“Our true nationality is mankind.”H.G.

መራራው መረራ (ከአንተነህ መርዕድ)

ከአንተነህ መርዕድ

መረራ ትናንትም ዛሬም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ተግቶ የታገለና አሁንም የሚታገል የአገር ጀግና ነው። ማሰር፣ ማሰቃየትና መግደል መረራ ጉዲናንና ሌሎችን ኢትዮጵያውያን ዝም የሚያሰኝ፤ አምባገነናዊ አገዛዝንም ባለበት የሚያፀና ቢሆን ኖሮ ደርግ ባልወደቀም ነበር። መረራም ሆነ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ትግላቸውን አላቆሙም።

Dr. Merera Gudina

ወያኔዎች ታግለን ጣልነው ካሉት ደርግ የወረሱት ዙፋኑን ብቻ ሳይሆን የአገዛዝ መመርያውንም (ማንዋሉን) ጭምር በመሆኑ ድርጊታቸው ሁሉ ደርግን በሚያስከነዳ ጭካኔና ዘረፋ ላይ የተመሰረተ ነው።

ዛሬ መረራ ጉዲናን ነቅሼ በማውጣት በሱ ዙርያ ብዕሬን ሳነሳ የሁሉንም ለዴሞክራሲ የሚታገል ኢትዮጵያዊ ህይወት ይዳስሳል በሚል ነው። በዚች መከረኛ አገር ውስጥ የሚታገሉትም ሆኑ የሚሰቃዩት ሚሊዮኖች ናቸውና።መረራ በለጋነቱ በርካታ ለአገራቸው በጎ አሳቢ ወጣቶችን ህይወት ውጣ ውረድ ያለፈ ህያው ምስክር ሲሆን፤ በጎልማሳነቱ ደግሞ የነዛኑ ወጣቶችን ህልም እውን ለማድረግ የሚተጋ ቅን ፖለቲከኛ ነው። በደርግ የደረሰበትን ጠባሳ እያሻሸ፣ ተስፋ በመቁረጥ የተቀመጠ ሳይሆን ከትናንት ውድቀቱ በኑሮና በትምህርት ራሱን ያሳደገ፣ ለሌላ ዙር ትግልም ራሱን የማገደ ጀግና ነው። “እውነት መራራ ናት ፍሬዋ ግን ጣፋጭ ነው” እንዲሉ መረራ እንደስሙ እውነትን ላልተላበሱ አምባገነኖችና አስመሳይ ዘረኞች መራራ ነው።

መረራ አምባገነን ገዥዎችን ሆነ የነገዋ ኢትዮጵያ ብሩህ ህልም ደንቃራ የሚሆኑ ፅንፈኞችን የሚሸነቁጥበት ልዩ አንደበት አለው። ከብዙ ፖለቲከኞች የሚለየው የመረረ ጥላቻ ሳያሳይ ቀርቦ እያሳሳቀ በአጭር ቃል እውነትን የሚያፈርጥ ደፋር መሆኑ ነው። ጓዳ ከሚደረግ የፖለቲካ ሽረቫ ወጣ ብሎ ጎትቶ አደባባይ ለሙግት የሚጋብዝ ገራገር፣ ቢሰድቡት መልሶ የሚስቅና የሚቀልድ፣ ለጠብ የማይመች ሰላማዊ ታጋይ ነው። የመረራ ጡጫ በቀልድ የተዋዛ ቢሆንም አጥንት የሚሰብር እውነትና ኃይል ስለአለው፤ ውሸትንና ስሜታዊነትን መሰረት አድርገው ራሳቸውን በትልቅነት የኮፈሱትን እንደኩይሳ ይበትናቸዋል።

የመረራ ጡጫ ደጋግሞ ያረፈበት ወያኔ ምን ያህል እደደማ ግልጽ ነው። “የሚበላውን ያጣ ህዝብ መሪዎችን ይበላል”፣ “ቅርንጫፍ እንጂ ግንድ አይገነጠልም”፣ “ኢህአዴግ ደህንነትን፣ መከላከያንና ምርጫ ቦርድን እንደክራንች ተጠቅሞ የሚንቀሳቀስ ሽባ ድርጅት ነው” የሚሉትና ሊሎችም አባባሎች ቢተነተኑ ትልቅ ጥራዝ ይወጣቸዋል። ይህንን እውነት ላለመስማት ጀሮአቸውን የደፈኑት ወያኔዎች እስከ አጥንቱ የጋጡት ህዝብ ሊበላቸው መቃረቡን ባለመቀበል  እውነቱን ያዳፈኑ መስሏቸው መካሪያቸውን መረራን አስረዋል። እስር ለእሱ መች አዲስ ሆነና! በመጨረሻ አሳሪ ተሸናፊ፤ ታሳሪም አሸናፊ እንደሚሆን በህይወቱ በተግባር ያየ ነውና። ትናንት እስርቤቶችን ለነለገሰና ለነፍቅረስላሴ አስረክቦ የወጣው ትውልድ በቅርቡ ለነአቦይ ስብሃ፣ ለነአባዱላ አስረክቦ የሚወጣ መሆኑ የታመነ ነው። ይህ የመከራ አዙሪት ቀለበት እንዲሰበር ብንመኘውም እምቢ ስለተባለ ማነህ ባለሳምንት(ተረኛ?) መባሉ አይቀርም።

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

የህወሃት መሪዎች አባቶቻቸው ለጣልያን አድረው በባንዳነት ኢትዮጵያን እንዳሰቃዩአት ሁሉ ዛሬ እነሱ ከየጎሳው ባንዳዎችን መልምለው አማራውን በብአዴን ፣ ኦሮሞውን በኦህዴድ፣ ደቡቡን በደህዴድ ተጠቅመው ቅኝ ሲገዙ የጉረሮ ላይ አጥንት የሆነባቸው፣ ኦህዴድን ሽባ ያደረገባቸው የመረራና የጓዶቹ ትግል ነው። ዛሬ አብዛኞቹን አመራሮች ቢያስሩና ቢገድሉም በህዝቡ ዘንድ የለኮሱትን የዴሞክራሲ ትግል ነበልባል ከቶውንም ሊያዳፍኑት አይችሉም።

መረራ ለማንኛውም ዓይነት ጠባብ ዘረኛ እንቅስቃሴ የማይመች አሎሎ ነው። ሁለቱን ታላላቅ ህዝቦች ማለትም ኦሮሞና አማራን ለማጋጨት ህወሃት የተጠቀመበት ኦነግ ለኢትዮጵያ ህልውናና ለኦሮሞውም እኩልነት በሚመጥን ደረጃ ላይ ሆኖ ባለመገኘቱ ገበናውን በማጋለጥ እንዲስተካከል ጠንክሮ የተቸው የመጀመርያው  ኦሮሞ መረራ ጉዲና ነው። ጦቢያ መጽሄት ላይ በተከታታይ ባቀረበው ትችት በጊዜው አይነኬ የነበረውን የኦነግን መሰረታዊ ስህተት አጋልጧል። ኦነግ የኦሮሞን ህዝብ ሳይሆን የሚሲዮናውያንን ተልዕኮ ለመፈፀም በአንድ መንደር ልጆች የሚመራ መሆኑን መተቸቱ የሚመር ቢሆንም ብዙ የኦነግ ተከታዮችን እንዲባንኑ አድርጓል። በአማራና በኦሮሞ መካከል ቅራኔውን ለማስፋት ሌት ተቀን ይማስኑ የነበሩ አመራሮችንም < ቀን ስለአማራ መጥፎነት ስትሰብኩ ውላችሁ ማታ አማራ ከሆኑ ከጎጃሜና ከጎንደሬ ሚስቶቻችሁ ተቃቅፋችሁ ታድራላችሁ። ከነሱ የወለዳችሁአቸውን ልጆቻችሁን ምን ይሁኑ ነው የምትሉት?> በማለት በማስረጃ አስደግፎ በማቅረቡ የዘረኝነትንና የጠባብነትን አደጋ ኦነጎች ሊመክቱት በማይችሉት ምት አደባይቷቸዋል። ይህንን ያህል በመዳፈሩ ብዙ ፈተና ደርሶበታል። እንኳን እሱ በመጽሄቱ የምንሠራው ጋዜጠኞችም የ”እንገድላችሁአለን” ማስፈራርያ ደርሶናል። ሰውየው መረራ ነውና ግንባሩን አላጠፈም። በሰነዘረው ምት ኦነግ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አላንሰራራም። ወይንም የኢትዮጵያን ህዝብና የሰፊውን የኦሮሞ ፍላጎት በሚያካትት ሁኔታ ተስተካክሎ አልተነሳም። ብዙ ቦታ የተከፋፈለ የግለሰቦች ድርጅት ሆኖ አብቅቷል።

ዛሬ መረራ ሲታሰር ከሁሉም በኩል ያሉ ፅንፈኞች ያለወትሮአቸው ድምፃቸውን ያጠፉት አደባባይ የማያወጡት ደስታ ላይ ስለሆኑ ነው። በእውነት የታገለለት የኦሮሞ ህብረተሰብ ሆነ ሃቀኛ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ልብ ላይ መረራ አለ። የሰሞኑ የአምቦዎችና ሌሎችም ተቃውሞ የዝህን ዕውነት ያረጋግጣል።

“የትግራይ ልሂቃን <ስልጣን ወይንም ሞት> ብለው ስልጣን ላይ የሙጥኝ እስካሉ ድረስ፤ አብዛኛው የአማራ ልሂቃን በአፄዎች ዘመን የነበረውን የበላይነት መልሼ አገኛለሁ ብሎ የሚያስበውን የህልም ፖለቲካ እስካልተወ ድረስ፤ ብዙሃኑ የኦሮሞ ልሂቃን ኦሮምያን ለብቻ የማውጣቱን ህልም እስካልተው ድረስ ሀገራችን ከአደጋ ቀጠናና ቀውስ የምትወጣ አይመስለኝም”  በማለት ሶስቱንም የጨለማ ሃይሎች አጥብቆ የሚተቻቸው መረራ በበጎ ዐይን እንደማይታይ ግልፅ ነው።

Related stories   በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ- ትህነግ “ክብሪት” የተባለ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙ ታወቀ፣

መረራ ባለፉት በርካታ ዓመታት ሳይታክት መስዋዕት እየከፈለ ያስተማረውና የታገለለት ዓላማ ለሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያን መፍጠር ነው። ይህ ደግሞ የብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን ዓላማ በመሆኑ ትግሉን ህዝቡ በሰፊው ተቀላቅሎታል።  የእሱ መታሰር ትግሉን የማያቆም ለመሆኑ ብዙ መረጃ መደርደር ይቻላል።

  • ኢትዮጵያዊ ፍቅር በልቡ የሚነድደው አንዳርጋቸው ጽጌ ባለፉት ጥቂት ዓመታት መለስ ዜናዊና ጓደኞቹ በትዕቢት “እንደኛ ጫካ ግቡ። መንገዱንም ጨርቅ ያድርግላችሁ” እያሉ ሲመፃደቁ ሰምቶ አልተቀመጠም። እሱ ቢታሰርም አምጦ የወለደው የአርበኞች ግንቦት ሰባት ሰራዊት <ቁጭብዬዎቹ> ኤርትራ በረሃ ፍየል ይጠብቃል ሲሉት መሃል አገር መገኘቱን ወያኔ ተገድዶ እየነገረን ነው።
  • የግለሰቦች እስር ዋጋ የሌለው መሆኑን ኮሎኔ ደመቀ የለኮሰው የአማራ ተጋድሎ ሰላማዊ ዜጎችን በአደባባይ እየገደለ ይፏልል የነበረውን ወያኔን የራሱን እሬሳ እያስቆጠረው፣ ታቦት ተሸክሞ ለመማለድ የሚሄድበት መንገድ ከጨርቅም ቡትት እያደረገው ነው።
  • እስር ትግልን የሚያቆም ቢሆን መታሰርን በፀጋ ተቀብሎ ለትግል ቆርጦ ተገባውን ጀግናውን በቀለ ገርባን ማሰቃየት የኦሮሞ ልጆችን ተቃውሞ በገታው ነበር። በጥቂት ቃላት የወያኔን የመሬት ዘረፋ እውነት በቀላሉ በህዝብ ልብ ውስጥ በማስቀመጡ ለትግሉ የማይጠፋ እሳተገሞራ ሆኖ ይኖራል።
  • አይበገሬዎቹ እስከንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ውብሸት ታዬና በርካታ ጛዜጠኞችን ማሰር፣ ማሰቃየና ማሰደድ ቢቻልም የህዝብን ድምፅ ማልፈን አልተቻለም። ኢሳት፣ ኦ ኤም ኤን፣ ፍኖተ ዴሞክራሲ፣ የአማራ ድምፅ፣ ህብር ሬድዮ፣ ቪኦኤ፣ የጀርመን ድምፅ፤ በርካታ ድረግፆች፣ ፌስቡክ ወዘተ.. ወያኔን እርቃኑን የሚያስቀሩት ሊገዳደራቸው የማይችላቸው ጠላቶቹ ሆነው ወጥተዋል።
  • የኢትዮጵያውያን መሰደድ ለወያኔ እፎይታ የማይሰጥ ለመሆኑ በመላው ዓለም የዲያስፖራው ተጋድሎ ለግዥዎች የእግር ውስጥ እሾህ ከመሆኑ አልፎ የሌሊሳ ፈይሳ ዓለም ዐይኑን ገልጦ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈፀመውን ግፍ እንዲያይ ማድረጉ፣ ኦባንግ ሜቶ በመላ ዓለም እየዞረ ጋምቤላዎች መጨፍጨፍና ደማቸው ሳይደርቅ የወያኔ መኳንንት ምርት ሊያፍሱ የፈፀሙትን የዘር ፍጅት (ጄኖሳይድ) ማጋለጡ ምስክር ነው።

መረራ ጉዲና በእስር የተቀላቀለው ትንሽነትና የዘረኝነት በሽታ ከሚያሰቃያቸው ከወያኔ ወይንም በአምሳሉ ከተፈጠሩና እየተፈለፈሉ ካሉ ስር የለሽ የሶሻል ሚድያ ፅንፈኞች ሳይሆን የኢትዮጵያ ህሊና ከሆኑ በሩቁ ከሚታዩ ከዋከብት ከበቀለ ገርባ፣ ከአንዳርጋቸው ጽጌ፣ ከእስክንድር ነጋ፣ ከተመስገን ደሳለኝ፣ ከአንዱዓልም አራጌ፣ ከኮሎኔል ደመቀና ከብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ነው።

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

የትኛው የወያኔ ሰው ነው? የትኛው ከኮምፒዩተር ጀርባ ብቻ የተደበቀ የሶሻል ሚድያ ውሻል ነው በእስር የሚማቅቁትን ኢትዮጵያውያን ስብዕና ጫፍ የሚደርስ??

ጽሁፌን መራራው መረራ  በመጽሃፎቹ በሶስቱ የጨለማ ኃይሎች ላይ የሰነዘረውን እውነትና ኢትዮጵያውያንም ልብ ልንለው የሚገባውን ቁምነገር በመጥቀስ ላብቃ።

“በተቃዋሚው ጎራ፣ ብዙ ሳይንቀሳቀስ እያየሁ ያለሁት የኦሮሞና የአማራ ልሂቃን ፖለቲካ ነው። የሁለቱ ልሂቃን ፖለቲካ በዋናነት በሁለት ጫፎች ላይ ቆሞ ገመድ ከመጓተት ወደ መሃል መጥቶ የጋራ ዴሞክራቲክ አጀንዳ መቅረጽ አላስቻላቸውም ። ብዙዎቹ ሂሳብ የማወራረድ ፖለቲካን የዛሬ 30 እና 40 ዓመታት ብቻ ሳይሆን፣ የዛሬ 130 እና 140 ዓመታት በፊት የነበረውም ጭምር የታሪክ ሂሳብ እንተሳሰብ የሚሉ ይመስሉኛል። የኦሮሞ ልሂቃን ዋናው ችግራቸው የጋራ የፖለቲካ አጀንዳ ለመቅረጽ ከመጣር ይልቅ ለብቻቸው የሚያደርጉትን ትግል የመንግሥተ ሰማያት አስተማማኝ መንገድ አድርገው ማምለካቸው ነው”።

“የአማራው ልሂቃን ዋናው በሽታቸው በዋናነት በአማራልሂቃን የተፈጠረችው የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በዋናነት እንደዛው ትቀጥል፤ መቀጠልም ትችላለች የሚል ነው። ባለፉት አርባ ዓመታት የሃገሪቷ ፖለቲካ ዋናው የቀውስ ምንጭም እንደነበረች መቀጠል ያለመቻልዋ መሆኑን በውል መገንዘብ ያቃታቸው ይመስለኛል።….. ሁለቱም ከታሰሩበት የታሪክ እስር ቤት ወጥተው በጋራ የዴሞክራቲክ አጀንዳ ላይ ተስማምተው በመሃል መንገድ ላይ ካልተገናኙ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአሁኑ ትውልድ ዘመን ፈቀቅ የሚል አይመስለኝም”። ሲል ወያኔዎችን ደግሞ እንዲህ ሲል ይመክራቸዋል።

“ዛሬ ለጊዜው የሃገሪቷ የወደፊት ዕድል፣ የህዝቦቿንም እድል፣ የራሳችሁንም ዕድል፣ ምናልባትም የልጆቻችሁን ዕድል የሚወስን ሥልጣን ይዛችኋል። ውንድማዊ ምክሬ ይህንን ስልጣን ሃገርንና ህዝቦቿን ለመታደግና፤ ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያን ለመፍጠር ተጠቀሙ ነው”።

ይህ  የመረራ ጉዲና ምክር የተሰነዘረላችሁ አካላት መራራ እውነት ቢሆንም አዳምጣችሁ ወደህሊናችሁ ተመልሳችሁ አገርንና እራሳችሁን በማዳን ተግባር ላይ ብትሳተፉ ጊዜው የዘገየ አይሆንም። መረራማ ታሰረም፣ ተፈታም ዓላማውና ፅናቱ በህዝቡ ልብ ውስጥ ገብቶ ቁሳዊ ኃይል በመሆን ኢትዮጵያውያንን ሲያንቀሳቅስ ይኖራል።

Amerid2000@gmail.com

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0