የስደተኛዋና የፖሊሱ አስገራሚው ታሪክ

ሲኤን ኤን ዘገባውን ሲጀምር አስገራሚው የፍቅር ታሪክ በሚል ነው።

ባለፈው መጋቢት ወር ኢራቃዊት የ20 ዓመቷ ኖራ አርካቫዚ እና የእሷ ቤተሰብ ማለትም ወላጆቿ፣ታናሽ ወንድሟና እህቶቿ አስከፊውን የስደት ጉዟቸውን ጀምረዋል።

ዲያላ በምትባለው የኢራቅ አካባቢ ሃብትና ንብረት አፍርተው በሰላም ይኖሩ የነበሩት እነ ኖራ በአሸባሪው አይ ኤስ ምክንያት ከሞቀ ኑሯቸው ወደ አውሮፓ ለመግባት እንደማንኛውም ኢራቃዊ ስደተኛ ጉዟቸውን ቀጥለዋል።

ኖራ ራሱን እስላማዊ መንግስት በሚል ከሚጠራው አይ ኤስ ከሚያደርሰው ጦርነትና የሚሰጠውን አስነዋሪ አመለካከት ትምህርት ላለመሸከም ስትል ከኢራቋ ዲያላ አካባቢ የተሰደደች ሙስሊም ነች፤ቦቢ ዶደቨስኪ ደግሞ በሜቄዶንያ የድንበር ጠባቂ ፖሊስ ባለሙያና በሃይማኖቱም ክርሲቲያን ነው።

እሷ በስደት ከቤተሰቦቿ ጋር የስደት ጎዞዋን ድንበርና በረሃውን በማቆራረጥ ሜቄዶንያ ድንበር አካባቢ ስትደርስና እሱም የተለመደ የድንበር ጥበቃ ስራውን በሚያካሂድበት ወቅት ሁለቱም አይን ለዓይን ይተያያሉ። ሁለቱም በመጀመሪያ ቀን የዓይን ለዓይን ትይይታቸው በፍቅር መፈላለግ ውስጥ ይወድቃሉ። ተጋብተው በጋራ መኖር እንችላለን የሚል ሃሳቡ ግን አልነበራቸውም፤ምክንያቱም ግንኙነታቸው ቅጽበታዊ ስለነበር። የድንበር ጠባቂ ፖሊስ ቦቢ ዶደቨስኪ በወቅቱ የእንግሊዝኛ ተናጋሪ ብቸኛው ተረኛ የፖሊስ ባለሙያ ስለነበርና ስደተኛዋ ኖራ አርካቫዚም እንግሊዝኛን ጨምሮ ስድስት ቋንቋዎችን መናገር ስለምትችል ለሁለቱ ግንኙነት የዓይን ምልክት ቢሆንም ለመግባባት ግን ዋናው መሳሪያ ሆነ።

ኖራና ቦቢ ለሲኤን ኤን እንደተናገሩት በመጋቢት 20 ድንበር ላይ ዓይን ለዓይን በተያዩት መሰረት ወደ እውነተኛ የተግባር ፍቅር በመቀየርና እየዋለእያደርም ወደ ቁም ነገር ተቀይሮ ከወራት የአብሮነት የፍቅር ቆይታ በኋላ በሃምሌ ወር ወደ ጋብቻ እምርተው በትዳር መጣመር ችለዋል።

ቦቢና ኖራ በጋብቻ አብረው ለመኖር በመወሰን ፍቅር የሞላበት ትዳራቸውን ሲቀጥሉ የኖራ ቤተሰቦች ግን የስደት ጉዟቸውን በመቀጠል በጀርመን የጥገኝነት ጥያቄ አቅርበው መኖር ጀምረዋል። ኖራ በሜቄዶንያ ከቦቢ ጋር በትዳር ለመኖር ስትወስን በቤተሰቦቿ ዘንድ የዘላቂነቱ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኖ ነበር። ይሁን እንጅ የሁለቱ ጥንዶች ግንኙነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ ወደ ማይበጠስ የትዳር ህይወት ገብተዋል። አሁን ኖራ ከቦቢ ጋር ዘላቂ ህይወቷን ለመቀጠል እዛው ሜቄዶንያ ውስጥ ባለ የቀይ መስቀል መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥራ እየሰራች ትገኛለች።

ቦቢም ለ15 ዓመታት በቆየበት የፖሊስነት ስራው እንደቀጠለ ነው። ይህ ስራው የሚወዳት የትዳር አጋሩን በማስገኘቱ ከበፊቱ የበለጠ ወዶታል። እናም በሃይማኖት የተለያዩ የሆኑት ሁለቱ ጥንዶች ልዩነታቸውን በመቻቻልና በመከባበር በአሁኑ ወቅት በሜቄዶንያ ኩማኖቮ በተባለ አካባቢ መንፈሳዊ ቅናት በሚያሳድር የትዳር ግንኙነት ውስጥ እየኖሩ ናቸው።

የዓለም ህዝብ ተቻችሎ የመኖር ባህል ማሳያዎች

ኖራ ህይወቷን ሙሉ ከምትወደው ባለቤቷ ቦቢ ጋር ለማድረግም የአኗኗር ዘይቤዋን በቀላሉ ከሜቄዶንያውያን ጋር አዋህዳለች። “ህዝቡ፣ አገሩ፣ ከተማው በሙሉ አቀራረቡ እንደስደተኛና መጤ እንዳይሰማኝ የሚያደርግ ነው” ብላለች ኖራ። ማህበረሰቡ፣ ጎረቤቶችና የሁለቱም ቤተሰቦች ጋብቻቸውን በፍጥነት እንደተቀበሉትና እንደሚያከብሯቸውም ነው ኖራ የምትናገረው። ” ሜቄዶንያ የአኗኗር ዘይቤው ባህላዊና ዘመናዊነት የተቀላቀለበትና በሃይማኖትም ሙስሊምና ክርስቲያን የሚኖሩባት ሃገር ነች፤ ብዙ ሙስሊም ጓደኞች አሉኝ እናም የእነሱን ረመዳን ሲያከብሩ አብሬ ቤታቸው በመሄድ አከብራለሁ” ብሏል ቦቢ።

በተመሳሳይ ኖራ ያደገችው ብዝሃነት ባለባት ኢራቅ በመሆኑ” የእኔ ቤተሰብ ያደገው ከክርስቲያን ህዝቦች ጋር ነው፤ ሁሉንም የሚቀበልና የሚያገናዝብ አካባቢ ነው የተወለድኩት፣ያደኩት” ብላለች። እናም አሁን ሁለቱም በየአስተዳደግ ሂደታቸው ባዩት ተቻችሎ የመኖር ባህልን አዳብረው በአንድ ጎጆ ጥላስር የመኖር ጅማሮዋቸውን በሚያስደምም ፍቅር ጀምረውታል፤የነገ ፍሬያቸውንም በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

ኖራ አሁን የአራት ወራት ነፍሰጡር ሴት ነች።

ይህ የሁለቱ ጥንዶች የፍቅር ታሪክ የሚያሳየው የዓለምን ተቻችሎ፣ ተከባብሮና ተዋዶ የመኖር ባህል እውነታን ነው። ኖራና ቤተሰቦቿ የአይ ኤስን ጽንፈኛ አስተሳሰብ ላለመሸከም ሲሉ ስደትን መርጠዋል። ቦቢም በልዩነት ውስጥ ተከባብሮና ተፋቅሮ መኖርን በተግባር እያሳየ ይገኛል። እናም በአሁኑ ሰዓት አይኤስን ጨምሮ ሌሎች ለዓለም ዋነኛ ስጋት የሆኑት ጽንፈኛና ሽብርተኛ ድርጅቶች ይህን የዓለምን ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖር ባህልን ለማደፍረስ ሌት ተቀን በሚሰሩበት ወቅት በአንጻሩ ዓለምአቀፉ ማህበረሰብ የእነዚህን ጽንፈኞች እኩይ ተግባር በመመከት የዓለም ህዝብ በልዩነቶች ውስጥ ተከባብሮና ተቻችሎ የመኖርን ነባራዊ እውነታ አጠናክሮ መቀጠሉን ኖራና ቦቢ ማሳያዎች ናቸው።

ታደሰ ዳኛቸው/ኢዜአ/

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *