“Our true nationality is mankind.”H.G.

በፕ/ሮ ኃይሌ ላሬቦ፣ ኢሳት- የሕዝብ አስተያየት- የሰርጸ እይታ

እስኪ ነገሩን በእርጋታ ለመቃኘት እሞክራለሁ እኔንም ትንሽ ቢያበሳጨኝም፡፡ ሰሞኑን ብዙ አወዛጋቢ ሆኖ የቆየው በኢሳት ቃለ ምልልስ የተደረገላቸው ፕ/ር ኃይሌ ላሬቦ በቃለምልልሱ ወቅት የተናገሯቸው አንዳንድ ነገሮች ናቸው፡፡ ኃይሌ ብዙ የታሪክ ጭብጥነት ያለው ጉዳይ ቢያሳውቁንም አንዳንድ ቦታ ላይ መጀመሪያ ራሳቸው እንደተናገሩት በሙሉ ምሁራዊ ገለልተኝነት ሳይሆን አነጋገራቸው ወገንተኝነት ነገር የሚታይባቸውን አገላለጽ የተጠቀሙ መስሎ ተሰምቶኛል፡፡ ወደ መጨረሻው አወዛጋቢ የቃላት አጠቃቀማቸው ከመድረሳቸውም በፊት አንዳንድ ቦታ ላይ እረ የሚያስብል ንግግር ይደመጥባቸው ነበር፡፡ እንግዲህ እውንም የሚያምኑበትን ነው ወይስ እንደው የሆነ ለራስ ምኞትና ፍቃድ ከማድላት የሚለው ነገር ለራሳቸው ልተውላቸውና ወደ ዋናው ብዙዎችን ያነጋገረው የመጨረሻው የኦሮሞን ሕዝብ የገለጹበት አነጋገር ለውሰዳችሁ፡፡

ይህ የቃል አጠቃቀም እውንም ከንጹህ ምሁራዊ አገላለጽ ነው ወይስ ለብዙዎቻችንም ጆሮ እንዳሳከከን ከጎደፈ አእምሮ የሚለውን እንወያይ፡፡ ኃይሌ በሌላ ቪዲዮ ማብራሪያ እንደሰጡበት ከሆነ መልካም እውንም ነጻ ናቸው ያሰኛል፡፡ በእርግጥም ማብራሪያ በሰጡበት መልኩ ቃሉ ምንም ነውር የለውም እንድውም የመልካምነት መገለጫ ነው፡፡ በእርግጥም ኃይሌ በቃለምልልሳቸው ወቅት የባዕድ ቃል ላለመጠቀም አንዳንድ በአማርኛም ብዙም ተዘውትረው የማይነገሩ ቃላትን ሲጠቀሙ እናያለን፡፡ ይሄ መልካም ነው፡፡ ይህ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ግን በቃለ ምልልሳቸው ወቅት የኦሮሞን ሕዝብ ለመግለጽ የተጠቀሙበት አገላለጽ ለብዙዎቻችን የተሰማን ከመልካምነቱ አንጻር አደለም፡፡

ቃሉ በመልካምነት ሲነሳና በተንኮል ሲነሳ የተለያየ ድምጸት አለው፡፡ ኃይሌ እረኛ የሚለው ቃል በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ አንድን ሰው በመልካም ወይም በንጹኅ ህሊና ለመግለጽ እንማይሆን አይረዱትም የሚል እምነት የለኝም፡፡ በእርግጥም በመልካም ወይም በነጻ ህሊና እረኛ የሚለው ቃል ለሰው ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህንንም ሕዝብ ይረዳል፡፡ ይህ ግን ሊሆን የሚችለው ማብራሪያ ወይም አጭር ሊገልጹበት የፈለጉት ትርጎም በይፋ ከተነገረ ነው፡፡ ወይም አጠቃላይ የንግግሩ ሂደት መልካምነቱን ለማመልከት የሚያሳይ ሆኖ ሲገኝ፡፡ ኃይሌ እረኛ የሚለውን ቃል የተጠቀሙበት የንግግራቸው ሂደት ግን ይሄንን አያመላክትም፡፡ ሂደቱ ይሄንን በማያመለክትበት ሁኔታ ቃሉ በሕዝብ ዘንድ በጎ ያልሆነ ትርጉም እንዳለው እያወቁ በወቅቱም ቃሉን የተጠቀሙበትን አግባብ ትርጉም መናገር ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ያንን አላደረጉትም በተከታታይም ልክ ያልሆነ ቦታ ያንንው ቃል በተመሳሳይ ስሜት መጠቀምን ቀጠሉ፡፡

ይሄንን ለል የፈለኩት በኢንግሊዘኛው ”ፓሰቶራል” እንደሚባለው ነው ብሎ ማስተባበል ከአንጀት አያደርስም፡፡  ይህ አንዱ ችግር ነው፡፡ አዎ ከኦሮሞ ሕዝብ መካከል ድሮ ብቻም ሳይሆን ዛሬም ድረስ ከብት አርቢ ሆኖ የሚኖር ሕዝብ አለ፡፡ በእርግጥም ከብት ማርባት አንዱ የመተዳደሪያ ዘርፍ ነው፡፡ ታዋቂውና በእኔ አመለካከት ከሌሎች ሁሉ ፍትሀዊነትንና ስብዕናን ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው የቦረና ሕዝብ በአብዛኛው ዛሬም ድረስ ከብት አርቢ ነው፡፡ ጉጂና ከረዩም አሉ፡፡ በአጠቃላይ ኃይሌ መጀመሪያ ለቃለምልልሱ ሲቀርቡ እንደነገሩን በገለልተኝነት ታሪክን የሚተርኩ ሳይሆን እሳቸውም እንደሌላው የሚወዱትን እያገነኑ የማይወዱትን እያንኳስሱ ከሚናገሩት “የታሪክ ተመራማሪ” እንደ አንዱ በጥርጣሬ እንድናያቸው ዳርጎናል፡፡

ኢሳት ያንን የሚያህል ሰዓት ቃለምልልሱን አስደምጦንና ከራሱ ማህደር (በቀጥታ ስላልነበረ) አቅርቦልን ሳለ፣ የኃይሌን ስህተት ሙሉ በሙሉ ኃላፊነቱ የተጠያቂው ነው ማለቱ ሌላው ሕዝብን የሚያበሳጭ ሆኖ ተሰምቶኛል፡፡ በእርግጥም በቀጥታ ለሚተላለፍ ዝግጅት እንዲህ ያለው ኃላፊነት የተጠያቂው ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ ያም ቢሆን በቃለምልልስ ወቅት ማረም ኢሳትን የወከለው የጋዜጠኛው ኃላፊነት ጭምር ነው፡፡ ከማሕደር የሚቀርብ ዝግጅት ግን ከተናጋሪው ይልቅ የኢሳት ኃላፊነት እንደሆነ ለኢሳቶች ልንነግራቸው ይገባል፡፡ የተሳሳተው ስህተት ሳያንስ የራስን ስህተት ለሌላው መስጠትና ለወደፊትም እንዲህ ያለ ሥህተት ቢፈጠር እኔን አይመለከተኝም ማለት ሌላው ትልቁ ስህተት ነው፡፡ እና ኢሳቶች ተሳስታችኋል፡፡ በይፋ የኦሮሞን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መላውን አድማጭ ሙሉ ኃላፊነቱ የእኛው ነበር ስትሉ ይቅርታ ጠይቁ፡፡

ሌላው ኦሮሞ ነን ለምትሉት ጨምሮ ሌሎች ሁሉ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ከስሜታዊነት በጸዳ ስህተት የፈጸመውን ድርጅት ወይም ግለሰብ ማውገዝ እንጂ አንድ ግለሰብ በፈጠረው ስህተት እንደገና ከሕዝብ ጋር የተገናኘ ስድብንና ነውርን በመናገር ከመጀመሪያው ስህተት የከፋ ስህተት እንዳትሰሩ፡፡ በእርግጥ አጋጣሚው አንዳንድ ጥቂትም ቢሆኑ በጣም በሳል አስተሳሰብ ያላቸውንም ለማየት ዕድል ፈጥሮልናል፡፡  እዚህ ላይ አንዲት ወጣት ኦሮምኛም አማርኛም የምትናገር ልጅ የነበራትን አስተያየትና እርጋታ በጣም አድንቄያለሁ፡፡ ልጅቱ በእድሜ ስትታይ ከብዙዎቻችን ምን አልባትም በየሚዲያው ከምናቅራራው ሁሉ ልጅ ትመስላለች፡፡ በዚህ እድሜዋ ስሜቷን በመቆጣጠር ማስተላለፍ የፈለገቸውን ሀሰብ ለማስተላለፍ የምታደርገው ጥረት እጅግ ያስደንቃታል https://www.youtube.com/watch?v=fxvyYgdwccU&t=506s ሌላም ጊዜ ልጅቱ የምትሰጠው አስተያየት ፊትለፊትና፣ ከልብ የሆነ፣ ድፍረትና ቅንነት የታከለበት ነው፡፡ አብዛኞች  የሰጡት አስተያየት ግን አስቸጋሪና የማይመጥን ነው፡፡

አንድ በብዙዎች ኦሮሞ ነን በሚሉ ዘንድ የተነሳ ሌላ አስነዋሪ ቃል ግን እኔንም ግራ አጋብቶኛል፡፡ ይህን ቃል ብዙ ኦሮሞ ነን የሚሉ ያልታረሙ ሰዎች በተለይ አማራ የተባለውን ሕዝብ ለመስደብ የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም ነበር፡፡ ይሄውም የሥጋ ደዌን በሽታ ከአማራ ሕዝብ ጋር ብቻ ማያያዛቸው እጅግ አስገርሞኛል፡፡ ይሄ እኮ በሽታ ነው፡፡ በሁሉም ማህበረሰብ ሊኖር የሚችል፡፡ እርግጥ ነው በተወሰነ በሽታው ከቤተሰብ ይመጣል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሕክምና የሚድን ነው፡፡ በማሕበረሰብ ደረጃ ግን በሁሉም ባይሆን ቢያንስ ይህ በሽታ በኦሮምኛ ተናጋሪውም ማሕበረሰብ አንድ ችግር እንደሆነ ነው የማውቀው፡፡ ቢያንስ የሻሻመኔውና በዛው በቅርብ ከአርሲ ነጌሌ በ25ኪ.ሜ ምስራቅ የሚገኘው ሆስፒታሎች ይህን በሽታ ለመከላከል የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ከግንዛቤ በመውሰድ ለብዙ ዘመን ይሰሩ እንደነበር ነው የሚታወቀው፡፡ ሲጀምር አንድን ሰው በብሽታ ምክነያት መሳደብ ከምንም የከፋ ስህተት ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን እውነትንም አለመረዳትና እኔ ነጻ ነኝ ሌሎች የዚህ ተጠቂ ናቸው ብሎ ማሰብ አለመብሰል ነው፡፡

ሥጋ ደዌ  በአርሲና በሐረር በብዛት የሚታይ፣ የኦሮሞ ማህበረሰብም ችግር እንደሆነ ነው የሚገባኝ፡፡ ወለጋ ላይኖር ይችል ይሆናል፡፡ እንዳልኳችሁ ነው በሽታው በተወሰነ፣ በቤተሰብም፣ በአካባቢም፣ ከአንዱ ወደ አንዱ ሊተላለፍ ይችላል፡፡ ሥጋ ደዌ በኦሮምኛም በአማርኛም ተናጋሪ ሕዝብ ላይ አለ፡፡ ወለጋ ላይኖር ይችላል፣ ይፋት ላይኖር ይችላል፡፡ ግን በብዙ አካባቢዎች አልፎ አልፎ አለ፡፡ እውነታውን በዚህ መልኩ ከመረዳት በተቃራኒ ማሰበ ደግ አይደለምና ከእንደዚህ አይነት የሒሊና ጉድፍ ራሳችሁን አጽዱ፡፡ በዚሁ አጋጣሚ በስሜት የምትነዱ ኦሮሞ ነን የምትሉ ንግግራችሁ ሕዝብን እንደሚወክል አስቡ፡፡ ልዩ ሴራ ካላችሁ ሥራችሁ ነውና ቀጥሉበት፡፡ ባለማወቅ ግን የምትናገሩት ግን ተጠንቀቁ፡፡

አንዳንዶች አሁን ይህ ገብቷቸው ስሜታቸውን ወደጎን ትተው አሸናፊ የሆነውን ማንነታቸውን እየተጠቀሙበት ነው፡፡ ብዙዎች የኦሮሞን ሕዝብ ጉልበት የሚያሳጡበት ስልት ሆን ብለው ከሕዝቡ ጋር የተያያዘ ስድብ አዘል ቃላትን በመጠቀም ነው፡፡ ሁሉም ሊረዳው የሚገባው ነገር ቢኖር ኦሮሞ ‘የዋህ’ ነው የሚለው ቃል እኔን አይመቸኝም፡፡ ጉዳዩ ደግ፣ ለሰው አዛኝ፣ ሩሩህ ለማለት ሳይሆን በውስጥ ሞኝ ነው እንደፈለግን እንነዳዋለን ነው፡፡ እንዲህ እንዲህ ብለው መጨረሻ የሆነ ቦታ ሲደርሱ ምን እንደሚሉ አስተውሉ፡፡ ሰሞኑን እረኛ የምትለው ቃል አመጣጧ እንዲህ ባለ ሂደት ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ የማውቀው ኦሮሞ ከዚህ ይለያል፡፡

ኦሮሞ ጦረኛ፣ብልህ፣ልዩ ሚስጢራዊ ነው፡፡ ሌላ ትርጉም እንዳትሰጡት ከጥንት ጀምሮ በጦርነት ስልት የሚታወቅ ሕዝብ ነው፡፡ ሶስኒዮስን ጨምሮ ኢትዮጵያን የመሩ መሪዎች ወታደሮቻቸውን በብዛት የኦሮሞ ተወላጆችን የሚያደርጉት ስለገባቸው ነው፡፡ ሚኒሊክ ያደረጉት ይሄ ነው፡፡ በዚህ መንግስት እንጂ እስከደርግ ድረስ የምናውቃቸው ታላላቅ ጀነራሎች በእርግጥም ከኦሮሞ ሕዝብ የወጡ ናቸው፡፡ ኦሮሞ ብልህ ነው፡፡ ለሚኒሊክ አስተዳደር ስኬታማነት ዋና ተዋናዮች እቴጌይቱን ጣይቱን ጨምሮ፣ ሀብተጊዮርጊስና ዲነግዴና ሌሎች ኦሮሞዎች እንደሆኑ እንሰማለን እንጂ እያስተዋልን አይደለም፡፡

አጠቃላይህ ይህ አሁን ያለው የኦሮሞ ትውልድ በተለይ ከሚኒሊክ ጋር ያለውን ታሪክ ሲሳደብ ማንን እየሰደበ እንደሆነ አያስተውልም፡፡ ይህን ነው ብዙዎች የኦሮሞ ሕዝብ ጠላቶች የሚፈልጉት፡፡ የሚኒሊክ ታሪክ ከየትኛውም የኢትዮጵያ ታሪክ ይልቅ በወርቅ ሊጻፍ የሚገባው የኦሮሞ ልጆች የአስተዳደርና የውትድርና ብቃት የታየበት ነው፡፡ ማንም አይሸወድ ዓላማው ሁሉ ከአንዱ ግለሰብ ከሚኒሊክ ጋር የተገናኘ ሳይሆን በዚያን ዘመን የተከወኑ የታሪክ ስኬቶች ሁሉ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር እንዳይያያዝ ሆን ተብሎ በኦሮሞ ሕዝብ ጠላቶችና አንዳንድ የሌላ አገርም (አረብ)ሴራ ያን ታሪክ አሁን ላለው የኦሮሞ ትውልድ ሲዖል ሆኖ እንዲያየው ነው ዕንቅልፍ አጥተው የሚሰሩት፡፡ እነዚህ ሃይሎች ከሞላ ጎደል ተሳክቶላቸዋል፡፡

የአኖሌው ጦርነት እውነታ እኮ ዛሬ እንደሚወራው ሳይሆን ጦርነቱ የተካሄደው በሁለት ጀግኖች መካከል ነበር፡፡ በእርግጥም ጦርነት እንደጦርነቱ የሰው ልጅን ሕይወት የሚጠፋበት በመሆኑ ትልቁ ጥፋት ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ግን የአርሲው ጦርነት ዛሬ ላይ ተንኮለኞቹ እንደሚጠቀሙበት ሳይሆን በወቅቱ በእርግጥም ብዙ ጥፋት እንደጠፋ ራሳቸው ንጉሱ ሚኒሊክ ተረድተው በጣም ስለሕዝቡ አዝነው ወታደሮቻቸው ሕዝቡን አሸንፌዋለሁ በሚል እንዳይበድል አዋጅ ያወጡበት ነው፡፡ የተገዳደራቸውንም የአኖሌውን መሪ ሚኒሊክም ሆኑ ሌሎች የወቅቱ ተዋጊዎች እንደተራ ሰው ሳይሆን የሚያዩት እንደ ጀግና ነው፡፡ ችግሩም እኮ ሁለት ጀግኖች ጦርነት መጋጠማቸው ነው፡፡ ፈሪማ ቢሆነ ጦርነቱም አይኖርም፡፡ ከሽንፈት በኋላም በዚያ ዘመን ያሉ ሰዎች ሲዋጋቸው የነበረውን ሰው እንደጠላት አያዩትም፡፡ ይልቁንም በዓላማ ከተግባቡ በኋላ ይመራው የነበረውን ሕዝብ እንዲመራ ነው የሚሾሙት፡፡

ጦና ከጦርነት በኋላ የተሾሙበት ሂደት የዚሁ አንዱ መገለጫው ነበር፡፡ እንደኔ እንደ እውነቱም ሚኒሊክ ከየትኛውም ሕዝብ በላይ ለኦሮሞው ማሕበረሰብ ትልቅ ግምትና አክብሮት የሚጡ መሪ ነበሩ፡፡ ማሰብ ከቻላችሁ ምንሊክን ከብዙ የውስጥ ሰዎች ፈተና ሆኖባቸው ከነበረው ምክነያት አንዱ ከኦሮሞ ሕዝብ ጋር ባላቸው የጠበቀ ግንኙነት እንደሆነ አስተውሉ፡፡ እስኪ ተመራማሪ ነን የምትሉም ይህን ነገር በዝርዝር እዩት፡፡ መጨረሻም በብዙ ፈተና ኢያሱን ማንገሳቸው ዓላማው ለኦሮሞ ሕዝብ የመጨረሻውን ክብር መስጠታቸው ነበር፡፡ አሁን ስለሚኒሊክ መጥፎነት የምትናገር ኦሮሞ ነኝ ባይ የጠላቶችህን ሴራ እያካሄድህ የጀግኖችና ብልህ  አባቶችህን ክብር እያዋረድህ መሆኑን አስተውል፡፡ እንዴት ይህ እንደተጋረደባችሁ አልገባኝም፡፡ ልብ ወለድ እያነበበን እወነቱን የአባቶቻችንን ክብር አዋረደናልና ይህ እስከሚገባንና የአባቶቻችንን ታሪክ ይቅርታ እስከምንጠይቅ ጊዜ ነጻነት የለም፡፡ ይህ የእኔ የሁል ጊዜ መልዕክት ነው፡፡

ማንም እየተነሳ የሆነ ቃል በተናገረ ቁጥር እየተነሱ በስሜት መደንፋት አያስፈልግም፡፡ ይህ ሴረኞች የሚፈልጉት ነው፡፡ እርግጥ ነው ከላይ እንዳልኩት አጋጣሚው ቢያንስ ትቂት  በሳል አስተያየት ያላቸውን ሰዎች እንድንሰማና ሌሎችም ያልተናገሩ ብዙዎች እንዳሉ ምልክት ሆኖናል፡፡ አጋጣሚዊን መልካም ነገርን ለማስተላልፍ የተጠቀማችሁበት እናመሰግናለን፡፡ አጋጣሚውን በስሜትም ባለማስተዋል ለስድብ የተጠቀማችሁበት አስተውሉ፡፡ ሴራዊ ሂሊና ላላችሁ ግን ሁሌም እንዲህ ያለውን አጋጣሚ ለራሳችሁ ስለሆን የሚትጠቀሙበት እናንተን  እናንተ ቀጥሉ፡፡ ለብዙ ዘመን ከነጭርሱ ከሕዝቡ ጋር የማይገናኙ ዋና የኦሮሞ ሕዝብ ነጻነት አቀንቃኝ መስለው የህዝቡን ትግል አቅጣጫ የሚያስቀይሩ ግለሰቦች እንዳሉም እናያለን፡፡ አንዳንዶቹ ማንነታቸውን ማመን እንኳን ያዳግታል፡፡ ሥማቸውን ሳይቀር የኦሮሞ አድርገው ነው የሚነግዱት፡፡ ለዚህ ደግሞ የትውልዱ ስሜታዊነትና ማስተዋል ማጣት አግዟቸዋል፡፡ ሁሉንም ጊዜ ያወጣዋል፡፡

አመሰግናለሁ!  ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይጠብቅ! አሜን!

 ከሰርጸ ደስታ
ዝግጅት ክፍሉ- በጽሁፉ ላይ የፊደል ለቀማ ከማደርገ በተጨማሪ በጸሃፊው አስተያየት ላይ የሚከተለውን ማከል ወደናል። ጠብታ ውሃ ሲጠራቀም ወራጅ እንደሚሆን ሁሉ በየቀኑ፣ በየጊዜው፣ በየሰዓቱ የሚሰነዘሩ ሃሳቦችና የሚነሱ ጉዳዮች እየተከማቹ ህዝብን ወደማለያየትና ወደ ማቃቃር እያመሩ ናቸውና ጥንቃቄ ቢወሰድ እንላለን። ስህተት ተፈጠረ ቢባልም/ አንጻራዊ ነው/ በጨዋነት ሌላ ስህተት ሳይደገም ሊስተካከል የሚችልበትን መንገድ ማፈላለግ አግባብ ቢሆን፤ በተለይ የኤዲቲንግ ስራ በሚዲያዎች ላይ እንደ ጉደለት ይታያል። ሁሉም ሚዲያዎች በቃለመጠይቅ ወቀትም ሆነ በኤዲቲን ይህዝብን ስሜት ከሚጎዱ ጉዳዮች ላይ ጥንቃቄ ለናደርግ ይገባል።

Share and Enjoy !

0Shares
0
0Shares
0