“Our true nationality is mankind.”H.G.

የስስታሙ ነጋዴ ታሪክ

በአንድ ወቅት አንድ ፈጣሪ በሰጠው ፀጋ አመስግኖ የማያውቅ ስስታም ነጋዴ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን ለንግድ ሥራ ከሄደበት ገበያ ወደ ቤቱ
ሲመለስ 100 የወርቅ ሳንቲም ይጠፋበታል፡፡ ነጋዴው “100 የወርቅ ሳንቲም ያገኘ ካለ ወረታው ከፋይ ነኝ” እያለ ቢለፍፍም ሊያገኘው
አልቻለም፡፡ አንድ ቀን ተስፋ ቆርጦ እቤቱ ቁጭ ብሎ እያለ አንድ ልብሱ የቆሸሸ፤ ገፅታው የተጎሳቆለ ሰውዬ የነጋዴውን ቤት አንኳኳ፡፡

በር ተከፍቶ ወደ ሳሎን ቤቱ ሲዘልቅ እንግዳው ሰውዬ የመጣበትን ጉዳይ እንዲህ ሲል አስረዳ፡-“ጌታዬ 100 የወርቅ ሳንቲም እመንገድ ላይ አግኝቼ ነበር፡፡ ባለቤቱም እርሶ እንደሆኑ ነው የተነገረኝ፡፡ ምንም የዕለት ጉርሻ የሌለኝ ድሀ ብሆንም የሰው ንብረት አልመኝም፡፡ ስለሆነም የወርቅ ሳንቲምዎን ይዤሎት መጥቻለሁ” አለ የሚሰጠው ጉርሻ ምን ሊሆን እንደሚችል በልቡ እያሰበ፡፡


ነጋዴው ይህን ሲሰማ በአንዴ ፊቱ ተለዋወጠ፡፡ “አንተ እንዳልከው 100 የወርቅ ሳንቲም ብቻ አይደለም የጠፋብኝ፡፡ በአጠቃላይ የጠፋብኝ የወርቅ ሳንቲም መጠን 125 ነው፡፡ ስለዚህ 25 የወርቅ ሳንቲም አስቀርተኸብኛል፡፡ አሁን ሌላ ጣጣ ሳይከተልብህ 25ቱን ሳንቲም መልስልኝ” ሲል አስፈራራው፡፡ ምስኪኑ ሰውዬ ከቅንነት ተነሳስቶ ያደረገው ነገር ያላሰበው ጣጣ ስላመጣበት እጅግ ተጨነቀ፡፡ “ጌታዬ እኔ ያገኘሁት ይሄ ብቻ ነው፡፡ ምናልባት ሌላ ቦታ ወድቆ እንዳይሆን፡፡ በእግዚአብሔር እምልሎታለሁ እኔ አልወሰድኩም” በማለት ሊያስረዳው ሞከረ፡፡ ይሁን እንጂ ሀብታሙ ነጋዴ አእምሮው በጥቅም ታውሮ ምንም ዓይነት የርህራሄ ስሜት ሊያሳይ አልቻለም፡፡ በዚህም 25 የወርቅ ሳንቲም ወስዶብኛል በሚል ከሰሰው፡፡

ድሃው ሰውዬ ከዳኛ ፊት ቀርቦ እንዲህ ሲል ተከራከረ፡- “ክቡር ዳኛ ከ100 የወርቅ ሳንቲም ውጭ ሌላ ነገር አላገኘሁም፡፡ አግኝቷል
የሚል ምስክር ከተገኘ ግን የሚሰጠኝን ቅጣት በፀጋ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ” ሲል ተናገረ፡፡ በዚህ ጊዜ ጉዳዩን ይመለከቱ የነበሩት ዳኛ ጠፋ የተባለውን የወርቅ ሳንቲም መጠን ምን ያህል እንደሆነ ቀደም ብሎ መረጃ ደርሷቸው ስለነበር የሚከተለውን ውሳኔ አስተላለፉ፡-
“ጠፋ የተባለው የወርቅ ሳንቲም 100 ብቻ እንደሆነ መረጃ አለን፡፡ እርስዎየተከበሩ ከሳሽ ጠፋብኝ እያሉ ያሉት ደግሞ 125 ነው፡፡ ስለዚህ 100ው  የወርቅ ሳንቲም የእርስዎ ሊሆን አይችልም፡፡ ምናልባት 125 የወርቅ ሳንቲም የወሰደ ሰው እስኪገኝ ድረስ ይጠብቁ፡፡ አሁን የተገኘው ሳንቲም ግን ትክክለኛ ባለቤቱ እስካልተገኘ ድረስ ላገኘው ሰው እንዲሰጥ ወስነናል” የሚል ፍርድ ሰጡ፡፡

በመጨረሻም ድሃው ሰውዬ ሀብት በሀብት ሆኖ ሲመለስ ስግብግቡ ነጋዴ ደግሞ ባዶ እጁ ለመመለስ ተገደደ፡፡ አትርፍ ባይ አጉዳይ ይሉት እንዲህ ነው፡፡ የኛ ያልሆነውን ነገር መመኘት ዞሮ ዞሮ ኪሳራ እንጂ ምንም ትርፍ የለውም፡፡
ምንጭ – ከደራሲያን አለም –   
Meron Tilahun

Share and Enjoy !

Shares
Related stories   መሠረታዊ የኮምፒውተር ደህንነት መጠበቂያ መንገዶች
0Shares
0