልባሌ ምግባር መጠመድ ጭንቀቷ ሆኗል፡፡ ሴተኛ አዳሪነትና ልመና የዘወትር ገጽታዎች ናቸው፡፡ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው ፍልሰት ማስተናገጃ አዲስ አበባ ናት፡፡ እነዚህ ሁሉ የቤት ሥራዎች ከፊቷ በተደቀኑ ከተማ ላይ ነባሩን አመራር ሳይነካኩ ተዛዝሎ ለማሻገር ማሰብ ውድቀት ነው፡፡ ‹‹ጥልቅ ተሃድሶ›› አድርገናል እያሉ ለቀናት በር ዘግቶ ተመሳሳይ ዲስኩር መደርደር ሕዝብን የሚያሳዝን፣ መንግሥትንም ትዝብት ላይ የሚጥልና አገርንም የሚጎዳ ተግባር ነው፡፡ ‹‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይወረውሩሃል!!›› የሚባለው ተረት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

credit Reoprter Amharic