በደርግ ጊዜ ጉዋድ ኮምጨ ፤በደብረማርቆስ አደባባይ ገበሬዎችን ሰብስቦ ይሰረብታል :: (በጎጃም አማርኛ ሰረበተ ማለት ፕሮፖጋንዳ አደረገ ማለት ነው::)

” ያገራችን አርሶ አደር ከቻይና ገበሬዎች ልምድ መቅሰም አለበት ” አለ ኮምጨ ፤” የቻይና ገበሬዎች፤ የአብዮቱን ፈታኝ ዘመን ለማለፍ ጫማቸውን እስከመብላት ደርሰዋል “ይሄን ግዜ አንዱ አድማጭ ገበሬ” እኛኮ እንደቻይና ገበሬ ጫማ የለንም ፤ምን እንብላ?”

ጉዋድ ኮምጨ ያልጠበቀው መልስ ስለነበር ተናዶ ፤ “ዋ! እና የኔን ጫማ ልትበላ አምሮሃል ?! ተፈልግህ፣ ለምን ቁርጭምጭሚትህን አትበላም?” አለው ይባላል::

ጠቅላይ ምኒስትሩ ” ቻይናና ኮርያ እኛ በነበርንበት ደረጃ ላይ ፤የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት ሲሉ የሴቶቻቸውን ፀጉር ይሸጡ ነበር “ብለው ተናገሩ ሲባል ብሰማ ይሄ ወግ ትዝ አለኝ::

Related stories   የመረጃ መንታፊዎች ዋትሳፕን እንደ ጥቃት ማድረሻ መሳሪያ እየተጠቀሙ መሆኑ ተገለጸ

ባጋጣሚ ይቺን እየፃፍኩ ሳለ፣ምሽቴ ከፀጉር ቤት ተመልሳ ፤በሩን ከፍታ ገባች ፤ መቸም ሁለመናየ ግጥም ነውና እንዲህ የሚል ግጥም አመለጠኝ

ፀጉርሽን ተሰርተሽ፤
ጀርባሽ ላይ ነስንሰሽ
ተሽሞንሙነሽ ፤መጣሽ
ቡዳስ መቸም የለም ፤ ከመንግስት አይን ያውጣሽ::

እናቶቻችን የሴት አንበሳን አርአያ በመከተል፤ ፀጉራቸውን ያሳጥሩ ነበር:: ወይዛዝርት ሆይ !ፀጉራችሁን በመሸለት የአናቶቻችንን ባህል አስፋፉ:: ኢኮኖሚውንም ደግፉ::

ግመል ወደ ሁዋላ የሚሸናው በአህያ ሴራ ምክንያት መሆኑን ያውቁ ኑሩዋል?

በመጀመርያ ፣ አይመረመሬው ወንድ ፍጥረታትን ፈጠረ:: የርቢ አካል እንደሚያስፈጋቸውም ተገነዘበ:: ብልት ያከፋፍል ዘንድ አህያን ሾመው:: አህያ ስልጣኑን አላግባብ በመጠቀም ፣ ዘለግ ያለውን ብልት ለራሱ መርጦ አመድ ውስጥ ሸሸገው::
ከዚያም በወረፋ ደጅ ለሚጠኑት ፍጥረታት እንደ ሸንኮራ እየቆረጠ ማደል ጀመረ:: አዳም መጣ አስመዝኖ ተከራክሮ ድርሻውን ወሰደ:: በሬ መጣ፤ ተረከበ:: አውራ ዶሮም መጣ ከፍቅፋቂው ማህል ድርሻውን አነሳ:: ሲመሽ ፤ ጉዋድ አመዶ ፣ ለሁሉም ፍጥረታት ድርሻቸውን ማስረከቡን አምኖ ፣የራሱን ድርሻ ለመትከል ሆዱ አካባቢ ቦታ ሲያማርጥ ኮቴ ሰማ:: ቀና ሲል ግመል ከፊቱ ቁሙዋል::

Related stories   እኛ የምንመርጠው አባትና አያቶቻችን የመረጡትን ነው።

“ይቅርታ ትንሽ ስራ በዝቶብኝ ዘገየሁ:: ድርሻየን ወዲህ በል” አለ ግመል እያለከለከ:: “የማውቅልህ ነገር የለም:: በሰኣቱ ያለውን ሁሉ አከፋፍየ ጨርሻለሁ::” አለ አህያ በንዴት ጋማውን እየነጨ::

ከጥቂት ርግጫ ቀረሽ ጭቅጭቅ በሁዋላ ግመል ” እምቢ ካልክ ለፈጣሪየ እከስሃለሁ “ብሎ ዞር ብሎ መጋለብ ጀመረ:: ይህን ጊዜ አህያ በጣም ተናዶ፤ ለራሱ ካስቀመጠው ትንሽ ጎርዶ “ያውልህ “ብሎ ቢወረውር በግመል ጉያ ላይ ተገልብጦ ተለጠፈ:: ተዚያን ጊዜ ጀምሮ ግመል የሁዋሊት ይሸናል::

Related stories   የመረጃ መንታፊዎች ዋትሳፕን እንደ ጥቃት ማድረሻ መሳሪያ እየተጠቀሙ መሆኑ ተገለጸ
Bewketu Seyoum fb.

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *