ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ቀንበር የከበዳቸው አህዮች ስብሰባ

“ቀና ብለን ስንሄድ እነሱን ስለምንመስል አቀርቅረን እንጓዝ ዘንድ ሌላ ጭነት ይጨምሩብናል፤ ለወሲብ እንኳ ጊዜ እስክናጣ! ለወሲብ”

‹‹መቼም በእኔ እድሜ ይሄን ስብሰባ መጥራት በራሱ አሳፋሪ ነገር ነው!….…ወጣት አህዮች ‹‹እንቢ›› የሚለው ቃል ከአፋቸው ሲሰለብ ምን እናድርግ! ቀንበር ከበደ! ገዢዎቻችን ጨከኑ! እላያችን ላይ ያለው ሳይወርድ ሌላ ይጭኑናል! ቀና ብለን ስንሄድ እነሱን ስለምንመስል አቀርቅረን እንጓዝ ዘንድ ሌላ ጭነት ይጨምሩብናል፤ ለወሲብ እንኳ ጊዜ እስክናጣ! ለወሲብ….››…ሃሳባቸውን ሳይጨርሱ የእንባ ሳግ አንደበታቸውን ያዘው….
.
የጋጡ ዝምታ የጨነቀው አንድ ጎልማሳ አህያ ለመናገር ተቁነጠነጠ….ይህ አህያ ዘወትር ከፊት እየቀደመ ከኋላ ያሉትን አህች በገዢዎች የሚያስገርፍ ነው፡፡ ቀደም ቀደም በማለቱ ከኋላ የቀሩት ለግመዋል በሚል ቂጣቸው እስኪላጥ ይገረፋሉ…………ሳያስፈቅድ መናገር ጀመረ….‹‹እውነት ነው በኛ ላይ የሚደርሰው በደል ከሌሎች ጥቅም አልባ እንሰሶች አንጻር ሲመዘን ይህ ስብሰባ ዘግይቷል ባይ ነኝ!…..(ብዙዎች ቂጣቸውን ዳበሱ! በንግግሩ አናታቸው ያለፍቃዱ ይወዛወዛል! ምላሱ ያሸንፋቸዋል) ድመትን ውሰዷት! ትራስ ላይ ትተኛለች ከገዢዎቻችን ገበታ ጥቂት ስንዝር ራቅ ብላ ከእጃቸው ስብ ትቀበላለች፡፡ አገልግሎቷ ግን ምንድነው?! (ምንም! ምንም! ምንም!…..አመለጣቸው…!) አይጥ እንኳ አድና ብትይዝ ልትበላው ነው፡፡…››
.
‹‹ይበቃሃል›› አንድ ወጣት አህያ በቁጣ አቋረጠው…. ‹‹እዚህ የተሰበሰብነው ላንተ ዲስኩር ልናጨበጭብ አይደለም …..ፈጣሪ ሲወለድ ትንፋሽ የገበርን ወደ ከተማ ሲገባ በጀርባችን ያዘልን አይነት ታሪክ እያወራህ ጊዜያችንን አትግደል፡፡ ይልቅ ቅድም አባታችን እንዳሉት ‹‹ወጣት አህዮች እንቢ ማለት አለባቸው!›› እኔ የመጀመርያው በመሆን ከፊት እመራለው! በኔ ላይ ስለሚሆነው ነገር አታስቡ! ዘላለም ስለሜዳ አህያ ነጻነት ታሪክ እየሰማሁ መኖር ሰልችቶኛል!..
.
አዛውንቱ…‹‹የኔ ልጅ ተው እንደሱ አይደለም ‹‹ሰከን በል››! ብቻህን እንቢ ብትል በበትራቸው አናት አናትህን ቀጥቅጠው በሽተኛ ያደርጉሃል! እርግጥ ወንድሞችህ ተሰፍሮ የተሰጣቸውን እያመነዠጉ ቀንበራቸውን ለመርሳት ከልክ በላይ እያናፉ(ሂሃሃሃሃ ሂሃሃሃሃ) ተመሳስለው ቢኖሩም ከፍታው ላይ ስላልወጡ ነውና በነሱም አይፈረድም! የታየህ አልታያቸውም! ጎበዝ ከሆናችሁ ማታ ማታ ከምናንቀላፋ እንዲህ እንመካከር፤ እንከራከር፤ እንወያይ ያኔ መብታቸው የት ድረስ እንደሆነ ይገባናል! በሰውነት እና በአህያት መሃል ግልጽ መስመር ይሰመራል! ያለኛ እንደማይነግሱ ይገለጥልናል! ይሰሙናል››
.
ጎልማሳው አህያ ሃሳብ አለኝ ሲል ሸኮናውን ሽቅብ አወጣ! ተፈቀደለት ‹‹ የሁላችሁንም ሃሳብ አደንቃለው! ስሜታችሁም ይገባኛል….…ግን የአንዳንድ ምሳሌዎች ትርጉም አወላክፈን ባንረዳ ጥሩ ነው!……ለምሳሌ የሜዳ አህያን አንደ ነጻነት ተምሳሌት ስትጠቀስ ሰምቻለው! እኔ ከሷ ነጻነት የገዢዎቼ ጭቆና ሺ ጊዜ ይበልጥብኛል! በነጻነቷ ልክ እኮ ጠላቶቿም ያን ያህል ናቸው! አንበሳው ነብሩ አቦ ሸማኔው እኮ እንደ ፓፓያ እና ጊሽጣ እኮ አይደለም የሚያያት……ቁርስ ምሳ እና እራቱን ተንከባክባ እንደምታሳድግ ባሪያው እንጂ! ባርነትም እኮ ይወዳደራል እናንተ!…..›› ብዙ ሸሆናዎች በጭብጨባ ጋጡን አናወጡት…..
.
‹‹የሜዳ አህያን ኑሮ አርነት እንጂ ባርነት አልለውም!›› አለ ወጣቱ አህያ …‹‹ ‹‹ማምሻም እድሜ ነው›› ይላሉ የሰው ልጆች ሲተርቱ! መኖርን በእድሜ እምንለካ ከሆነማ ዝንብ 8 ቀን አይደል የምትኖር! እሷ ምን ሆነች ልንል ነው!….. እኔ እንደ ኤሊ 120 እና 200 አመት በሳጥን ውስጥ ከመኖር እንደዝንም ያሻኝ ቦታ እርፌ ወደሻን በርሬ 8 የአርነት ቀናትን በደስታ ብሞት ይሻለኛል!…ምንም ቢሆን እኮ አያቶቻችን የአርበኞችን ድንኳን ተሸክመው አድዋ ድረስ ዘምተዋል! ስንት የጀግና ክላሾች አዝለን እኮ ጦር ሜዳ ተገኝተናል…››….እንደገና ሌላ ጭብጨባ .፣
ስበሰባው ቀጥሏል!

ተጻፈ በበሃይሉ ሙሉጌታ ህዳር 2009 ዓ.ም  ከስንዱ አበበ የፌስ ቡክ ገጽ ተወሰደ