“Our true nationality is mankind.”H.G.

የጦርነትና የድል ብስራት ዜናዎች – ከ “የነጻነት ታጋዮች፣ ከከፋኞች፣ ከአርበኞች ግንቦት 7” እና ከ”ኢህአዴግ… “

ከአንድ ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያ በመጠኑም፣ በአይነቱም፣ በጥንካሬውም ሆነ በአገሪቱ ሰፊ ሽፋን ያለው አመጽ ታይቷል። በኦሮሚያ ተጀመሮ አማራ ክልል የዘለቀውና አልፎ አልፎ በደቡብ ኮንሶ የተነሳው የህዝብ አመጽ ኢህአዴግ ራሱ ያመነው፣ ” ጠልቄ ታድሼ ለአመጹ መልስ እሰጣለሁ” ሲል ቃል የገባበት ነው። ከዚያም በላይ የችግሩ አሳሳቢነትና ኢህአዴግን ገፍትሮ የመጣል ሂደቱ እንደ ኩፉኝ በመራባቱ አስቸኳይ አዋጅና ኮማንድ ፖስት የተቋቋመበት እውነታ ነው ያለው።
የአስጨኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ በሁዋላ አገሪቱ ወደ ቀድሞ መረጋጋቷ መመለሷ በጠ/ሚ ሃይለማርያም፣ እንዲሁም በኮማንድ ፓስቱ በተደጋጋሚ ቢገለጽም የጦርነት ዜናዎች እያበቡ መምጣታቸው ነገሩን ” እንዴት እንዴት..” እያስባለው ነው። የዚያኑ ያህል ደግሞ በጦርነቱ ” ኮፒ ራይት ” የሚሰማው ውዝግብ ጉድ የሚያሰኝ ነው።
መረጃውን ከትክክለኛ የጉዳዩ ባለቤቶች በመጠየቅ ለመዘገብ የአካሄዱ ባህሪ የሚፈቅድ ባለመሆኑ የነጠረ መረጃ ለማቅረብ ያስቸግራል። ከሁሉም በላይ የ” ጦርነት ኮፒራይት” ንትርኩ አመል የለየለት ባለመሆኑ ይህንኑ ለማድረግም አይጋብዝም። ንትርኩ እንዳለ ሆኖ መረጃዋች የሚወጡት በውስን የመረጃ ቋት አለመሆኑ ደግሞ ሌላ ውስብስብ ጉዳይ ነው።
ያም ሆኖ ግን በነፍጥ የታገዘ ግጭት ወይም ጦርነት ስለመኖሩ አይካድም። የመንግስት ሚዲያዎች ራሳቸው ይፋ እንዳደረጉት በሁለት ዙር ከኤርትራ ምድር ተወርውሮ የመጣ ቡደን ተማርኳል። ተገሏል። ቆስሏል… የሚሉ ዜናዎች በምስል አስደግፈው አስይተዋል። ተማረኩ ተብለው የታዩት የአርበኞች ግንቦት 7 ሃይሎች መሆናቸውም አደባባይ ወጥቷል።
“ዜናውን በከፊል እውነታ ያለው ነገር ግን የተጋነነ” ሲል አርበኞች ግንቦት7 በኢሳት በኩል አጣጥሎታል። ይልቁኑም ቦታና ስም ጠቅሶ ” ወያኔ ላይ ድል አገኘሁ” ብሏል። በተለያዩ ወቅቶችም በመቶዎች የሚቆጠሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ንቀናቄውን ከነሙሉ ትጥቃቸው መቀላቀላቸውን አውጇል። በ11.12.16 ኢሳት ንቅናቄውን ጠቅሶ 46 የሚሆኑ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከነሙሉ ትጥቃቸው መንግስትን መካዳቸውን የመሳሪያና የትጥቅ ዝርዝር ይፋ አድርጓል። በተለያዩ ወቅቶች የተላለፉት ዜናዎች ግን በስልክ ድምጽ ከመደገፋቸው ውጪ የምስል ማጠናከሪያ አልቀረበባቸውም።
ራሳቸውን ” የለውጥ ሃይሎች፣ የነጻነት ሃይሎች፣ የአማራ ነጻ አውጪ፣ ከፋኝ… ” በማለት የሚጠሩት ክፍሎች ደግሞ ከመንግስት ወገን የተገደሉትን አዋጊዎች ስም ዝርዝር በመጥቀስ፣ ከራሳቸውም ወገን የወደቁባቸውን ይፋ በማድረግ፣ አንዳንዴም በቪዲዮ ታጋዮቻቸውን በማነጋገር ይፋ የሚያደርጉት መረጃዎች አሉ። እነዚህ ክፍሎች አንድ ወጥ የመረጃ ማደራጃና ማፍሰሻ ቋት ስለሌላቸው ተመሳሳይ ዜናዎች ስጋና ደም እየተጨመረባቸው የማህበራዊ መገናኛዎች ፍጆታ ሆነው ይስተዋላሉ።
በዚሁ ” የጦርነት ኮፒ ራይት” አለመግባባት መነሾና የመረጃው ፍሰት ማዕከል የጠበቀ አለመሆኑ የነጠረ መርጃ አንድ ራሱን ሃላፊና ተጠያቂ ካደረገ ክፍል ማግኘት አላስቻለም። ምንም ሆነ ምን ግን በነፍጥ የተደገፈ ግጭት ስለመኖሩ ማስተባበል የሚችል አካል ሊኖር አይችልም። የጉዞ ማስጠንቀቂያ የሰጡት የአውሮፓ አገራትና አሜሪካ በግልጽ የጠቀሱዋቸው የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል፣ በተለይም ጎንደር መሆናቸው ግጭቱ ስለመኖሩ አጉሊ ማስረጃ ነው።
ቪኦኤ ያናገራቸው የአይን ምስክር ጦርነት ስለመኖሩ አስረግጠው ነው የተናገሩት። ሌሎችም በመስክር ደረጃ ይህንኑ የጦርነት ዜና ያረጋግጣሉ። ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የአማራ ክልል ቃል አቀባይ በተመሳስይ ከቪኦኤ ጥያቄ ቀርቦላቸው የመንግስት መገናኛዎች ይፋ ያደረጉዋቸውን ጉዳዮች እንኳን ” አላውቅም” ሲሉ ነበር መልስ የሰጡት።
ቦታና ስም እየተጠቀሰ፣ የተገደሉ አዋጊዎች ስም እየተዘረዘር ለሚቀርቡ ዜናዎች ኢህአዴግም ሆነ መከላከያ ምላሽ ሲሰጡ አልተሰማም። ይልቁኑ አሁን እያሰጋ ያለውን የኢኮኖሚ ጉዳይ ለመጠገን ባለሃብቶች ወደ አገር ቤት እንዲገቡ እየወተወተ ነው። ባለ ሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ ድጎማዎችና ማባበያ ለማድረግ መወሰኑንን እየጠቆመ ነው።
“አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አገሪቱን ስላረጋግ ወደ ልማት” የሚል መርህ ሰለመያዙ በስፋት የሚናገረው መንግስት አሁን በአገሪቱ አለ የሚባለውን ውጥረት ለማስተንፈስ ከሃይል የዘለለ ሌላ አማራጭ የመያዝ እቅድ ያለው አይመስልም። የውጪ ታዋቂ ሚዲያዎችና የፖለቲካ ተንታኞች፣ እንዲኡም የአገር ውስጥ ፖለቲከኞች አገሪቱ ወደማይፈለግ የሲቪል ጦርነትና መተራመስ ውስጥ እንዳትገባ እያሳሰቡ ነው። ብሄርተኛነትና በቄዬ ማሰብ እየገነነ በመምጣቱ መንግስት የሰከነ አካሄድን ሊከተል እንደሚገባው ፣ የሚወሰዱ ርምጃዎች ይበልጥ ጥላቻና ቂምን እንዳያባብሱ ወደ ተረጴዛ ዙሪያ ውይይት መመለስ ግድ እንደሆነ የበርካቶች እምነት ነው።
ዝግጅት ክፍሊ፡- ይህንን ዜና ስንሰራ ዝርዝር ጉዳዮችን ያላነሳነው ከላይ በገለስነው ምክንያት ነው። በመሆኑም የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ አካሎች የጽሁፍም ሆነ የቃል ምላሽ ካላቸው አመጣጥነን ለመዘገብ ዝግጁ ነን፤

0Shares
0