ስልጠና ወሰዱ የተባሉ 9.800 ይፈታሉ

ኮማንድ ፓስት የሚባለው ጊዚያዊ የኢትዮጵያ አስተዳደር በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት መስፈኑን ሲገልጽ ቢቆይም የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደማይነሳ በተዘዋዋሪ አመለከተ። ” የአዋጁ መነሳት አለመነሳት የሚወሰነው በመጣው ለውጥ ብቻ ሳይሆን በሚያመጣው አስተማማኝ የሰላምና መረጋጋት ውጤት ነው” ማለቱን የዘገቡት የመንግስት መገናኛዎች ናቸው።
የኮማንድ ፖስቱን ሴክሬታር በመጥቀስ መገናኛዎቹ እንደዘገቡት አሁንም ሰዎች ” ተጠርጣሪ” እየተባሉ ይታሰራሉ። ይህንኑ እስር የታሳሪ ቤተሰቦች፣ የተጻራሪ ፖለቲካ ድርጅቶችና የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች አየኮነኑት ናቸው። እንደ ዜናው መሰረት የሞባይል ኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የመቆጣጠሪያ ስልት ተዘርግቷል። አምነሰቲ እንዲህ አይነቱ ተግባር አፈናና የሰው ለጆችን መብት የሚጥስ እንደሆነ በመጠቀስ የተቃውሞ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል
አምነስቲ በኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት ወዲህ የተቀሰቀሰዉን ሕዝባዊ ተቃሞና ከዚያም በታወጀዉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት መንግሥት የማኅበራዊ መገናኛ አዉታሮች በማፈን ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈረመችዉን የፖለቲካና ሲቪል መብቶች ስምምነት አንቀጽ 19 ላይ የተጠቀሰዉን ሃሳብን በነጻ የመግለፅና መረጃን የመፈለግና የማሰራጨት መብት አፍናለች ሲል ወቀሷል።
ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ መንግሥት በተቀነባበረና ሕገ-ወጥ በሆነ መንገድ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን፣ የዜና ማሰራጫና ድረ-ገፆችን በመዝጋት የመንግሥት ወታደሮች ለተቃውሞ በወጡ ሰዎች ላይ የሚፈጽሙትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ይፋ እንዳይወጡ አድርጓል፤ በዚህም የሰብዓዊ መብትን ገድቧል ሲል ዘገባ አዉጥቶአል። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ አቶ ፍስሀ ተክሌ፤ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ ተቃዉሞ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ዋትሳፕን ጨምሮ 16 የዜና መቀበያዎች መዘጋታቸዉን አረጋግጠናል ሲሉ ገልፀዋል።
አቶ ፍስሃ አምነስቲ ይህን ጥናት ያካሄደዉ በኢንተርኔት ሰርቪስ አገልግሎት ላይ አላግባብ የሆነ ጣልቃ ገብነትን የሚቆጣጠረዉ ከጎርጎረሳዉያኑ 2001 ዓ,ም ጀምሮ የተቋቋመ «Open Observatory of Network Interference» ድርጅት ጋር መሆኑን ገልፀዋል የዚህ ድርጅት ባልደረባና ተመራማሪ ማርያ ዛይ እንደገለፁት ፍተሻዉ የተካሄደዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉ።
«ድርጅታችን አንድ ድረገድ መታገድ አለመታገዱን እንዲሁም እንዴት እንደታገደ የሚመረምር ሶፍት ዊር ያመርታል። « በኢትዮጵያ ይህን ፍተሻ ለማካሄድ እኔ እራሴ አልሄድኩም። ስማቸዉን የማንጠቅሳቸዉ እዝያ ያሉ ኢትዮጵያዉያን ተመራማሪዎች ይህ ድርጅቱ ያመረተዉን ሶፍት ዌር ሃገር ዉስጥ በመጠቀም ነዉ የታገዱትን የመረጃ አዉታሮች ለማወቅ የበቁት። ተመራማሪዎቹ ከአገር ዉስጥ ብቻ ሳይሆን ከሌላም ሃገርም ኢትዮጵያ የሄዱ ናቸዉ። አብዛኛዉን ፍተሻ ያደረግነዉ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ሆነን ነዉ»
የኦኒ ድርጅት ባልደረባ ማርያ ዛይ በመቀጠል ምርምሩና ፍተሻዉ የተካሄደዉ አሉ፤ «ሙከራዉ የተካሄደዉ ከጎርጎሮሳዊዉ 2016 ሰኔ ወር እስከ ጎርጎረሳዊዉ ጥቅምት 7 ድረስ ነዉ፤ ጥቂት ወራት ማለት ነዉ። በሀገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲደነገግ ለደህንነት ስንል ሥራችንን አቋርጠን፤ ምርምራችንንም አጠናቀቅን።»
ኢንተርኔትን ማገዱ ሕጋዊ መሠረት የሌለዉና በሀገሪቱ ለተነሳው ተቃውሞ የተወሰደ ሌላ ያልተመጣጠነ እርምጃ ነው፤ በሕገ ወጥ መንገድ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችና የመረጃ አቅራቢ ድረ ገጾችን ማገድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነዉ፤ ሲሉ በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪ አቶ ፍስሀ ተክሌ ተናግረዋል።
የኦኒ ድርጅት ባልደረባ ማርያ ዛይ እንደ ገለፁት ድርጅታቸዉ የድረገጽ እገዳና አፈና በርግጥ ከማን በኩል እንደተፈፀመ እና እንዴት ነዉ እንደሆነ ለማየትና ለማወቅ አልቻልንም፤ እንደኔ ከዚህ ቀደም የኔ ባልደረቦች በቱክሚኒስታን የኢንተርኔት አገልግሎችን ለመገደብ ጥቅም ላይ የዋለዉ አይነት ዘዴ ነዉ የሚል ግምት አለኝ ግን ይህ ጥርጣሪና ግምት ብቻ ነዉ።» ሲሉ መናገራቸውን የጀርመን ሬዲዮ ዘግባ ያስረዳል።
የመንግስት ሚዲያዎች ኮማንድ ፓስቱን ጠቅሰው ይፋ እንዳደረጉት በሁለተኛ ዙር 12 ሺህ 500 ተጠርጣሪ የተባሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል። በመጀመሪያው ከታሰሩት ከ11 ሺህ በላይ እስረኞች ጋር በጥቅሉ የታሳሪዎች ቁጥር ከ21 ሺህ በላይ መሆኑ ታውቋል። በአንደኛው ዙር በቁጥጥር ስር ከዋሉት ተጠርጣሪዎች ስልጠና ተሰጥቷቸዋል የተባሉ 9 ሺህ 800 እስረኞች በመጪው ረቡዕ እንዲፈቱ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል። 2 ሺህ 449 ተጠርጣሪዎች ፍርድ ይጠብቃቸዋል።
በመጀመሪያው ዙር ራሳቸውን ሸሽገው የነበሩ 12.500 ሰዎች በቁጥትር ስር ውለዋል። 19 ሽብር ለመፈጠር የተንቀሳቀሱ ቡድኖች የተባሉ ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ 4.000 የሚሆኑ ተለይተው ሰንቀሌ የፖሊስ ማሰልጠኛ ካምፕ እንደሚገቡ ተነግሯል።
18 የፀጥታ ሀይሎች በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጉና የስነ ምግባር ችግር ያለባቸው 12 የፀጥታ ሀይሎች የስነስርዓት እርምጃ እንደተወሰደባቸው፣ በህገውጥ የፀጥታ ሀይሎችን ልብስ ለብሰው ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 10 የፀጥታ ሀይሉ አባል ያልሆኑ ሰዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ተጠቁሟል። ኮማንድ ፖስቱ ህዝብ ተባባሪ እንደሆነው አመልክቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *