“Our true nationality is mankind.”H.G.

ታሪካችንን ባለማወቃችን ሁሌም ወደኋላ በመገስገስ ላይ እንገኛለን፤ ሰሞኑን አንዳንድ ዜና መዋዕሎችን ማንበብ ጀምሬ እስካሁን አራት ያህል አንብቤአለሁ፤ ከዚህ በፊት እየተንገዳገድሁ በግዕዝ አንብቤአቸዋለሁ፤ ዛሬ የሲራክ አሳታሚ ድርጅት በአማርኛ እያሳተማቸው በመሆኑ ምስጋና ይድረሰውና ሳልንገዳገድ በአማርኛ እያነበብሁ ነው፤ በዚህ ንባቤ ውስጥ አንዳንድ ያገኘኋቸው ሀሳቦች ስለራሳችን ያለን እውቀት ምን ያህል ጎደሎ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው፤ ለዛሬው ሁለት ሀሳቦችን ከላሊበላ ዜና መዋዕል፤ አንድ ደግሞ ከሱስንዮስ መርጫለሁ፤ እኔን እንዳስደነቁኝ ሌሎችንም ያስደንቃሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡

አንደኛ፤ ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት በ1160 ዓ.ም. የነገሠው ገብረ መስቀል የሚባለው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት “በነገሠ በአሥር ዓመቱ መራ ከተባለው አጠገብ የነበረውን ቤተ መንግሥት ወደሌላ ለማዛወር አስቦ ቀይት ከተባለችው ባላባት ከሚዳቋ ገደል በላይ፣ ከመካልት በመለስ፣ ከጉሮ በታች፣ ከገጠርጌ አፋፍ በላይ ያለውን ቦታ በአርባ ጊደር ገዝቶ ቤተ መንግሥቱን መካነ ልዕልት ብሎ እሰየመው ቦታ ላይ ሠራና በዚያው አቅራቢያ ታላላቅ ቋጥኝ ደንጊያዎች መኖራቸውን ስላረጋገጠ …” የላሊበላን አሥር የድንጋይ ፍልፍል ቤተ ክርስቲያኖች አሠራ፤ እነዚህን በዓለም ተወዳዳሪ የሌላቸውን ዕጹብ-ድንቅ የሚባሉ ቤተ ክርስቲያኖች ለማሠራት ሃያ ሦስት ዓመታት ብቻ ፈጀበት፡፡

Related stories   በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ- ትህነግ “ክብሪት” የተባለ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙ ታወቀ፣

ከአጼ ምኒልክ በቀር እስከዛሬ በእንደዚህ ያለ አጭር ጊዜ ውስጥ እንዲህ ያለ ትልቅ ሥራ ያበረከተልን ንጉሠ ነገሥት ያለ አይመስለኝም፡፡

ሁለተኛ፤ “አጼ ገብረ መስቀል በተወለደ በሰባ ሰባት፣ በነገሠ በሠላሳ ሰባት ዓመቱ የአጎቱን ልጅ ነአኩቶ ለአብን በመንግሥቱ አስቀምጦ ሥርዓተ መንግሥቱን እንዲያጠና በቅርብ እየተቆጣጠረ እስከ ሦስት ዓመት ጠበቀው፤ ከሦስት ዓመት በኋላ በነገሠ በአርባ ዓመት፣ በተወለደ በሰማንያ ዓመቱ” ዐረፈ፤ ልብ በሉ፤ የአጎቱን ልጅ መርጦ አንግሦት፣ አጠገቡ ሆኖ እያስተማረው ለሦስት ዓመታት ያህል ቆይቶ ሞተ፡፡

Related stories   ‹‹የህዳሴው ግድብ ለሱዳን ከፍተኛ ጥቅም አለው፤ የቀጠናውን የኢኮኖሚ ትስስር ያጠነክራል››

ከዛሬ ሦስት መቶ ዓመታት በፊት ደግሞ ከአጼ ሱስንዮስ ዜና መዋዕል (1597-1625) ያገኘሁት የሕዝብን ንቃትና ቆራጥነት የሚያሳይና የሚያስደንቅ ታሪክ ነው፤

የእናርያ ሰዎች ቤነሮ የሚባል ሹማቸውን ገደሉና ለአጼ ሱስንዮስ ደብዳቤ ላኩለት፤ “እነሆ ሰዎችን ያለፍርድ ስለገደለ፣ የሰዎችን እጅና እግርም ስለቆረጠ፣ የሰዎችን ዓይንም ስላጠፋ፣ … በወጣቶችና በሽማግሌዎች፣ በሕጻናትም ላይ ስላርራራ፣ እኛ ከየቤታችን ያዋጣነውን የንጉሥ ግብርም ስለወሰደ፣ በቅሚያና በዝርፊያም የሰውን ሁሉ ገንዘብ ስለሰበሰበ፣ የሰውን ሚስት ስለቀማ፣ ስለሽርሙጥናውና ስለስስቱም፣ የወንድሙን ሚስት ስለወሰደ፣ በላያችን ላይም ግፍን ስለፈጸመ፣ ሴት ዘጠኝ ወር አርግዛ በአሥረኛው ወር ልጅን እንደምትወልድ እኛም ለዘጠኝ ዓመታት ያህል የሱን ተንኮል ሁሉ አረገዝን፤ በአሥረኛውም ዓመት ሞትን ወለድንለት፤ የእናርያ ሰዎችን ሁሉ ያጠፋ ዘንድም ስለጸናና ስለጨከነ ገደልነው፡፡”

Related stories   በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ከተሞች የሽብር ጥቃት ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብር ቡድን በቁጥጥር ስር ዋለ- ትህነግ “ክብሪት” የተባለ ገዳይ ቡድን ማቋቋሙ ታወቀ፣

አጼ ሱስንዮስም ለወጉ ተቆጣና ሌላ ሾመላቸው፡፡

ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም
ጥር 2009 (ከህንድ)

(ምንጭ: Mesfin Wolde-Mariam Blog)

Share and Enjoy !

Shares
0Shares
0