–  በጋምቤላ ክልል አንዳንድ ክፍሎች ሥርጭቱ 23 በመቶ ሆኗል፤

–  በኦሮሚያ ሻኪሶ አሥር በመቶ ሆኗል፤

–  በየዓመቱ 21 ሺሕ ሰዎች በኤችአይቪ ቫይረስ ይያዛሉ፤

–  32 በመቶ የሚሆኑት ከ15 እስከ 24 የዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፤

ኤችአይቪ ቫይረስ ኬዝ በትክክል ለመጀመሪያው ጊዜ መቼ ታየ ለሚለው ጥያቄ እስከዛሬ ምላሽ አልተገኘለትም፡፡ ይሁንና ከ30 ዓመታት በፊት በአንዳንድ ሰዎች ላይ መታየቱን ተከትሎ የመጀመሪያው ኬዝ በዚያው ሰሞን የተከሰተ ሊሆን እንደሚችል ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

 በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች የሚታይባቸው አንዳንድ እንግዳ የሆኑ የበሽታው ምልክቶች የሕክምና ባለሙያዎችንም ሆነ የዓለምን ሕዝብ ግራ ያጋባ ነበር፡፡ መነሻውንም ለማወቅ ችግር ነበር፡፡ አጥኚዎች ስለበሽታው መነሻ ለማወቅ ብዙ ጥረት ካደረጉ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1999 ቫይረሱ ከጦጣ ወደ ሰው የተላለፈ እንደሆነ መላምት ሰጡ፡፡ መድኃኒቱን ማግኘት ግን መነሻውን እንደመገመት አልቀለለም፡፡

 መድኃኒቱን ለማግኘት ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ባለሙያዎች ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡ ነገር ግን እስካሁን መድኃኒቱን ማግኘት የማይፈታ  እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ በደም፣ ልቅ በሆነ ግብረሥጋ ግንኙነትና በመሳሰሉት ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፈው የኤችአይቪ ቫይረስ እስካሁን 70 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎችን አጥቅቷል፡፡ 35 ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች ሞትም ምክንያት ነው፡፡

ነጭ የደም ሴሎችን በማጥቃት የሰዎችን በሽታ የመከላከል አቅም በማዳከም ለተለየዩ በሽታዎች መዳረጉ በዚያ ዘመን ትልቅ እንቆቅልሽ ነበር፡፡ ቫይረሱን ከደም ውስጥ ማጥፋት የሚችል መድኃኒት ባይገኝም የፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት መገኘት ትልቅ እፎይታን ፈጥሯል፡፡

ይሁንና ይህንን ሳያገኙ ሕይወታቸው ያለፈ ብዙዎች መገለልና መድሎ ደርሶባቸዋል፡፡ የእያንዳንዱን ቤት አንኳኩቷል፡፡ ሕፃናትን ያለ ወላጅ አስቀርቷል፡፡ ወንድምና እህታቸውን ያጡም ብዙ ናቸው፡፡ ከኤችአይቪ ጋር የሚወለዱ ሕፃናትም እንደቅጠል ረግፈዋል፡፡ ቫይረሱ በደማቸው መኖሩ እንደተነገራቸው ራሳቸውን ያጠፉ ጥቂት አይደሉም፡፡ የሞት ፍርድ እንደተፈረደባቸው ሁሉ አንበላም አንጠጣም ብለው በከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ገብተው ሞታቸውን የሚጠባበቁም ነበሩ፡፡ ቤተሰብ አግልሏቸው ወደ ጎዳና የወጡም ያጋጥሙ ነበር፡፡

የተለያዩ ለጋሽ ድርጅቶች ትኩረት አድርገውበት በመሥራታቸው የነበረውን የተዛባ አመለካከት ከብዙ ጊዜ በኋላ በመጠኑም ቢሆን ለመቀየር ችለዋል፡፡ ሰዎችም ስለ ኤችአይቪ መተላለፊያ መንገዶች ተረድተው ራሳቸውን እንዲጠብቁ በቫይረሱ የተጠቁን እንዳያገሉ  ለማድረግ ተችሏል፡፡

የቡና ጠጡ ፕሮግራሞች፣ ኤችአይቪ ላይ አተኩረው የሚሠሩ የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ፕሮግራሞች ድራማዎች፣ ፊልሞች፣ መዝሙሮች በፀረ ኤድስ ዘመቻ ወቅት የኅብረተሰቡን ንቃት በመጨመር እያዝናኑ ማኅበረሰቡ ስለ ቫይረሱ መሠረታዊ መረጃ እንዲኖረው ጥቅም ላይ የዋሉ መሳሪያዎች ነበሩ፡፡ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትም የቫይረሱን ስርጭት በመቆጣጠር ረገድ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡

 ይህ ሥርጭቱን ከመቆጣጠር ባለፈ ስለ ኤችአይቪ የነበረው የግንዛቤ ችግር እንዲቀየርና ኤች አይቪም እንደማንኛውም በሽታ እንዲታይ አድርጓል፡፡ በ2030 ኤችአይቪን ከዓለም ላይ ለማጥፋት እቅድ ተይዞ እየተሰራ ያለውም በዚሁ መነሻ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሥርጭቱ በስፋት ይታይባቸው የነበሩ አገሮች ሥርጭቱን በመቀነስ ረገድ አበረታች ለውጥ ማሳየት ጀመሩ፡፡ ነገር ግን ይህንን ተከትሎ ኤችአይቪን ዋነኛ አጀንዳቸው አድርገው ይሠሩ የነበሩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ትኩረታቸውን ወደ ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች አደረጉ፡፡

ይህ ማህበረሰቡ ኤችአይቪ ቫይረስ የጠፋ ያህል ዝንጉ እንዲሆን አረንጓዴ መብራት የማሳየት ያህል መሆኑን የተረዱት ግን ቆይተው አሁን ነው፡፡ እ.አ.አ. በ1990ዎቹ አካባቢ 20 በመቶ የሚሆኑትነፍሰ ጡር እናቶች  የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ይገኝ ነበር፡፡ ይህ ቁጥር ወደ 12 በመቶ ዝቅ ብሎም ነበር፡፡ በ2000 ዓ.ም. አምስት በመቶ የሚሆኑ የአገሪቱ ወጣቶች የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው ውስጥ ይገኝ ነበር፡፡

በየጊዜው የተሠሩ የፀረ ኤድስ ዘመቻዎች በአሁኑ ወቅት  ያለው የኤችአይቪ ሥርጭት መጠን ወደ 1.2 በመቶ ዝቅ እንዲል አስችለዋል፡፡ ይህ አበረታች ለውጥ ቢሆንም አገሪቱ ከኤችአይቪ ወረርሽኝ ነፃ ሆናለች ለማለት ግን ገና ብዙ ይቀራል፡፡ አንድ በሽታ ወረርሽኝ አይደለም የሚባለው የሥርጭት መጠኑ ከአንድ በመቶ በታች ሲሆን ነውና፡፡ አገሪቱ እዚህ ላይ ለመድረስ ጥቂትማ ቢሆን ይቀራል፡፡ በቅርብ ዓመታት ውስጥ የሥርጭት መጠኑን ከአንድ በመቶ በታች ለማውረድና በ2030 ደግሞ ኤችአይቪን ለማጥፋት የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት በምታስብበት በአሁኑ ‹‹ወቅት ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ›› ዓይነት ከተያዘው የለውጥ መንገድ ወደኋላ የሚጎትቱ የሚመስሉ ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡

ረቡዕ ጥር 17 ቀን 2009 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል ተዘጋጅቶ በነበረው የአንድ ቀን ወርክሾፕ ላይ ከቀረቡ ጥናቶች መረዳት የሚቻለው ይህንኑ ነው፡፡ በትግራይ ክልል በመተግበር ላይ ባለው ካሳ የተሰኘ በኤች አይቪ ዙሪያ የሚሠራ ፐሮጀክት በክልሉ ያለውን የኤችአይቪ ቫይረስ ሥርጭትን በተመለከተ ያሉት ክፍተቶች ለይ ጥናት በማድረግ የባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውጤቱን ይፋ አድርጓል፡፡ በጥናቱ በአንዳንድ የክልሉ ክፍሎች የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ መጠን መኖሩንና የግንዛቤ ችግር መኖሩ ተጠቁሟል፡፡

 በዕለቱ ከተገኙት ባለሙያዎች መካከል የሕፃናት ሐኪም ስፔሻሊስትና በመ<span style=”font-size:12.0pt;mso-bidi-font-size:11.0pt;line-height:200%;font-family: &quot;Ge” ez-1=”” numbers”,”sans-serif”‘=””>Gለ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሐይደር ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ሎኮ አብርሃም አንዱ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ በክልሉ የሚገኙ ወጣቶች ስለ ኤችአይቪ ኤድስ ያላቸው ግንዛቤ አነስተኛ ነው፡፡ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ ሆነው የሚወለዱ ሕፃናትም አሉ፡፡ ነገሮች በዚህ መልኩ ከቀጠሉና ተገቢው ትኩረት ተደርጎ ካልተሠራ ወረርሽኙ ሊያገረሽ ይችላል፡፡

      በክልሉ ያለው አጠቃላይ የቫረሱ ሥርጭት 1.6 በመቶ ነው፡፡ ይሁንና ሥርጭቱ ከቦታ ቦታ ከገጠር ገጠር የተለያየ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተክላይ ወልደማርያም ይናገራሉ፡፡ በደቡብ ትግራይ አላማጣ፣ ራያና አዘቦ እንዲሁም ምዕራብ ትግራይና የክልሉ ዋና ከተማ መ<span style=”font-size: 12.0pt;mso-bidi-font-size:11.0pt;line-height:200%;font-family:&quot;Ge” ez-1=”” numbers”,”sans-serif”‘=””>Gለ ከፍተኛ የኤችአይቪ ሥርጭት የሚታይባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ ‹‹እኛም የተለየ ትኩረት አድርገን እየሠራን ያለነው በእነዚህ ቦታዎች ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ በትግራይ ብቻ የታየ አይደለም፡፡ በአገሪቱ በሚገኙ የተለያዩ ቦታዎችም ተማሳሳይ ሁኔታዎች ተስተውለዋል፡፡ በከተሞች ያለው የሥርጭት መጠን 4.2 በመቶ ሲሆን፣ በገጠር ያለው ደግሞ 0.6 በመቶ ነው፡፡ ንግድና ኢንዱስትሪ እንዲሁም የኮንስትራክሽን ሥራዎች በሚበዙባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ያለው የሥርጭት መጠን ከሌሎቹ አንፃር በጣም ከፍተኛ ሊባል የሚችል ነው፡፡

ለምሳሌ በጋምቤላ ክልል ያለው አጠቃላይ የሥርጭት መጠን አምስት በመቶ ነው፡፡ ነገር ግን በክልሉ በሚገኙ አንዳንድ ቦታዎች የኤችአይቪ ሥርጭት መጠን 23 በመቶ ደርሷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ያለው የኤችአይቪ ሥርጭት መጠን ከጋምቤላ ክልል በተቃራኒ ቀላል የሚባል 0.8 በመቶ ቢሆንም በክልሉ ውስጥ በሚገኘው ሻኪሶ ያለው የሥርጭት መጠን አሥር በመቶ ነው፡፡ በደቡብ ክልልም እንደዚሁ ተመሳሳይ የስርጭት መጠን እየተስተዋለ ነው፡፡

የሥርጭት መጠኑ ከቦታ ቦታ እንደሚለያይ ሁሉ በተለያዩ የኅብረተሰቡ ክፍሎች፣ በዕድሜ ክልልና ከፆታ አንፃር ይለያያል፡፡ 23 በመቶ የሚሆኑት ሴተኛ አዳሪዎች ከቫይረሱ ጋር አብረው ይኖራሉ፡፡ አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚሠሩ ሾፌሮሽ ደግሞ ከአራት በመቶ በላይ የሚሆኑት የቫይረሱ ተጠቂ ናቸው፡፡ 32 በመቶ የሚሆኑ አዲስ በቫይረሱ የሚያዙ የኅብረተሰቡ ክፍሎችም ከ15 እስከ 24 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ናቸው፡፡ በአገሪቱ በየዓመቱ አዲስ በቫይረሱ ከሚያዙ 21,000 ሰዎች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ 740,000 የሚሆኑ ከቫይረሱ ጋር ከሚኖሩ ሰዎች መካከል ተመርምረው ራሳቸውን ያወቁት 62 በመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ ፀረ ኤች አይቪ መድኃኒት እየወሰዱ የሚገኙት 53 በመቶ የሚሆኑ ናቸው፡፡

‹‹በ2020፣ 90 በመቶ የሚሆኑት የቫይረሱ ተጠቂዎች ራሳቸውን አውቀው መድኃኒት መውሰድ መጀመር አለባቸው የሚል ስትራቴጂክ ዕቅድ ይዘን እየሠራን ነው›› ያሉት በፌዴራል የኤችአይቪ መከላከልና መቆጣጠር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሻሎ ዳባ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ መድኃኒት ከመውሰድ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ ማግለልና መድሎ አሁንም ድረስ አልቀረም የሚሉት ኃላፊው ቫይረሱ በደማቸው ውስጥ የሚገኝ አንዳንድ ሰዎች ማግለልና መድልዎን ሽሽት ራቅ ያለ አካባቢ ካለ ሆስፒታል ሕክምናና መድኃኒት መከታተል እንደሚጀምሩ፣ ነገር ግን ብዙም ሳይገፉበት መንገዱ አድክሟቸው መድኃኒቱን ለማቋረጥ እንደሚገደዱ ተናግረዋል፡፡

አጋጣማው ቫይረሱ ከመድኃኒት ጋር እንዲለማመድ ያደርገዋል፡፡ በመሆኑም ሁለተኛ ደረጃ ፀረ ኤችአይቪ መድኃኒት እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ ይህኛው መድሀኒት  ግን ዋጋው ውድና ለአገሪቱም የማይመከር ነው ሲሉ ሰዎች ተከታትለው መድኃኒቱን መውሰድ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹ሰው በፊት ስለ ኤችአይቪ ሲሰማ ይደነግጥ ነበር፡፡ አሁን ማንም አይፈራም፡፡›› በማለት አስፈላጊው ትኩረት ሰጥቶ ካልተሠራ በ2030 የተቀመጠውን ግብ ማሳካት ቀርቶ ሊያገረሽ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ለአገሪቱ በዚህ መጠን ሥጋት የሆነው የኤችአይቪ ሥርጭት መታየት ዋና ምክንያትም ማኅበረሰቡ ስለ በሽታው ያለው ግንዛቤ በተለያዩ ምክንያቶች ማሽቆልቆሉ ነው፡፡

በቅርቡ የተሠራ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ስለ ኤችአይቪ በቂ ግንዛቤ ያላቸው ሰዎች መጠን ከዚህ ቀደም ካለው ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ነው፡፡ በጥናቱ መሠረት ስለ ኤችአይቪ ግንዛቤ ያላቸው ወንዶች 31 በመቶ ሴቶች ደግሞ 18 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡

በስህተትና በግንዛቤ ማነስ  ቫይረሱ ከአንዱ ወደ ሌላ ከሚተላለፍበት አጋጣሚ በተቃራኒው ሆነ ብለው ቫይረሱን የሚያስተላልፉ መኖርም ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ዱከም ከተማ ውስጥ ታይቶ የነበረውን ነገር ማንሳት ይቻላል፡፡ ከተማው ከባድ ተሽከርካሪዎች የሚተላለፉበትና አባዛኛዎቹ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ሾፌሮች የሚያርፉበት ነው፡፡ ሴተኛ አዳሪዎችም ይበዙበታል፡፡

እነዚህን የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች እንደ አይነተኛ ገበያ ቆጥረው በአካባቢው የከተሙ ሴተኛ አዳሪዎች በኑሮ አስገዳጅነት የተሰማሩበት ሥራ ኤችአይቪ እንዳያስከትልባቸው ለራሳቸው ይጠነቀቃሉ፡፡ ያለኮንዶም ግብረሥጋ ግንኙነት መፈጸም በህይወታቸው ላይ የመፍረድ ያህል መሆኑን በአካባቢው የሚገኙ የፀረ ኤድስ ክበባት የሚሠሩ ሰዎች አስተምረዋቸዋል፡፡ ለዚህም ደንበኛቸው ያለኮንዶም ግንኙነት ለማድረግ ቢጠይቃቸውም ምላሻቸው አይሆንም ነው፡፡

በዚህ መልኩ ጥንቃቄ በጎደለው ወሲብ ሊከሰት ከሚችል ችግር ራሳቸውን ቢጠብቁም አንዳንድ ሰዎች ባልጠበቁት መንገድ የተወሰኑትን ለመሸወድ ችለዋል፡፡ በከተማው ሁለት ዓይነት ኮንዶም ይሸጥ ነበር፡፡ አንደኛው መደበኛ የሆነውና በየፋርማሲው የሚገኘው ኮንዶም ሲሆን ሌላኛው ደግሞ  ‹‹የተሠራ›› ኮንዶሙ ስፐርም እንዲያፈስ ተደርጎ በማያስታውቅ መልኩ በመርፌ ተበሳስቶ አንዳንድ ባለሱቆችና ጀብሎዎች የሚሸጡት ነው፡፡

ይህ ከሁለት አመታት በፊት በከተማው ተሰምቶ የነበረና ሪፖርተርም በቦታው ተገኝቶ የዘገበው ነው፡፡ የተሠራ የሚባለውን ኮንዶም ተጠቅመው ቫይረሱን ለማስተላለፍ ሲሞክሩ የነበሩ ሰዎች እስኪነቃባቸው ድረስ ምን ያህል ሰው እንደተጠቃ ማን ያውቃል፡፡

እንዲህ ባሉ እኩይ ተግባራት የተሰማሩ የሚያደርሱት ጥቃት በሌላ መንገድ የሚታይ ሲሆን በግንዛቤ ምክንያት የሚፈጠሩትን አዳዲስ ኬዞች ለመቀነስ አቶ ሻሎ እንደቀድሞው የፀረ ኤድስ ዘመቻ ሊካሄድና የመከላከል ሥራ ሊሠራ እንደሚባ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ በፊት የመከላከል ሥራ ይሠራ የነበረው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይለግሱ በነበረው የገንዘብ ድጋፍ ነበር፡፡ ዋና ለጋሽ የነበረው ግሎባል ፈንድ ሲሆን 334 ሚሊዮን ዶላር ይለግስ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ከድርጅቱ የሚገኘው የገንዘብ ድጋፍ ወደ 194 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ማለቱን፣ ይህ ደግሞ ከመድኃኒት ግዢ ባለፈ የሚፈይደው እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሕዝቡ የእኛ ነው፡፡ ችግሩም የእኛ ነው፡፡ የውጭ ድጋፍ መጣም አልመጣም አገር ውስጥ ያለውን ኃይል ተጠቅመን መሥራት አለብን›› በማለት ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

 

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *