ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ውሃ ውስጥ ብዙ ከመቆየቱ የተነሳ በቀላሉ ሊለይ ያልቻለ የ’ ኢትዮጵያዊያን’ አስከሬን ተገኝ – ጫካ ውስጥ ደክመው የተሸሸጉ ታስረዋል፤ ሃሳባቸው ወደ ደቡብ አፍሪካ ነበር

በታንዛንያ ዳሬ ሰላም ከተማ አቅራቢያ የኢትዮጵያውን እንደሆነ የተጠረጠረ ሰባት አስክሬን ከወንዝ ተጥሎ ተገኝቷል፡፡ የሀገሬው ፖሊሶች በአስክሬኖቹ ላይ ምርመራ እያደረጉ ሲሆን በአቅራቢያው ባለ ጫካ 81 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መያዛቸው ሟቾቹ ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ አይቀርም የሚለውን ጥርጣሬ አጠናክሮታል፡፡
81 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በአቅራቢያው ካለ ጫካ ተይዘዋል
አስክሬኖቹ የተገኙት ከዳሬ ሰላም በስተሰሜን በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ባጋሞዮ አውራጃ ውስጥ ነው፡፡ ስድስቱ አስክሬኖች አውራጃውን አቋርጦ በሚያልፈው ሪቩ ወንዝ ላይ ተንሳፍፈው የተገኙት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ኅዳር 28 ነበር፡፡ ከአንድ ቀን በኋላ ቀሪው አስከሬን እንደ ሌሎቹ ሁሉ በላስቲክ ተጠቅልሎ እና ድንጋይ ታስሮበት ተጥሎ ተገኝቷል፡፡addis-ababa-imirrationአስክሬኖቹ እንደተገኙ የታንዛንያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሚዊጉሉ ንቼምባ በአንድ ቴሌቭዥን ጣቢያ ቀርበው ሰጡት በተባለ አስተያየት ሟቾቹ ሕገወጥ ስደተኞች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ እና የኩሽ ዝርያ እንደሆኑ መለየቱን ተናግረዋል፡፡ ቀሪው አስክሬን በተገኘበት ዕለት የአካባቢው ፖሊስ በአቅራቢያው ባለ ጫካ በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን መያዙ “ሟቾቹ ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ አይቀርም” የሚለውን ጥርጣሬ አጉልቶታል፡፡

Related stories   ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

አስክሬኖቹ የተገኙበት ክልል የፖሊስ ኃላፊ ቦናቫንቹር ሞሹንጊ 81 ኢትዮጵያውያን ከአቅራቢያው ጫካ መያዛቸውን ለዶይቸ ቨለ አረጋግጠዋል፡፡ ሆኖም ሟቾቹ “ኢትዮጵያውያን ይሁኑ አይሆኑ አልታወቀም” ብለዋል፡፡
“ከኢትዮጵያ ናቸው ለማለት አንችልም፡፡ ከየት እንደመጡ እና ዘራቸው ምን አንደሆነ ለማወቅ ምርምራ ገና እያካሄድን ነው፡፡ አስክሬኖቹ በመበስበሳቸው ማንነታቸውን ለማወቅ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ አሁንም የአስክሬን ምርመራ ውጤቱን እየጠበቅን ነው፡፡ አስክሬኖቹን ካገኘን በኋላ በመጥፎ ሁኔታ ላይ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን አግኝተናል፡፡ አማርኛ እንጂ እንግሊዘኛ የማይናገሩ በመሆናቸው እነርሱን ለማነጋገር ችግር ገጥሞናል፡፡ ሆኖም ወደ ደቡብ አፍሪካ እየሄዱ እንደነበር ነግረውናል” ይላሉ የፖሊስ ኃላፊው፡፡
በህይወት የተገኙት ኢትዮጵያውያን ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 35 ባለው መካከል እንደሚሆን እና ሁሉም ወንዶች መሆናቸውን የፖሊስ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ባጋሞዮ በሚገኝ የማቆያ እስር ቤት እንደሚገኙ፣ ፍርድ ቤት ቀርበው የጊዜ ቀጠሮ እንደተጠየቀባቸው ገልጸዋል፡፡ በሳምንት ወይም በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተመልሰው ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ነገር ግን በቋንቋ የመግባባት ችግር ስላጋጠማቸው አስተርጓሚ እያፈላለጉ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
የፖሊስ ኃላፊው “አስክሬኖቹ የኢትዮጵያውያን መሆናቸው አልተረጋገጠም” ይበሉ እንጂ ጉዳዩን “ዘ ሲትዝን” በተሰኘው የሀገሪቱ ጋዜጣ ለንባብ ያበቃው ጋዜጠኛ አቱማን ሙቱሊያ አስከሬኖቹ ኢትዮጵያዊያን የመሆን ዕድል እንዳላቸው ከእርሳቸው አፍ ሰምቼያለሁ ይላል፡፡
“የፖሊስ ኃላፊው ጋር ደውዬ [የሀገር ውስጥ ጉዳዮች] ሚኒስትሩ ስለተናገሩት በተለይ ስጠይቃቸው ከምንመለከታቸው ነገሮች አንዱ ነው ብለውኛል፡፡ ምክንያቱም አስክሬኖቹ በተገኙበት ወቅት የእዚያ ዘር ምልክቶች አግኝተዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን ናቸው ብለን መደምደም ባንችልም ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል አለ ብለውኛል” ሲል ለዶይቸ ቨለ ተናግሯል፡፡
ጋዜጠኛው በርካታ አስክሬን በአንድ ቦታ ተጥሎ መገኘቱ ጉዳዩን አነጋጋሪ አንዳደረገው እና የሀገሪቱን ፖለቲከኞች ትኩረት እንደሳበ ይናገራል፡፡ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ካሲም ማጃሊዋ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ምርመራ እንዲደረግ አዝዘዋል ሲል ጉዳዩ ያገኘውን ትኩረት ያስረዳል፡፡
ኢትዮጵያ በታንዛንያ ኤምባሲ የሌላት ሲሆን በዚያ ያሉ ጉዳዮችን የሚከታተለው ተቀማጭነቱን ናይሮቢ ኬንያ ያደረገው ኤምባሲ ነው፡፡ የኢትዮጵያውያኑን ሁኔታ አስመልክቶ ጥያቄ ያቀረብንላቸው በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ጉዳዩን ለማጣራት እየሞከሩ እንደሆነ ከመናገር ውጭ ተጨማሪ መረጃ አልሰጡም።

Related stories   አውሮፓ ህብረት - ላለፉት 28 ዓመታት በኢትዮያ ተላላኪ መንግስት እንደነበር ለኢትዮጵያ ህዝብ አመነ

ተስፋለም ወልደየስ እና ሸዋዬ ለገሰ- ጀርመን ድምጽ

ምስል 1- የባህር ላይ ሰቆቃ የሚያሳይ- 2- የፓስፖርት ወረፋ  ከፋይል