“Our true nationality is mankind.”H.G.

ስብሃት ነጋ ኢህአዴግ ውስጥ ያለው ሙስና በሚገባ እርምጃ ካልተወሰደበት ‘አገር ያፈርሳል’ አሉ

አቶ ስብሃት ነጋ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ችግሮች ካልተፈቱና ቶሎ መላ ካልተፈለገላቸው አገሪቱ ወደ መፍረስ እንደመትሄድ አመልክተዋል። ብሄራዊ መግባባት መሬት ላይ በውል የሚታይ ጉዳይ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ስብሃት፣ ከዚህ አኳያ አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት በትንሹ ሁለት ዓመት ጊዜ እንደሚውስድ ጠቁመዋል። ምን አልባት የምርጫ ጊዜ ወደ ማራዘም ሊያመራ ይሆን?
የስርዓቱ አደአጋ ያሉትን ሙስና አስመልክቶ “… ከማን እንደሚጀምር ባላውቅም ኢህአዴግ ያጠፋውን የሚጠይቅበት፣ ተቻችሎ መሄድን የሚያቆምበት ውሳኔ ላይ መድረሱን አውቃለሁ፤ ኢህአዴግ ይሄንን በምሬት እንደሚሄድበትም እረዳለሁ፤ ካልሄደበት ደግሞ ችግሩ ይቀጥላል፤ አገርም ይፈርሳል ነው ያሉት…” ሙሉ ዜናው እንዲህ ይነበባል።
– የኢህአዴግ ጉባኤ አካሄዱ ተቻችሎ የማለፍ፣ ህዝባዊነት የተሸረሸረበትና ነገሮችን አስቀድሞ ያለማየት ችግር ያለበት ነው
የኢህአዴግ ጉባኤ አሰራሩ የብሄራዊ ድርጅቶችን ወቅታዊና ትክክለኛ አቋም የሚያሳይ ነው ብለው እንደማያምኑና መፈተሽ እንዳለበት አንጋፋው የኢህአዴግ ታጋይ/የህወሓት መስራች/ አቶ ስብሃት ነጋ ተናገሩ፡፡ ኢህአዴግ ባመነው ልክ ሙሰኞችን ካልከሰሰ አገሪቷ ወደ ብተና ማምራቷ አይቀርም ብለዋል፡፡
አቶ ስብሃት ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ብቻ በሰጡት ቃለ መጠይቅ እንደተናገሩት፤ የኢህአዴግ ጉባኤ አካሄዱ ተቻችሎ የማለፍ፣ ህዝባዊነት የተሸረሸረበትና ነገሮችን አስቀድሞ ያለማየት ችግር ያለበት በመሆኑ አካሄዱ በጥልቀት መፈተሽ አለበት የሚል እምነት አላቸው፡፡
እንደ አቶ ስብሀት ገለጻም፤ በጉባኤው ዋዜማ ህዝቡና አባሉ በአጀንዳዎቹ ላይ የሚወያይበት፣ ጉባኤተኛው አመራሩን በጥልቀት የሚያውቅበት፣ የአስር እና ሃያ አመት ፖሊሲና ስትራቴጂ የሚወጣበትና አርቆ የሚያይ ጉባኤ ቢሆን ምኞታቸው ነው፡፡ ወደፊትም የዚህን አይነት አካሄድ ይከተላል የሚል ግምት አላቸው፡፡
በጉባኤው ላይ ብሄራዊ ድርጅቶቹ ያሉበትን ትክክለኛ ገፅታ አያቀርቡም፤ ቢያቀርቡ ኖሮማ 10ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ በተካሄደ በወራት ውስጥ በአማራም ይሁን በኦሮሚያ የተከሰተው ችግር ባልተፈጠረ ነበር በሚል ትችት የሚያቀርቡ አካላት አሉ፤ ተብለው የተጠየቁት አቶ ስብሃት በምላሻቸው፤ “የእኔም ድምዳሜ እንደዚያ ነው፤ ጉባኤተኛው ያለበትን ችግር አምኖ የሚመጣና ጉባኤውን መደምደሚያ ማድረግ ነው ያለበት፡፡ እያንዳንዱ ድርጅት በራሱ በሚያካሂደው ጉባኤ ላይም እንደ ኢትዮጵያ አንድ ላይ ለመቀጠል የሚያስቸግር የአመለካከት ችግር አለብን ብሎ ያለ ምህረት ተገማግሞ ሲያበቃ ነው ወደ ድርጅቱ አጠቃላይ ጉባኤ መምጣት ያለበት፡፡ ከዚህ አንጻር ያለፉት ጉባኤዎችም መገምገም አለባቸው” ብለዋል፡፡
አገሪቷ የገባችበት ወቅታዊ ችግርን በተመለከተም አቶ ስብሃት በሰጡት ማብራሪያ፤ አሁን እየታየ ያለው ችግር መንስኤው ከ15 አመት በፊት በተካሄደው ተሀድሶ አሁን ባለው ልክ ችግሮች በጥልቀት አለመፈተሻቸው፣ እጥረቶችንም አደባባይ በግልጽ አለማውጣትና ተቻችሎ የመሄድ ችግሮች ናቸው ብለዋል፡፡ ጠባብነትና ትምክህት የስርዓቱ አደጋ እንደሆኑ ከአመታት በፊት ቢለዩም በትኩረት ስላልተሰራባቸው ለተፈጠረው ሁከት ተጨማሪ ምክንያት ሆነዋል፡፡ አሁን በጥልቀት መታደስ የሚለው መፍትሄም አዋጅ ሳይሆን ሂደት በመሆኑ በዚህ ጊዜ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደማይቀመጥ ገልጸዋል፡፡
ኢህአዴግ ችግሮቹን አንድ ሁለት ብሎ ለይቶ አስቀምጧል፤ እስካሁን እግረ መንገድ ችግሮቹን ሲጠቅስ ቆይቷል እንጂ እንደ አሁኑ በጥልቀት አልለየም ነበር፡፡ በጥልቀት መታደስም ችግሩን በጥልቀት ከመረዳት ይጀምራል፡፡ የተለዩትን ችግሮችን ሳንፈታም አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበረሰብ መፍጠር አይቻልም፡፡ መፍትሄው ጊዜ እንደሚፈልግ ህዝቡ መረዳትና መታገስ አለበት፤ ኢህአዴግም መፍጠንና መስራት ይኖርበታል፡፡ ይሄ ችግር በአንድ አመትና ሁለት አመት አይፈታም ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ ለገባበት ችግር ያስቀመጠው መፍትሄ በጥልቀት መታደስ የሚልና እስከ ካቢኔን መልሶ ማዋቀር የደረሰ እርምጃ ትክክለኛ መፍትሄ ይሆናል ብለው ያምናሉ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ስብሀት፤ “ሰው ማስቀመጥ በራሱ ለውጥ አያመጣም፤ ማስቀመጥና በተቋሙ ተጠያቂ ማድረግ ከተቻለ ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ ለውጡ ተቋማዊ ሆኖ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበት ስርዓት ፈጥረው ይሄዳሉ ወይ? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ መፍትሄው ተሿሚዎቹ ወደ ተቋማቸው ሄደው በሚሰሩት ስራ ላይ ይወሰናል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ብሄራዊ መግባባትን በተመለከተም አቶ ስብሀት፤ መግባባቱ ከአመለካከት እንደሚጀምር በመግለጽ በዚያ ደረጃ የተሰሩ ስራዎች ጠባብነትና ትምክህትን ማሸነፍ ያልቻሉ በመሆናቸው መግባባቱ ገና ቀሪ ስራ አለበት ብለዋል፡፡ የአንዱ ብሄር ባለሀብት በሌላው ብሄር አካባቢ ሄዶ ቢያለማ እንደ አካባቢው ባለሀብት እኩል ይታያል ወይ? አዎን ከሆነ ምላሹ ብሄራዊ መግባባት ተፈጥሯል ማለት እንችላለን፤ አያየውም ከሆነም አልተፈጠረም ነው ምላሹ፡፡ ምክንያቱም መግባባት በአየር ከላይ ሳይሆን በመሬት ላይ ነውና ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ህዝቡ የሚያነሳው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር የገለጹትን የሙስና ችግር በጅምላ “የሙስና ችግር አለ” ከማለት በዘለለ ሙሰኛው ማን እንደሆነ በግልጽ የሚነገርና የሚጠየቅ የለምና በዚህ ዙሪያ ምን አስተያየት አለዎት? ተብለው የተጠየቁት አቶ ስብሃት ሲመልሱ፤ የመንግስትን ስልጣን ለግል ጥቅም ማዋል ችግር አለ ተብሎ በግልጽ ተለይቷል፤ የተሀድሶውም አጀንዳ ሆኗል፤ ህዝቡም የሚጠብቀው ይሄንን ነው፤ ይሄ መቼና ከማን እንደሚጀምር ባላውቅም ኢህአዴግ ያጠፋውን የሚጠይቅበት፣ ተቻችሎ መሄድን የሚያቆምበት ውሳኔ ላይ መድረሱን አውቃለሁ፤ ኢህአዴግ ይሄንን በምሬት እንደሚሄድበትም እረዳለሁ፤ ካልሄደበት ደግሞ ችግሩ ይቀጥላል፤ አገርም ይፈርሳል ነው ያሉት፡፡
ኢህአዴግ በታሪኩ ካጋጠሙት ፈተናዎች ሁሉ አሁን የገባበት ችግር ከፍተኛውን ደረጃ እንደሚይዝ የተናገሩት አቶ ስብሃት፤ ከዚህ ችግር ለመውጣት ደግሞ ድርጅቱ በታሪኩ ጥልቅ በሆነ መልኩ ያሉበትን እጥረቶች ዘርዝሮ ማስቀመጡን ገልጸው፤ ያስቀመጣቸውን መፍትሄዎች አንድ ሁለት ብሎ ከፈጸማቸው በታሪኩ ከደረሰበትም በላይ ደረጃ መድረስና ይሄን አገርና ህዝብ ወደ ታላቅ ደረጃ ማድረስ ይችላል ብለዋል፡፡
http://ethpress.gov.et/…/nat…/item/10652-2016-12-28-17-03-59

0Shares
0