ከተፈቀደው የክብደት መጠን በላይ ጭናቹዋል በሚል 43 ሺህ ኩንታል ስኳር የጫኑ ተሽከርካሪዎች አዋሽ አርባ ቆመዋል

አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ የክልል ከተማ ነዋሪዎች የስኳር አጣን ጥያቄ እያቀረቡ ባለበት በዚህ ስአት ከውጭ ሀገር የተገዛ 43 ሺህ ኩንታል ስኳር የጫኑ ተሽከርካሪዎች ካሳለፍነው አርብ ጀምሮ አዋሽ አርባ ፍተሻ ጣቢያ ላይ ቆመው ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ተሽከርካሪዎቹ አዋሽ አርባን እንዳያልፉ የተደረጉት መጫን ከተፈቀደላቸው ክብደት በላይ ስለጫኑ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ደግሞ፥ አዋሽ አርባ ላይ በተሽካርካሪዎች ተጭኖ ያለው ስኳር በምርቱ አቅርቦት ላይ ችግር አልፈጠረም ሲል ይደመጣል።

የደረቅ ትራንስፖርት ማህበራት በበኩላቸው፥ 101 ተሽከርካሪዎች ካለፈው አርብ ጀምሮ ስኳር እንደ ጫኑ አዋሽ ፍተሻ ጣቢያ ላይ ቆመዋል። ተሸክርካሪዎቹ ጭነው የቆሙት ስኳር የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በ2008 በጀት ዓመት ከውጭ ገበያ የገዛው የ3 ሚሊየን ኩንታል አካል ነው። በኮርፖሬሽኑ የኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው አይችሉም፥ ከተገዛው 3 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ውስጥ በመጀመሪያው ዙር 1 ነጥብ 4 ሚሊየን ስኳር ወደ ሀገር ውስጥ ገብቶ ለሸማቹ ተከፋፍሏል ብለዋል።

ቀሪውን የማስገባቱ ስራም ተጀምሯል ያሉት አቶ ጋሻው፥ ከቀሪው 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ስኳር ውስጥ 50 ሺህ ኩንታሉን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ማጓጓዝ ተጀምሯል ሲሉም ተናግረዋል። ዘጠኝ የደረቅ ትራንስፖርት ማህበራት ተሽከርካሪዎችም ምርቱን በማመላለስ ላይ የነበሩ ሲሆን፥ በአሁኑ ጊዜ 101 ተሽከርካሪዎች አዋሽ አርባን እንዳያለፉ መከልከላቸው ነው የተነገረው። በተናጥል ከ430 እስከ 450 ኩንታል በድምሩ ከ43 ሺህ እስከ 45 ሺህ ኩንታል የጫኑትን ተሽከርካሪዎች ባሉበት እንዲቆሙ ያዘዘው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሰልጣን ነው።

Related stories   የደህንነትና ፀጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አገር ለማተራመስ በህቡዕ የተደራጁ በርካታ ግለሰቦችን ከነመዋቅራቸውና መስሪያዎቻቸው በቁጥጥር ስር አዋለ፤

ተሽክርካሪዎቹ ለምን አዋሽ አርባ ላይ እንዲቆሙ ተደረገ ለሚለው ጥያቄ በኮርፖሬሽኑ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ሳምሶን ወንደሙ፥ ተሸከርካሪዎቹ ህግን ስለተላላፉ እና ትርፍ የመጣውን ጭነት ማራገፍ ስላለባቸው ነው እንዲቆሙ የተደረገው የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። የመንገድ ደህንነትን ለመጠበቅ የወጣው ህግ ተሽከርካሪዎች ከተቀመጠላቸው የመጫን መጠን በላይ መጫን እንደሌለባቸው ይደንግገጋል።

ጥያቄው ማህበራቱ ለምን ከተፈቀደላቸው መጠን ወይም ፖርታታ በላይ ጫኑ የሚል ነው። የብራይ ደረቅ ጭነት ማህበር ኦፕሬኝን ዘርፍ ስራ አስፈፃሚ አቶ አበጀ በዛብህ እና የአንድነት ደረቅ ጭነት የማህበር የቦርድ ተወካይ፥ የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ሊብሬ ላይ የሰፈረው የመጫን አቅም ከ397 እስከ 400 ኩንታል ብቻ መጫንን ይፈቅዳል ይላሉ።

Related stories   ሱዳን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደምታነሳ አስጠነቀቀች፤ "ብሄራዊ የጀግንነት ጥሪ ያፈልጋል"

ህጉም ይህ የመጫን ልክ እንዲተገበር ያስገድዳል ያሉት የማህበራቱ ሀላፊዎች፥ ያም ሆኖ ባለፈው አመት ከተፈቀደው የጭነት መጠን በላይ መጫን በመንገዶች ባለስልጣን ተፈቅዶ ነበር እኛም እሱን ተከትለን ጫንን የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል። የባለስልጣኑ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሃላፊ አቶ ሳምሶን በበኩላቸው፥ በእርግጥ ተፈቅዶ ነበር፤ ወቅታዊ እና ተፈጥሯዊ ችግርን ተከትሎ የተሰጠው ፈቃድ ግን ተነስቷል ሲሉም ያብራራሉ።

ይህንንም ለማህበራቱ በአካል እና በመገናኛ ብዙሃን በተላለፉ መልእክቶች አሳውቀናል ያሉት አቶ ሳምሶን፥ ተሽከርካሪዎቹ ህግን ስለተላለፉ ሊቀጡም ይገባል ብለዋል።  የብራይ ደረቅ ጭነት ማህበር ኦፕሬኝን ዘርፍ ስራ አስፈፃሚው አቶ አበጀ በዛብህ፥ ከተፈቀደው በላይ ስኳር ለመጫኑ ስኳሩን ያስጫነው አካል ተጠያቂ ነው የሚል ሃሳብንም አንስተዋል።

በስኳር ኮርፖሬሽን የኮሚዩኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ጋሻው አይችሉም ለዚህ በሰጡት ምላሽ፥ “ኮርፖሬሽኑ ስኳር አምጡኝ የሚል ውል ገባሁ እንጂ፤ በአንድ ተሸከርካሪ ይህን ያህል ኩንታል ጫኑ የሚል ትእዛዝ አልሰጠውም” ይላል። ስለዚህ ስኳር ጭነው አዋሽ አርባ ላይ የቆሙት ተሽከርካሪዎች እጣ ፈንታ በኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን እና የተሽከርካሪዎቹ ባለቤት በሆኑት ማህበራት እጅ ነው።

Related stories   የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲሰየሙ ወሰነ

ማህበራቱ የገንዘብ ቅጣት ይበቃል፤ ትርፍ የጫናችሁትን አራግፉ የሚለው ተጨማሪ ቅጣት አግባብ አይደለም የሚል ሀሳብም አቅርበዋል። ኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ደግሞ የህጉ አላማ መንገዱን ከጉዳት መታደግ እንጂ በቅጣት ገንዘብ መሰብሰብ አይደለም የሚል አቋም ይዟል። ማህበራቱ የጫኑት ስኳር የመንግስት ነው፤ ትርፉን በማራገፉ ሂደት ሊፈጠር የሚችል ብልሽት እና ብክነት ኪሳራው በማን ይሆናል ሲሉም ይደመጣሉ። የስኳሩ ባለቤት ስካር ኮርፖሬሽን፥ በዚህ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አልገባም፤ ጉዳዩ በህጉ መሰረት እልባት ያገኝ የሚል ምላሽን ሰጥቷል።

በዚህ መሀል 43 ሺህ ኩንታል ስኳር አዋሽ አርባ ላይ ከቆመ አምስት ቀናትን አስቆጥሯል፤ ህብረተሰቡ ደግሞ ስኳር አጣሁ የሚል ድምፅን ያሰማል። ስኳር ኮርፖሬሽን፥ በ101 ተሽከርካሪዎች ላይ ያለው ስኳር አዋሽ አርባ ላይ መቆም የስኳር እጥረትን አያስከትልም ብሏል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ደግሞ የተሸከርካሪዎቹ እጣ ፈንታ በባለቤቶቹ እጅ ላይ ነው የሚል ቁርጥ ውሳኔን አሳልፏል።

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 4፣ 2009 (ኤፍ.ቢ.ሲ)  በዳዊት መስፍን

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *