“Our true nationality is mankind.”H.G.

“ታላቋ ትግራዋይ”

ያበደው እንግድነት በተቀመጠበት ቤት ዙሪያውን ያማትራል። ገና ከመቀመጡ የጥያቄ መዐት አንጎሉን እየበወዘው ነው። ቤቱ የአንድ “ልማታዊ ድሃ” ምሳሌ ነው። በአራቱም መአዘን ግድግዳ ላይ ምስሎች አሉ። መለስ በትልቁ ጉብ ብለዋል። ጣታቸውን ቀስረው የ “ወደፊቷን ኢትዮጵያ” ያመላክታሉ። ሌላም ትልቅ ስዕል አለ። ስዕሉ ካርታ ነው። ካርታው ማብራሪያ አለበት። ከካርታው ላይ ያለው ጽሁፍ “ ታላቋ ትግራዋይ” ይላል። አዎ “ ታላቅ ነበርን ዳግም ታላቅ እንሆናለን” ድንገት “ የተሰውት” የመለስ መፈክር!!

የጥሩ “ልማታዊ ደሃ” ቤት ገና ሲገባ ቤቱን መተናፈሻ የሚያሳጣ ዳንቴል ጣል ጣል ያለበት ሶፋ ይገኛል። ሶፋው በጨርቅ ይሸፈናል። አንዳንዴም የሶፋውን ቀለም ባለቤቶች ይረሱታል። የጅማን ደን ያወደም ቡፌ፣ አልጋና ቁምሳጥን አለ። ቤቱ በሲሚንቶ ሊሾ ይደረግና የላስቲክ ምንጥፍ ይለብሳል። ቦርጫሙ ቴሌቪዥን ቀን ከሆነ ልብስ ለብሶ ይታያል። ስልክ በሳጥን ውስጥ ተከርችሞባት፣ ዳንቴል ይደረበባታል። አዲስ ልሳን፣ ራእይ፣ ዘመን፣ ጽጌሬዳ፣ ሃትሪክጋዜጦች ከሶፋው ስር አይጠፉም። ከሳሎኑ ግርጌ የኤሌክትሪክ ምጣድ አይጠፋም። ቆጣሪው የቤተሰቡ አባል ይመስል አንገቱን አስግጎ ይታያል። ግድግዳው የፎቶ አልበም ነው የሚመስለው። የፊልም አክተሮችም አይታጡም። አንዳንዶቹ ለፋሲካ የሚወጣ የሽንኩርት መፍጫ አላቸው። ፍሪጅም አይታጣም።

ያበደው በካርታውም ሆነ በማብራሪያው አላዘነም። አልተከፋም። እንደውም ፎክር ፎክር አለው። “ ታላቋ ትግራዋይ”!! እትት፣ ዘራፍ፣ ዘራፍ … ቢል ምንኛ ደስ ባለው! ጋባዥ አንድ እናት ናቸው። ልክ እንደ ቦሰና እናት ያው የአበሻ እናት…. የሚበላ ለማቅረብ ጎንበስ ቀና ይላሉ። ሰው በልቶ የሚጠግብ አይመስላቸውም። ተጫዋች፣ ሩህሩህ፣ ተግባቢናቸው። ያበደው በላ ጠጣ። ከዛም ቀስ ብሎ ጨዋታ ጀመረ። ስለ ካርታው ጠየቃቸው።

ከየት አመጡት” ዋይሳቁ። “ ምኑን?” አሉ በፈገግታ ግድግዳቸው ላይ የተገጠገጠውን ስዕል እያዩ። ያበደው ተነሳና አሳያቸው። ወሬ ተጀመረ። ካርታቸው በደምና በአጥንት የተገነባ እንደሆን አብራሩ። “ ትግራዋይ” ታላቅ ሆና ሳያዩ ፈጣሪ እንዳይገላቸው የዘወትር ምኞታቸው እንደሆነ ወደላይ አማተቡና ተናገሩ። ያበደው ፈገግ አለ። ስማቸውን ጠራቸውና “ በቃ ከኢትዮጵያ ልትለዩ? እንደ ኤርትራ ልትገነጠሉ? አክሱም የሚባል ብር ልታሳትሙበቃ ልንለያይ ?”

ምን?” ሲሉ ጠየቁ። አከሉና አጠገባቸው ያለውን ደብር ስም ጠርተው አማተቡ። ቢሞቱ ከአዲስ አበባ ንቅንቅ እንደማይሉ አረጋገጡ። “ ታላቋ ትግራይ ስትመሰረት እኮ አንድ አገር ነው የምትሆኑት፣ ልክ እንደ ኬኒያ፣ ኤርትራ.፣ አሜሪካ፣ እንግሊዝ….” ከት ብለው ሳቁ። ደጋግመው “ አሜሪካ” አሉ። ወደ ቀልባቸው ተመለሱና “ እንደዚሁ እየኖርን ታላቅ መሆን አንችልም?” ሲሉ ጠየቁ። አሁን ያበደው መረር ማድረግ እንዳለበት ገባውና “ የሌሎችን ፈቃድ ማግኘት ግድ ነው” አላቸው።

መፈክር ሳይገባቸው ተሸክመው የሚኖሩ አሉ። ገብቷቸውም እንደ ማተብ አንገታቸው ላይ አድርገው የሚኖሩ አሉ። ያበደው ባየውና በሰማው አላዘነም። ግን ታላቋ ኦሮሚያ፣ ታላቋ አማራ፣ ታላቋ ሶማሊ ክልል፣ አፋር፣ ታላቁ የደቡብ ህዝቦች ሪፐብሊክታላቋ ጋምቤላ፣ ታላቋ ቤኒሻንጉል፣ ታላቋ ኦጋዴን….. ሁሉም ጋር ግን ያልተፈታ እንቆቅለሽ አለ። ያልተመለሰ ጥያቄ አለ። ወደ ጸብ አረንቋ የማምራት ምልክት አለ። አሁን በታሰበው መንገድ የመቀጠሉ ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ ነው። ኢትዮጵያን የሚያከስመው ጥርጊያ መንገድ በፍጥነት አስፓልት ሆኖ ዘየት እየተረጨበት ይመስላል። ሁሉም “ጠቦ፣ ታላቅ መሆን ” ተመኝቷል። ያበደው ክልሎች ታላቅ ቢሆኑ ጸብ የለውም። ኢትዮጵያን የሚያመነዥግ ታላቅነት ግን አይገባውም።

አሁን ባለው እውነታ “ የታላቅነት” የመጨረሻ ግብ አገር አልባነት ነው። የአርነት ንቅናቄዎች በዝተዋል። ራሱ ገዢው ህወሃትም የሚጠራው “አርነት” ተብሎ ነው። ኢትዮጵያዊነት ላይ አተኩረው የሚሰሩ ልሳናቸው እየተዘጋ ነው። ሰለው ወደ መጥፋት እያመሩ ነው። አማራም “ ራሴን ላድን” ብሎ በጠቅላይ ግዛትና በወንዝ ተደራጀ። ኢትዮጵያ የቀራት ነገር ቢኖር የሚሰራባት ድራማ ሲጠናቀቅ ማየት ነው።

ያበደው እምባው መጣ። አገሩ አሳዘነችው። አዎ ኢትዮጵያ ታማለች። እሳት ላይ ተጥዶ በሚንተከተክ ማሰሮ ተመስላለች። ማሰሮው ውስጥ ያለው ህዝብ ነው። ህዝብ እየነፈረ ነው። ፖለቲከኞች “ታላቅ” እንሆናለን በሚል ህልም ከውስጥም ከውጭም ማገዶ ይጨምራሉ። ማሰሮው ይንተከተካል። ማገዶ የሚቀንስ፣ እሳቱን የሚያጠፋ፣ ክዳኑንን ከፍቶ የሚያስተነፍስ የለም። የታፈነው ማሰሮ አማራጩ መገንፈል ነው። ከገነፈለ ገነፈለ ነው።

እኚህ እናት “ ታላቅነት” በመገንጠል ሳይሆን በአንድነት ውስጥ ነበር የሚመስላቸው። እንደ እሳቸው አስተሳሰብና እምነት ከሆነ “ ታላቅ” መሆን ለሌላውም ኩራት ነው። ሳይረዱ እኚህን እናት የሚጠሉ አሉ። እሳቸውም ሌሎችም ሳይገባቡ ይኖራሉ። አንዱ ሌላው ላይ ሳይገባው ጥርስ ነክሶ ይኖራል። የመለስ ራዕይ እየዋለ ብዙ ያሰማናል። አሁናሁን ህወሃትም ሰለቸው መሰል “ መለስ መለስ እያላችሁ አታላዝኑ” ሲል አሳስቧል። ትክክል ነው። ቢቻል የመለስን ውጥን ሁሉ ብታፈራርሱና “ ዳግም ኢትዮጵያን ታላቅ እናድርግ” በሚል መፈክር ብትነሱ መከላከያ፣ ኮማንድ ፖስትአስቸኳይ አዋጅ…. የሚባል ነገር እንደማይኖር ያበደው ማረጋገጫ የሰጣል!!

ያበደው ቦሰና ያለችው ታወሳው። ቦሰና ለኢትዮጵያ መፈትሄ አላት። በየክልሉ ህዝብ የሚወዳቸው ድርጅቶች አሉ። ህዝብ ለሚወዳቸው ክብር አለው። ለሚወዳቸው ይታዘዛል። ስለዚህ በሚወዳቸው እንዲተዳደር ሊፈቀድለት ይገባል። ምርጫው የራሱ እንጂ የሌሎች መሆን የለበትም። ትላለች። የዚያኔ ያበደው “ ሲያምርሽ ይቅር” ይልና ያሾፍባታል። እሷ ግን የምሯን ነው። ካልሆነ አደጋው ጊዜውን ጠብቆ ይመጣል። ባለሜንጫዎች አጋጣሚው ይሳካላቸዋል። … “ቦሰና ጆሮ ቢሰማ ዋጋ የለውም” ትላለች። ንጉሱ ምክር ገፉ፣ መንግስቱ ምክር አጣጣሉ፣ አሁንም ምክር የሚሰማ የለም። እስር መፍትሄ አይሆንም። የሚያኮርፉ ወገኖችን ማራባት አይጠቀምም። ቆም ብለን እናስብ። ከጥላቻ እንውጣ!! ሃውዜኖች እየበዙ ነው!!

ፖለቲካ ሸፍጥ ቢሆንም፣አይን ያወጣ የፖለቲካ ሽፋጥ ይቁም!! መንግስት ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚ ጎራውም ከማምታታት የታቀበ ይሁን። ህዝብ በሚሰማው ተሰላችቷል። በሁሉም ወገኖች ዘንድ መደማመጥ የለም። የመታገል የጥበብ መጀመሪያ መዘላለፍ ሆኗል። ጸያፍ ስድቦችን ያበደው ሰሞኑንን አይቷል። አማራን ነጻ አወጣለሁ የሚለው ሰው “ እናትህ ምናምን ትሁን ብሎ…”

አሁን ያበደው ደክሞታል። ደጎል ይጠብቀዋል። ደጎልን ከማዝናናትና ከእሱ ጋር ከመሆን በላይ ያበደውን የሚያስደስት ነገር የለም። “ ኢትዮጵያን ዳግም ታላቅ እናድርግ” የምትሉ ተባረኩ። ኢህአዴግ እስኪ በዚህ ሃሳብ ሞክር!! ሰላም ሰላም … ቸር እንሰንበት!!

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0