ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

ስጋ የበላሁ ቀን እንዲህ ያደርገኛል…

Teym Tsigereda Gonfa

በመጀመሪያ አራት እግሮች ብቻ ላሉት አንድ በግ 2ሺህ ብር መከፈሉ ያናድደኛል…(ለነገሩ አንዳንዶች ሁለት እግሮች ብቻ ላሉት አንድ ሱሪም 2ሺህ ብር ይከፍላሉ) ቀጥሎም አንድ ኪሎ ግራም ስጋ 250 ብር መሆኑ ይጎረብጠኛል… በአይብ በቆጮ እና በጎመን ለተደጋገፈ አንድ ጣባ ክትፎ 300 ብር መውጣቱ ይኮሰኩሰኛል…
በዋናነት ግን ስጋ አልወድም፡፡ እደግመዋለሁ ስጋ አልወድም፡፡ አያስደስተኝም፡፡ አያዝናናኝም፡፡ አይመቸኝም፡፡ አይስማማኝም፡፡ ብዙ ነገር – ኝም፡፡ አንዱ ጉርሻ ጥብስ ስጋ ኮብል ስቶን እንደመዋጥ ሆኖብኝ ጨጓራዬ መሃል ይገላበጥብኛል፡፡ ወላ አንቦ ውሃ ወላ ሌመን የማያነቃንቀው ምርጊት ሆኖ የገዛ ሆዴ ይከብደኛል፡፡ ድማሚት ጎርሼ እንደ ካባ ድንጋይ መበተን ሁሉ ያምረኛል፡፡ ዱለትማ ጨጓራን በጨጓራ ለመፍጨት መሞከር ድንጋይ በድንጋይ ለማድቀቅ እንደመሞከር የቀን ስራ ይመስለኛል፡፡ አካሌ ይደነዝዝብኛል፡፡ መንፈሴ ይፈዝብኛል፡፡ አዕምሮዬ ያዘግምብኛል፡፡ የአስተሳሰብ ደረጃዬ IQ ይቀንስብኛል፡፡ ለወትሮው በቀላሉ የማሰላው ሂሳብ(ከስራዬ ጋር በተገናኘ) ኳንተም ፊዚክስ ይሆንብኛል፡፡ እንኳን መፅሐፍ አንብቦ ለመረዳት ተራ የንግድ ቤት ስሞችን ማንበብ ያዳግተኛል፡፡ እንኳን ፅፎ ለማስረዳት ‘አበበ በሶ በላ’ የሚል ቀላል አረፍተነገር መመስረት ያዳግተኛል፡፡እንቅልፍ እንቅልፍ ይለኛል …ብዙ ነገር- ኛል… ስጋ የበላሁ ቀን እንዲህ ያደርገኛል…
.
የሆነ… ደም ፈሶ… የሆነ ፍጡር ነፍስ ያለ ሐጢአቱ ተቀጥፎ ቆዳው ተገፍፎ መምጣቱን ሳውቅ አንዳች የጥፋተኝነት ስሜት ሰቅዞ ይይዘኛል… የምበላው ስጋ መጠኑ በጨመረ ቁጥርም የጥፋተኝነት ስሜቱ ገዝፎ ይሰማኛል… ከጥጋብ በኋላ ራሴን እጠላለሁ … የማቴዎስ ወንጌል 15 ላይ “ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፍ የሚገባ አይደለም፥ ከአፍ የሚወጣው ግን ሰውን የሚያረክሰው ይህ ነው…”
በተባለው ቃል ባምንም ከስጋ ገበታ በኋላ ተንበርክኬ ንሰሃ መግባት ሁሉ ያምረኛል፡፡ lol
.
ይህ በአማረኛ ቋንቋ ተፅፎ ማየቱን ያላመነ ድፍን ኢትዮጵያዊ ስጋ ይወዳል የሚል ‘ጠቅልል’ አይጠፋም መቼም…እነሆ እኔ! ከስጋ ቁርጥ ቲማቲም ቁርጥ…ከስጋ ክትፎ ጎመን ክትፎ …ከስጋ ቅቅል ድንች ቅቅል እመርጣለሁ (ስኳር ድንችማ ቢገኝ ፓ!) አትክልትና ፍራፍሬ … አዝዕርት እና ጥራጥሬ…ከስጋ የተሻለ የጤና ጠቀሜታ እንዳላቸው የ’ፉድ’ እና ‘ኒውትሪሽን’ ባለሙያዎች በጥናታቸው ደጋግመው ያረጋገጡት ጉዳይ ነው…አዎ አትክልት ስበላ እነቃቃለሁ…አካሌ ይበለረታል አእምሮዬ ይሰላል ያኔ ብሩህነቴ ጨምሮ አልበርት አንስታይን አጎቴ ሁሉ ይመስለኛል…
ይሁንና የሐብትም የምቾትም የባህልም መገለጫ ሆኖበት ወገኔ ምክር አልሰማ ብሎ ስጋን የሙጢኝ ብሏል…
‘በፍየል ዘመን በግ አትሁን’ የሚል የታክሲ ላይ ጥቅስ ሲያይ የፍየል ጥብስ ትዝ ይለዋል… ‘እኔ የበጎች እረኛ ነኝ’ ተብሎ ቤተክሲያን ሲሰበክ ‘ታድሎ ዱለት ይበላል’ ብሎ ይጎመዣል…
.
በሁለተኛ ደረጃ ስጋ መብላት ሙሉ ትኩረት ይፈልጋል…ስጋ እየቆረጠም ሆነ እየጎረሰ ያለ ሰው ሌላ ምንም ነገር መስራት አይችልም ትንሽ ሳት ብሎት ሐሳብ ከገባው አፍንጫውን በስል ቢላ ያጭዳል ይህ አለመሆኑም እንደ የሐበሻ ጀብዱ ፀሐፊ ዘወትር ያስደንቀኛል…ወይም ለቁርጥ የሰነዘረው ስለት አቅጣጫውን ስቶ የጣቱን ደም ከበጉ ደም ጋር ይደባልቃል…(በድምፅ አልባ መሳሪያ የተሰራ አድቬንቸር ፊልም ነው እኮ የሚመስለው) የሚበላው ክትፎ እንኳ ቢሆን ምላሱን መንከሱ አይቀርም … አትክልት ፍራፍሬና ጥራጥሬ ተመጋቢ ግን መሰል ስጋት የለበትም… ለምሳሌ ይኸንን በቀኝ እጄ ስፅፍላችሁ በግራ እጄ ሙዝ እየገመጥኩ ነው
… የገብስ እና የሽንብራ ቆሎ ከተገኘም መዝገን እችላለሁ… ጭማቂ ከመጣልኝም በስትሮ እጠጣለሁ…ይህንን በስጋ ሞክሩት የማይሆን ነገር ነው …ቀድሞ ነገር ስጋ አይዘገን አይገመጥ አይጠጣ…መቁረጥ እና ማኘክ ብቻ…ማኘክ ደሞ እንዴት አሰልቺ ነገር ነው? ቀኑን ሙሉ መስቲካ የሚያኝክ ሰው ይገርመኛል አንዳንድ ቀን ሆዴ እንደ ጃኬት ዚፕ በኖረውና ምግቡን ራሱ ከሰሃን ቀጥታ ወደ ጨጓራዬ መላክ ብችል ብዬ እመኛለሁ፡፡ (From table to bowel) ማኘክ ይሰለቻል፡፡ ደግነቱ ጭማቂ ምሳ ይሆናል …ሂደቱም ‘ፍሮም ስትሮ ቱ ጉሮሮ’ (ጥርሴ ያለ ነገር አልነጣም)ስጋ የሚበላ ሰው ግን ወደደም ጠላ ማኘክና ማላመጥ አለበት…
.
አጥንት መጋጥ ደግሞ በጣም የሚያስቀኝ ተግባር ነው፡፡ አንድ አጥንት የሚግጥን ሰው እስቲ ትኩር ብላችሁ ተመልከቱት …ከፊቱ መጨማደድ… ከጥርሱ መሾል… ከዓይኑ መፍጠጥ… የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰው ዓይናችሁ እያየ ወደ ‘ሀንተር እና ጋዘረር’ ሰውነት ይቀየራል (ዝግመተ ለውጥ ይላችኀል) ከዛም ‘አጥንቱን እንደ ጨረሰ ይዞርብኝ ይሆን? ከእግሬ ይሆን ከእጄ የሚጀምረው?’ የሚል ስጋት ወጥሮ ይይዛችኋል … እኔማ “ሩጪ ሩጪ… አምልጪ አምልጪ…አንቺ ሴት ራስሽን አድኚ” የሚል ድምፅ ሁሉ ከውስጤ እሰማለሁ…እሱ አልበቃ ብሎት… ስጋውን ግጦ እንደጨረሰ ቀጥቅጦ መቅኔዋን ለመምጠጥ ዘነዘና ጨብጦ ድንጋይ ፍለጋ ሲያማትር…ሰው ውስጥ የተደበቀ አውሬነት ሲያንሰራራ ይታየኛል… ገዝቶ… አላምዶ … አስሮ…አርዶ…ገፍፎ…ቆራርጦ…ቀቅሎ…ጠብሶ…ግጦ የበላው ሳያንሰው አጥንት ሲቀጠቅጥ ሳይ…የትኛውም እንሰሳ የሚመገበው ሌላ እንሰሳ ላይ በዚህ ደረጃ አይጨክንምና “የሰው ልብ ከሁሉ ይልቅ ክፉ እጅግም ተንኮለኛ ነው” የሚለው ቃል ይበልጥ ግልፅ ይሆንልኛል…
.
የገናን በዓል ምክንያት በማድረግ ይህንን ፅሑፍ በክብር ስፓንሰር ያደረገላችሁን ኢትፍሩትን ከልብ አመሰግናለሁ!