ጠበቆች ዶ/ር መረራን ማግኘት አልቻልንም አሉ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የወጣውን መመሪያ ጥሰዋል በሚል የታሰሩት ዶ/ር መረራ ጉዲናን ለማነጋገር ያደረጉት ተደጋጋሚ ሙከራ አለመሳካቱን ጠበቆቻቸው አስታወቁ፡፡ የጤንነታቸው ሁኔታም አሳሳቢ ነው ብለዋል፡፡ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስም (ኦፌኮ) አመራሮች ዶ/ር መረራን ለመጎብኘት እንዳልተፈቀደላቸው ተናግረዋል፡፡
አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:00


ጤንነታቸው እንደተቃወሰ ተገልጿል
ባለፈው ዓርብ ኅዳር 30 ተከብሮ የዋለውን ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ቀን አስመልከቶ ተቀማጭነታቸውን በኢትዮጵያ ያደረጉ የዘጠኝ ሃገራት አምባሳደሮች እና ምክትል አምባሳደሮች የጋራ መልዕክት ለንባብ አብቅተው ነበር፡፡ የአሜሪካ፣ እንግሊዝ እና የጀርመን ዲፕሎማቶች የተካተቱበት መልዕክት ከዳሰሳቸው ጉዳዮች ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አንዱ ነው፡፡
እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ሁላችንም ለሰብዓዊ መብቶች ዘብ የመቆም ግዴታ አለብን ያሉት ዲፕሎማቶች ይህንን ሲሉም ይበልጥ ትኩረት የሚያሻቸው ያሏቸውን ጉዳዮች በመዘርዝር ነው፡፡ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን በቀዳሚነት አስቀምጠዋል። ሃገራቱ በተናጠል በየጊዜው በሚያወጧቸው መግለጫዎች ሀሳባቸውን በነጻነት በመግለጻቸው እና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን በመጠቀማቸው ለእስር የሚዳረጉ ሰዎች ሁኔታ በጥልቅ እንደሚያሳስባቸው ሲገልጹም ቆይተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልከቶ በአውሮጳ ኅብረት የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ኮሚቴ በጠራው ውይይት ላይ ሀሳባቸውን አካፍለው ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ የታሰሩት የዶ/ር መረራ ጉዳይም የዲፕሎማቶቹ የሰሞኑ መነጋገሪያ መሆኑ እየታየ ነዉ፡፡ ዶ/ር መረራ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የወጣውን መመሪያ ጥሰዋል በሚል ከታሰሩ 12 ቀናቶች ቢያልፋቸውም እስካሁንም ድረስ ጠበቆቻቸው ሊያገኟቸው እንዳልቻሉ ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር መረራ ታስረው ወደሚገኙበት እና በተለምዶ ማዕከላዊ ተብሎ ወደሚጠራው በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል ከአንድም ሦስት ጊዜ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መመላለሳቸውን ከጠበቆቻቸው አንዱ ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም ይናገራሉ፡፡
“ጠበቆቹ ሁለት ነን፡፡ እኔ እና አቶ ወንደሙ የሚባል ሰው ነን፡፡ ከዚህ በፊት ሁለቴ ሄደን ልናነጋግር ሞክረን ነበር፡፡ አልተቻለም፡፡ ጠበቆች ማዕከላዊ ሄደው ደንበኞቻቸውን ሊያነጋግሩ የሚችሉት ረቡዕ እና ዓርብ ከሰዓት በኋላ ብቻ ነው፡፡ ያለፈውም ዓርብም እኮ ሄደን ሞክረናል፡፡ እንደዚሁ ተመልሰናል፡፡ በድጋሚ ‘ምርመራ ላይ ናቸው፤ አሁን ሊቀርቡ አይችሉም’ ብለው መለሱን፡፡ አሁንም ደግሞ እንደገና ረቡዕ ዕለትም እንሄዳለን፡፡ እንግዲህ እስከተፈቀደ ድረስ፣ ፍርድ ቤት እስከሚቀርብ ድረስ እንሄዳለን፡፡ ፍርድ ቤት ሲቀርብ መቼም መቅረብ እንችላለን፡፡ እስከዚያ ድረስ ብናገኘው ብዙ ነገር መነጋገር ያስፈልግ ነበር፡፡ ይሄ ደግሞ በሕጉም፣ በሕገ-መንግሥቱም፣ በዓለም አቀፋዊ ሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችም በሙሉ የተከበረ መብት ነው” ይላሉ ዶ/ር ያዕቆብ፡፡
የዛሬ 68 ዓመት ግድም የጸደቀውን የዓለም አቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌን አብዛኛውን አንቀጾች ያካተተው የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት በቁጥጥር ስር ያሉ ሰዎችን መብት ደንግጓል፡፡ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 21 በጥበቃ ስር ያሉ ሰዎች “ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኟቸውም ዕድል የማግኘት መብት አላቸው” ይላል፡፡
Gambia Street in Addis Abeba, Äthiopien (picture alliance/dpa)
ዶ/ር ያዕቆብ ይህ ድንጋጌ አለመከበሩን ይናገራሉ፡፡ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ሙላቱ ገመቹም በዚህ ይስማማሉ፡፡ በፓርቲ ደረጃ ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱንም ይገልጻሉ፡፡
“እስካሁን ድረስ ማንም ሊጎበኛቸው አልቻለም፡፡ ቤተሰቦች በየጊዜው ቀለብ ከማቀበል በስተቀር ምንም በአካል ያገኙት ነገር የለም፡፡ ሊያገኙትም አልቻሉም፡፡ ሕጋዊ የሆነ ጠበቃ አንግዲህ ባለጉዳይን ማነጋገር ይችላል፡፡ በእኛ ጋር አንግዲህ እንዲህ ዓይነቱ አሁን በዶ/ር መረራ አካባቢ አልተቻለም፡፡ ፓርቲው እኮ በግሉ የሚያደርጋቸው ነገሮች የት አሉ? መቼ ተቀባይነትስ አለው? እኛ በየጊዜው በቤተሰብ በኩል ነው የምንሞክረው፡፡ ፓርቲው ሄዶ ለማየት ሙከራ አድርጎ ነበር፡፡ የማረሚያ ቤቶች በራሳቸው ያላቸው [አሰራር] ጉብኝትም ቢሆን ከቤተሰብ ውጭ ሌላ ሰው ሊጎበኝ እንደማይችል ነው” ሲሉ የገጠማቸውን ችግር ያስረዳሉ፡፡
ዶ/ር መረራ ሲታሰሩ የሚያሳድጓቸው ሁለት የዘመድ ልጆች አብረዋቸው ወደ እስር ቤት መወሰዳቸው የሚታወስ ሲሆን ከቀናት በኋላ መፈታታቸው ተዘግቧል፡፡ ሦስቱም ወደ ማዕከላዊ ቢወሰዱም በተለያየ ክፍሎች አንዲታሰሩ በመደረጉ የዶ/ር መረራን የደህንነት ሁኔታ በአካል ለማረጋገጥ እንዳልተቻለ ዶ/ር ያዕቆብም ሆነ አቶ ገመቹ ያስረዳሉ፡፡ ምግብ ከሚወስዱላቸው የዘመድ ልጆች ግን የዶ/ር መረራ የጤንነት ሁኔታ እንደተቃወሰ መረዳታቸውን ዶ/ር ያዕቆብ ይገልጻሉ፡፡
“በጤናው በኩል ዶ/ር መረራ ትንሽ ችግር እንደገጠመው አንዳንድ ጊዜም ሳይበላ ምግብ እንደሚመለስ ነግረውናል፡፡ እንግዲህ እኔ ዶ/ር መረራን በደንብ አውቀዋለሁ እና ስለ ጤናው ሁኔታም አውቅ ነበር፡፡ ብዙም ሰው እንደሚያውቀው የስኳር ችግር አለው፡፡ አሁን ደግሞ ቅርብ ጊዜ ‘ቶንስላይትስ’ በአማርኛ እንጥል ነው መሰለኝ የሚባለው የእርሱም ችግር እንደተፈጠረበት ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በፊትም የሚታወቅ አንዳንድ የጤና ችግሮች እንደነበሩ እኔ በግሌም የማውቀው ነገር አለ፡፡ አንግዲህ በአሁን ሁኔታ ህክምና ማግኘቱን እጠራጠራለሁ፡፡ እርግጥ ህክምና ማግኘት አለበት፡፡ በሕጉም የተደነገገ ነገር ነው፡፡ ግን ያግኝ አያግኝ በአሁኑ ጊዜ የማውቀው ነገር የለም” ሲሉ ዶ/ር መረራ የጤንነት ሁኔታ የሚያውቁትን ተናግረዋል፡፡
የዶ/ር መረራ ጠበቆች ታህሳስ 20 ከሚውለው መጪ የፍርድ ቤት ቀጠሯቸው በፊት ደንበኛቸውን ለማግኘት ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ለዶይቸ ቬለ ገልጸዋል፡፡ ዶ/ር መረራ ከታሰሩ በኋላ ያለጠበቆቻቸው ፍርድ ቤት ቀርበው የ28 ቀን የፍርድ ቤት ቀነ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡

Related stories   "ኢትዮጵያን የውስጥና የውጭ ጠላቶች ግንባር ፈጥረው ሊያጠፏት የተነሱበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤ ሁሉም አንድ መሆን ይገባዋል – የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም

ተስፋለም ወልደየስ ሸዋዬ ለገሰ ጀርመን ሬዲዮ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *