“Our true nationality is mankind.”H.G.

በገዢው ፓርቲ ጥልቅ ተሐድሶ ፍኖተ ሐሳብ፣ ተራማጅ ኃይሎች ከወዴት ናቸው?

በ2008 ዓ.ም. ህዳር ወር ጀምሮ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች የተነሣሣው ሕዝባዊ ቁጣ ለበርካታ ሕይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያት መሆኑ የአደባባይ እውነት ነው። ቀውሱን ተከትሎ የተለመደው ህግ የማስከበር ሥርዓት አደጋ ላይ በመውደቁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ ሁኔታዎች አስገድደዋል። ዐዋጁ በሥራ ላይ በሚቆይባቸው ስድስት ወራት ሀገሪቱ በተቋቋመው ኮማንድ ፖስት እንደምትመራ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርበውም አጸድቀዋል።
በወቅቱ በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ የተደናገጠው ገዢው ፓርቲ የችግሩ ምንጭ የመልካም አስተዳደር እጦት እንደሆነ መግለጹ የሚታወስ ነው። ይህም በመሆኑ ‘ጥልቅ ተሃድሶ’ ለገዢው ፓርቲ እና ለሥርዓተ-መንግስቱ አስፈላጊ መሆኑ ተነገረ። በይፋም ገዥው ግንባር የተሃድሶ ክተት ዐውጆ የፓርቲ እና የመንግስት መዋቅርን ለማፅዳት እየተፍጨረጨረ ይገኛል።
‘ጥልቅ ተሃድሶ’ እየተባለ በፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች በተለያዩ መድረኮች እና በመገናኛ ብዙሃን የሚለፈፈው፣ አነጋጋሪ ብቻ ሳይሆን፣ “ለምጣዱ ሲባል፣ አይጧ ትለፍ” እንዲባሉ፤ ልፈፋው የቀድሞውን ሊቀመንበር አገላለጽ የሚያስታውስ ሆኖ ነው ኅብረተሰቡ ያገኘው።
አብዛኞቹ የፓርቲው የፖለቲካ አመራሮች ስለጥልቅ ተሃድሶው መሰረታዊ አስተሳሰቦች ሲያብራሩ፣ “የአስተሳሰብ መታነጽ፣ የተንሸዋረረን አመለካከት መለየትና ማስተካከል፣ የሥርዓተ-መንግስትን ስልጣን እና የፓርቲን ስልጣን መለየትና እንደአግባቡ መጠቀም” የሚሉ ሐረጎች ሲጠቀሙ ይደመጣሉ። የጥልቅ ተሐድሶው አፈፃጸም ጓዶቻቸውን “የግድ መጠየቅ እና ማሰር ላይጨምር ይችላል፤ ዋናው የአመለካከት ለውጥ ማምጣት ነው፤ ሲሉ ተደምጠዋል።
ሆኖም ግን ከፖለቲካ አመራሮቹ የሚሰማው “የአመለካከት ለውጥ ማምጣት” የሚለው ፍሬ ነገር መነሻው ግልጽ አይደለም፤ ምክንያቱም የሚባለው ኪራይ ሰብሳቢነት ከዝንባሌም አልፎም በተግባር ከገነገነ በኋላ ሁኔታውን እንደምን በተሐድሶ ለመቀየር እንደሚቻል አመራሮቹ ብቻ ነው የሚያውቁት። ከእነርሱም አንዳንዶቹ በዚሁ የአመለካከት እና የተግባር ንቅዘት ውስጥ የተነከሩ መሆናቸው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው።
ራሳቸውን ያላጸዱ ወይም መፅዳት የማይፈልጉ የፖለቲካ አመራሮች፣ ጓዶቻቸውን እና ሌሎች የሲቨል ሰርቪስ ሠራተኞችን ወደ አመለካከት ጥራት ለማምጣት እንዴት ይቻላቸዋል?
ገዢው ግንባር አሁን በሚገኝበት ፖለቲካዊ ቁመና፣ በነጭ እና በጥቁር የሚመሰሉ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች ናቸው ያሉት፤ ብሎ መደምደም ይቻላል። የግራጫውን ማለትም የቀናውንና የሚበጀውን ቦታ የያዙ እንዳሉ ለማሰብ ያዳግታል፤ አሉ ቢባልም እንኳን የበላይነቱን ከተቆጣጠሩቱ ኪራይ ሰብሳቢ የሆኑት የፖለቲካ አመራሮች የሚደርስባቸውን ጫና ለመቋቋም ይሳናቸዋል፡፡ ስለዚህም ምርጫው የበላይነቱን ከያዙት ኪራይ ሰብሳቢ የፖለቲካ አመራሮች ጋር በግልጽ መቀላቀል አልያም ከውስጣዊው የፓርቲ ትግል ራሳቸውን አርቀውና የታዛቢነት ሚና ወስደው የለውጥ ሒደት እስኪጀመር በአማራጭነት መጠበቅ ብቻ ነው።
በሚለፈለፈው “ጥልቅ ተሃድሶ” ምንአልባት ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ ተብለው ተስፋ የተጣለባቸው እነዚሁ ከውስጣዊ ትግል ራሳቸውን አርቀው የታዛቢነት ሚና ወስደው የሚበጀውን የለውጥ ሒደት በአማራጭነት እየተጠባበቁ ካሉ አመራሮች ነው። የንቅዘት ፈረስ ሲጋልቡ የነበሩቱ ግን ዛሬ ላይ በሀገር መከላከያ ሰራዊት እና በደህንነት ኃይሎች ዋጋ በተረጋጋ ሀገር የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚን “ከእኛ” በላይ የሚደፍቀው የለም እያሉ በአደባባይ ቢለፈልፉም፣ በሕዝብ የተተፉ ኃይሎች ናቸው።
ለዚህም ነው፣ የጥልቅ ተሃድሶው ፍኖተ ሐሳብ በቀለም አልባ መስመሮች የተሰመረ ነው የሚባለው። ፍኖተ ሐሳቡ ከውስጣዊ የፓርቲው የፖለቲካ ትግል ወደ ሰፊው ሕዝብ መሰመር አለበት የሚባለው። ይህም ሲባል በ‘ጥልቅ ተሃድሶ’ ይቀጣጠላል የተባለው የፖለቲካ ትግል፤ በፓርቲው እና በሥርዓተ-መንግስቱ ውስጥ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ከዝንባሌም አልፎ በተግባር እንዲንሰፋራ ያደረጉትን አመራሮች ቆርጦ በመጣል መገለጽ አለበት ነው፤ እየተባለ ያለው። ከዚህ ውጪ ከአመለካከት ወደ ተግባር፤ ከተግባር ወደ አመለካከት እንቀይራለን እየተባለ የሚለፈፈው ከቃል ነቢብ በዘለለ ፋይዳ እንደማይኖረው ነው የሚታመነው፡፡
ቢያንስ ባለፉት አዐሥራ አምስት የዕድገት አመታት ውስጥ አንዳንድ ተጠቃሽ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች ዝቅጠት፤ ከአመለካከት ወደ ተጨባጭ ተግባር የገነገነውን የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚን፣ “በሶስት ወር “የጥልቅ ተሃድሶ” ወደ ሕዝባዊ መስመር እንመልሰዋለን” መባሉ አመክንዮአዊ ያልሆነና ሕዝባዊነትን ያላስቀደመ ለፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ ፍጆታ ብቻ የሚነገር ያስመስለዋል፡፡ የፓርቲውን ባለድርሻ አካላት ሳይቀር ውዥንብር ውስጥ መክተቱ አይቀርም፡፡
“ጥልቅ ተሃድሶ” የአመለካከት ለውጥ በማድረግ የሚመጣ መሆኑ ቢገለጽም በፓርቲ ውስጥ የመወሰን ስልጣንን ባላቸው ኃይሎች የሚወሰን ነው፡፡ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ አራማጆችን በውስጠ ፓርቲ ትግል ከሥሩ ነቅሎ መጣል እስከአልተቻለ ድረስ፤ የሚካሄድ ማኅበራዊ አብዮት እንደሚኖር ነብይነት አይጠይቅም፡፡
በግልፅ ለመናገር፣ ኢትዮጵያ በአሁን ሰዓት የተረጋጋ የፖለቲካ አየር ያገኘችው፣ ሕገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን የመጠበቅ ኃላፊነት በተጣለባቸው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና በደህንነት ተቋማት እንጂ የፖለቲካ አመራሩ በዘረጋቸው የሲቪል ተቋማት አለመሆኑ ግንዛቤ መውሰዱ ጠቃሚ ነው። ለዚህም ነው፤ ገዢው ፓርቲ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ከደህንነት ተቋማት ድጋፍ ውጪ፤ ሕዝባዊ መሰረት ባለው የፖለቲካዊ ቁመና ላይ ፈጥኖ መገኘት አለበት፤ የሚባለው፤ ወይም ግፊት እየተደረገበት ያለው።
ይህ እንዳይሆን ግን፣ በገዢው ግንባር ውስጥ አንዱ ሌላው ላይ ላለመደራረስ የወሰኑ የሚመስሉ ከፍተኛ የፖለቲካ አመራሮች ቁጥር፣ በግልፅ ለመፈታተሽ ፈቃደኛ ከሆኑት ከፍተኛ አመራሮች የበዙና የገዘፉ እንደሆኑ አሳማኝ ምልክቶች አሉ። ይህም በመሆኑ ነው፣ ከሥርነቀል ለውጥ ይልቅ ጥገናዊ ለውጥ ማድረግን በአማራጭነት ይዘው የቀረቡት። ለዚህም ነው፣ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሕዝባዊነትን የዘነጉ የፖለቲካ አመራሮች፣ በሌላ ቦታ እንደገንዘብ ታጥበው ብቅ እንዲሉ በፓርቲው ውስጥ በዘረጉት ኔትዎርክ የሚፈቀድላቸው። ለምን እንደዚህ ይሆናል ተብሎ ሲጠየቅም፣ የአመለካከት ለውጥ እንጂ ሰዎችን በማሰር ወይም በማሳደድ የሚመጣ ውጤት የለም፣ እየተባለ የኔትዎርኮቹን ቁልፈ በያዙ አመራሮች የሚገለጸው፡፡
በኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ አመለካከትና ተግባር ውስጥ የተዘፈቁና ሕብረተሰቡ በአደባባይ የሚያውቃቸው የፖለቲካ አመራሮች፤ በተለያዩ ትንታኔዎች ሽፋን ሾልከው የሚያልፉበት አሰራር መዘርጋቱ አጠያያቂ ከመሆን አይዘልም፤ በአስቸኳይም መቆም ይኖርበታል፡፡ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የደህንነት ተቋማትም፤ ገዢው ፓርቲ፣ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን መሰረት ባደረገ መልኩ ኪራይ ሰብሳቢ የፖለቲካ አመራሮቹን እንዲታገላቸው ጫና ማሳደር ይጠበቅባቸዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀው፣ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ እንጂ፣ ገዢው ፓርቲ ኪራይ ሰብሳቢ የፖለቲካ አመራሮቹን እንደተሸከመ ከመጣበት ፖለቲካዊ ቀውስ እንዲሻገር አይደለም። ገዢው ፓርቲ ለሕዝቡ ፍላጎት እንዲገዛ ማስገደድ ወይም በጎ ተፅዕኖ ማሳደር ሕገ መንግስታዊ ተልዕኮ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ተግባር ነው፤ ይገባልም።
ገዢው ፓርቲ፣ “በጥልቅ ተሃድሶ የአመለካከት ለውጥ” ትንታኔ ሽፋን፣ ኪራይ ሰብሳቢ የፖለቲካ አመራሮችን ተሸክሞ የተሃድሶ ጉዞውን ደምድመአለው ካለ፤ በቀጣይ ለሚፈጠራው ማኅበራዊ አብዮት ከተጠያቂነት አያመልጥም፤ ለሚደርሰውም ጥፋት ግንባር ቀደም ተጠያቂ እንደሚሆን ሊታወቅ ይገባል፡፡ ማሕበራዊ አብዮቱ መከሰቱ አይቀሬ ከሆነ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና የደኅንነት ተቋማት ከሕዝቡ ጋር በመሆኑ ሒደቱን ከግብ ለማድረስ ከወዲሁ ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
ሊከሠት የሚችለው ማሕበራዊ አብዮት፣ የኪራይ ሰብሳቢ ፖለቲካ ኢኮኖሚ የተሸከመውን ሥርዓት አራግፎ፣ በተራማጅ ማኅበራዊ ሥርዓት የሚተካ ነው የሚሆነው። በምትኩም አዲስ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሥርዓት ነው የሚፈጥረው። ይኽውም የማሕበራዊ አብዮት ጥያቄ፣ የመንግስት ሥልጣን ጥያቄ በመሆኑ ነው። ለዚህም ነው፣ ማሕበራዊ አብዮት ከመፈንቅለ መንግስት የሚለየው። አሁን እየተከናወነ ያለው ‘ጥልቅ ተሃድሶው’ በመገለጫው፤ የፓርቲና የመንግስት ሰዎችን በሌላ መተካትና በብዙሃን ዋጋ የጥቂት ኪራይ ሰብሳቢ ኃይሎችን ፍላጐት ይዞ ከማስቀጠል የዘለለ መሠረታዊ ለውጥ እስካላመጣ ድረስ የማኅበራዊ አብዮቱ መከሰት የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው የሚሆነው።
ከላይ የሰፈሩት ሁኔታዎች ከመከሰታቸው በፊት፣ ገዢው ፓርቲ እራሱን ሊያርም የሚችልበት እድሎች በጣም ሰፊ ናቸው።በመሰረታዊነት ግን፣ በፓርቲው ውስጣዊ ትግል ኪራይ ሰብሳቢው የፖለቲካ አመራር በተራማጅ ኃይሎች ሳይውል ሳያድር መተካት አለበት። ተራማጅ ኃይሎች እነማን ናቸው? ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያላቸው፣ ሕዝብን ለማገልገል የተሰጡ፣ የጋራ ብልፅግናን የሚሹ፣ ኢኮኖሚያዊና ማሕበራዊ ፍትህን የሚደግፉ እና ለዚህም መሳካት ቁርጠኛ የሆኑ ናቸው። ከማሕፀን ኪራይ እስከ ሕዝባዊ ቁስ ኪራይ ሰብሳቢነት ኔትዎርክ ውስጥ የሌሉ ኃይሎች ናቸው። እነዚህን ሕዝቡ አጥብቆ ይሻል። “ለምጣዱ ሲባል፣ አይጧ ትለፍ” የሚለው ብሂል፣ ኪራይ ሰብሳቢ አመራሮችን ለመሸከም ከዋለ ምጣዱን መስበር ተገቢነቱ ምትክ አልባ ነው።

Related stories   በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ- ትህነግ “ክብሪት” የተባለ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙ ታወቀ፣

 በፋኑኤል ክንፉ     (www.sendeknewspaper.com)

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0