ZAGGOLE – ዛጎል

“Our true nationality is mankind.”H.G.

የሰሞኑ የአቶ ሥብሐት ነጋ ንግግርና ሎሎች ጉዳዮች

በዚህ ሳምንት የአቶ ሥብሐት ነጋን ንግግርና ተያያዥ ክስተቶች እንዲሁም ሎሎች ሰሞኑን ትኩረት የተሰጣቸውን ጉዳዮች ስታዘብ ነበር፡፡ እንደ እውነቱ እኔን ብዙም ትኩረት የሰጡኝ ጉዳዮች ሆነው ሳይሆን እንደውም ላነሳቸው የፈለኩት ምን አልባት እኔ ያየሁበትን እይታ ሎሎችም ይጋሩት እንደሆነና ጉዳዮቹም የሳቧቸው እውን ጉዳዮቹ ትኩረት የሚሰጡ ሆነው ነው ወይስ የአተያያችን ነገር ይሄን ያህል ተራርቆ የሚለውን እግረመንገዴን ሁላችንም ራሳችንን እንድንታዘብ ወይም አመክንዮዋዊ መሆናችንን ረጋ ብለን እንድናስብ ነው፡፡ እኔ እንደነገርኳችሁ ዋናዎቹ ጉዳዮች ሳይሆኑ እነሱን ተከትሎ የሚመጡት እይታዎች ናቸው ትኩረቴን የሳቡት፡፡ እንደሚከተሉት አቅርቤያቸዋለሁ ተከተሉኝ፡፡

የአቶሥብሐት ነጋና ንግግርና የሌሎች አስተያየት፡-

ብዙዎቻችን ሥብሐት ነጋን እንዴት እንደምንረዳቸው አላውቅም፡፡ ከዛም በላይ እሳቸው የመሩትን እስከዛሬም የሚመሩትን ወያኔን ባህሪና ማንነት በውል እያስተዋልነው እንደሆነና እንዳልሆነም አላውቅም፡፡ እኔ የምናገረው የራሴን አረዳድ በእርግጥም ከማቃቸው ጉዳዮች ጋር በማዛመድ ነው፡፡ ሥብሐት ነጋ ሕወሐት የተባለውን ቡድን በዋናነት የሚመሩት ሰው ናቸው በዬ ነው የማምነው፡፡ሟቹ መለስ ነገሮችን አራጊ ፈጣሪ ተደርገው ይታሰቡ ነበር፡፡ በእርግጥም መለስ ቡዙ ነገር ላይ ሥልጣን ነበራቸው፡፡ ያም ሆኖ የወያኔን ቡድን ሕልውናና ከቡድኑ ጋር የተያያዙ ማናቸውም ጉዳዮች ያለ ሥብሐት እውቅናና ይሁንታ የሚደረጉ አይመስለኝም፡፡ እሳቸው ስለቡድናቸው ከማንም በላይ ያውቁታል፡፡ በትልቁ ኢሕአዴግ ውስጥ ደግሞ ሁሉንም አራጊ ፈጣሪው ሕወሐት የተባለው ቡድን እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይሄው ቡድን ላለፉት 25 ዓመታት አገሪቱ ውስጥ ያለምንም ገደብና ሥርዓት የፈለገውን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥና እስከዛሬም  ስብሀት ዋነኛው ተዋናይ ናቸው፡፡ ብዙዎች እንደሚሉት ግን ስብሐት እንደፈለጋቸው በዚያች አገር የሚያወሩ የፈለጋቸውን የሚናገሩ ሰው እንደሆኑ አላውቅም፡፡ የሰሞኑም ንግግራቸው እንደፈለጋቸው ሳይሆን በጣም አስልተውና ምን መናገር እንዳለባቸው አስበውበት ነው፡፡ ስብሐት እንደውም ንግግር ውስጥም ሆነ ሚዲያ ላይ የሚታወቁ ሰው አደሉም፡፡ ይልቁንም ሥብሐት እንደፈለጋቸው መናገር ሳይሆን እንደፈለጉት ሁሉንም የሚዘውሩ ዘመናቸውን ሁሉ ከውስጥ ሆነው ዋናውን የወያኔን ቡድን ዕቅድና መደረግ የሚገባውን ትዕዛዝ የሚያስተላልፉ ሰው ናቸው ባይ ነኝ፡፡

የሰሞኑን ንግግራቸውን አስመልክቶ ብዙ ሌሎች የየራሳቸውን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ እኔን ግን ከሁሉም የታዘብኩት በኢሳት የተሰጠውን ሁለት የኢሳት አባላት እርስ በእርስ የተወያዩበትን ነው (ሥም አልጠራም ያ ዓላማዬ አደለም)፡፡ ትዝብቴ ደግሞ የሁለቱ የስብሀትን ንግግር ለመተንተን ከቀረቡት ግለሰቦች ጉዳዩን ከገለልተኝነት አንጻር ሙያዊ በሆነ መልኩ ብቻ ከመተንተን አቅማቸውና ከአላቸው እውቀት ይጀምራል፡፡ ከተንታኞቹ አንዱ ውስጥ አዋቂ ነኝ ስለሚልም ጭራሽ ሰዎችን በማያውቀውና ባልተረዳው ነገር እያሳት እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡ ተንታኞቹ ከስብሐት ነግግር ሕጋዊነት ይጀምራሉ፡፡ በእነሱ አመለካከት የሥብሐት ንግግር ሕገጋዊ አደለም፡፡ እኔ ሙሉውን የስብሐትን ንግግር አላነበብኩትም፡፡ በእርግጥም ተንታኞቹም አላነበቡትም ገና ጋዜጣ ላይ የወጣን የንግግራቸውን ይዘት የሚያመለክቱ አጫጭር መልክቶችን ተንተርሰው ነው ትንታኔ ላይ የዘለቁት፡፡ ተንታኞቹ የስብሐትን ንግግር ሕጋዊነቱን ያጣጣሉት ጠቅላይ ሚኒስቴሩም ይሁኑ ሌላ አሁን ሥልጣን ላይ ያለ ሰው የማይናገረውን እሳቸው በማን አለብኝነት ተናገሩት የሚል ነው፡፡ በእኔ አረዳድ ደግሞ ሥብሐት የቱንም ያህል ወያኔንም ይሁን ዋናውን ቡድን በዋነኝነት የሚያሾሩት ዋናው ሰው ቢሆኑም በዚህ ንግግራቸው ራሳቸውን ያቀረቡት እንደማንኛውም በቡድኑ እንደተሳተፈና በቡድኑ ከነበረው ልምድ አንጻር የግል አስተያየታቸውን እንጂ የቡድኑን አቋም በማንጸባረቅ አደለም፡፡ ይህ ደግሞ ከ”ሕጋዊነት” አንጻር አንድም ሥሕተት አይታይበትም፡፡ እንደውም ጋዜጠኛው የሚያውቁት ሚስጢር ካለ እያለ ሲጠይቅ የሥብሐት መልስ የማውቀው ሚስጢር የለም የሚመስለኝን ነው የምለው እንጂ እያሉ ሲያረጋግጡ እንሰማቸዋለን፡፡ አጠቃላይ የስብሐት ነጋን አስተያየት ቀደም ብለው የግላቸውን አስተያየት ከሰጡት ከእነ ጀነራል ጻድቃንን አስተያየት የተለየ ሆኖ “ሕጋዊነት” የሌለው የሚያስብል ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ በእርግጥም ሥብሐት የግል አስተያየታቸውን መስጠት መብታቸው ነው፡፡ ንግግራቸውም በየትኛውም አንጻር በሕግ የሚያስጠይቅም አደለም፡፡ ይህ አይነት አስተያየት የትኛውም የቡድኑ አባል ሊሰጠው የሚችል ጉዳይ ነው፡፡ እዚህ ላይ ስብሐት የተለየ መብትና እንደፈለጉ ተናጋሪነታቸውን የሚያሳይ አንዳችም ነገር የለም፡፡  በእኔ ግንዛቤ ተንታኞቹ ያሉበት አቅም በገለልተኝነት ትክክለኛ መረጃውን ለሕዝብ ማቅረብ የቻለ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ ከዛም ባለፈ የመገናኛ ብዙሀንን ሥርዓት ደረጃ ያልጠበቁ ቃላቶችን ይናገሩ እንደነበር ታዝቤያለሁ፡፡ ሥብሐትን በግል ያዋረዱ ለመምሰል እንደሆነም አላውቅም ሌላ ሥብሐት የ84 ዓመት ሽማግሌ እንደሆኑ እየጠቀሱ አንተ ብሎ መናገር በመገናኛ ብዙሀን አጠቃቀም ደረጃውን የጠበቀ አደለም ባይ ነኝ፡፡

ሌላው ተወያዮቹ ምን ያህል እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ለመተንተን ሙያዊ ብቃት አላቸው የሚለው አንዱ ጥያቄ ነው፡፡ አንድኛው ወያኔ በሚመራው የኢሕአዴግ ቡድን ውስጥ አልፌያለሁ በሚል ጭራሽ እያረጋገጠ የሚናገራቸው ጉዳዮች በሕዝብ ዘንድ ሌላ ውዥንብር እንደሚፈጥሩም እሰጋለሁ፡፡ በእኔ ግንዛቤ ግን እንኳን ቡድኑን ለማሟሟቅ በቲፎዞነት የተሳተፈ ቀርቶ ከመሥራቾቹም ብዙዎቹ ስብሐት የሚዘውረውን ሕወሐትም ሆነ ዋናውን ቡድን አሰራር ብዙ ቦታ አልተረዱትም፡፡ አንዳንዶችም እራሳቸውን ሳያውቁ ለአደጋ ዳርገዋል፡፡ ከዚህ በተሻለ በፖለቲካና ተመሳሳይ ጉዳዮች በቂ እውቀት የላቸውን ከሙያቸው አንጻር ብቻ መተንትን የሚችሉ ግለሰቦች መጋበዝና ማወያየት ጠቀሜታው የጎላ ነበር፡፡ ይልቁንም የሥብሐትን ንግግር ሕጋዊነትና ሕጋዊ አለመሆን ሳይሆን ይህን ንግግር በዚህ ወቅት ለምን ተናገሩት የሚለውን የተሻለ ጭብት ማስያዝ በተቻለ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ስብሐት ከመቼውም በላይ ቡድናቸውን  የከፋ ተግዳሮት እንደገጠመው የተናገሩትን ንግግር ተንታኞቹ ሲያደንቁና እውንም ሕወሐት አደጋ ላይ ወድቋል የሚል ድምዳሜ  ሊያሲይዙ ይሞክራሉ፡፡ ይህ ሌላው አደገኛ ስህተት ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በእኔ ግንዛቤ ሥብሐት የወረወሯቸው ቃላት ሁሉ በጣም የታሰበባቸው አደገኛ ማዘናጊያ እንጂ ቡድኑን ከገጠመውን ፈተና ክብደት ጋር የተያያዘ አደለም፡፡ ፈተናው ቀላል ነው እያልኩ ሳይሆን ሥብሐት እንዚህ ቃላቶች የተናገሩት ሆን ብለው መዘናጋትን ለመፍጠር ነው፡፡ ከዚህ ሌላም ሥብሐት ወሳኝ ያሏቸውን ነጥቦች አንስተዋል፡፡ ለምሳሌ ስለብሔራዊ መግባባት፡፡ ለሥብሐት የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ከአገርና ሕዝቦች ደህንነት ጋር የተያያዘ አደለም፡፡ ለእሳቸው አሁን ባለው ሁኔታ እንደልብ እሳቸውና ቤተሰባቸው በየትኛውም ክልል እየሄደ የፈለጉትን ቢዝነስ ማካሄድ አለመቻሉ ነው ትልቁ ስጋታቸው፡፡ ጠባብነት፣ ትምክህት ሌላም ብዙ ጊዜ የሰማናቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከስብሐት አንደበት ግን እየወጡ ያሉት ቢዝነሳችንን እንደፈለግነው እንዳንሰራ ያደረጉን የሕዝብ ተቃውሞዎች በእነዚህ አመካኝተን እርምጃ መውሰድን ማጠንከር አለብን ነው፡፡ ሥብሐት ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር የተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ይሁን ሌሎች ከሕዝብ ጎን ያሉ ቡድኖችን ተሳትፎ አስፈላጊነት አይቀበሉም፡፡ እነሱ ከተሳተፉማ ምኑን እንደልብ ሆነ፡፡ ዕድል መሥጠት ፈጽሞ የለብንም የሚል ልዩ ሚስጢራዊ አቋም ነው፡፡ የኢሳቶቹ ተንታኞች የሌሎች ባለስልጣናትንም አስተያየት ከስብሐት ጋር እያያዙ ሊተቹ ሞክረዋል፡፡ ሳይገባቸው የሚናገሩ ነው የመሠለኝ፡፡ በረከትም ሆኑ፣ ደመቀ፣ ኃይለማሪያምም ቢሆኑ ይህን አይነት አስተያየት ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ በእርግጥ አስተያየቶቹ ከመሰጠታቸው በፊት ስብሐት ማወቅ ይኖርባቸው ይሆናል፡፡ ሥብሐትም ቢሆኑ ሊሰጡ ያሰቡትን አስተያየት በሌሎች አስገምግመው ታስቦበት እንደሆን እናስብ፡፡ የጻድቃን አስተያየት በደረጃ ከሥብሐት የራቀ አልነበረም፡፡ የአስተያየታቸውም አላማ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ጻድቃን ቀደም ብለው መጡ ሥብሐት ምን አልባትም የመጨረሻ አማራጭ ሆነው ለቡድናቸው ቀረቡ፡፡ የእነሱ ስጋት የአካበቱት ሐብት እንጂ አገርና ሕዝብ አደለም፡፡ ለዚህ አላማቸው ስንት ለወያኔ ቡድን ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያደረጉትን ብዙ የራሳቸውን ጓደኞች ሳይቀር  አረደዋል፡፡ ሥልጣን ከያዙ እንኳን በኋላ ቡድኑ  በሰበሰ በቃው የተባለለት ዘመን የሞተው የደህንነቱ ኃላፊ ክንፈ ገብረመድህን፣ በየመንና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ በነበረው የሐኒሽ ደሴቶች ውዝግብ ምክነያት ኢትዮጵያ ራሴን ችያለሁ የምትለውን ኤርትራን ከአሁን በኋላ መርዳት የለባትም ብሎ አቋም ይዞ የነበረው ኃይሎም አርዓ የሞቱባቸው ሂደቶች ላስተዋለ የእነ ሥብሐት ቡድን ለየትኛውም ከአገርና ሕዝብ ጋር በተያያዘ የሚያስብን አባል በዘላቂነት አይፈልግም፡፡ እነዚህ ለእነ ሥብሐትና መሰሎቻቸው የቡድኑን አላማ የሚያደናቅፉ ናቸው፡፡ ቡድኑም ይሄ ነው፡፡ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥም ኤርትራ ውስጥም መሪ ሚና ያለው የሥባሕትና ቤተሰባቸው (ኢሳያስን ጨምሮ) ቡድን ነው፡፡ ሻቢያና ወያኔ ልዩነት የላቸውም የምንለው ለዛ ነው፡፡ ያን ሁሉ የሕዝብ ልጅ የጨረሰውን ጦርነት ለዘላቂ ሕልውናቸው ድራማ እስከመስራት የሚደርስ ልዩ ሚስጢራዊ ትስስር እንዳላቸው ለብዙዎች አይገባንም፡፡ አሁን እያደረጉ ያሉት የተቻላቸውን ሁሉ አድርገው በሥልጣን መቆየት ካልሆነ ግን በተቻላቸው ሁሉ አገሪቱን መበታተን ነው፡፡ አገሪቱን እርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ከተው በዚህ አጋጣሚ ትግራይ ውስጥ የራሳቸውን መንግስት ለማስቀጠል አንዱ አማራጫቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ካልተበታተነች ትግራይ ላይ እነመሠርተዋለን ያሉትን የሥብሐትን መንግስት ማለመም አይቻልም፡፡ 25 ዓመት የተለፋው አሁንም አስተማማኝ ሆኖ ያላገኙት ይሄ ነው፡፡ ትንሽ ገፋ አድርገው ኢትዮጵያን በመበታተን ላይ መሥራት ነው አሁን ትግላቸው፡፡  የመከላከያውን ጨምሮ ሁሉንም የአገሪቱን ቁልፍ ቦታዎች እነሱ በሚያምኑዋቸው ትግሬዎች ሲያሲዙ ተመልካች ሆኖ የታለፈባቸው ዘመኖች ሳያንሱ አሁንም ሌላ ውዥንብር ውስጥ አገርንና ሕዝብን ለመክተት የዚህ ቡድን ተጨማሪ አቅም እየሆኑ ያሉት የተቃዋሚ ድርጅቶችና መገናኛ ብዙሐኖች እንደሆነ እናስተውል፡፡

በአጠቃላይ የሥብሐት ንግግር ሕጋዊነትና ሕጋዊ አለመሆን ጉዳይ ሳይሆን ከንግግሩ ጀርባ እየተሰሩ ያሉትን ሴራዎች ነው እኔ ልታዘብ የቻልኩት፡፡ ኢሳትም በራሳቸው ሊያውም ገለልተኛነት በሌለውና ሙያዊ ብቃቱም በሌላቸው ግለሰቦች ጉዳዮችን በተዛባ መልኩ ከሚተነትኑ ባለሙያዎችን ጋብዘው ቢያወያዩ እላለሁ፡፡

የዶ/ር ፍቅሬ ቶሎ(ላ)ሳ መጸሐፍና የቀረበበት ትችት፡፡

እኔ መጻሕፉን ስላላነበብኩት ምን ይዘት እንዳለው አላውቅም፡፡ ከደራሲውና ከተችዎቹ ከሰማሁት ውጭ፡፡ ለእኔ መጻፉ ይዟል የተባለው የኦሮሞና የአማራ የደም ትስስር ከታሪክ አንጻር ብቻም ሳይሆን አሁን ዛሬ ላይም የማየው እውነታ ስለሆነ ደራሲው እነዚህ ሕዝቦች በዘር አንድ ናቸው ማለታቸው የሚያስወቅሳቸው አይመስለኝም፡፡ ተቺዎቹ ያነሱት ነጥብ እውነት ነው አይደለም ሳይሆን ደራሲው በትንታኔያቸው የሰጧቸው የማጣቀሻ ዋቢዎች አሳማኝ አደሉም ወይም በቂ አደሉም የሚል ይመስለኛል፡፡ ይሄ እንግዲህ ተችዎቹ መጽሐፉን አንብበው ራሳቸው ከሚየውቁት የታሪክ እውነታ አንጻር በዋቢነት ሊወሰድ የሚችል መጻህፍ ለመሆን አቅም ያንሰዋል ነው፡፡ በእርግጥም ደራሲው ከታሪክ አንጻር ጽፌዋለሁ ከአሉ ከሚጠበቁባቸው ነገሮች አንዱ ለሚያነሷቸው ታሪካዊ ኩነታት በቂ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርባቸዋል ባይ ነኝ፡፡ ደራሲው በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለምልልስ እንደምሁር በተቻለ መጠን ማስረጃ ካልሆን ቢያንስ አመክንዮዋዊ (ሎጂካል) ማሳመኛ ከማቅረብ ይልቅ ስሜትን ቀስቃሽ የሚመስሉ የካህን፣ ካህን፣ የነብይ ነብይ፣ ዘሮች ነን ሲሉ አደምጬያለሁ፡፡ አባባላቸው መልካም ነው ማንም ያንን አይጠላም ግን እውነት ነው ወይ? አዎ ከአሉም መረጃውን አሁን ከአለውም ነበራዊ ሁኔታ ጋር አያይዘው ማቀረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በቃለምልልሱ እንደሰማኋቸው ያሉ አገላለጾች የሚያይሉበት መጽሀፍ ከሆነ እንደልብ ወለድ ሊሆን ይችላል ግን እንደተባለውም በዋቢነት ሊጠቅም የሚችል የምሁራዊ ምርምር ውጤት መሆኑ እኔም እንደተችዎቹ ሥጋት አለኝ፡፡ ደራሲው በአንድ ወቅት በያን አሶባ ከተባሉ በዛን ወቅት ኦብነግ የሚባል የኦሮሞ ደርጅት (መቼም ይሄ አሮሞ ፈርዶበታል) መሪ ከነበሩ ሰው ጋር በገቡት እሰጥ አገባ ሁለቱም ይመላለሷቸው የነበሩትን መልዕክቶች እከታተል ነበር፡፡ በመጨረሻም የራሴን አስተያየት ለመስጠት ሞክሬያለሁ፡፡ በዛን ወቅት ዶ/ር ቶሎ(ላ)ሳ ሲያቀርቧቸው የነበሩት ታሪካዊ ጉዳዮች እኔን አልተዋጡልኝም ነበር፡፡ እርግጥ እኔ የታሪክም የፖለቲካም ሰው አደለሁም፡፡ አስተያየቴንም የሰጠሁት ይሄንኑ ማንነቴን ገልጬ ነው፡፡ የኔ ችግር የነበረው የተጠቀሱት የታሪክ ኩነታት እውነት መሆን ከአለመሆናቸው ጋር የተያያዘ ሳይሆን እነዛ የተነሱ የታሪክ ማጣቀሻዎች አሁን ከአለው ነባራዊ ሁኔታጋር አልያያዝ ስላለኝ ነው፡፡ የምሁር አንዱ ሥራው ደግሞ ሰዎች የማይረዱትንና በዘመን ርቀት ማንም የማያውቀውን ታሪክ መናገር ሳይሆን ያ ታሪክ እንዴትና እንዴት ሆኖ ዛሬ ላይ ያለውን ሁኔታ እንደፈጠረ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተከታታይ በኢትዮጵያ ሕዝቦች (ኦሮሞና አማራን ጨምሮ) የመለዘር (ጀኔቲክስ) ጥናት ሪፖረቶች እየወጡ ነው፡፡ ከዛም በላይ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዘረመል አወቃቀር (Genetic structure) ብዙ ሳይንቲስቶችን ትኩረት እየሳበ መጥቷል፡፡ ለግንዛቤ እንዲረዳ የተወሰኑትን ሊንኮች እዚህ ላይ ልተው፡፡

https://www.ncbi.nlm.nih.gov/pmc/articles/PMC3397267/pdf/main.pdfhttp://journals.plos.org/plosgenetics/article?id=10.1371%2Fjournal.pgen.1005397

file:///C:/Users/Era%20Agrilink%20PLC/Downloads/2015%20Gallego-Llorente.Supplentary%20Material%20Science%20(1).pdf

እንደነዚህ የመሳሰሉና በአለም ላይ ትልልቅ ሥም በአላቸው ሳይንስና ኔቸር በተባሉት የሳይንስ አሳታሚ መጼሔቶች ሳይቀር ነው ታትመው የምናያቸው፡፡ ከዚህም በተረፈ የታላላቅ መገናኛ ብዙሀንም (ቢቢሲና የመሳሰሉት) ትልቅ ሽፋን ተሰጥቷቸው ያሉ ናቸው አንዳንዶቹ፡፡ ሳይንሳዊ ሪፖረትን በመገናኛ ብዙሀን የዚህን ያህል ትኩረት ሰጥቶ መዘገብ እምብዛም አይደለም ልዩ ነገር ሲሆኑ እንጂ፡፡ ዶ/ር ቶሎ(ላ)ሳ ስለኦሮሞና አማራ የዘር ግንኙነት ከጻፉ ከላይ ያነሳኋቸው የሳይንስ ግኝቶች ዋና ዋቢያቸው ሊሆኑ ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ከሪፖረቶቹ በአንዱ በተለይ የኦሮሞንና አማራን ብቻ አይደለም የኢትዮጵያን ሕዝቦች በአጠቃላይ ማለት ይቻላል ምን አይነት የደም ትስስር እንዳላቸው በግልጽ ያስነበባል በተጨማሪም ስዕላዊ መግለጫም ይሰጣል፡፡ ኦሮሞና አማራ በደም አይለያይም ከሆነ የዶ/ር ፍቅሬ መጽሐፍ ትኩረት አዎ ትክክል ነው ከላይ ሊንክ ከሰጠኋችሁ አንዱ ይሄንኑ ነው የሚናገረው፡፡ ሳይንቲስቶቹ ታሪካዊ ትስስርን ለማግኘት ወደኋላ ብዙ ሄደዋል፡፡ በቤተመንግስትና ቤተከህነት አካባቢ የሚገኙ መዛግብቶችን ተመልክተዋል፡፡ ምን ዓለባትም ዶ/ር ፍቅሬ ለመጻህፋቸው የተጠቀሟቸውን ታሪካዊ ማጣቀሻዎችንም መርምረዋል፡፡ ልብ በሉ እነዚህ ሳይንቲስቶች የዛሬ እውነታ ብቻ ሳይሆን እዚህ ድረስ የደረሰውን ታሪካዊ እውነታን ነው ለማወቅ የሚፈልጉት፡፡ ታሪክን ወደኋላ ማዋቀር (history reconstruction) ይባላል፡፡  ዶ/ር ፍቅሬ እነዘህን መዛግብቶች እንደማጣቀሻ ወስደው ከሆነ ጥሩ ካልሆነ ግን ወደፊትም እንደነዚህ ያሉ የዛሬውን እውነት ከድሮው ጋር የሚያገናኙ መረጃዎች ስለሆኑ ቢጠቀሙባቸው፡፡  በአጠቃላይ ግን የዶ/ር ፍቅሬ ጽሑፍ በድክመት ምክነያት ትልቅ ትኩረት መሆኑ የመጽሐፉን ይዘት አጠያያቂ አድርጎት የኦሮሞና አማራን አንድነቱን ለወደዱት ሐዘን ላልወደዱት ደግሞ ደስታ እንደፈጠረ ተቺዎቹን ተከትለው ከሚሰጡ አስተያየቶች እናያለን፡፡ የኦሮሞንና የአማራን እንዲሁመ ሌላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የዘር ትስስር ግን ለማወቅ ለምትፈልጉ ሁሉ ከላይ የጠቁምኳቸውን መረጃዎች ተመልከቱ፡፡

የሔኖክ የሺጥላና አበበ በለው የተባሉ ግለሰቦች እሰጥ አገባ፡

ሔኖክ የሺጥላ የሚባለው አማራ ቤሔረተኛ ነኜ ከሚሉት አንዱ ይመስለኛል፡፡ አበበ በለው ደግሞ የአንደ ሬዲዮ ድምጽ አዘጋጅ፡፡  አበበና ሔኖክ ቃለምልልስ ይሁን ምን እንደምለው አላውቅም ግን ሲጨቃጨቁ ያሰሙን ድምጽ አይመችም፡፡ ሔኖክ የተጠየቀውን ጉዳይ ነው አይደለም ብሎ መናገር ሲችል አላስፈላጊ ቃላቶችን መጠቀሙ ስህተት መሆኑ ሳያበቃ እንደገና ራሱን እንደተለየ ሰው አድርጎ የሚያቀርብባቸው አካሂዶቹ  እንደ እኔ ሌላ ስህተት ነው፡፡ አበበ በለው ከንግግሩ በስተጀርባ የሆነ ስህተት ሰርቶ ሊሆን ይችላል ግን በሰማንወ ድምጽ ክፉ የሚባል ነገር አልሰማንበትም፡፡ በአጠቃላይ የግል አተካራን ለሕዝብ ማቅረብ ስህተት ነው፡፡ ስለነሱ ይህን ካልኩ ከእነሱ አተካራን አስመልክቶ በማህበራዊ ድረ ገፆች ትኩረት ከሳቡ ጉዳዮች አንዱ መሆኑ ግን እኔን ሌላ ትዝብት ጭሮብኛል፡፡ እንዲህ ያለው ጉዳይ ለብዙዎች ማህበራዊ ድረ ገጾች የዚያን ያህል ትኩረት አግኝቶ መወያያ መሆኑ በራሱ ችግር ነው፡፡ እንዲህ ያለን ጉዳይ የሚከታተሉ ድረገጾች ብዙ ቢሉ አይደንቅም፡፡ ግን ትልልቅ አገራዊና ሕዝባዊ ኩነታትን እንዘግባለን በሚሉ ድረገጾች የራሳቸው መስፈርት ቢኖራቸው ይመረጣል፡፡ በእንደዚህ ያለ ስህተት ብዙዎች ምንም ሳይሆኑ በጫጫታ ብቻ ዛሬ ትልቅ ሆነው ለአገርና ሕዝብ አደጋ የሆኑም እንዳሉ አንዘንጋ፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጉዳይ ማንም ከሜዳ እየተነሳ ዋና ተንታኝ ሲሆንበት እናያለን፡፡ ከላይ ያነሳሁት ኢሳትን ጨምሮ የግሎቹ ሚዲያዎች ለእንደነዚህ ያሉ ግለሰቦች መስተናገኛ እንደሆኑ ብዙ ታዝበናል፡፡ አልፎ አልፎም የአማርኛው ድምፅ (ኦሮምኛና ትግሪኛም ሊሆን ይችላል) የቪኦኤና ጀርመን ሬድዮዎች ሳይቀሩ ለሕዝብ የሚመጥን ሙያዊ ትንታኔ የመስጠት አቅም ያሌላቸውን ግለሰቦች እየጋበዙ ስህተት ሲሰሩ እናያለን፡፡ ግለሰቦቹ እንደዚያ ያለውን አጋጣሚ ለራሳቸው ማንነት ምስክር እያደረጉ ምንም ሳይሆን ገዝፈውበት እናያለን፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ቆይተውም በሕዝብና አገር ላይ ዋና ሆነው ሲነግዱ እንታዘባልን፡፡ የማሕበራዊ ድረገጾችም ይሁኑ መገናኛ ብዙሐን መስፈርት ቢኖራቸው እላለሁ፡፡

አመሰግናለሁ!   ልዑል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ! አሜን