ሃያ ሳንቲም ብቻ ነበረኝ። ከታክሲ መልስ የተረፈች። ስራ ቦታ ስደርስ ደሞዜ አልደረሰም ነበር። እንደ ቀን ሰራተኛ ክፍያዬ በውል አይታወቅም። እናም አለቃዬ ዋናው አይደለም። ደሞዜን አላዘጋጀልኝም። ጽሁፍ ልሰጥ ጋዜጠኞች ቢሮ ስገባ ደሞዝ ወስደው እቁብ ሲጥሉ አይቼ ነበርና የሚያበድረኝ ሰው አሰብኩ። አንድ ጨብራራ ልጅ ላይ አይኔ አረፈ። እናም ጠጋ ብዬ ” አንዴ ላናግርሽ” አልኳት።
ራሴን እያሻሸሁ 20 ሳንቲም ብቻ እንዳለኝ ገለጬ ብድር ጠየኳት። ፈገግ አለችና ” ለዚህ የሚገማ ብር፣ ለዚህ ቆሻሻ ነገር እንዲህ ተጨንቀህ ትጠይቀኛለህ” አለችና ደሞዙዋን በሙሉ ከቦርሳዋ አውጣችና ” ግማሹን ውሰደው” አለችኝ። ” መክፈል ይክብደኛል” አልኩ። ” ወደፊት እንሰጣጣለን” አለቺኝ። ግማሹን ወሰድኩ…senedu-2
“… ቡና ልጋብዝህ” አለቺኝና ከቢሮ ወጣን። አነጋግሬያት ስለማላውቅ ለመጀመሪያ ጨዋታ መክፈቻ ” ምን ተወጃለሽ” አልኳት” ሰው ማማት፤ ሰው መዘልዘል፤ ታዲያ ሰለ ጉንዳን አናወራ ስለሰው እንጂ…” በሳቅ ሞትኩ። የሚያስጀምረኝ ካገኘሁ እኔም ወሬኛ ስለሆነኩ… ቀደድን። ስንዱ አበበን እንዲህ አወኳት። ሃሪፍ፣ የገባት፣ ደግ፣ ተጫዋች፣ ቀጥተኛ፣ ለህሊናዋ ቅርብ፣ ስስ ስሜት ያላት፣ ቦጅቧጃ፣ መዝናናት የምትወድ፣ ለሰው ተቆርቋሪ፣ ሳቂታ፣ የሚገርሙ ታሪኮች ቋት፣ ብዙ ገጠመኞች ያሏት… የራሷን ማስታወሻ ሰብሰባ ማተም ያቃታት ሰነፍ!! ወይም ዋጋዋን ያልተረዳች… እንደ ሌሎች ብልጠት ያላለፈባት ምርጥ ስንድዬ
አንድ ቀን ቢሮ አብረን ቁጭ ብለን ሳለ ስሙን የማልገለጸው የስነጽሁፍ ሰው መጣና አስጠራት። አፍታ ቆይታ እንባዋን እየረጨች መጣች። በጣም ተናዳ ” እባክህን ሶስት መቶ ብር ካለህ ስጠኝ” አለችኝ። ሰጠኋት። አድርሳ ስትመለስ ምን አጋጥሟት እንደምታለቅስ ጠየኳት። ” ሰው ሞራል አቷል” አለች። አሁንም ታለቅሳለች።
ቢሮ በር ላይ ያስጠራት ሰው ” ቤቴ ባዶ ነው። ሽሮ የለም። በርበሬ የለም። የሚላስ የሚቀመስ የለም። ልጆቼን የማበላው ነገር አጥሁ…” በማለት በምሬት ነግሯት ነበር። እንደሷ ገለጻ ያናደዳትና ያስለቀሳት ሰው ለሱስ ብሎ ይህንን ሁሉ ማውራቱ ነው። ዝም ብሎ ቢጠይቃት እንደመትሰጠው እያወቀ የቤተሰቡን ጉዳይ ማውራቱ… ” ሰው ሞራል አጣ…”
ከስንድዬ ጋር ብዙ አሳልፈናል። እንደ ሙያ አጋር፣ እንደ ጓደኛ፣ ሚስጥር ባታውቅም እንደ ሚስጢራኛ… ቀን ከማታ ሳንለያይ ዓመታትን ስናሳልፍ ከደግነቷ በቀር ስለ እሷ የማውቀው ነገር አላገኘሁም። አሁን ድረስ ወዳጄ ናት። ዛሬ ያገናኘን “የባለቅኔ መሃላ” የአያ ሙሌ ጉዳይ ነው። ስንዱ አያ ሙሌን በሚገባ ታውቀዋለች። እሱን ማወቅ የሚቻለው ” በመናበብ፣ በልብ መናበብ ብቻ ነው” ትላለች። የልብ መናበበ ከሌለ እሱን ማወቅ አይቻልም። ስንዱ ገና የሚዘመርለት፣ ደብር የሚደበርለት ሰው እንደሚሆን በድፍረት ትናገራለች። በህይወት እያለ ያልተዘመረለት፣ ያልተነገረለት፣ መድረክ የተዘጋበት… ቲፎዞ ሰለሌለው እንደሆነ ትናገራለች። ዘመኑ የአጎብዳጆች ነውና!! የዛሬ እንግዳዬ ስንዱ አበባ ቲያትረኛ፣ ጋዜጠኛ፣ አሳታሚ፣ ብዙ ልምድና ገጠመኝ ያላት ሰው ።
ዛጎል፡- በተደጋጋሚ ሙያዊ መማገጥ ስትዪ ይሰማል፤ ብሶት ወይስ ሌላ?
ስንዱ፡- ብሶት የለብኝም። ብሶት የሚባል ነገር አላውቅም። ይከፋኛል ግን ወዲያው እረሳለሁ። የምነግርህ ጥቅሉን ነው። ጋዜጠጠኛም እንደነበርኩ አትርሳ። መረጃዎች አሉኝ። ሙያን የዝሙት ያህል የሚሻቀጡበት በዙ። የቡድን ስሜት፣ ተራ መሞጋገስ፣ ማጎብደድ … ነው የሚታየው። ጥበቡ ዙሪያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም መስክ ይኸው ነው። በማህበር ተቧድነው መግቢያውን ይቆሉፉታል። ብቃትና ችሎታ በአርማታ ታሽገው ማጎብደድ፣ ጭራ መቁላት፣ መሞዳሞድ ነግሷል። እንዲህ ያለ ሙያዊ ውስልትና ያሳፍራል። ወደ ሌላ ጉዳይ እናምራ…..
ዛጎል፡- በተለይ ያዘንሽበት ጉዳይ አለ?
ስንዱ፡- አይደለም። እኔ ተራ ሰው ነኝ። ግን ሙያዊ መማገጥ ያስጠላል። ባለሙያ ራሱን ማክበርና መጠበቅ አለበት። በጥበቡ ዙሪያ ያለው ሙያዊ ውድቀት፣ ውስልትና፣ ብልግና… ሌሎችን አስገድዶ የመድፈር ያህል ወንጀል ሆኖ ይሰማኛል። በዚህ ውስልትና ሜዳሊያ ሳይቀር ተነጣጥቀናል። ለሰሩና ለደከሙ ሳይሆን ላልሰሩና ላልደከሙ አጎብዳጆች፣ በቡድን ለሚዘመርላቸው ሽልማትና እውቀና መስጠት … ተወኝ!
ዛጎል፡- አያ ሙሌ ምንሽ ነው?
ስንዱ፡- አጠያየቅህን ቀጥ ብታደርገው ምን አለበት። ወዳጄ፣ ደግ፣ ጽድት ያለ ልቡና ያለው። የምንናበብ ወዳጄ ነው። የልብ …
ዛጎል፡- አንቺ “ጽድት” ያለ ትየዋለሽ። ሰሞኑን “እብድ” እያሉት ነው፤
ስንዱ፡- እብድ ማለት ምን ማለት ነው? አየህ ከላይ የገለጽኩልህ ጉዳይ እዚህ ጋር ይመጣል። የተለመደው አይነት ባህሪ ማጎብደድ፣ ህሊናን አለማክበር፣ ልቡናን መሳት፣ ማምታት፣ ጭራ መቁላት፣ ክፋት እየሰሩ በጭንቀት መኖር ሰለሆነ ከዚህ ውጪ የሆኑ ሰዎች ሲታዩ ” እብድ” ይባላሉ። ግን ማን ነው እብድ? በአንድ ወቅት የቡድን ስም ወቶልን ነበር።mule
ዛጎል፡- ምን የሚል? እነማን ናችሁ?
ስንዱ፡- እኔ፣ አቦይ ስብሃት እና አያ ሙሌ ” ከጥልቁ” ወገን ናቸው ተብለን በመጽሔት ላይ አውጥተውን ነበር። አንግዲህ ጥልቁ ሲሉ የሰይጣን ደቀ መዝሙር ለማለት ነው። እንደዚህ ያሉን ሰዎች “ኢየሱስ ፍቅር ነው” እያሉ ሲዘመሩ የሚውሉ ናቸው። አልትመቸናቸውም መሰለኝ ስም አወጡልንና ምእመኖቻቸው ለእኛ እንዳጸልዩ አዋጅ አሳወጁ። እራስህን ለመሆንና ሌላውን ሳትነካ እንደሚመችህ ስትኖር አትወደድም። ማጎብደድ የሚባለውን ሙያዊ ዝሙት መፈጸም ግዴታ ነው።
ዛጎል፡- አያ ሙሌና አንቺን ምን አገናኛችሁ?
ስንዱ፡- ነብሱን ይማረወና ኢህአዴግ የገባ ሰሞን ኢያሱ በርሄ ትግራይ እንዲወስደኝ ጠይቄው በቀጠሮ ሰዓት ስንገናኝ አያ ሙሌን አስከትሎ መጣ።
ዛጎል፡- ምን ይመስል ነበር?
ስንዱ፡- ኢህአዴጋዊ አለባበስ የለበሰ፣ ጨብራራ፣Kahlil Gibran የካህሊል ጅብራን መጽሃፍ በጁ የያዝ በቃ እሱ እንደሚለው ” ለዓይን የማይሞላ” ግን ታጋዮች መጽሃፍ የሚያነቡ ሰለማይመስለኝ ነበዩን ይዞ ስመለከተው ገረመኝ። ካህሊል ጅብራን አሳቢ ሰው ነው። በግሌ ከሱ በላይ አሳቢ ያለ አይመስለኝም። አጥናፍ ዘልቆ ይመራመራል። ብሩህ ነው። አያ ሙሌና ካህሊል ይተዋወቃሉ።
ዛጎል፡- ለመጀመሪያ ጊዜ አንቺ ውይስ እሱ ተነፈሳችሁ?
ስንዱ፡- እኔና ኢያሱ እስክንጨርስ ምንም አላለም። ጨርሰን ቻው ስላቸው ” ወዴት ነው?” አለኝ። ”ጓደኞቼ ጋር” አልኩት። ” ምን ልትሰሩ?” ሲል ጠየቀኝ። ” ዱአ ልናደርግ፣ ልናወራ፣ ልንጫወት..” አልኩት። አስከትሎ ከእኔ ጋር መምጣት እንደሚችል ፈቃድ ጠየቀ። ይዤው ሄድኩ … ስድስት ኪሎ ማይክ ቤት ሄደን ፍልስፍናና ፖለቲካ በለትን። ወደዱት፤ ወደዳቸው። ሙሉጌታ በወሎ ዘዬ ሁለት ደቂቃ ካወራልህ ተወደዋለህ። አፉ ማር ነው።…. ብቻ እዛ ዋልንና ሲመሽ ወደቤቴ ሸኘኝ።
ዛጎል፡- ከዛስ?
ስንዱ፡- ምን ከዛ አለው። የት ይዞኝ የሄደ መሰለህ? ቤቴ ስንደርስ እዚህ ደርሶ ቤት ሳይገባ? አልኩና ግባ አለኩት። ገና እግሩ ወደ ቤት ከመግባቱ አባቴ ተነስቶ ” ሙሉጌታ ተሰፋዬ ከየት መጣህ? ከየት ተገኝህ?” ሲለው ጭንቅላቱን ይዞ አባቴ እግር ላይ ወደቀ።
ዛጎል፡- ዘምድ ሆኖ ተገኘ?
ስንዱ፡- አባቴ ወልደያ አስተምሮታል። በነገራችን ላይ አባቴ ሼኽ መሐመድ አል- አሙዲንንም እዛው ወልደያ አስተምሮታል። አያ ሙሌ ሲጫወት አደረ። በዛው ቤተሰብ ሆነ።
ዛጎል፡- በዘመኑ ቋንቋ ” ጥልቅ” ጓደኛ የሆናችሁት እንዴት ነው?aya-mule
ስንዱ፡- እሱ ጠይቆልኝ ይመስለኛል አብዮታዊ ዴሞክራሲ ተቀጠርኩ። ስራ ቦታችን አንድ ሆነ ፤ተናበብን። ጥልቅ በለው ስምጥ ታሪኩ ይሄ ነው።
ዛጎል፡- እና ኢህአዴግ አድርጎ መለመለሽ ማለት ነው?
ስንዱ፡- ወዴ ወዴት? እኔ በድርጅት ደረጃ የቤተሰቤ አባል ከመሆን በዘለለ የማውቀው ነገር የለም። ደግሞም ባህሪዬና ፍጥረቴ አይፈቅድም። ብዙም አልሰራሁም። አቶ መለስን ለምን ያልተባልሺውን ጠየቀሽ አሉ። በዛው ተሰነባበትን።
ዛጎል፡- ከአያ ሙሌ ጋር የሚያመሳስል ነገር አላችሁ?
ስንዱ፡- የሚያመሳስል ሳይሆን የሚያሳስብ…

ዛጎል፡- ይሚያሳስብ?
ስንዱ፡- የልብ መናበብ…
ዛጎል፡- የልብ መናበብ?
ስንዱ፡- አይገለጽም። ለራስህ የሚገባህ ስሜት ነው። ጥልቅ ነገር ነው። በቃ መናበብ ነው። በነገራችን ላይ ሙሌን ካላነበብከው አትረዳውም። እሱም አይረዳህም። ይህ ክፍተት ነው።
ዛጎል፡- አንዳንዶች ከተስፋዬ ገብረ አብ ጋር ያመሳስሏቸዋል፤
ስንዱ፡-ሳቅ!! ጮኸች… መስፈሪያ ቢስ መሆን ማለት ይህ ነው። ፈስና ፉጨት እንዲት አንድ ይሆናሉ። የማይሆን። ሊሆን የማይችል ማወዳደር …. የለሁበትም!!
ዛጎል፡- ምን አልባት በስብዕና እንዳይሆን?
ስንዱ፡- ሁለቱ የሚመሳሰሉበት አንድ ነጥብ ነገር የለም። ፈስና ፋጭት…. ሙሉጌታ እኮ ይቅርታ ለቃሉ ጻድቅ ነው። በስማቸው ጻድቅ ተብለው መጠሪያ እንደተሰየመላቸው ሁሉ እሱም ሊደረግለት የሚገባው ነው። አያ ሙሌ ወደፊት ቀና ትውልድ ሲመጣ የሚገን ሰው ነው። ታሪኩ የሚዘከር ሰው ይሆናል።
ዛጎል፡- አልገባኝም። እስከ ጽድቅና አደረሺው…
ስንዱ፡- እሱን ለማንበብ እና እሱ እንዲያነብህ የታደልክ ሰው ብትሆን አባባሉ ግራ አይገባህም ነበር።
ዛጎል፡- አውቀዋለሁ እኮ..
ስንዱ፡- ማወቅና መናበብ አይለያይም?
ዛጎል፡- ይለያያል። እጅግ ሰፊ ልዩነት አላቸው። ግን ፍቅርሽ እንዳይጋነን ብዬ ነው፤
ስንዱ፡- የሙሌ የአስተሳሰቡ ደረጃ፣ አኗኗሩ፣ ደግነቱ፣ ሁሉም ነገሩ ኢየሱሳዊ ነው። አያግበሰብስም። ስራ ሲሰራም በማሪያም መንገድ ነው። መፈራረም ፣ውል መግባት… አይወድም። ሰው ያምናል። ሁሉኑም ነው የሚያምነው። ሲክዱት እንኳን ” ስቡንም፣ ስሙንም ትቼላቸዋለሁ። እዛው ይድመቁበት” ነው የሚለው። ክስ፣ ወቀሳ፣ ሃሜት፣ …. አልተፈጠሩበትም።
ዛጎል፡- ለውጫዊ ውበት ምን ሃሳብ አለው?
ስንዱ፡- የገባው ነው። የነቃ ነው። ” እኔ ለአይን አልሞላም ” ይላል። ከእኔ ጋር ጸባችን senedu-1እዚህ ላይ ነው። እሱ ለዓይን የሚሞላ ሰው አይደለሁም እና ስለ እኔ ብለሽ አትከራከሪ ይላል። ዋናው ጉዳይ የውስጥ መናበብ ካለ የውጪው ጉዳይ ብዙም ነው። ላይታይም ይችላል። መጽሃፉ የውስጥ አይን ሲበራ…. እንደሚለው
ዛጎል፡- እሱን ለማወቅ የግድ በጥልቀት መቅረብ ግድ ነው? እያልሽ ነው?
ስንዱ፡-የጊዜና የጥልቅ ጉዳይ አይደለም። እሱን ለመረዳት ግን ደግ መሆን ግድ ነው። እጅግ ቸር ያልሆነ ሰው እሱን ሊረዳው አይችልም። ” በልተህ ላትበላ ማዕድ አታስፈትፍተኝ፣ ጠጥተህ ላትጠጣ ጋን አታስከፍተኝ ውጣ” የሚለው አባባል አለው። ሙሌ ከማይመቸው ሰው ጋር ሁለት ደቂቃ አይቀመጥም።
ዛጎል፡- ደጋግመሽ ቸር ትይዋለሽ …
ስንዱ፡- አዎ! ያለውን ሳይሸሽግ የሰጠ ሰው ነው። ቢያንስ ግጥሞቹ፣ ሙዚቃዎች… ይመሰከራሉ
ዛጎል፡- ታዲያ ለምን ገኖ አለወጣም? ለምሳሌ በሚዲያዎች
ስንዱ፡- ኽም!! ሙሉጌታን ዋንኞች ፖለቲካኞች፣ ባለስልጣናት፣ሙዚቀኞች፣ ጋዜጠኞች፣ ሚዲያውዎች ሁሉም ያውቁታል። አገሪቱ ግን የቡድንና የአሸርጋጆች፣ የአጎብዳጆችና የሰጋጆች በመሆኗ እድሉን አላገኘም። ”አላጎነብስም” የሚል ሰው ስለሆነ .. ከላይ እንዳልኩት ነው ሙያዊ ዝሙት በነገሰበት፣ ሙያዊ መራከስና ሙያዊ… ኢህአዴጎቹ የድግሳቸው አድማቂ ያደርጉታል። በአል ሲኖራቸው ሁሉም እሱን ፈላጊ ናቸው። እሱ ያላደመቀው በአል የለም። ግን አጎብዳጅ ባለመሆኑ የሚገባውን ቦታ አላገኘም። እኔ እስከማውቀው አለቤ ሾው፣ ፈርጥ መጽሄትና ሪፖርተር ብቻ ናቸው ያስተዋወቁት።
ዛጎል፡- ጥላሁን ገሰሰ በጥፊ እንደመታው አጫውቶሻል?
ስንዱ፡- አንድ የሙዚቀኞች ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ጥላሁን ” እኔን የሚተካኝ የለም” ሲል ” ለምን ትታበያለህ” አለው። የዛኔ ጥላሁን በጥፊ አጮለው። ”ዝም አልከው ታዲያ” ስለው፣ ” ጥፊ እርዝቄ/ ሽልማቴ ነው” ብዬ መጣሁ አለኝ።
ዛጎል፡- ሱሰኛ ነበር?
ስንዱ፡- የሌለበት ሱስ የለም። ተፈጥሮንም የማነጋገር ሱስ ነበረበት።
ዛጎል፡- እንዴት?
ስንዱ፡- ትላትል፣ ዝንብ፣ ዛፍ፣ ወፎች፣ ፍጥረት በሙሉ ያናግራል።
ዛጎል፡- አስኪ አንድ ምሳሌ ስጪኝ፤
ስንዱ፡- አንዴ ጉኖ ዘመናይ ስሚ አለኝ።
ዛጎል፡- ማን ነች ጉኖ?
ስንዱ፡- እኔው ነኛ!! ጉኖ ዘብናይ ነው የሚለኝ። እና አንድ ቀን ጉኖ ዘመናይ ስሚ አለኝ እና ይህንን ነገረኝ። የአበበ ተካን ካሴት የሰራበትን ከ100 ሺህ በር በላይ ይዞ እትውልድ ስፍራው ሄደ። እዛ ሁሉንም አንበሽብሾ ብሩ አለቀበት። ወደ አዲስ አበባ መመለሻ አጣ። ጓደኞቹ አዋጡና አሳፈሩት።አውቶቡስ ውስጥ ተቀምጦ እየተጓዘ ሳለ ቱኳን ነከሰው። እጁን ትኳኑ እለመዘገው ቦታ ሰዶ ያዘው። በጣትና በጣቱ ይዞ አፈጠጠበት። ” እኔ እየቆነጠጥኩህ ባላነቃህ ኖሮ እዚህ ትደርስ ነበር?” ሲል ቱኳኑ መለሰለት።
ዛጎል፡- ከዛ ገደለው?
ስንዱ፡-አበድክ እንዴ? እያነጋገረው እንዴት ይገለዋል? ሙሌ ምንም ነገር ገሎ አያውቅም።
ዛጎል፡- እና ቀስ ብሎ ቦታው መለሰው?
ስንዱ፡- አይ ሙሌ መከራህ አልኩ እንጂ ቀጣዩን አልጠየኩትም።
ዛጎል፡- ሙዚቃ ይሰማል?
ስንዱ፡-በጣም። ድንገት ያልሰማው ቆንጆ ሙዚቃ ሲሰማ ” ይህንን ሁሉ ሳላውቅ እንዴት በክቼ ኖሬያለሁ” ይላል።
ዛጎል፡- ስራ እንዴት ለቀቀ?
ስንዱ፡- እሱ በጻፈው ግጥም ውስጥ አንድ ቃል ተቀይሮበት፤
ዛጎል፡- ብታስረጂኝ?
ስንዱ፡- አንድ ግጥም ውስጥ ” ቅቅርት” የሚል ቃል ተጠቅሞ ነበር። ከዛ የቃሉን ትርጉም የሚያውቅ ጠፋ። ከዛም ኤዲተሮቹ ቅቅርት የሚለውን ቃል ከግጥሙ ፍሰት አንጻር ” ብሎን” ይሆን አሉና ቀየሩት። እሱ ግጥሙን ሰጥቶ ስለሄደ ሊያገኙት አልቻሉም። ተቀይሮ ታትሞ ሲያይ ተናደደ። “እንዴት ተቀየረ” ብሎ አበደ። ቢሮውን ጥሎ ወጣ። ቀረ! ቀረ!
ዛጎል፡- ግን እኮ ሁሌም ስራ ይቅራል፤
ስንዱ፡- አዎ!! ” ተውሎብኛል፤ የዋለብኝ አይጠቀም፤ የት እንደምውል፣ ማን እንደሚውልብኝ አለውቅም” ይላቸዋል። በዛው ግምገማው ይቆማል።
ዛጎል፡- ከዛ ለመመለስ አልተሞከረም?
ስንዱ፡- ብን ብሎ ጠፋ። የት እንደገባ የሚያውቅ ጠፋ። ሰንጋተራ ራሺያ አፓርታማ ይኖር ነበር እሱንም ለቆ ተሰወረ።
ዛጎል፡- በስተመጨረሻ የት ተገኘ?
ስንዱ፡- አንድ ቀን ለሞውሊድ አባቴ ቤት መጣ፤
ዛጎል፡- ስንት ልጆች ነበሩት?
ስንዱ፡- ሁለት ናቸው። ሃዋ ብስል እና ዳኔል ሙሉጌታ/ ሼኽ አብዱ እሱ በጠፋበት ወቅት ዳንኤልም ጠፋ። ሃዋን ቤቴ ወስጄ ከእኔ ጋር መኖር ጀመረች።
ዛጎል፡- ግን ሲመጣ የት ጠፋሁ አለ?
ስንዱ፡- ማን ይጠይቀዋል? ሲጠፋ ይጠፋል። ሲመጣ መጣ ነው።

ዛጎል፡- ከአቦይ ስብሃት ጋር እንዴት ይናበባሉ?
ስንዱ፡- እኔ ቤት ተዋወቁ። እሱ ግጥም ያነባል። እሳቸው ስቅስቅ ብለው ያለቅሳሉ። ” ሎሬት” ነበር የሚሉት። በጣም ያከብሩታል። እሱም ” መርቁኝ” ይላቸው ነበር።
ዛጎል፡- ሁለቱ የተለየ ገጠመኝ አላቸው?
ስንዱ፡- እሱ ግጥም ሲያነብ እሳቸው ያለቅሳሉ። ስቅስቅ ብለው!!
ዛጎል፡- ስለ አላሙዲን ያወራል?
ስንዱ፡- እንደውም። አንስቶም አያውቅም። እሱ ሰለ ድሆች፣ ስል ወፎች፣ ስለ ማርያም፣ ስለ አምላክ፣ ስለ ኢየሱስ ነው ማውራት የሚወደው።
ዛጎል፡- በከፍተኛ ደረጃ ተፈጽሞበታል የምትየው ክህደት አለ?
ስንዱ፡-ሙሌ ሙሉ ማንነቱ የተካደ ሰው ነው። በተለይ ሜጋ ማንነቱን ሳይቀር ውጦታል። እሱን ያልካደ አዝማሪ የለም።
ዛጎል፡- የአቶ በረከት ስምዖን አፍቃሪ ነው ይባላል?
ስንዱ፡- በጣም ይወደዋል።” ከኢህአዴግ ጋር ያጋባኝ ስር ሚዜዬ” ሲለው እሰማለሁ።
ዛጎል፡- ኢህአዴግን ይወዳል?
ስንዱ፡- በጣም። ” የእነሱ ወዳጅ ነኝ። የምታገለውም እነሱኑ ነው” ይል ነበር።
ዛጎል፡- በረሃ ነበር?
ስንዱ፡-“ከሃብተ ጊዮርጊስ ድልድይ ነው የተቀላቀለኩት” ይል ነበር።
ዛጎል፡- ይበሳጭባቸዋል?
ስንዱ፡- ጥሎ ከመጥፋት ሌላ ምን አለ?
”አማራ ነኝ ደሜ አረንጓዴ፤ የማንም ጣባ ስር የማልላገት ….” ብሎ ፊታቸው ገጥሞላቸዋል።
ዛጎል፡- በህይወትሽ የማትረሺው ነገር አለ?
ስንዱ፡- ቅዱስም ንጉስም መሆን ከሚፈልግ ሰው ጋር መኖር ልዩ ነውና አይረሳም። ይኸው ሞቶም ይዘከራል። ቅዱስ ላሊበላ የእሱ ጀግና ነው።
ዛጎል፡- ለምን?
ስንዱ፡- መቀደስም መንገስም ይፈልግ ነበራ!
ዛጎል፡- ከሌለሽ በርሽ ላይ ኩርምት ብሎ ይጠብቅሽ ነበር ተብሎ ተጽፏል?
ስንዱ፡- ምስኪን ነው ኩርምት የሚለው። እሱ ንጉስ ነው። የሚያኮማትረው ነገር የለም። ካለሁ ይገባል። ከሌለሁ በር ላይ ካሉት ጋር እየተጫወተ ይጠብቀኛል። ምስኪን የሚሉት ለዓይን ስለማይሞላ ይሆናል። ነገር ግን እሱ ማንም ጸጥ ለጥ ብሎ የሚያስተናግደው ንጉስ ነው።
ዛጎል፡- የሱን ስራዎች ሰብስበሽ ለማሳተም እንዴት ተነሳሳሽ?
ስንዱ፡- ኢህአዴጎቹ ስም መጥራት አልፈልግም ስራዎቹን ሰብስቢና ይታተም አሉኝ። በዚሁ መሰረት እነሱ ጋር ጽሁፎቹ ተጻፉ። በመካከሉ ሃሳባቸውን ቀየሩ። እልህ ያዘኝና ራሴ አሳተምኩት። ግንቦት 20 ቀን ሆነ ብዬ ድንኳን ጥዬ አስመረኩት።
ዛጎል፡- ተሸጠ?
ስንዱ፡- አከሰሩኝ፤
ዛጎል፡- እንዴት?
ስንዱ፡- ሜጋ ባሉት የመጽሃፍት መደብሮች ውስጥ ገብቶ እንዳይሸጥ አሉ።
ዛጎል፡- ለምን?
ስንዱ፡- ጠይቃቸው፤ ለእኔም በወቅቱ ግራ የገባኝ ጉዳይ ነው።
ዛጎል፡- እና ምን ሆነ?
ስንዱ፡-የተወሰነ ተሸጠ፤ የተቀራውን ማተሚያ ቤት እንዳለ ትቼው ጠፋሁ። ባለ እዳ ነኝ። ይኸው ነው፤
ዛጎል፡- ይቅርታ እንደው በባህል እንደሚባለው ዛር፣ መንፈስ፣ …. አለብኝ ብሎሽ ያውቃል?
ስንዱ፡- እኔ እንዲህ ነው ለማለት ይከብደኛል። ግጥም ሲጽፍ ”አሺያ ጨብራሪት” መጣች ይላል። እሷ ሹክ እያለችኝ ነው የምጽፈው ይላል።
ዛጎል፡- ትንቢት ምናምን ይሞካክራል?
ስንዱ፡- ምን የማይለው ነገር አለ ብለህ ነው። ሁሉንም ያደርጋል። ይተንብያል። የፍርድ ንግግርም ይናገራል.. ያለው ይሆናል።
ዛጎል፡- አንዳንዴ ያሰፈራራል?
ስንዱ፡- በፍጹም አያስፈራም። ትሁት ሰው ነው፤
ዛጎል፡- የልጆቹ እናትስ?
ስንዱ፡- ገጠር ናት። ስለ እሷ ብዙም አይናገርም። አንዴ ውል ብሎበት ”ሃዋ ስትወለድ ሚስቴን ያወለደኩት እኔ ነኝ” ብሎኛል።
ዛጎል፡- ከሱ ምን ተማርሽ?
ስንዱ፡- ደግነትን!!
ዛጎል፡-እና ደግ ነሽ?
ስንዱ፡- እንዳንተ፤
ዛጎል፡-እኔ ደግ ነኝ?
ስንዱ፡- ስትሞት ይወራልሃል፤
ዛጎል፡- የስብሃትና የአያ ሙሌ አኗኗር ተጭኖሻል የሚሉ አሉ?
ስንዱ፡- ደግነት ውስጣዊና ተፈጥሯዊ ይመስለኛል። በእርግጥ ሁለቱም ነጻ ሰዎች ስለሆኑ የነሱን የወረስኩ ይመስለኛል። ከእነሱ ጋር መኖር የለምደ ከሌሎች ጋር ለመኖር ይቸገራቸዋል። እኔም ላይ ይህ የተንጸባረቀ እንደሆነ ይሰማኛል። ግን እኮ ነጻ ሆኖ እንደመኖር የሚመች ነገር የለም።
ዛጎል ፡-ሰለ አያ ሙሌ የተጻፈውን አዲሱን የባለቅኔው ኑዛዜ መጽሃፍ አየሺው?
ስንዱ፡- አልደረሰኝም። ላኩልኝ ብያለሁ። ስለዚህ ስለመጽሃፉ ለመተንፈስ የሚያስችለኝ መረጃ የለኝም። በበጎም ሆነ በመጥፎ።
ዛጎል፡- ቀደም ሲል መረጃው አልነበረሽም?
ስንዱ፡- መጽሐፉን ያዘጋጀው ፋሲካ የሚባል ወጣት የሙሉጌታን ህይወት ማጥናት እፈለጋለሁ ብሎ ስራዎቹን በሙሉ አትሜ ሰጥቼዋለሁ። አሁን ያለሁት አገር ቤት ባለመሆኑ እንዴት አድርጎ እንደሰራው መረጃ የለኝም።
ዛጎል፡- ልጁ ቅሬታ አላት እየተባለ ነው?
ስንዱ፡- ሰምቻለሁ። የመጨረሻውን ጽሁፍ ሳያሳያት ነው ያሳተመው የሚል ነገር አለ። ባይሆን ጥሩ ነበር። ይህን እንግዲህ የምንገመግመው ስናነበው ነው። የሌለ ነገር ተብሎ ከሆነ ደግ አይደለም። በዚህ ጉዳይ ወድፊት ብንወያይ?
ዛጎል፡- ሊሎች የሱ ስራዎች እጅሽ ላይ አሉ?
ስንዱ፡- አዎ!! አንድ ስድስት ሰዓት የሚፈጅ ቲያትር ወይም ፊልም ሊሆን የሚችል ድርሰት አለ። የተማሪዎች ንቅናቄ ታሪክን የያዘ። የእነ ዋለልኝ ታሪክ ከሽኖ ሰርቶታል። እዲሰራ ለአቶ በረከት ስምዖን አራብቼ ሰጥቼዋለሁ። ሌላም ቲያትር ለአቶ በረከት እንደሰጠ ርዕሱን ጨምሮ ነግሮኛል። ብዙ ስራዎች ኢህአዴጎች ጋር እንደሚኖር አልጠራጠርም።

sendu-4
ዛጎል፡- አንቺ ጋር ያሉ የሱን ስራዎች የሚፈልግ ቢመጣ ለመተባበር ፈቃደኛ ነሽ?
ስንዱ፡- የሙሉጌታ ስራዎች የህዝብ ናቸው። ማንም ሳያጭበረብር መጠቀም ከፈለገ ለመተባበር ዝግጁ ነኝ። እኔ የምጠላው ተራ ማጭበርበር ብቻ ነው።
ዛጎል፡- ሰለ አሟሟቱ ምን ታውቂያለሽ?
ስንዱ፡- እንደሚፈልገኝ ደውለው ነገሩኝ። ላገኘው ወደ አለም ገና እየሄድኩ ሳለ መልሰው ደውለው ህይወቱ ማለፉን ነገሩኝ። ደንግጬ ለኢህአዴጎች ነገርኩ። ጥሩ አድርገው ቀበሩት።
ዛጎል፡- አሟሟቱ ያጠራጥራል?
ስንዱ፡- በግሌ እጠራጠራለሁ። ጌታ ይወቀው። ለነገሩ የኖሩት ከሞቱት ሲሻሉ አይደል? አየህ በዛን ሰሞን ቤት ተከራይቶ በአግባቡ መኖር ጀምሮ ነበር። ወደ ሞት የሚያመራ ነገር አይታየበትም ነበር። ተወኝ ባክህ አንዱም መጽሃፉን ማንበብ የፈለኩት ለዚሁ ነው። ሆቴል ውስጥ ምን እና እንዴት ሆቴል  ወስጥ ህይወቱን እንዳለፈ… ያሳዝናል።
ዛጎል፡- ምን እየሰራሽ ነው?
ስንዱ፡-የፈረንጅ አገር ስራ ነዋ! አንተስ?
ዛጎል፡- አንቺን ቃለመጠይቅ እያደረኩ፤
ስንዱ፡- እስኪ ይሁን…..

ከስንዱ አበበ ጋር የማደርገው ቃለ ምልልስ አላለቀም። በህየወትዋ፣ ከጋዜጠኛነት ስራዋ ጋር በተያያዘ፣ በአሳታሚነት እንዲሁም አሁን በአሜሪካ ይቀጥላል።

“የባለቅኔው ኑዛዜ”-አያ ሙሌ ከአፍቅሮተ ነዋይ የራቀ የከተማ መናኝ!!  ሊንኩን ተጭነው ያንበቡ

Share and Enjoy !

0Shares
0

1 Comment

  1. Aya Mule = Saint
    Senedu = Compassionate

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *