አንዷ ያገሬ ሴት ደጋግማ ስታወራኝ ነው አንዱን የፌስ ቡክ ዝነኛ ታጋይ ያወቅሁት። እንዴት እስካሁን እንዳላየሁት ገርሞኝ በስሙ ፈልጌ ገባሁ። ጊዜየን አላጠፋሁም። ዘጋሁት። ካሁን ቀደም እንዴት የፌስ ቡክ ገጼ ላይ እንደመጣ ሳላውቀው ገጭ ብሎ ባገኘው ከፍቼ አይቸው፣ ሰምቼው… ወዲያው ነበር የዘጋሁት። ያኔ ለመጀመሪያ ጊዜ ሳየው፣ ነብያችን ድንገት ተከስተውለት ኖሮ፣ አዲስ ሙስሊም (convert) ሆኖ ነው መሰለኝ፣ ጥቂት የማውቃቸው ሙስሊም የፌስ ቡክ ወዳጆቼ፣ ላይክ አድርገው “ኢንሻላህ! ሱብሃናሁ ወተዓላ…”፣ “… እንኳን ወደ እውነተኛው እምነት መጣህ ወንድማችን…” … ወዘተ የሚሉ ጽሁፎች ገጹ ስር ተኮልኩለው አይቼ ሳምንት ሳይሞላኝ ነው ያቺው ያገሬ ሴት ስትነግረኝ እንደገና ፈልጌ የገባሁት። ላካንስ ሰውየው (ካሁን በኋላሰውየውስል ይኸኑ ሰውየ ነው) ባንድ ሳምንት ውስጥ ተመልሶ የተዋህዶውን ክርስትና ተጠምቆ ቆየኝ፣ “እንዲያ ነው እንጂ! እማምላክ ትሻል ለች” አይነት ጽሁፎች በስሩ ተሰድረው አነበብሁ። ታሪኩን ከዚች ያገሬ ሴት ስሰማ፣ ለካንስ እስላም ተመሆኑም በፊት ደሞ የጌታ መንፈስ አድሮበት፣ የወንጌሉም እየሱስ ቤት ገብቶ ተመልሶ ወጥቶ ኖሯል፤ መቼም “ጌታ የተባረከ ይሁን…” አይነት ምርቃት እንደማይጠፋ ነው ያኔም።…

መቼም ገጣሚ እና … (ለምን “ሎሬት” እንዳላሉት ገርሞኛል፣ “ሎሬት” ከመባሉ በፊት ጸጋዬ ገ/መድህንም “ገጣሚ” ሳይባል አይቀርም ይመስለኛል። ወይ ገጣሚ ሄኖክ!… እውነት ለመናገር ሄኖክ እና የፖለቲካ አቋሙን በተመለከተ ለትችት የሚበቃ እንኳን የፖለቲካ ሃሳብ የለውም። ገጹ ውስጥ ብዙ ገብቼ አላውቅም። እጅግ በወረደው ሃሳቡ ላይ እንዲሁ ጊዜዬን የማባክን ይመስለኛል። ስለ “ገጣሚ”ነቱ ግን በሚቀጥሉት ጽሁፎቼ በዝርዝር እመለሳለሁ።

ሰውየው ከዚህ ሁሉ (በአንድ ወር ውስጥ ሶስት ሃይማኖት መቀያየር) በኋላም ያለው ተከታይ እንዲህ የዋዛ አይደለም። “ስንቱ ሰው እንዲህ ስራ ፈት ሆኗል” የሚል የጅል ሃሳብም የለኝም፤ ብልስ ስንቱ የፌስ ቡክ ተጋዳላይ ጋር ተጨቃጭቄ እና ተጣልቼ ስንቱን ስድብ እችለዋለሁ? አንዳንዶቹን ባልነካካቸው ይሻለኛል፣ ቀድሞ ነገር ልቅ ናቸው። የነዚህ ሰዎች ድርጊት ስራ-ፈትነት አይመስለኝም፤ ይልቅዬ ስራ ነው ያገኙት፣ እነ ሄኖክ እንደሚባለው ደመወዝ እየተቆረጠላቸው ካልሆነ በቀር እውነት እንዴት እንዲህ ያለ የፖለቲካ አቋም ይዘው እንደመጡ ለመገመት ያስቸግራል (ለመሆኑ የነሱ ኪስ የሚሞላው፣ ከስንት ኢትዮጵያዊ ሞት በኋላ ነው?)… የሚገርመኝ … እስኪ አሁን አማራ እንዳይደራጅ እና እንዳይዋጋ አንድም ጊዜ ሲናገሩ ተሰምተው በማያውቁት ግንቦት ሰባትም ሆነ ኢሳት ላይ ያን ያህል የማውገዝ ዘመቻን ምን አመጣው? የህወሃት መገናኛ ብዙሃን ራሱ “…የተማረኩ የግንቦት ሰባት…” ብሎ ሲናገር ከመስማትና ከማየት በላይ ግ7 በትጥቅ ትግል ላይ እንዳለ ምን ማስረጃ ይምጣ? የህወሃት ካድሬዎች እንደ ድመት ጣራ ለጣራ እየዘለሉ ዲሽ ሲያወርዱ እያየን የኢሳትን ድርሻ ማሳነስ ምን ይባላል? በሚሊዩን የሚቆጠር ገንዘብ መድቦ ኢሳትን መዝጋት ያልቻለው መሆኑን ከአለም አቀፍ ምንጮች ከመስማት በላይ ምን ይምጣ? … እንዲያው ያልገባኝ ነገር፣ ግንቦት ሰባት ከኤርትራ ሆኖ አልቻለውም ያሉትን የትጥቅ ትግል እነሱ እንዴት ብለው ሆሊ ዉድ አፋፍ እና ቨርጂኒያ ቢች ላይ ሆነው እንደሚመሩት ነው። … ደሞ ያንዳንዱ ስድብ’ኮ አይጣል ነው። በአንዳንዶቹ አይን ይኼ በአንድ ወር ውስጥ የሶስቱንም ሃይማኖት ተከታይ የነበረው ሰውየ  ምስጋን ይጣ!… ሰውየው የራሱ የሆኑ  በርካታ ተከታይ የማህበረሰብ ክፍሎች ግን አሉት። የሰባ ሶስት አመቷ አማቴ አንዷ ነች፦

Related stories   የመረጃ መንታፊዎች ዋትሳፕን እንደ ጥቃት ማድረሻ መሳሪያ እየተጠቀሙ መሆኑ ተገለጸ

“ሰው ማለት ‘ሰውየው’ ነው!…” አለችኝ አንድ ቀን።

“ስሙ እኮ እንደሱ አይደለም….” ተማለቴ፣

“እዲያ! አንተ ደሞ ቡሊስ ይመስል ነገር ቶሎ አይገባህም… በላስት ኔሙ  ነው’ኮ…” አለችኝ።

“…ፖሊስስ ቢሆን ደጋግሞ የሚጠይቅ የነገር ብልት ለማወቅ ብሎ እንጂ ነገር ሳይገባው ቀርቶ መስለሽ?” አልኳት።

“… አንተን ሙግት እና ነገር ማን ይችላል እናቴ! ልጄ’ኮ እንዲያው ልፊ ቢላት ነውንጂ ‘ስፖርት፣ ጂምናስቲክ…’ እያለች መከራዋን የምታየው፣ ያንተ ንግግር እና ሙግት ብቻውን ወትሮም ያመነመናት ናት…” አለችኝ፤ እናም ቀጠለች፡-

“…ከ‘ሰውየው’ ወዲያ ንግግር ላሳር ነው፣ ያንን ወደላ ያማሪካ የቡና ሲኒ ይዞ…. ሲስቅ እኮ… አቤት ፈገግታው! ሳቁ ይምጣብኝ አቦ! አሳሳቁኮ እንጨት ያስፈልጣል…። ደሞ የሲኒ አያያዙ! …. ባይሆን ሃይማኖቱን አላጠብቅ አለ እንጂ” አለች። ቀጠለች “ደሞ አለ እንጂ! ትንታግ የሆነ ልጅ ተነስቶልሃል!…ሄኖክ የሚሉት! አቤት እውቀት! አቤት ቅኔ!… ዛሬ የጣፈውን አላየህም እንዴ?” አለችኝ።

እኔና አማቴ አንድ ኮምፒውተር ነው የምንጠቀመው፣ እሷ ከፍታ ሳትዘጋው ሄዳ በአጋጣሚ ሄኖክ የለጠፈውን ከማየት በቀር ለሱ የሚሆን የተረፈ ጊዜ የለኝም። እስኪ አሁን “መደመር ሳትችል ስለመጨመር እንዴት ልታወራ ትችላለህ?” የሚለውን ቅኔውን ለመረዳት ሊቀ ሊቃውንት መሆንን ሳይጠይቅ ይቀራል? አማቴ ግን የሱ ቅኔዎች ፍንትው ብለው ሳይታይዋት አይቀረም፣ የ“መደመር…” ቅኔው አንድ ኮሜንት እና 3 ሼር አስገኝቶለታል፣ አንዷ አማቴ ናት። ስታደንቀው ለጉድ ነው። እናም፦ “ደሞ ዛሬ ምን ጻፈ?” አልኳት።

“ ‘… እንደ ቅንድብ ስራ ፈት ከመሆን ያድናችሁ…’ አለ’ኮ።…

“… ስራ ፈት ማይም እሱ ራሱ ነው፣ ቅንድብ ስራ አለው፤ ውሃ፣ ላብ እና ሌላም ቆሻሻ ወደ አይናችን እንዳይገባ ተፈጥሮ የሰጠችን መከላከያ ነው። አፍንጫችን፣ ጆሯችን ውስጥ ያለው ጠጉር ሁሉ ቆሻሻ እንዳይገባብን እንደሚከላከለው ሁሉ…” አልኳት። ዝም አለች።

henokበሄኖክም ሆነ በሌሎቹም በርካታ የፌስቡክ የዘር አቀንቃኝ ታጋዩች ተከታዩቻቸው ውስጥ ራሴን አየሁት፣ እስኪ አሁን “በፈረንጅ ትምህርት….” የሚል ጽሁፉን አንብቦ ምን ማለት እንደሆነ የሚነግረኝ ሰው አለ? በእውነት አዘንኩ። ማዘን ብቻውን ግን ምንም አያደርግም፤ በዘር መደራጀት እና መታገል አለብን የሚሉት ሰዎች በአደባባይ እየወጡ መናገራቸው እና መጻፋቸው የሃሳብ መፋጨትን ያመጣ ይሆናል። ይሁን። ጉዳት ሊሆን የሚችለው፣ በተቃራኒው፣ አገራችን ውስጥ ያለው ችግር በአንድነት ካልሆነ በቀር በተናጠል የሚደረግ ትግል የትም እንደማይደርስ፣ ትግሉ ህወሃትን ቢያስወግድ እንኳን ሊከተል ከሚችለው ምስቅልቅል ለመዳን ያለው አማራጭ በአንድነት መታገል መሆኑን የሚያምኑ ሰዎች በየሚዲያው መሳተፍ እና መሬት ላይ እየሆነ ያለውን ተጋድሎ በማንኛውም መልኩ ማገዝ ካልቻሉ ብቻ ነው።

Related stories   እኛ የምንመርጠው አባትና አያቶቻችን የመረጡትን ነው።

እንደ ሄኖክ አይነቶቹን የፌስቡክ አርበኞች ጋር ዶ/ር ፍስሃ እሸቱን ለርዕስ የመረጥሁበት አንዱ ምንክያት ግን እንዲያው የፌስ ቡክ ተጋዳላዩም ተሳዳቢውም እንዴት እንደበዛ እና እንደ ሄኖክ አይነቱ ስንቱ እንቶ ፈንቶ ራሱ ስራ ፈትቶ ስንቱን ሰው ስራ አስፈትቶ እንደሚውል ለማሳየት እንጂ፣ ችግሮቹ እንዳሉ ሆነው፣ ዶ/ር ፍስሃን ከሄኖክም ሆነ ከሰውየው ጋር እያነጻጽርኩ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። እንዲያውም በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ፍጹም በሆነ አቋማቸው የሚታወቁ ሰዎችን በመጋበዝ አቋሙን በሚገባ ያሳየ፣ እልፍም ሲል እየመሰረተ ያለው ድርጅት ስሙ ራሱ የአንድነት ነው። ሁለተኛው ምክንያቴ ደሞ መረን ከለቀቀ ስድብ እና ዘለፋ ለመዳንም ጭምር ነው። እንዲሁ የምዕራቡ ዲሞክራሲ ተመቸኝ ብሎ ሞቅ ባለን ቁጥር በየሜዲያው እየወጡ የሆነ ያልሆነውን የሚናገሩ ሰዎች የሚያደርሱት ጉዳት እና፣ ትግል እንኳን ቢባል ለየብቻ የሚካሄደው “ትግል” የትም እንደማያደርስ እና ይልቁንም የባሰ መደናገርን የሚፈጥር መሆኑን እና ይሄም ለህወሃት ‘ሰርግና ምላሽ’ መሆኑንም ለማሳየትም ነው። ለዚህ ደሞ ዶ/ር አሰማሃኝ በኢሳት የተናገሩት ጥሩ ይመስለኛል፡~

“ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማየው ነገር … አንዱ የፖለቲካ ሃይል ሌላውን ጥሎ ለማለፍ እና መፍትሄውን በራሱ ለማምጣት የመሄድ መንገድ አለ እና… አስቸጋሪ ይመስለኛል… የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር የሚፈታው በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ህብረት ወይም መግባባት ነው፣ መደራደር ነው እንጂ አንድ የፖለቲካ ድርጅት ብቻውን የሚፈታው ላይሆን ይችላል፣ … የበለጠ ትግሉን ሲጎዳ ነው የምናየው… መግባባት ላይ መደረስ አለበት፣ አለበለዚያ ግን የዚህን ስርዓት ማራዘም ነው የሚሆነው፣ በሚሊዩን የሚቆጠር ህዝብ እየተራበ፣ እየተሰደደ ባለበት አገር … ልንከፍለው የማንችለው ዋጋ ሊኖር አይገባም… የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ የባንዲራ… ጥያቄ አይደለም፣ የመኖር እና ያለመኖር ጥያቄ ነው…” ያሉትን፣ በተለይም 48ኛው ደቂቃ ጀምሮ ያለውን እዚህ ያዳምጡ

የዩኒቲው (በቀድሞው) ዶ/ር ፍስሃ እሸቱ “ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት” እንዳቋቁሙ የነገሩን አሜሪካ በገቡ በማግስቱ ነበር (ፌብርዋሪ 2012)፣ በሶስት ፌዝ የሚያልቅ ዘመቻ መጀመራቸውን፣ እንዲያውም በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ነበር ተስፋቸውን የነገሩን። ዛሬ ደግሞ የዚያን ዘመቻ መጨረሻውን ሳናይ ሌላ “አንድ ኢትዮጵያ” የሚባል ድርጅት ከመሰረቱ አንድ ወር አልፏቸዋል፤ ካናዳ፣ አሜሪካ፣ ጄኒቭ፣ ሲድኒ. … ኗሪ የሆኑ አባላት እንዳሰባሰቡ እና በአንድ ወሩ ድርጅታቸው በእግሩ እየቆመ እንደሆነ ነግረውናል። ትናንት በስቲያ ደግሞ እንዲያውም የሬዲዩ ስርጭት መጀመራቸውን እና እንዲያውም “… ልብ ወለድ ድርሰትም… ያላችሁ ላኩልን…” ሲል አስነግሯል።

ከመሰረታዊ ፍላጎቶች (ምግብ መጠለያ እና ልብስ) ውጭ መኪናም አይሮፕላንም ገዝቶ በፈለገበት ግዛት ውስጥ በፈለገው ጊዜ ሄዶ መስራት፣ መብረር፣ መኖር በሚችልበት በምዕራቡ አገር ውስጥ ሆኖ ስለ ቅንነት እና ፍቅር መስበክ አልጋ ባልጋ ነው። በዚህ ሰው እንደፈለገ በነጻነት በሚኖርበት አገር ውስጥ ሆነህ ስለ ፍቅር፣ አንድነት፣ ባንዲራ … ወዘተ  መስበክ ቀላል ነው፣ አገር ቤት ውስጥ ሆኖ መስበክ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ለነገሩ ዛሬ ዛሬ ህወሃትም የሳይበር ካድሬዎቹን ሁሉ አሰማርቶ ስለ “ፍቅር እና ሰላም ይሰብካል፣ ካድሬ ደብተራዎቹንም በየቤተክርስቲያኑ ሰግስጎ ስለ ሰላም ብቻ ሳይሆን፣ “…መንግስት በግዜር ትዛዝ የመጣ ነው…” እያስባለ እየሰበከን፣ እኛም እየተሰበክን ያለንበት ዘመን ላይ ነው ያለነው።

Related stories   የመረጃ መንታፊዎች ዋትሳፕን እንደ ጥቃት ማድረሻ መሳሪያ እየተጠቀሙ መሆኑ ተገለጸ

ዶ/ር ፍስሃ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያፈራባት አገሩ ናት ኢትዮጵያ፤ ሃብት ቢያፈራባትም “conscious guilty (የህሊና ወቀሳ) የራሱ ቋንቋ ነው” ቢበዛበት እና ከገንዘብ በላይ በህወሃት መንግስት በህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ አንገፍግፎት ዩኒቨርሲቲውን በሚሊዩን ደረጃ ሸጦ አገር ጥሎ ወጥቷል። ኢትዮጵያዊነቱ እስኪያስጠላው (ይሄም የራሱ ቃል ነው) ድረስ ደርሷል። አንተ ኢትዮጵያዊነትህ አስጠልቶሃል። ስለ ፍቅር እና ስለ ባንዲራ የነገርከን ዶ/ር ፍስሃ ሆይ! እባክህ ይኸን ቅጂ ላፍታ እይልኝ እና በዚህ በሚጮኸው ልጅ፣ ወይም በሚጎተተው ልጅ ቦታ ራስህን አስቀምጥ … እና አንዱ መጥቶ “ፍስሃ ሆይ! አይዞህ ‘ኢትዩጵያን እና ባንዲራዋን አፍቅር” ፍቅር እና እግዚአብሄርን ከያዝክ ምንም አትሆንም…” ብሎ ሲነግርህ ምን እንደምታስብ “…እየየም ሲዳላ ነው”።

ወዳጄ! ግፍና መከራው ያለው መሬት ላይ ነው፣ ኢትዮጵያ ከምንላት መሬት ላይ፣ መከራ እና ግፉ እየተፈጸመ ያለው እዚያ ነው፣ መፍትሄውም የሚመጣው እዚያው መሬት ላይ ነው። በመስዋዕትነት ነው። እናም አሁንም መስዋዕትነት መክፈል እንደሚቻል፣ በ“conscious guilty” ምክንያት፣ ልክ እንደኔና እንዳንተ በምዕራብ አለም፣ ሉክሰምበርግ ላይ ይኖር የነበረው ሻለቃ መሳፍንት መስዋዕት ሆኖ፣ አንዳርጋቸው በትግል ላይ ሆኖ ተጠልፎ ሄዶ ዋጋ እየከፈለ፣ ሌሎቹም የምዕራቡ አለም ኑሯቸውን ጥለው በረሃ ሄደው ዋጋ እየከፈሉ እያሳዩን ነው። ዜጎችም አገር ቤት ውስጥ እየወደቁ እና እየጣሉ ነው። እንደ አቶ በቀለ ገርባ፣ አንዷለም፣ እስክንድር፣ ምናልባትም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ታስረው ዋጋ እየከፈሉ ያሉበት ትግል አለ… ዶ/ር መረራ ዋጋ እየከፈሉ ነው።

ሞት፣ ስቅየት፣ ግርፋት፣ ስደት፣ ረሃብ፣ ጥማት፣ መከራና አበሳው ያለው አገርቤት ውስጥ ነው፣  … ዶ/ር ፍስሃ ከኢሳቱ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጋር ያኔ በ2012 ሲነጋገሩ ያነሳው የናፖሊዩን ጥቅስ “… if it is for France, I will sleep with prostitute (ለፈረንሳይ [የሚጠቅም] ከሆነ ከሸርሙጣ ጋር እተኛለሁ” ያለው ግሩም ጥቅስ ነው። ይህ ጥሪ ለዶ/ር ፍስሃ ብቻ አይደለም፣ ለሌሎቹም በየፌስ ቡኩ ለሚጽፉ እና ለሚናገሩትም ነው። በጅምላ እየተገደለ፣ እየታሰረ፣ እየተሰቃየ ላለው ለኢትዮጵያ ህዝብ ስትሉ፣ ይኼን ትግል ከመከፋፈል፣ ብትችሉ ህብረት ፈጥራችሁ ትግሉን ልታግዙ የምትችሉበትን መንገድ ማሰብ ትችላላችሁን? (ፎቶ: ምንጭ)

tafeseworku2016@gmail.com

ታፈሰ ወርቁ

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *