“Our true nationality is mankind.”H.G.

አማራ ማነው? ስለሌሎችስ ማን ይንገረን?

(በዶክተር አበባ ፈቃደ) – ክፍል አንድ

ዶክተር አበባ ፈቃደ የአእምሮ ስነልቦና /Neuropsychology/ ምሁር ናት። በአሜሪካን ሃገር የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እና ኮሌጆች በመምህርነት እና ተመራማሪነት እንዲሁም በአማራ ህዝብ ፖለቲካዊ እና ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ላይ ፊታውራሪ ሆና የምትታገል ነች። ዶክተር አበባን ለየት የሚያደርጋት ነገር ‘እኔ አማራ ነኝ’ ብላ ስለ አማራ ህዝብ እና ማንነት ፊት ለፊት በመናገር እና ሰዎችን በማስተማር እንዲሁም ገዥው ስርዓትን በመቃወም ነው። ዶክተር አበባ በተለያዩ ሚዲያዎች ቃለመጠይቆችን ያካሄደች ሲሆን ለዛሬው ‘አማራ ማነው’ በሚል ርእስ ያደረገችውን ረዘም ያለ ገለጻ በአጭር በአጭሩ እንዳስሳለን!

እንደ ዶክተር አበባ ገለጻ አማራ የሚታወቅባቸው ብዙ ለየት ያሉ የራሱ የሆኑ የስነልቦና ባህሪያት ያሉት ሲሆን ዋናዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው።

1. መንፈሳዊነቱ/spirituality

መንፈሳዊነት ሲባል ሃይማኖት ማለት አይደለም። ሰዎች የተለያየ ሃይማኖት ሊከተሉ ይችላሉ። ነገር ግን እዚህ ጋር መንፈሳዊነት ሲባል የአማራ ህዝብ ባህሪውን፤ ማንነቱን፤ ታሪኩን እና ባህሉን የሚገልጽበት ጥልቅ ስሜቱ ማለት ነው። አማራ አኗኗሩ እንስሳዊ ባህሪይ ሳይሆን ከእኔ በላይ የፈጣሪ ሃይል አለ ብሎ የሚያምን ፤ ከሰው ልጅ በላይ የረቀቀ ነገር አለ ብሎ የሚያስብ እና የሰው ልጅ ሁሉ ረቂቅ እና በህገ ልቦና የሚተዳደር እንጂ በደመነፍስ የሚመራ አይደለም ብሎ የሚያስብ ፈሪሃ ፈጣሪ ያለበት ህዝብ ነው። አማራ በህገ ልቦናው ያደረውን ረቂቅ መንፈሱን ራሱን የመተርጎሚያ እንዲሁም ከሌላው ማህበረሰብ ጋር መልካም ግንኙነት የሚያደርግበት ድልድይ አድርጎ ነው የሚወስደው። ይህንን መንፈሳዊነቱን ለሃገር ግንባታ፤ ለመንግስት አወቃቀር እና ለተለያዩ ማህበረሰባዊ ተግባራት ይጠቀምበታል። አምሃራ- አም(ነጻ) እንዲሁም ሃራ(ህዝብ) የተባለውም ነጻ አስተሳሰብ፤ በምድር ላይ ከፈጣሪ በታች ሌላ ሃይል የሌለ እና ነጻነት መጎናጸፍ ተፈጥሮአዊ እና መንፈሳዊ ባህሪ ነው ብሎ የሚያስብ ነው።

Related stories   መሠረታዊ የኮምፒውተር ደህንነት መጠበቂያ መንገዶች

2.ማህበራዊነቱ(sociability)

ምንም እንኳ ሌላው ማህበረሰብም የራሱ የሆነ ማህበራዊ መገለጫ ቢኖረውም አማራ የራሱ የግል ማህተም ተደርጎ የሚገለጽበት ነገር ቢኖር ሲበዛ ማህበራዊ ፍጡር መሆኑ ነው። አማራ በጋርዮሽ አብሮ መኖርን ባህሉ ያደረገ ህዝብ ነው። አማራ ከአምላኩ ጋር ያለው ግንኙነት ብቻ ሳይሆን አማራ ከአማራው፤ አማራው ከሌላው ህዝብ እንዲሁም አማራ ከአለም ህዝብ ጋር ያለው ግንኙነት ከግለሰባዊ ይልቅ ማህበራዊ መስተጋብሮ ያይላል። ከጎሳዊነት ይልቅ ጋርዮሽን ወይንም የአብሮነት መስተጋብርን ቅድሚያ ይሰጣል። አብሮነት ለአማራ ተፈጥሯዊ ፍላጎት/human need/ ተደርጎ የሚወሰድ መለያ ባህሪው ነው። አማራ ከራሱ ይልቅ ወደ ውጭ የሚመለከት፤ ሁሉን አቀፍ፤ አድማሱ ሰፊ የሆነ የመተዳደሪያ እሴቶች ስላሉት ራሱ እንኳ ቢጎዳ ሌሎች እንዳይጎዱ በሚል ይሉኝታን፤ ውለታን፤ ህገ-አክብሮትን የሚያስቀድም ብሄር ነው። አማራ ማንነቱን የሚተረጉመው በብቸኝነቱ ሳይሆን ከሌላ ጋር አብሮ በመኖር ላይ በመመስረት ነው።

Related stories   መሠረታዊ የኮምፒውተር ደህንነት መጠበቂያ መንገዶች

ይሉኝታው የሚመነጨው ከመንፈሳዊነቱ ላይ ሲሆን ከራሱ ይልቅ ለሌሎች ቅድሚያ በመስጠት ይገለጻል። ሌላው ምን ይለኛል፤ ሌላው ምን ያስባል ፤ሌላው ምን ይሰማዋል ብሎ የሚጨነቅ ህዝብ ነው። ይህንን ባደርግ፤ ይህንን ብናገር፤ ይህንን ብሰጥ እና በዚህ ብኖር ሌሎች ምን ይሉ ይሆን ብሎ ከራሱ ደህንነት፤ ጥቅም እና ስሜት ይልቅ ስለሌሎች የሚጨነቅ ነው። በዚህም የተነሳ ሌሎችን ማህበረሰቦችን የሚጠሉ/xenophobic/ ያሉ ሲሆን አማራ በተቃራኒው ደግሞ ሌሎችን የሚወድ /xenophilia/ ማህበራዊ ፍጡር ነው። ይህ በጋራ አብሮ የመኖር ዝንባሌው ከሌሎች ማህበረሰቦች ጋር ባለው ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ግንኙነቱ ላይ የስኬትም የውድቀትም መንስኤ ሲሆን ይታያል።

ነገር ግን ማህበራዊነቱ ጊዜ፤ ቦታ እና ሁኔታን ጠብቆ ካልሆነ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ይሉኝታንና ውለታን የሚገነዘብ ዘመናዊ ማህበረሰብ ከተገነባ እኒህ እሴቶች አማራ ነጻ ህዝብ፤ በራሱ የሚተማመን እና ታላቅ ህዝብ እንዲሆን ያደርጉታል። ሌሎች ይህንን መልካም ባህሪውን ደግሞ የሚበዘብዙት ከሆነ ጉዳቱም ያን ያክል ነው። እናም ማህበራዊነቱ ለውደቀቱም ለስኬቱም ምክንያት ሊሆን የሚችል በሁለት በኩል የተሳለ ስለት ስለሆነ ልዩ ጥንቃቄን ይሻል።

3. ጀግንነት ወይንም አርበኝነት/bravery or heroism/

ጀግንነት ወይንም አርበኝነት የአማራ ልዩ ጥልቅ ባህሪው ነው። ይህ ባህሪው ዝም ብሎ ለማስመሰል የተፈጠረ ወይንም ዛሬ የተፈበረከ ሳይሆን ዘመናትን ተሻግሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ስነልቦናዊ ስሪቱ እና ጥንካሬው ነው። በክርክር፤ ሙግት ፤ እንካስላንቲያ እና እንቆቅልሽ አይነት ሰነቃላዊ ትውፊቶች ላይ የሚንጸባረቁ ገጸ ባህሪያት እና አባባሎች ላይ የጀግንነት ምሳሌዎች በብዛት የሚቀርቡት ጀግንነት የአማራ ህዝብ ስነልቦናዊ ስሪት በመሆኑ ነው። አማራ ልበ ሙሉ ነው። በራሱ የሚተማመን እና ሰውን የሚያምን ነው። ይህ ደግሞ ከውስጥ በሚወጣ ጀግንነት እና ፍጹም አርበኝነት የሚገለጽ ሲሆን ‘እኔ ነጻ ህዝብ ነኝ ማንም አያዝዘኝም’ ብሎ እንዲያስብ የሚያደርገው መልካም እሴቱ ነው። ጀብደኝነቱን መግለጹ፤ የራሱ በሆኑ ሃብቶች መመካቱ ፤ ለሚያምንበት እና ለጋራ ለሆነ ነገር ራሱን አሳልፎ መስዋእት የሚያደርግ መሆኑ የአርበኝነት እና አልበገር ባይነት ስነልቦናው መገለጫዎች ናቸው።

Related stories   መሠረታዊ የኮምፒውተር ደህንነት መጠበቂያ መንገዶች

ምፅዓተ-አማራ አሁን ነዉ – ከሚለው የፌስ ቡክ ገጽ የተወሰደ

ይቀጥላል…

ዝግጅት ክፍሉ- ይህንን ጽሁፍ ያተምነው ከላይ የተጠቀሰው ምንጭ ተጠቅሶልን በተላከልን መሰረት ነው። ” ስለሌሎቹ ማን ይንገረን? ስንል ጠይቀናል። ቀጣዩን የ”አማራ ማን ነው” ጽሁፍ ሲላክልን እናትማለን። መጨረሻችን ውርዶ ዝር ውስጥ መቀርቀሩ ግን አሳዛኝ ጉዳይ ነው!!

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0