ሚዲያ እንደ ሰዎች አረዳድ የሚሰጠው ደረጃና አቅም የተለያየ ቢሆንም ያለ አንዳች ማመንታት “ኃይል” ወይም ኃይል ያላቸው መገልገያ መሆኑ ጥርጥር የለውም። ሁሉም ሚዲያ “የሕዝብ” መሆናቸውን ቢገልጹም ፍጹም ነጻና ገለልተኛ ሆነው አይታዩም። ወደ አገራችን ሚዲያ ስንመጣ በውጭ ያሉትም ሆኑ በአገር ቤት፣ የግል የሚባሉትም ሆነ የመንግሥት የራሳቸው ወገንተኛነትና መንሸዋረር ይታይባቸዋል። ይህ እውነት ባደጉት አገሮችም ቢሆን ረቀቅ ባለ መልኩ የሚዘወተር ነው። ከሁሉም የሚቀፈው ግን ፍጹም ጭፍንነት ነው። ምክንያቱም በጭፍንነት ውስጥ አንድ ሰው ከተነገረውና ከተሞላው በቀር አሻግሮ ማየት አይችልምና ነው።

“መቃብር ቆፋሪው እና የሬሳ ሳጥን ሻጩ የሚለው ተውኔት የተሰረቀ ነው” የማለት አዝማሚያ በሚስተዋልበት ስሜት የተጀመረ ቃለ ምልልስ። ሲጠናቀቅም የተለያዩ ጉዳዮች ውስጥ ትገባለህ “የባከንክ ነህ” በሚል “ስድብ” ነው። የግል ዝንባሌዎችን (ሆቢ) እንኳን ማከናወን የተነፈገ የመሰለበት ቃለ ምልልስ!

ጠያቂ ቴዎድሮስ ጸጋዬ፣ የ“ርዕዮት” አዘጋጅ ነው። ቃለ ምልልሱ የቀረበውም በebs ሲሆን በዩትዩብ ላይ የታተመው  26 ዲሰምበር 2016 ነው። ተጠያቂ ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ሲሆኑ መነሻ ጉዳዩም በቅርቡ ለንባብ ያበቁትና ሰፊ መነጋገሪያ የሆነው “የኦሮሞና አማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” የሚለው መጽሃፋቸው ነው።

ቃለመጠየቁ መከራከሪያ የሚሆኑ ሃሳቦችን የሚያነሳ ቢሆንም የተጠያቂውን የመናገር መብት፣ የመከራከር ስልጣን፣ የማስረዳት ጊዜ የነፈገ ነበር። ከሁሉም በላይ ዶ/ር ፍቅሬን ለማሳጣት፣ ለማንቋሸሽ፣ ስራዎቻቸው ላይ ጥያቄ ለማስነሳትና፣ እጀ ሰባራ አድርጎ ለማሳየት ሆን ተብሎ የታለመ ይመስላል። ጠያቂው ከሌሎች የሙያ ባለቤቶች ጋር ያደረገውን ዓይነት ቃለምልልስ ለፍቅሬ ቶሎሣ መንፈጉ ትልቅ ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል። ማስረጃውን አንባቢ ተመልክቶ እንዲፈርድ እተወዋለሁ።

አንድን ሰው ሚዲያ ላይ አቅርቦ “አሁን ይህ ግጥም ነው፤ አሁን ይህ ሃሳብ ነው፣ አሁን እንደዚህ ለማለት መማር ያስፈልጋል፣ ብኩንነት…” እያለ መዛለፍ አግባብ መስሎ ስላልታየኝ አጭር አስተያየት ለማስፈር ወደድኩ።

በፌስቡክ በቀላሉ የሚጻፉ አነስተኛ ጉዳዮች ሳይቀሩ ተለቅመው ለስድብና ሰውን አሳንሶ ለማሳየት የቀረበበት ይህ ቃለ ምልልስ አማራና ኦሮሞን ለማባላት የፈሰሰውን “መዋዕለ ነዋይ” በሙሉ ገደል ውስጥ የሚከት ሆኖ መገኘቱ የፈጠረው ስሜት ይሆናል የሚል ግምት አለኝ። ለሁሉም ግን በአንድ ጉዳይ ጭፍን ሆኖ አንድን ሰው፣ ለአንድ ስውር ግን ግልጽ ለሆነ ዓላማ ዋጋ ቢስ አድርጎ ለማሳየት መሞከር “ጎዶሎ” አስተሳሰብ ከመሆን የዘለለ አይሆንም።

ዶ/ር ፍቅሬ መናገር ተከልክለው፣ እየተሰደቡ ለአፍታ እንኳን ኃይለቃል ሳያሰሙ አመስግነው ቢሮውን ለቀው መውጣታቸው የሚያስመሰግናቸው ቢሆንም ለአድማጭ ይገባው ዘንድ መልዕክት ማስተላለፍ አለመቻላቸው አግባብ ሆኖ አላገኘሁትም። ይህንን ስል ግን ገና ለገና ተሰዱ ተብሎ እርሳቸውን በጭፍን መደገፍ ይገባል ማለቴ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መጽሃፋቸው ላይ የሚነሱትን የጭብጥ ወቀሳዎች አስመልክቶ በራሳቸው ፈቃደኛነት ማጠናከሪያ ቢያቀርቡ ደግ ነው እላለሁ። ሰውን መዝለፍ፣ ማሳጣትና ገና ለገና ሚዲያ አለኝ በሚል ስርዓት መልቀቅ ብዙ ውሎ አድሮ ከራስ ህሊና ጋር ያጋጫልና ሚዛን ቢጠበቅ መልካም ነው ለማለት እወዳለሁ።

ጠንካራ ዝግጅት ማቅረብ የሚቻለው ሰውን በመዛለፍ፣ በማቆሸሽ ሳይሆን በጨዋነት ሊሆን ግድ ነው!! ይህ ካልሆነ የህሊና መጨለምን ያመጣልና ከማይታየው የጽልመት በሽታ መውጣት አስፈላጊ ነው። ቃለ መጠይቁን በማዳመጥ አንባቢያን ለቡናዊ ምስክርነት እንድትሰጡ እማጸናለሁ።

ግርማ መርሃጽዮን ከስዊድን

 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *