በእስር ላይ ያሉት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ሊቀ መንበር የዶ/ር መረራ ጉዲና ጠበቆች ያቀረቡት የዋስትና ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ። ጠበቆቻቸው የክስ ሒደቱ እንዲጀመር ያቀረቡት ጥያቄም ውድቅ ተደርጎ ሌላ ቀጠሮ  ለየካቲት 16፣ 2009 ዓም ተሰጠ።

“አንድ ተጠርጣሪ የዋስትና መብት የሚከለከለው ማስረጃዎች ያጠፋል፤ ምስክሮችን ያባብላል፤ ወንጀል ይፈፅማል አለያም ከሐገር ይኮበልላል የሚል ሥጋት ሲኖር ብቻ ነው” ይላሉ ከዶ/ር መረራ ጉዲና ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ለዶቸቬሌ ሲናገሩ። ዶ/ር መረራ ግን ከእነዚህ ስጋቶች ሁሉ ነፃ ናቸው በሚል እምነት ዋስትና መጠየቃቸውን ጠበቃቸው አመለክተዋል። አክለውም ከምርመራ በኋላ ክስ በይፋ ሲመሰረት በድጋሚ ዋስትና እንደሚጠይቁም ተናግረዋል። ጠበቆቹ ተጠርጣሪው ወደ ሁለት ወር ገደማ በመታሰራቸው ክርክሩ እንዲጀመር ያቀረቡትንም ጥያቄ ፍርድ ቤቱ ሳይቀበለው ቀርቷል።

ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ደንበኛቸውን በሳምንት ሁለት ቀናት (ረቡዕ እና ዓርብ) ማግኘት እንደሚችሉ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ ዶ/ር መረራ ጉዲና አሁንም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ አልተፈቀደላቸውም። የዶ/ር መረራ ጉዲና የምርመራ ሒደት እስከ አራት ወራት ሊዘልቅ ቢችልም ጠበቃቸው በድጋሚ ተቃውሟቸውን እንደሚያሰሙ ተናግረዋል። መርማሪ ፖሊስ በተደጋጋሚ ሌላ ቀነ ቀጠሮ ሊጠይቅ ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው ዶ/ር ያዕቆብ፣ መረጃ የማሰባሰቡ ሒደት እስካሁን መጠናቀቅ ነበረበት ብለዋል። ዛሬ ያስቻለው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት የዶ/ር መረራ ጉዲናን ጉዳይ  ለመጪው የካቲት 16 ቀን 2009 ዓ.ም. እንደቀጠረው ከጀርመን ድምጽ ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።

ኢህአዴግ ከተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር የሰላም ንግግር ለማደረግ ውስኛለሁ ማለቱና፣ የሃይማኖት ” አባቶች” የአገሪቱን ችግር በእርቅ ለመፍታት እንቅሰቃሴ ማድረጋቸውን ተከትሎ እስረኞችን መፍታት፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት እንዲሁም ከዚህ በፊት የጠፋውን እምነት መገንባት ዋና ጉዳይ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚሰጥ አስተያየት ነው። ፕርቲዎችም ቅድሚያ እስረኞችን ማስፈታት አጀናዳቸው እንደሚሆን ከወዲሁ እየተናገሩ ነው።

Related stories   የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ለስድስት ወራት ተግባራዊ እንደሚደረግ ሲራጅ ፈጌሣ ገለፁ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *