“Our true nationality is mankind.”H.G.

“ኤርትራ” የሚለው ስም ከመቸ ጀምሮ፣ ከየት፣ በማንና በምንስ ምክንያት መጣ?

Physical map of Eritrea.

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
አንዱ የመሸበት ወገናችን ታች አምና አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ከኢሳት ራዲዮና ቴሌቪዥን (ነጋሪተወግና ምርዓየኩነት) ጋር ቃለ ምልልስ እንዳደረጉ ወዲያውኑ “አስቂኙ የአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ቃለ ምልልስ!” በሚል ርእስ በቃለ ምልልሱ በተነሡ ነጥቦችና በአጠቃላይ ጉዳዮች ዙሪያ የሰጠሁትን ትንታኔ በስንት ጊዜው ሰሞኑን አንብቦ ነው መሰለኝ “እንዴት ኤርትራ የሚለው ስም የባርነት ስም ነው ትላለህ? ኤርትራ የሚለው ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በብዙ ቦታዎች ተጠቅሶ የለም ወይ?” አለኝ፡፡
እዛው ላይ የገለጽኩት በቂ መስሎኝ ነበረ፡፡ ይሄ ወገናችን ብቻ ሳይሆን በርካቶቻችን ይሄ ብዥታ ያለብን ይመስለኛል፡፡ እርግጥ ነው “ኤርትራ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ በተለይም በኦሪት ዘጸአት ላይ በርካታ ጊዜ ተጠቅሷል፡፡ የተጠቀሰው ግን ልብ በሉ በአማርኛና ከጣሊያን ወረራ ወዲህ በተጻፉ የግእዝ መጻሕፍት ላይ ብቻ ነው እንጅ ከጣሊያን ወረራ በፊት በተጻፉ መጻሕፍቶቻችን እንዲሁም በዕብራይስጡ፣ በሮማይስጡ፣ በጽርኡ ወይም በግሪክኛው፣ በዓረብኛውና በእንግሊዝኛውም ባጠቃላይ መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈባቸው ቋንቋዎች ሁሉ ብታዩ ግን “ቀይ ባሕር” ይላል እንጅ “የኤርትራ ባሕር” የሚል ቃል አታገኙም፡፡
“መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ግእዝና አማርኛ ከተተረጎመባቸው ከሌሎች ቋንቋዎች የሌለው ቃል እንዴት አማርኛው ላይ አልፎም ግእዙ ላይ ሊሠፍር ሊገኝ ቻለ?” ያላቹህኝ እንደሆነ ይሄንን ስሕተት የሠሩት በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት መጽሐፍ ቅዱስን ወደ አማርኛ የተረጎሙ ሰዎች ናቸው፡፡ ከእነሱም አንዳንዶቹ ይሄንን ያደረጉት ሆን ብለው በጣሊያን ተገዝተው እንደሆነ እገምታለሁ፡፡
እጅግ የሚያሳዝነው ነገር ግን የዋሐን አባቶቻችን የዚህን ተንኮል ዓላማ ሳይረዱ ይሔንን ቃል ወደ አብነት ትምህርት ቤቶችም ወስደውት እንደ የመጽሐፍ ቤትና የቅኔ ቤት ባሉ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት ትምህርት ቤቶች ይሄንን ተንኮለኞች የሰነቀሩትን ቃል ወስደው መክተታቸውና መጠቀማቸውም ነው፡፡ የቆዩ መጻሕፍትን ደግመው በሚጽፉበት ጊዜም የነበረውን ቃል እየተው ይሄንን ኤርትራ የሚል ቃል ከተው በመጻፍ ከባድ ስሕተት ፈጽመዋል፡፡
ይሄ መሆኑም “ኤርትራ” ብሎ ወራሪው ፋሺስት ጣሊያን የጠራት የሀገራችን ግማድ ሀገር ከጥንቱም እራሷን ችላ ለብቻዋ የነበረች፣ የኢትዮጵያ አካል ያልነበረች መስላ እንድትታሰብ አድርጓል፡፡ አሳሳቾቹም መጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎቹን አሳስተው ወይም ገዝተው ይሄንን ቃል እንዲከቱ ያደረጉበት ዓላማም ይሄው ነው፡፡ ባሕረምድር (በባርነት ስሟ ኤርትራ) ከጥንት ከኦሪት ጀምሮ እራሷን የቻለች፣ የኢትዮጵያ አካል ያልነበረች ሀገር አስመስሎ ለማሳየት፡፡
እውነቱ ግን ፋሺስት ጣሊያን በዐፄ ዮሐንስ 4ኛ ዘመነ መንግሥት ሰሜናዊ የሀገራችንን ክፍል ወሮ ሲይዝ ዐፄ ዮሐንስ 4ኛ መጀመሪያ አሰብን በኋላም ደጋውን የባሕረምድርን (የኤርትራን) ክፍል እየያዘ ሲሔድ ዐፄው ከሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ይልቅ በወቅቱ ለነበረባቸው የሥልጣን ሽኩቻ ጉዳይ ቅድሚያና ብልጫ በመስጠታቸውና ሸፍጥ ወይም የቁማር ስሌት ውስጥ በመግባታቸው እዛው አፍንጫቸው ስር ያለውን ወራሪውን ኃይል በዓይናቸው ስር እየተስፋፋ ሲሔድ በዝምታ በመመልከት በኋላም ሳያስወጡት ዐፄው አርቀው ማሰብ ካለመቻላቸውና ካለመብሰላቸው የተነሣ እጅግ በተሳሳተ እርምጃ በገዛ እጃቸው በራሳቸውና በሀገራችን ላይ በፈጠሩት ጠላት ከደርቡሾች ወይም ከመሐዲስቶች ጋር ባደረጉት ጦርነት ለሕልፈት በመዳረጋቸው ዐፄው እንዳሴሩትም ከባዱና ውስብስቡ የቤት ሥራ ለዐፄ ምኒልክ 2ኛ በመቆየቱ ወራሪው ጣሊያን ጭራሽም ያ ሳይበቃው በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት መላ ሀገራችንን ቅኝ ለማድረግ በማሰብ ተሻግሮ ለመግባት ባደረገው ሙከራ በ1888ዓ.ም. አድዋ ላይ ድል መመታቱ ይታወቃል፡፡
ይሁንና ዐፄ ምኒልክ 2ኛ የጣሊያንን መላ ኢትዮጵያን ወሮ ቅኝ የማድረግ ሕልሙን ቢያጨናግፉበትም በሁለት ዐበይት ምክንያቶች ከዚያ አልፈው በመሔድ ወራሪውን ኃይል ከባሕረ ምድርም ሳያስለቅቁት ሳያባርሩት ቀሩ፡፡
1ኛው ምክንያት ዐፄ ምኒልክ ሠራዊታቸው በጦርነቱ ምክንያት በሙትና ቁስለኛ ተጎድቶ ስለነበር፣ ስንቅና ትጥቅም አሟጦ ጨርሶ ከአካባቢው ሕዝብ በግዥ እንኳን ቢፈለግም የአካባቢው ሕዝብ ተንኮል በማሰቡ የሚላስ የሚቀመስ ሊገኝ ባለመቻሉ እንዲህ በሆነበት ሁኔታ ደግሞ ገፍተው ቀጥለው ቢሆን ኖሮ ጭራሹኑ ተሸንፈው መላ ኢትዮጵያ ለቅኝ ግዛት ልትዳረግ በመሆኑ ሌላ ጊዜ ተመልሰው ኃይላቸውን በሚገባ አጠናክረውና አደራጅተው ለመመለስ በማሰብ እስከዚያው ድረስ ግን ወራሪውን ኃይል ባለበት ተወስኖ እንዲቆይ፣ የሚወጣም ከሆነ ለኢትዮጵያ አስረክቦ እንዲወጣ የሚያስገድድ ውል በማስፈረም፣ ከስምምነቱ ውጭ ወራሪው ኃይል ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ቢያደርግ ስምምነቱ ፈራሽ እንደሚሆን ግዴታ በማስገባት ኃይል ገንብተው ለመመለስ የሚያስችላቸውን ጊዜ ለማግኘት የሚያስችል እጅግ ብልህነት የተሞላበት ውል ወራሪውን አስፈርመው መቆየት ነባራዊው ሁኔታ አስገድዷቸው ስለነበረ ሲሆን፡፡
2ኛው ምክንያት ደግሞ “በጦርነቱ ወቅት የባሕረ ምድር (የኤርትራ) ተወላጆች በከፍተኛ ቁጥር የወራሪው የጣሊያን ወታደር (የባንዳ ጦር) በመሆን ከጣሊያን ጋር ተሰልፈው የገዛ ሀገራቸውንና ወገናቸውን ወግተው ስለነበር አገሬው ከጠላት ጋር አብሮ ተሰልፎ እየወጋ ባለበት ሁኔታ እንኳንና ስንቅና ትጥቅ የጨረሰና በጦርነቱ የተጎዳ ሠራዊት ተይዞ ሙሉ አቅም ተይዞ ቢሆንና ጦርነቱ ተደርጎ የጦር ሜዳ ድል ማግኘት የሚቻልበት ዕድል ቢኖር ኖሮም እንኳ የአገሬው ከጠላት ጋር ማበር የሚገኘውን ድል ትርጉመቢስ ስለሚያደርገውና የተሟላ ድል ስለማያደርገው በአረም ደጋግሞ የመመላለስን ችግር ስለሚያስከትል ይሄ ከመሆኑ በፊት ለቅኝ ገዥ ተሰልፈው የገዛ ሀገራቸውንና ሕዝባቸውን የወጉት ወገኖቻችን ለጠላት አድሮ መሥዋዕትነት ለመክፈል እስከመሰለፍ እራሳቸውን የሰጡለት ቅኝ ተገዥነት ወይም ባርነት ምን ያህል መራራና አዋራጅ እንደሆነ እንደ ጭቃ ተረግጠው፣ እንደ አህያ ተገጥበው፣ እንደ በሽተኛ ተገልለው፣ እንደ ባዕድ ተገፍተው ወዘተርፈ. የባርነትን ግፍና ሰቆቃ ዓይተውት እስኪረዱትና የነጻነትን፣ የክብርን፣ የኩራትን፣ የሉዓላዊነትን፣ የኢትዮጵያዊነትን ዋጋ እስኪረዱት ድረስ ዕድል ለመስጠት” የሚለው ደግሞ ሌላኛው ዐቢይ ምክንያታቸው ነበር፡፡
በእነኝህ ሁለት ዐበይት ምክንያቶች በአድዋ ጦርነት ወቅት ከአድዋ ድልም በኋላ ጦርነቱን በመቀጠል ባሕረ ምድርንም (ኤርትራንም) ነጻ ማውጣት ባለመቻሉ ባሕረምድር በወራሪው ጣሊያን ቅኝ ግዛት ስር ልትወድቅ ቻለች እንጅ አንዳንዶች “ስለተካድን ለባርነት ተላልፈን ስለተሰጠን ነው!” እንደሚሉት ሲበዛ የዋህነት የተሞላበት አስተሳሰብ አይደለም እውነታው፡፡ ከዚያም ወራሪው ጣልያን ያንን ምድር በራሱ ቋንቋ “ኤርትራ የጣሊያን ቅኝ ግዛት” ሲል ሠየመው፡፡ ከዚህ ጊዜ በፊት ግን ይህ ስም አይታወቅም፡፡ የዚያ የሀገራችን ክፍልም ይሁን የሌላ አካባቢ መጠሪያ ሆኖም አያውቅም፡፡
እናም እኔ ያኔ በዚያ ጽሑፌ “”በማንነቱ፣ በቀደመው ገናና ታሪኩ፣ በነጻነቱ ኩራት የሚሰማውና ለሰውነቱ፣ ለነጻነቱ፣ ለሉዓላዊነቱ፣ ለማንነቱ ዋጋና ክብር የሚሰጥ፣ ጤነኛ ሥነልቡና ሰብእናና አእምሮ ያለው የባሕረምድር ተወላጅ ቢኖር “ኤርትራ” በሚለው መጠሪያ፣ የቅኝ ገዥዎችን ዕኩይ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን የማዳከም የማፈንና የመስበር ዓላማን ተፈጻሚ ባደረገው መገንጠል እንዲሁም በጣሊያንኛ ስሞቻቸው ያፍራል፣ ይሸማቀቃል፣ ይብከነከናል እንጅ ባሕረምድርና ሕዝቡም ተጠቃሚ ያልሆነበትን መገንጠልን ደግፎ ጭራሽ ይሄንን የባርነት ስም እያሞካሸ ሊጠራ ሊኮራበትም ባልቻለ ነበር፡፡ ምክንያቱም እንደኛ እንደኛ ከሆነ ባርነት ማለትም ባሪያ መሆን ወይም ለወራሪ ለባዕድ በገዛ ሀገር ላይ የሰብእና ክብር ተገፎ እንደ አህያ ተገጣቢ ተሸካሚ ተረጋጭ አገልጋይ መሆን ሞት፣ አሳፋሪ አሸማቃቂ አጥንት ሰባሪ ውርደት ነው እንጅ በጭራሽ ኩራት አይደለምና፡፡
እናም እንደዚያ ዓይነት ቆፍጣና ስሜት ያለው ተወላጅ ቢኖር ኖሮ የቅኝ ገዥዎችን አንድ ሀገርን፣ አንድ ሕዝብን በመክፈል በመለያየት በማናቆር ሀገሪቱንና ሕዝቧን የማዳከምን፤ ተያይዘው በሚመጡ የተወሳሰቡ ችግሮች የማስመጥን ዕኩይ ዓላማ መሸከም መጫንና ተፈጻሚ ለማድረግም መታገልና ታግሎም ተፈጻሚ ማድረግ አህያነት ማለት ይሄ ነው እንጅ “እምቢ ለሀገሬ! እምቢ ለነጻነቴ! እምቢ ለማንነቴ! እምቢ ለሉዓላዊነቴ!” ብሎ ወራሪን ኃይል ተፋልሞ እያለቀ ድባቅ መቶ የሀገርንና የሕዝቧን ነጻነት ሉዓላዊነት ክብር ማስጠበቅ ማስከበር አለመሆኑን ባወቀ በተረዳ ነበረ፡፡
ያንን የአህያነት ተግባር የፈጸመ በዚያ ነውረኛና የደንቆሮ የእንስሳ የባንዳና የባሪያነት ድርጊቱ ትናንትና ባይሆንም ቢያንስ ዛሬ በዚህ ዘመን ሊያፍር ሊሸማቀቅ ሊሰማው ሊጸጸት ይገባል! ምክንያቱን ያ ድርጊቱ ስሕተት እንደነበረ ዘመኑና ውጤቱ ቁልጭ አድርጎ አሳይቷል እያሳየም ነውና፡፡ ይህ እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ ድርጊቱ ስሕተት እንደነበረ እንዲረዳ ካላደረገው ሊረዳ ያልቻለው ከባሪያነት ከአህያነት ማንነቱ የተነሣ ነውና ምንም ልንረዳው ባለመቻላችን እናዝናለን! እንዲህ ዓይነቱ አሳዛኝ ፍጥረት ሁሉ ከእኛ ጋር እኩል ለማውራት የሞራል (የቅስም) ብቃት ፈጽሞ እንደሌለው ጠንቅቆ ሊያውቅ ይገባል!”” ብየ ማለቴ ትክክል ነበር፡፡
ከዚህ አንጻር ተስፋ አደርጋለሁ መጭው የባሕረ ምድር ትውልድ በነጻነት የማሰብና የመወሰን ዕድል የሚገጥመው ከሆነ ይሄንን በዕኩያን ባዕዳን አሳሳችነት በቀደምቶቹ ትውልድ የተፈጸመውን አሳፋሪና አዋራጅ ስሕተት ሁሉ የሚረዳና የሚቆጭ ትክክለኛውን የእርምት እርምጃ በመውሰድም ማለትም ወደ እናት ሀገሩ በመቀላቀል ማንነቱን የሚያድስ፣ ክብሩን የሚመልስ፣ ሥነ ልቡናውን የሚቀድስ፣ መጻኤ ዕድሉን በተድላ የሚያርስ፣ በእድገት የሚገሰግስ፣ ትንሣኤው ላይ የሚደርስ እንደሚሆን፡፡
ከዚያ በፊት ግን በጊዜው መስሎት ተታሎ ተወናብዶ ወይም ተጭበርብሮ ይሄንን ታሪካዊ ስሕተት የፈጸመው ትውልድ ሀገሩንና ሕዝቡን ኪሳራ ውስጥ እንደዘፈቀ ከማለፉ በፊት እንኳን ሆንብሎ ለማሳሳት የሚጥር ክፉ መካሪ ባዕድ እያለ ቀርቶ ሰው ሆኖ የማይሳሳት የለምና ያንን ያህል ዘመን የተጋደለለትና መራር መሥዋዕትነት የከፈለለት ትግል የማይጠቅም ከዚያም ባሻገር ኪሳራና መከራ ያስከተለ ውጤት ማምጣቱ በሚፈጥርበት ሐፍረትና መሸማቀቅ ሥነልቡናው ክፉኛ ተጎድቶ የመታረም፣ ከጥፋት የመመለስ ትክክለኛ አስተሳሰብ ከአስተሳሰብ ሚዛኑ ላይ ጠፍቶ በስሕተት ላይ ስሕተትን በሚያስፈጽም የሥነልቡና ሁከት በሽታ ሳይለከፍ ነገሩ እንዳልሆነና የተሳሳተ እንደነበረ ከገባው ዘንዳ በአጉል ግትርነት፣ በ “እልህ ምላጭ ያስውጣል!” ክፉ የሥነልቡና ገመድ ታንቆ “ካፈርኩ አይመልሰኝ!” እንዳለ የታሪክ ተወቃሽና ተከሳሽ እንደሆነ ሳይቀር የእርማት እርምጃ ወስዶ ነገሩን የሀገርንና የሕዝብን ክብር ኩራት ማንነትና ጥቅም ወደሚያስጠብቀው ወደነበረበት ሁኔታ በመመለስ መራር የሕይዎት ዘመን ትግሉን በድል በማጠናቀቅ ክፉ መካሪንና ምቀኛ ጠላትን ማሳፈር፣ ሀገርንና ሕዝብን ስኬት እድገትና ብልጽግና በሚያገኙበት እርካብ ላይ ማስቀመጥ ቢችል ምንኛ አዋቂነት አስተዋይነት ብልህነትና ጀግንነት በነበረ??
ከነባራዊ ሁኔታዎች፣ ከአካባቢያዊና ዓለማቀፋዊ ፖለቲካዊ (እምነተ አሥተዳደራዊ) እና ኢኮኖሚያዊ (ምጣኔ ሀብታዊ) ጉዳዮች ላይ ተመሥርተን ስንተነብይ ወደፊት አንድነት መፈጠሩ የማይቀር ይመስላልና ሕዝባዊ ግንባርን ወይም ሸአቢያን የምመክረው ጉዳይ ቢኖር እናንተም መገመት እንደምትችሉት ይህ ጉዳይ የማይቀር ከሆነ ወደፊት በሚመጣ በሌላ አካል ከሚፈጸም ይልቅ ዕድሉ ሳያመልጣቹህ አሁን በራሳቹህ እንዲፈጸም ብታደርጉ ብልህነት አሳቢነት አስተዋይነት አዋቂነት ጀግንነት አይመስላቹህም ወይ???
ሕዝባቹህን መካስ ካለባቹህ ከዚህ የተሻለ ልታደርጉት የሚገባ ነገር ሊኖራቹህ አይችልምና ይሄን ዕድል ብትጠቀሙበት መልካም ነው እላለሁ፡፡ በዚህ 26 ዓመት ከገጠመን ችግር ማን ተጠቀመ? ማንስ አተረፈ? ምን ያህልስ ከሰርን? ኪሳራው በገንዘብ ብቻ ሊተመን የሚችል ነው ወይ? ይሄ ሁሉ ኪሳራ ሊደርስብን የቻለውና ልናገኘው እንችል የነበረውን ሁሉ ያላገኘነው ለምን ይመስላቹሀል? ይህ የሆነው ነገር ሁሉ በሆነው መልኩ ባይሆን ኖሮ እስከአሁን የት ልንደርስ እንችል እንደነበር ምንም ታስቧቹህ አያውቅም? ልንደርስበት እንችል ከነበረው ሁሉ ያልደረስነው በእኛው ስሕተት ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ መፍትሔውም ያለው በእኛው እጅ ነው ማለት ነው፡፡ እናም እባካቹህ አሁንም ቢሆን መብቱ የኛው ነው፡፡ እኛ ለማድረግ ከፈቀድንና ከወደድን ማንም ሊከለክለን የሚችል የለምና ያከሰረንን የማይጠቅመውንና ይባስም ዋጋ የሚያስከፍለውን መንገድ በደነቆረ አስተሳሰብ ማለትም በእልህ፣ በካፈርኩ አይመልሰኝና በምቀኝነት ቀጥለንበት በእኛው ጥፋት ከእኛም አልፎ ምንም በማያውቀው ነገር መጭውንም ትውልድ ለቅጣት ከምንዳርግ የሚበጀውን ነገር ብናደርግ የሚያዋጣ አይመስላቹህም ወይ??? እስኪ ፈጣሪ ይርዳቹህ!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

Related stories   ሕዝብን ማን ይሰራዋል?

ሰአሊ አምሳሉ እኔም አንዱ ይህን ጹሁፍ ዘግይተው ካነበቡት ውሰጥ አንዱ ብሆንም አንተ ሳታቀው የምትጽፈውን ታሪክ አይሉት ፖለቲካ ዝም ብሎ ተረትህን አይቼ ወገንህ እንዳይሳሳት በማሰብ አንተ ስትቀባ ያላነበብከውን ባገርህ ልጅ በንጹ አሞርኛ በታዋቂው ማሞ ውድነህ የተጻፈውን የሚለውን መጽሃፍ አንብበህ ስለ ኤርትራ ታሪክና ስለ ኤርትራ የሚለው ስም አመጣጥ እንድታውቅና ራስህን አርመህ ለመጪው እንዲህ አይነት ስህተት እንደማትሰራ ለነቄው ያገረህ ልጅ ቃል ግባለት። ደሞም ስእል ሲጣመም እንደሚያምር: ታራክም ሲጣመም ያምራል ብለህ አታስብ። ታራክ ሲጣመም ያማራል። አላዋቂነትህንም ይገልጻል። እናም ወገን አትሳሳት። ሳታውቅ አትጻፍ። ሲጀመር ሰአሊነትህ እንጂ የተረት ደራሲነትህ ስላልተገለጸ ነው ይህን የጻፍኩልህ። ወገን መስታወት አይደለም የምታስበወን የምታይበት።
እኔ የሰጠሁት አስተያየት ላይ የኤርትራ ታራክ የሚለው ቃል በማሞ ውድነህ የተጻፈ መጽሃፍ ተደልዟል። ይስተካከል።

0Shares
0