“Our true nationality is mankind.”H.G.

“በጥልቀት…” ወይም ወደጥልቁ!!

ሜንጫ፣ ሜንጫ፣ ሜንጫ፣ ሜንጫ፣ ሜንጫ… ህብረት፣ ህብረት፣ ህብረት፣…. ውህደት፣ ውህደት፣…. መነጣጠል፣ መነጣጠል፣ መነጣጠል…. አመጽ፣ አብዮት፣ የሽምቅ ጦርነት፣ የገሃድ ጦርነት፣ የድረ ገጽ ጦርነት፣ ሃስብን በነጻነት የመግለጽ ማእቀብ… ያበደው ተምታታበት። ውጥረት፣ ግምደላ፣ የሰለለ እውነት፣ የፋፋ ቱፋ፣ ህልም፣ ቅዠት፣ ክዳት፣ክፋት……ጥላቻ፣ መለያየት፣ ከያቅጣጫው ይዘንባል። ህዝብን ያበሰብሳል። የሚያስጠልል የለም። ከውስጥም ከውጭም ያፈሳል፣ ፈሳሹ አሁን አሁን ዶፍ እየሆነ ነው። ሟርት አይደለም። ሟርት ብሎ ነገር የለም። በሁሉም አቅጣጫ ሳስቷል። ሰከን፣ ሰከን፣ ሰከን፣ ሰከን….. ያበደው ዘፈን ባይወድም ዘፈነ!!
ሰላም ለናንተ ይሁን። ለተሰፋዬ ዲንቃ ነብስ ይማር። ቦሰና ለቤትሰቦችዎ መጽናናትን ልካለች። 10 ቢሊዮን ብር ” ባስቸኳይ ለታዘዘላችሁ ስራ ፈጣሪዎች” መልካም እድል። አትፍሩ ሶስት ሶስት ሆናችሁ ተደራጁና ይቅርታ “ተጠርነፉና” ተበደሩ። አምስት ዓመት ረዥም ነው። አምስት ዓመት ብሉ… ካላተረፋችሁም አትጨነቁ… ግን ተበደሩ፣ ሞክሩ፣… ከሚቀጥለው ምርጫ በሁዋላ ደግሞ ሌላ ፓኬጅ ይመጣል። ብድር ስረዛ!! አለያ አመጽ ይቀጥላል። ኢህአዴግም እንደገና ከ”ጥልቅ ተሃደሶ” ወደ ጥልቁ ይገባ ይሆናል። ባይገባም ስሙን ቀይሮ “ልታደስ” ማለቱ አይቀርም። የዛኔ የብደር በጀቱ ይጨምራል። እዳ ስረዛ … ያበደው ፈገግ አለ። መታደስ፣ በጥልቅ መታደስ… ከዚህ ሁሉ ከገቡበት ጥልቅ ህዝብ ጎትቶ እንዲያወጣቸው … አሁንም ያበደው ፈገገ!!
” ህዝብ ጭራ ነው” የሚሉ ታወሱት። አዎ ቀና መሪዎች፣ ህዝብ የሰየማቸው መሪዎች፣ ሲፈልግ የሚያወርዳቸው ሲሆን፣ አዎ!! ህዝብ ጭራ ነው። ይመራል። እንደውም ይነዳል። ህዝብ መርጦ ያላቆማቸው መሪዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ገዢዎች… ሲሆኑ፣ ህዝብ ወዶና ፈቀዶ ጭራ አይሆንም። በግድ ግን ጭራቸው ይሆናል። ከጭራም ዝቅ ብሎ እትቢያ ላይ ይንከባለላል። በየጊዜው ደሙን እየገበረ ይኖራል። ይህ የኢትዮጵያ አዙሪት ነው። ” የለምንም ደም ብለው” ጀምረው፣ በደም ተጨማለቀው ኖሩና…. ከዛም ” የሰፊው ህዝብ ብሶት የወለደው” መጣ… ብሶት እነሱን ብቻ ወልዳ የመከነች አድርገው የሚቆጥሩ፣ ወይም ሌሎች ብሶት የማይሰማቸው፣ ወይም ብሶት የሚባል ነገር በነሱ ያበቃ፣ ወይም የብሶት ትርጉሙ የጠፋባቸው ሆኑና ስራቸው ለማመን አዳገተ።
ያበደው አንድ ጥግ ቁጭ አለ። የከብቶች በረት እያየ ሃሳብ ጠለፈው። የእንሦች እርሻ … ሁሉም እንሰሳቶች እኩል ናቸው…. ያበደው ሳቀ። ሳቁ የደስታ አልነበረም። ቦሰና ስለዚህ ጉዳይ በማይም አንደበቷ ጥያቄም መከራከሪያም አላት። ” ህወሃት” ትላለች። እንደውም “ወያኔዎቹ” ነው የምትላቸው። እዚህ ላይ ያበደው ጥያቄ አለው። ” ወያኔ” ሲባል የሚናደዱ አሉ። ስማቸው እንደሆነ አሁን ድረስ ግልጥ ነው። እነሱ ያልቀየሩትን ስም ማን ይቀይርላቸው? ስማቸው የነጻ አውጪ ነው። ድሮም፣ ዛሬም… እናም ወዳጆቻቸው ወያኔ ሲባሉ ለምን ያማቸዋል። ግልጽ አይደለም። ያበደው በዚህ ጉዳይ ከቱባዎቹም ጋር አውርቶ ነበር። ምላሽ የለም። እናም ሲቀይሩት ፣ በቀየሩት ስም ልንጠራቸው ቀጠሮ እንይዛለን!!
ቦሰና ”ጥፋቱ የወያኔዎች ነው” እንደሆነ ሁሌም ትናገራላች። ሁሉም ክልል በፈለገውና በወደደው ድርጅት ሊመራ ይገባል። “መመራት ምርጫ ነው” ትላለች። ቦሰና የሚጠቀሱ አባብሎች አሉዋት። ያበደው አንጎልዋን ይወደዋል። ተደላድለው ማውራት ሲጀምሩ ብዙም ሳይቆዩ አጀንዳ ይቀየራል። መረፌና ክር ነው የሚሆኑት። ሰዓት አይመርጡም። ሲነሳባት እንደ ፉከራ ነገርም ይቃጣታል። ተደስታ ታስደስታለች። ሃፍረት አታውቅም። ነጻ ናት። ወሲብን ራስዋ የፈጠረችው ነው የሚመስለው። ጠረኗ ሁሉ ይቀየራል። መዓዛዋ … ሰለሜ ሰለሜ…
ኢህአዴግ ህዝብ በተቆጣ ቁጥር ” ተሃድሶ”!! ለኢትዮጵያ በልኳ የተሰፋላት ብቸኛ ድርጅት፣ “የዘላለም ገዢ” ተብሎ ቅባት ከላይ የተደፋበት ይመስል … አቶ በረከት እንዲህ በለወ ነበር ከወራት በፊት ” የኢህአዴግ የመጨረሻ ደስታ መጥፋት ነው”!!!! ” መጥፋት?” ምን ማለት ይሆን? መጥፋት…. ወዴት? እንዴት? በምን መልኩ? እንደነማ? ያበደው ራሱን አመመው። አጋዥ ፈለገ። ወዴት ነው የሚጠፋው? ወይስ ፋና ስብሰባውን ሲቆራርጠው እንደ መረራ ንግግር የሳቸውንም ቆምጦት ይሆን?
ህም!! መጥፋት፣ መሄድ፣…. ምላሽ ያስፈልገዋል። ንግግራቸውን በሜንጫ ጀምረው ነጻ ሊያወጡ የሚነሱ ተባዮች አሉ። አንገታችንን እንደሚሉን ሚዲያ ከፍተው ባደባባይ ያሽካካሉ። መልሰው የሌሎች ትግል ደረጃ መዳቢ ሆነው ይታያሉ። ችግሩ የሁሉም ነው። ዳያስፖራ ለማንገስ አንደኛ ነው። ለመኮነንም ፈጣን ነው። ዳያስፖራ የጅግና ረሃብተኛ፣ የመረጃ ረሃብተኛ!! አገር ወዳድ ህዝቦች። ዳያስፖራ … አሁን ጊዜ የለም። ደጎልን ማናፈስ ግድ ነው። ደጎል በዙ መርጃ አለው። አይቸኩልም። አይንጣጣም። ለሁሉም ጊዜ አለው። ጊዜ ውል አለው።አንዱ አባታችን ስራውን ሲጀምር በጊዜ ነው። አንደኛ ቀን፣ ሁለተኛ ቀን…. ስድስተኛ ቀን… ከዛም በመጨረሻው ቀን አረፈ!! አዎ እሱ የጊዜ አምላክ ነው። ” ነገሮችን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሰራው” አሜን!!
እስኪ እንረፍ። እስኪ ሰከን እንበል። የ ” ጦርነት ኮፒራይት” ውዝግብ ይቁም። እስኪ ተነጋገሩ። እስኪ ተወያዩ። ማንም ማንንም ሊያፍነው አይችልም። ዛሬ ብዙ መተንፈሻ በሮች አሉ። ጉዳያችሁን በግል ጨርሱ። በየአደባባዩ መዛለፍ ምን ይጠቀማል? ያለ ነቀፌታ ትግል የለም ያለው ማን ነው? ይቀፋል።ያሳዝናል። አገርቤት የርስ በርስ ጸብ፣ በውጪ ጸብ፣ ለሰሚው ግራ ነው። ምንድን ነው የሚያሻኩታችሁ? የአገራችን ፖለቲካ በምቧደን፣ እርስ ብርስ በማባላት ማጥ ውስጥ እስከመቼ? ለዩነት ያለ ነው። መነጋገር፣ መስማማት ካልተቻለ መቷቷውና የራስን ስራ መስራት። ህዝብ ማዥጎርጎር ምን ይጠቀማል? ኧረ ሁሉ በርጋታ ይሁን!! ያበደው የሰንበት ምክሩን ወረወረ። ቦሰና ቡናዋን ዝርግታለች። አሁን ቡና ነው። ደጎል ቡና ሲዘረጋ አይመቸውም። ትኩርት ያጣል። ቡና፣ ከቡና በሁዋላ ጨዋታ፣ ጨዋታ፣ ጨዋታ….. አንድ መሆን!! መዋሃድ፣ በቃ መሞቅ!! ቦሰና!! ሰላም እንሰንበት!!

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0