ዶናልድ ትራምፕ ኢትዮጵያዊ ቢሆኑ ኖሮ… ለኢትዮጵያ ፕሬዘዳንትነት ቢወዳደሩ ኖሮ.. አንደኛ የምመርጣቸው እኔ ነበርኩ፡፡በመመረጣቸውም ከተደሰቱት ጥቂት ኢትዮጵያውያን አንዷ ሳልሆን አልቀርም… (ደስታዬን እንዲህ በአደባባይ ለመግለፅ እድሉን ሳላገኝ ቆይቼ ነው የዘገየሁት) መቼም ይህን በማለቴ “እንዴት ሆኖ? ምን ሲደረግ? ካንቺ አይጠበቅም!”ካላችሁ ምክንያቶቼን እንደሚከተለው አስረዳለሁ፡፡የእናንተንም ኮሜንት መስጫው ላይ እጠብቃለሁ… የመጀመሪያው ነገር እውነትን መናገር ነው፡፡ ጊዜውና ዘመኑ ያጣው እንደ ትራምፕ ያሉ እውነተኛ ሰዎችን ነው፡፡ ከምንም ይልቅ የሚያደርጉትን “አደርጋለሁ” የማያደርጉትን “አላደርግም” የሚሉ እውነተኛ መሪዎች ያስፈልጉናል፡፡ መሪዎች እንዲህ እቅጭ እቅጩን እየተናገሩ ቢወዳደሩ ኖሮ ሃሳዊ እና የተታለሉ እልፍ ደጋፋዊዎችን ባላፈሩ ነበር ፡፡ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ወተት… በተግባር ግን እሬት… ባልሆኑም ነበር፡፡ ብዙ ድምፅ ለማግኘት ሲባል ስንቴ ተደለልን? … ተሸነገልን? የሚያስፈልገን ግን አብሮ ለመኖር ሲል አቋሙን የማይለዋውጥ … አፉና ድርጊቱ የማይጣረስ መሪ ነው፡፡ እውነትን ፊት ለፊት መናገር ቀላል ነገር ሆኖ አይደለም፡፡ ብዙ ፈተና እና ተቃውሞ ይኖረዋል፡፡ ህይወትን ጭምር ሊያስከፍል ይችላል… ግን እውነትትን የመነጋገር ባህልን ያዳብራል፡፡ እንደ እኔ አመለካከት የመቻቻል ፖለቲካው አለቅጥ ተጋኗል… ተለጥጧል ያለአግባብም ስራ ላይ ውሏል… ለመቻቻል እስከምን ምን ድረስ ዋጋ መክፈል እንዳለብን የተረዳነው አይመስለኝም፡፡ እውነትን መስዋእት አድርገን ተቻችለን እንኖራለን?… አብሮ መኖር እና መቻቻል መመስረት ያለበት በእውነት ላይ እንጂ በውሸት ላይ አይደለም፡፡ችግሮቻችን ዘለቄታዊ እና የተረጋጋ መፍትሄ የሚያገኙት በእውነት ብቻ ነው፡፡ ትራምፕ የሚናገሩት ነገር በተግባር መዋል አለመዋሉን ሳናይ እውነት/ ሃሰት ማለት ቢከብድም ቢያንስ በውድድር ወቅት ለመወደድ እና አብላጫን ድምፅ ለማግኘት የማይመስል ሽንገላ አልጨመሩበትም፡፡የማይነገሩ እውነቶችን አፍረጥርጠን ወተትን ነጭ ነው …አካፋን አካፋ ብንል … ‘እንደዚህ እባለለሁ ይህ ይደርስብኛል…’ በሚል ፍርሃት … እውነትን ጨፍልቆ የቆመ ማንኛውም ግንኙነት አይፀናም፡፡በመንግስት እና በህዝብ መካከል እንኳ ቢሆን…ውሸት የማይታወቅበት.. መተማመን የበለፀገበት.. ሌብነት መዝገበ ቃላት ላይ እንኳ የሌለበት ማህበረሰብ ቢኖረን አንጠላም፡፡ ይህ የሚመጣው ከመልካም አስተዳደር … በመንግስት እና በህዝብ እንዲሁም በማህበረሰብ መካከል የተዘረጋ መልካም አስተዳደር እንጂ በአፈጣጠራቸው ከሌሎቻችን የተሻለ ቅዱሳን እና ብፁአን ሆነው አይደለም፡፡እኛም ምንፈልገው የሀገሩን ክብር ብቻ የሚያስቀድም… “ትልቅ ነበርን…” ከሚል እንጉርጉሮ አውጥቶ ‘ትልቅ’ የሚያደርገን መሪ አይደለምን? . ሁለተኛው በስደተኞች ጉዳይ ነው፡፡ ይህን “ለመከላከል ድንበርን ማጠር መፍትሄ ነው” አሉ እሳቸው… እስማማለሁ፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ እኛም ድንበራችን መታጠር አለበት ባይ ነኝ ምክንያቱ ግን ሌሎች ወደ እኛ እንዳይገቡ ሳይሆን እኛ በህገወጥ መንገድ ድንበር ስናቋርጥ እንዳንሞት ነው ፡፡ በዛውም በሰሜን እና በምእራብ የሚደርስብንን የድንበር ጥያቄ ለዘለቄታው ለመፍታት ይረዳናል ባይ ነኝ፡፡የአንድ ሀገር ብቃት እኮ በችግር…በችጋር… በድህነት አለመፈተን አይደለም፡፡ “ዛሬ ማን ነን?” ነው ጥያቄው… ከሌሎች የባሰ ምን ድህነት ምን ችግር ገጠመን? ግን “እንዴት ባለ አስተዳደር እንደምን ባለ ስርአት ተወጣነው ነው?” ነው ጥያቄው…በነሱው አቆጣጠር በ1665 የለንደን ህዝብ 1/3ኛ በእሳት ቃጠሎ አልቋል ፡፡በቀጣዩ አመት 1666 ላይ ደግሞ 1/3ኛው በተስቦ ምክንያት ረግፏል…በአንድ አመት ውስጥ 1/3ኛ የሚሆን ህዝብ ብቻ በከተማዋ ቀርቶ ነበር… “ነበር” ን “ነበር” ማድረግ ስለቻሉ ዛሬ የምናውቃቸው ቦታ አሉ፡፡ ዛሬ በስደተኞች የሚማረሩት አውሮፓውያን ራሳቸው ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች በብዛት ተሰደዋል፡፡ …አያቶቻቸው እና ቅድመ አያቶቻቸው ጭቆናን ሸሽተው ሲሰደዱ የመሰረቷት ሃገር አሜሪካ ትልቅ ሆና ማየት የሚመኙት አባቶች እና እናቶች፤አሁንም ዋጋ የሚከፈልባት፤ ዜጋ በሃገሩ ተሸብሮ ተሸቆጥቁጦ የሚኖርባት እንዳትሆን የሚመኙ….የቀደመችው ታላቅ አሜሪካ የምትናፍቃቸው ተወላጆች…(የቀድሞ ስርአት ናፋቂ እንበላቸው ይሆን?) …ናቸው አሁን ላይ ለሪፐብሊካኑ ተወዳዳሪ ትራምፕ አብላጫ ድምፅ ሰጥተው ለፕሬዘደንሺያል ካንዲዴት ብሎም ለ’ኀይት ሃውስ’ ያበቋቸው፡፡ ቀድሞ ነገር ስደተኞች፤ አክራሪዎች ፤አደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪዎች ከሪፐብሊካን ጋር ምን ህብረት አላቸው? …ሰው በሀገሩ በነፃነት ለምን ይህን ፃፍክ ተብሎ የሚገደልባት(ቻርሊ ሄብዶ ጋዜጣ… ጋዜጠኞች የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው) አባቶቻቸው የሞቱለት ያ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ እና የመናገር መብት… ማንም መጤ ሊነጥቃቸው ከሞከረ… ከቻለ… የስደተኞችን ጉዳይ በትኩረት ማየት አግባብነት ያለው ነገር እንጂ የሚያስወቅስ አይመስለኝም፡፡ . የቀደሙት የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ አቦት ለስደተኞች በግልፅ እንዳሉት “እናንተ መጣችሁብኝ እንጂ እኛ አልመጣንባችሁም፡፡” ማንም ወዶ ከሀገሩ አይወጣም… ግን እንኳን ሰው ሀገር ሰው ቤት እንኳ እንግድነት ሲኬድ እንደቤቱ መኖር… መዋል ማደር የእንግዳ ወግ ነው…፡፡ እኔም የቀደመችውን ያቺ ታሪኳን ያነበብኩላት … ታላቋን ኢትዮጵያ በመናፈቅ እንደ ትራምፕ ያለ ሰው ለፕሬዘዳንትነት ቢወዳደር እመርጣለሁ እላለሁ፡፡ እንደ ሚዲያው ጩኸት እና ትራምፕን ጭራቅ ሂላሪን መልአክ አድርጎ እንደ መሳሉ (CNNም ለጥቅሙ)…የእንደ ሌላው ወገን ጥላቻ … ቢሆን ኖሮ እኮ ትራምፕ እዚህ ባልደረሱ ነበር…ነገር ግን የሃገሪቷን የቀደመ ክብር የሚመኙ ዜጎች ወደዋቸዋል፡፡መርጠዋቸዋል፡፡ እነሱ የሚበጃቸውን ያውቃሉ… አብዛኞቹ ሀገራት ከራሳቸው ፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ጥቅም አንፃር አይተው ተቃወሟቸው፡፡ ለሃገሪቱ ግን እንደሳቸው ያለ መሪ ከተወዳዳሪዎቹ መሃል ያለ አይመስለኝም፡፡ ታዲያ “እንደ ሮናልድ ሬገን ጊዜ ትልቅ አደርጋታለሁ ወደ ቀደመ ክብሯ እመልሳታለሁ” ማለታቸውን ብሰማ… ኢትዮጵያው ሆነው “ኢትዮጵያን በሚኒሊክ ጊዜ እንደነበረችው ታላቅ አደርጋታለሁ” ቢሉኝ ላልመርጣቸው ነው?(የቀድሞውን ስርዓት ስናፍቅ…) . ሶስተኛ ነገር የገንዘብ አቅም:- ገንዘብ ወደድንም ጠላንም የሌሎችን ትኩረት ይስብልናል፡፡ይህ ብቻ ሳይሆን ሃብታም ስልጣን ሲይዝ ቤተመንግስት ብርቁ አይሆንም፡፡ ከቤተ መንግስት እምብዛም ያልተናነሰ አኗኗር በግል መኖሪያ ቤቱ ካለው … ቅንጦት አታሎት ያለአግባብ የስልጣን ጊዜውን አያራዝምም፡፡እርግጥ ገንዘብና ስነምግባር የተገናኙ ነገሮች አይደሉም፡፡ ሃብታም ሆኖ ዘራፊ አለ፡፡ ደሃ ሆኖ ታማኝ አለ፡፡ ሃብታም ብር ስላለው ተጨማሪ አይፈልግም ማለት አይደለም፡፡ደሃም ስልጣን ሲይዝ ያለአግባብ የሀገር እና የህዝብ ሀብት ለግል ጥቅሙ ያውላል… በምዝበራ ያገኘውን ገንዘብ በዘመድ አዝማድ ስም በውጪ ባንኮች ያስቀምጣል ማለትም አይደለም፡፡ስልጣን እጅ ላይ ሲገባ ደሃም ሆነ ሀብታም እኩል ነው የሚያገኘው… እንደ እኔ እንደ እኔ ስልጣን ላይ የሚወጣ ሰው ከመካከለኛው የህብረተሰብ ክፍል ቢሆን ይመረጣል፡፡እጅግም በድህነት ተቆራምዶ ያደገ ከሆነ ባለሃብቶችን የመበቀል መንፈስ ይዞት ያለአግባብ በታክስ እና ቀረጥ እንዳያማርር…የስልጣን እና የቤተመንግስት አኗኗር ብርቅ ሆኖበት ጮማ እየቆረጠ ውስኪ ሲጎነጭ ሲጠግብና ሲንፈላሰስ ከመደበኛ ስራው እንዳይዘናጋ… እጅግም በቅንጦት ያደገ ከሆነ ድህነትን ስለማያውቅ ለድሆች አይራራም፡፡ ይልቁንም ባለፀጎች ሃብትን ለማከማቸት የሚለፉት ልፋት እና ጥረት እያሳዝነው ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍሉን ችላ ይላል፡፡ መካከለኛ ኑሮ ላይ ያለ ሰው ስልጣን ከያዘ ግን ሁለቱንም ያመጣጥናል … ዳሩ እኛ ሃገር መካከለኛ ኑሮ የለም፡፡ የምጣኔ ሃብት ሂደቱ ከስራቸው ብዙሃኑን ደሃዎች ያሰለፉ ጥቂት ሀብታሞች በብዙ መንገድ ሃብት እንዲያከማቹ የተመቻቸ ነው… ግን እንደው ከሁለቱ እንዱን መምረጥ ግድ ቢሆንብኝ አኔ በበኩሌ ሃብታሙን መሪ እመርጣለሁ፡፡ሰውዬው ደግሞ ቱጃር ናቸው፡፡ ክንዴ ብርታቴ… ሃይሌ ችሎቴ… ገንዘቤ ብቃቴ…. የሚል ትእቢት ካላነቃቸው… የቅንጦት ኑሮ ብርቅ ስለማይሆንባቸው በአግባቡ ያስተዳድራሉ የሚል ግምት አለኝ፡፡ እንግዲህ የውጪ ጉዳይ ፤ የምጣኔ ሃብት እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ያለቸው አቋም እንዳለ ሆኖ… ከላይ በጠቀስኳቸው ምክንያቶች ትራምፕን መሰል እጩ ለሐገሬ ፕሬዘዳንትነት ቢወዳደሩ አንደኛ መራጭ እኔ ነኝ ብያለሁ፡፡

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   “ወያኔ እየሠራው ባለው ግፍና በደል ትግራይ ከፍላ የማትጨርሰው ዕዳ እየተቆለለባት ነው!”ሲሉ ሰምቼ…

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *