ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የጀግናዋ – ምህላ ” ፈቀድኩለት – አልደፈረኝም”

… ይሸታል። ይቀረናል። ይገማል። ይቀፋል። ያስጠላል። ዛሬ ፍቅር ነገ ጸብ። ቀልብ የለውም። ውርጃ ነገር ነው። ግልቢያ ነው። እንደውም ግልብ ነው። ችግር ያለው ሁሉም ጋር ነው። “የዝንጀሮ ቆንጆ እንዲሉ” ትላለች ቦሰና። መዘላለፍ፣ መሰዳደብ፣ መካሰስ፣ መካካድ፣ አለመቻቻል፣ ተቀምጦ መነጋገር አለመቻል። ጣጣ ይዘው አደባባይ… የሚታገሉትን ገላጋይ አድርገው ጉዳቸውን ማፍረጥረጥ… እነሱ ሳይስማሙ ከሌላው ጋር… የእኛ አገር ፖለቲካ!! ያበደው ተወራጨና ከተቀመጠበት ተነሳ። ክፉ ስድብ ልቡናውን ሞላው። ወዲያው የጀግናዋ ምህላ ታወሰው።
ሰላም ለናንተ ይሁን!! በቅርቡ ሽንፈታቸውን ለተቀበሉት አፍሪካዊ መሪም ሰላም። ቦሰናና ደጎልም ሰላምታ አላቸው… ያበደው ስለ ጀግንነትና ጀግኖች አሰበ። ” አሁን ከዚህች ጀግና በላይ አለ?” ሲል ጠየቀ። ያልተነገረላቸው ጀግኖች መዘከር እንዳለባቸው አመነ። ራሳቸው ለሌሎች አሳልፈው የሚሰጡትን አሞካሸ። አዎ!! ጀግንነት ራስን ለህዝብ ማቅረብ ነው። በቃ ታምኖ መሞት!! ቦሰና ቆፍጠን ስትል ” ሞት አይቀር፤ የምን መርመጥ ነው” ትላለች።
ያበደው የሚያውቃት ጀግና 16 ዓመት ቢሞላት ነው። ጡቶቿ ገና አልበቀሉም። ሰውነቷ የጫጫ ነው። የፈዘዘ ውበት ይታይባታል። ያወቃት በድንገት አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ ነው። አስተናጋጅ ነች። መጠጥ ታሻሽጣለች። ራሰዋንም ተገበያለች። ከወዲያ ወዲህ ስትል ድንገት ተለካ የመጣች እንጂ የመሸታ ቤት ሰራተኛ አትመስልም።
ፋንታ ይዛ ከያበደው ጋር ተጫወቱ። ምን መሸታ ቤት እንደወረወራት ነገረችው። ያበደው ተክዞ ይቀዳት ነበር። እየተግባቡ ሲሄዱ ልጅት አንደበቷ ተዘረጋ። ማብራሪያዋ የልብ ምታት የሚጨምር ሆነ። እንዲህ ነው ታሪኩ።
ሁለት ወንድሞች አሉዋት። የ 6 እና የ 4 ዓመት ናቸው። አባቷ የሉም። አባቷና እናቷ ተለያይተው ሳለ እሷ ከአባቷ ጋር ነበረች። ሲሞቱ ሌላኛዋ የአባቷ ሚስት / ያበደው እንጀራ እናት፣ አባት ማለት አይወድም/ አሰናበተቻት። እናም ወደ ቀደመው መንደሯ ስትመለስ ሁለት ወንድሞቿና እናቷ እንዳልሆኑ ሆነው አገኘቻቸው። እንደ እሷ አባባል መኖር አቁመው ነበር። ሚቦካ፣ ሚጋገር፣ ሚወጠወጥ፣ የለም። ሌማትና ቡሃቃ ስራ አቁመዋል። በቃ እንደ ነገሩ መሽቶ ይነጋል።
ያበደው አሁን ካለበት ሆኖ እምባ አቆረዘዘ። የውስጥ ሱሪ ከገዙ 32 ዓመት የሞላቸው እናት ትዝ አሉት። ” እንዴት ሆነው ይሁን?” … ስንቱን ማሰብ ይቻላል። መለስ መናገር ይችላሉ። ” ትልቁ ጠላታችን ድህነት ነው” ያሉት እውነት ነው። አምስተኛ ጀርባ… ያበደው ተወው። ዝምታን መረጠ። ፖለቲከኞቻችን እንዲህ ያለውን ህዝብ ነው ” ወክያለሁ” የምትሉት።….
የቤቷና የቤተሰቦቿ ኑሮ ጤና የነሳት ልጅ አቋራጭ ፈለገች። ጉለበት ስለሌላት የቤት ሰራተኛ መሆን አይቻላትም። እናም በደላላ መሸታ ቤት ገባች። ” የቤተሰቤ ጀግና ሆንኩ” ስትል ስለውሳኔዋ ማሳያ ታቀርባለች ” ስለባድመ ጦርነት ሰምተሃል” ስትል ያበደውን ጠየቀችው። አዎ !! ባድመ ደም የጠገበ ምድር ነው። ” ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በፈንጂ የታጠረውን ክልል ማለፍ ግድ ነበር። እናም ሌሎች የፈንጂ ወረዳውን አልፈው ውጊያ እንዲገጥሙ፣ ሌሎች በፈንጂው ላይ መረማመድ ነበረባቸው” አለች። ያበደው ያዳምጣል።
“እናም ሌሎች እንዲያልፉ፣ ሌሎች ፋንጂ ላይ ሮጡ፤ ህይወታቸውን ለሌሎች መንገድ ጠረጉበት። እነሱ በጠረጉት መንገድ ስራ ተጀመረ። ጠላትን መግደለና ማሸነፍ የተቻለው ከዛ በሁዋላ ነው” ቀጠለች ” እነዛ መንገድ የከፈቱት ናቸው ጀግኖች” አለችና ” እኔም የቤተሰቤ ጅግና ነኝ፣ እራሴን ለነሱ አሳልፌ እሰጣለሁ” በማለት ኤድስ የሚባለውን የፈንጂ ወረዳ ልትረማመድበት እንደወሰነች ገለጠጭች። ስትጨርስ ደረቅ ፈገግታ አሳይታ ቅንድቧን ወደላይ ሰብስባ መለሰችው።
ያበደው በሰማው ተገረመ። ለመምከር አልሞከረም። ግናባሩን በመነቅነቅ አሳማኝ ማብራሪያ ስለመስማቱ ማረጋገጫ ሰጠ። የመጀመሪያ ቀን ያጋጠማትን …. ሰውየው ሾፌር ነው። ከጀቡቲ እንደጫነ ይመጣና እሷ ያለችበት መሸታ ቤት ለማደር ይወስናል። እናም አስተዳዳሪ ያስፈልገው ነበርና ጠራት። ትልቅ ሰው ቢሆንም ሲያያት ሰውነቱ ሞቀ። የምትፈልገውን ሰጠና ተያይዘው ወደ መኝታቸው ገቡ።
ልጅት ለመጀመሪያ ጊዜ ከወንድ ጋር በእንዲህ መልኩ ማደርዋ ነበርና ፈራች። ይህንኑ ስትነግረው ይበልጥ ቀነዘረበት። አንዳንዶች እንዲህ ያለውን አጋጣሚ የድል ያህል ይቆጥሩታል። ማታብ መውሰድ ከዲግሪ በላይ ክብር መስሎ ይታያቸዋል። አንዳንድ ሴቶችም ቢሆኑ ” እሰካሁን ተሸክሜው” እያሉ ሲመጻደቁና ሰው ሲመርጡበት ጊዜ ሞቶባቸው ይስልክ እንጭት ዘመን ላይ ይደርሳሉ።
እየፈራች እየተንቀጠቀጠች ከትልቁ ሰውዬ ጋር ተኙ። እብብቱ ውስጥ አስገብቶ ሲይዛት ጥላ መሰለችው። በማይታመን ሁኔታ ተሰፈንጥሮ ተነሳና አነባ። ቁጭ ብሎ ታሪኳን ይሰማ ጀመር። ነጋ። ጠዋት አንድ ኩንታል ጤፍ፣ ትልቅ ጀሪካን ዘይትና ከሰል ከመኪናው አስወርዶ በጋሪ አስጫነላት። አንድ ሺህ በር ሰጣትና ሄደ። በቀናት ልዩነት ተመልሶ መጥቶ መላ እንደሚፈለገላት ቃል እንደገባላት… ልጅት ስለሰውየው ስታወራ ቃላት ያንሱዋታል። ደግ መሆኑንን ስትናገር ….
ከሰል፣ ጤፍ፣ ዘይት፣ ሌሎች ማጣፈጫ ገዛዝታ “ስራ ” በገባች በማግስቱ ወደ ቤቷ ሄደች። የተሰቀሉ የማብሰያ ቁሳቁሶች ወረዱ። ቤቱ ተጫጫሰ። እናት ተዋከቡ። ጤፍ ተነፋ፣ ተፈጨ፣ ቦሃቃ ሊጥ ገባበት… ወንድሞቿ ቆርሰው ጎረሱ። እስኪጠግቡ በሉ። እናት አነቡ። እሷም አነባች።…. ልጅት በፈንጂ ወረዳው ላይ ትሩጥ አትሩጥ ያበደው መረጃ የለውም። በተለያዩ አገራት በስደት ለቤተሰቦቻቸው የሚቀልጡ አሉ። ለቤተሰብ ሲሉ ራሳቸውን የረሱ አሉ። ለቤተሰቦቻቸው ሲሉ እንደባከኑ የሚኖሩ አሉ። የኑሮ ግብግብ የስልክ እንጨት ዘመን ውስጥ ከቷቸው ወግ ማረጉን ሳያዩ ሌጣ ሆነው ተፈጥረው ፣ ሌጣ ሆነው የቀሩ ብዙ ናቸው። ያበደው እነዚህን ” ያልተነገረላቸው ጀግኖች” ይላቸዋል። ቴዲ አፍሮ ” ምን ይዤ ልመለስ፣ ወደ እናቴ ቤት…”
ያበደው ከሄደበት ነቃ። ያለው አንድ ማስታወቂያ ፊት ለፊት ነው። ማስታወቂያው የምርጫ ነው። “አዎ መምረጥና መመረጥ መብታችሁ ለሆነ … ” አለና ምራቁን ተፋ። ነጮቹ ይኖራሉ። እኛ በ20 ክፍለ ዘመን ገና መነጋገር አልጀመርንም። ያ – ጥቁር ሰውዬ የሚሰማው ቢያገኝ ደግ ነበር። ” መጀምሪያ እርስ በእርስ እንነጋገር” ሲል ጀምሮ ነበር። ያ-ገራችን ፖለቲካ…. !! ኢትዮጵያ ትቅደም። አቆርቋዧ ይውደም። አሁን ተሲይት ነው። የነጯ ቦሰና ጨዋታ ያስፈልጋል። ያበደው ሊከንፍ ነው። ሰዓት የለም። እዚህ መቀለድ የለም። ደጎልም ይናፍቃል። ሰላም ሁኑ፣ በየደቂቃው አዲስ ነገር አለ። አዲስ ነገር ይሁንላችሁ። ድህነትን ለማጥፋት ብንረባረብስ? ኢህአዴግም ብቻህን የድህነት አባራሪ አርበኛ እሆን ብለህ ጣጣህን ከምታይ ” እርዳታ” ጠይቅ። ብንረዳዳ ምን ይለናል? የቤተሰቦቿ ጀግና በሆነችው አንድ ፍሬ ልጅ ታሪክ ያበደው ይማጸናል። ይብቃ!! ሞትና ድህነት ላይ ወደፊት!!