በማህበረሰባችን መካከል ወልደህ ሳም የሚባል የተለመደ ምርቃን ነበር፤ ከአንደበት የሚወጣ ቃል ደግሞ በረከትን ወይም መርገምን ሊያስከትል እንደሚችል ይገመታል፤ በምድራችን ውስጥ ልጆች በጤና ተወልደው እንዲያድጉ ወላጆች የልጆቻቸውን የጤና ስጋት ለመቀነስ ሲሉ ገና ከእርግዝና በፊት ጀምሮ ገድል ከማሳዘልና እትፍ እትፍ ከሚሉ ሰዎች እስከ የቡና ስኒ ገልባጭ መናፍስት ጠሪዎች ድረስ በልጁ የማደግና የወደፊት የሕይወት እጣፋንታ ላይ ትንቢት መሰል ሟርት እያውጁበት እንዲያድግ ይደረጋል፤ በዚህ ሁሉ ግን ሁላችንም ምንም ዓይነት የጤና ድጋፍ በሌለበትና የመናፍስት ጠሪዎች ቁጥር በርካታ በሆነባት ምድር ውስጥ ተወልደን ማደጋችን ገብቶን በማወቅ ባናከብረውም የፈጣሪ ጥበቃና ምህረት እንደሆነ አምናለሁ።

ከዚህ ችግር ስፋትና ጥልቀት የተነሳ በርካታ ልጆች ተወልደው የማደግ እድል ሳያገኙ ከእናታቸው ጋር ሕይወታቸውን ያጡ ብዙ ናቸው፤ ሆኖም ግን ይህ ሁሉ ስጋት ታልፎ ተወልዶ፣ አድጎና ተምሮ ሃገር የሚረከብ ትውልድ በዘመናት ሁሉ ታጥቶ አለመታወቁ ምድርን ሙሏትና ግዟት የሚለው መለኮታዊ ትእዛዝ እስከ ፍጻሜው ድረስ የማያቋርጥ ለመሆኑ ምልክት ነው፤ ጥያቄ የሚሆነው ግን የዘመኑ ባላደራ ትውልድ ለተገኘበት ማህበረሰብ የሚበጅ ሥራ እያበረከተ ነውን? ወይስ ወላጆቹን በማስመረር ባልተወለድክ ወይም የወላድ መካን እያስባለ ነው? መልሱን ለአንባቢ ኀሊና ልተወው።

ይህ ጥያቄ ወደ እኔ አእምሮ የመጣው በድንገት አይደለም፤ ሁላችንም የተገኘንበት ማህበረሰብ በኑሮው እየደረሰበት ያለው መከራ ሳያንሰው ሰሞኑን መንፈሳዊ አስተማሪ የሆነው መምህር ምህረትአብ አሰፋ በፌስ ቡክና በዩቲዩብ የለቀቀው የጦርነት አዋጅ ነው፤ በመልካም አስተዳደር እጦት ለዘመናት እየተሰቃየ ባለ ሕዝብ ላይ ሌላ የሃይማኖት ጦርነት! ያውም ያገር እንደራሴ ሆና በቆየችው በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተወልደው ባደጉና ለሕዝቡ የፍቅር ምሳሌ ሊሆኑ በሚችሉ አገልጋዮች መካከል ሊፈጸም የታሰበ የወንድማማቾች የጦርነት አዋጅ! (እባክዎ የሚከተለውን ሊንክ በማስተዋል ይመልከቱና በመጽሐፍ ቅዱስ ይመዝኑት)

ለዚህ ነው በአንድ እጅ የፍቅር ምንጭ የሆነውን ወንጌለ ክርስቶስን፣ በሌላው እጅ ደግሞ ወንድምን ለመግደል የሚያስችል መሳሪያ አንግቦ በወገኖች መካከል የጦርነትን አዋጅ ለሚጎስሙ ለእነ ምህረተአብ አሰፋና መሰሎቹ በአውደ ምህረቱ ላይ እንደፈለጉ መፋነን የፈቀደች እናት ቤተ ክርስቲያናችንን እራሷን በእጇ ላይ ባለው መጽሐፍ ቅዱስ መዝና ወደ ቀደመ ማንነቷ ትመለስ/ትታደስ በማለት የምንጮኸው ይላሉ የዚችው ቤተ ክርስቲያን ካህናት፤ እዚህ ላይ እውነቱን ለይቶ የራስ ለማድረግ ግን የሁላችን ሃላፊነት መሆኑንና ሁሉንም ቆም ብለን በማስተዋል መዝነን የሚበጀንን መያዝ እንጂ በሃይማኖትና በባንዲራ ስም ለሚደረግ ጮኸት ሁሉ ሳይገባን ማጨብጨ የሌለብን።

እስቲ ተመልከቱ! ፍቅርና ጥል፣ ሐጢአትና ጽድቅ፣ ክርስቶስና ዲያብሎስ፣ ሞትና ሕይወት፣ ሥጋና መንፈስ፣ ጦርነትና የሰላም ወንጌል መቼ  ነው አብረው የሚሄዱት? ምናልባት ለምህረተአብ አዲስ ግኝት ወይም መገለጥ መስሎት ይሆን? ግን እኮ ሰይጣንም የብርሃን መልአክ መስሎ አይደል የሚመጣው? ስለዚህ ሁሉን መፈተን አምልጦ ማስመለጥ ስለሚሆን እናንተ ከእውነት የተወለዳችሁ ወገኖች በሙሉ እባካችሁ! ይህ የጠመጠመና መስቀል የጨበጠ ሁሉ እውነተኛ የመንፈስ አባት የሚመስለው የዋህ ወገናችን የጮሌዎች መጫዎቻ ሲሆን እያየን ዝም አንበል? የማህበረ ቅዱሳንና የተሐድሶ ጉዳይ ወደ አደባባይ ወጥቶና ሕዝብ በሙሉ አውቆት የራሱን ውሳኔ እንዲሰጥበት መድረኮች ይዘጋጁና ውይይት ይደረግበት፤ በውጭም በአገር ቤትም ያላችሁ የቤተ ክርስቲያኒቷ መሪ የሆናችሁ ጳጳሳትም ደግሞ እባካችሁ ዝምታውን ሰብራችሁ በመውጣት ይህ እግዚአብሔርን ፈልጎ ለማግኘ ከደብር ደብር በዚህ ጡንቸኛ ማህበር ስም የሚንከራተተው ምእመን እንዲያርፍና ከአሳራፊው ጋር እንዲገናኝ ሃላፊነታችሁን ተወጡ፤ እረፉ እኔም አምላክ እንደሆንኩ እወቁ ያለው ጌታ ቃሉን እንደ ሰው ለውጦ ከገዳም ገዳም ባዝኑ አላለምና።

በፖለቲካው መስክ የሚተራመሰው የህብረተሰብ ክፍል በዘር በሽታ ተልክፎ ለፖለቲካው ፍጆታ ሲል በዚህ አብሮ በኖረ ሕዝብ መካከል ይህን የዘር በሽታ መርዝ በማሰራጨቱ ምክንያት ወገናችን በሙሉ በማያባራ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገብቶ እየተሰቃየ ባለበት በዚህ ሁኔታ ላይ ይህን የመሰለ የሃይማኖት ጦርነት ማወጁ ለማን ጥቅም ነው? በእውነትስ የኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤ/ክርስቲያን እውነተኛ ተቆርቋሪና ወዳጅ ማነው? ወዘተ ለመሳሰሉት ጥያቄዎች በመረጃ የተደገፈ መልስ ሁላችንም በመስጠትና ሚናችንን በመለየት ለሃገርና ለወገን ዘለቄታ ጥቅም በእውነት ለእውነት መነሳት አለብን እላለሁ፤ ሁላችንንም ሊበላ ያለ እሳት በዚህ መልኩ በየዋሁ ወገናችን መካከል ያውም በመንፈሳዊ አስተማሪዎች ነን ባዮች ሲጫር እያየን ቸል ልንለው አይገባምና በአለንበት አካባቢ ጉዳዩን አንስተን በመወያየት አቋም መውሰድ ይገባናል እላለሁ። እስቲ በዚህ ጉዳይ ላይ አቋም ከመውሰዳችን በፊት ማን? ማነው? ምንስ እየሠራ ነው? የሚሉትን ዋና ዋና ጥያቄዎች ለመመለስ የምህረትአብ አሰፋን ቡድን አስተምህሮና የተከሳሹን የተሃድሶን ወገን አስተምህሮ የሁለቱም መንፈሳዊ የክርስትና ትምህርት መሰረት ዋና መመሪያ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ሚዛንነት አብረን እንየው፡

1/ ጦርነትን ያወጀው የምህረትአብና የመሰል ጓደኞቹ አስተምህሮ፡

 • እኛ ሃይማኖታችን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እንጂ ክርስቲያን አይደለንም፣ (ዩቲዩብ ላይ የምህረተአብ ትምህርትን ያዳምጡ)
 • የአዳም ሃይማኖት ኦርቶዶክስ ነበር ይላሉ፣
 • የአባታችን የአዳም አባት አፈር ስለሆነ አፈር አያታችን ነው፣
 • ስለዚህ ኦርቶዶክስ ቀጥተኛና እውነተኛ ሃይማኖት ስለሆነች ተሃድሶ ጨርሶ አያስፈልጋትም (ቃሉ ብቻ ይሰበክ=ተሃድሶ)
 • ልብሳችንን ለብሰው ተሃድሶ ብለው የተነሱት የአባቶቻችንን ሃይማኖት ለማጥፋት የተነሱ ናቸው ይላሉ (ቤተ ክርስቲያኒቱ ወልዳና አስተምራ ያሳደገችን ልጆቿ ስለሆን እንደ ፊተኛ ወገኖቻችን አኩርፈን ወይም እነ ምህረተአብ ባርከው ባልተረዳው ወገናችን እጅ የሚወርድብንን የድንጋይ በረዶ ፈርተን በመውጣት ወደ ሌላ ቤተ እምነት በመኮብለል እናት ቤተ ክርስቲያናችንን የወላድ መካን አናደርጋትምና የሚወጣው ይውጣ እንጂ እኛ አንወጣም፤ ልብሱና ቆቡም ቢሆን የምንወዳት እናታችን ያለበሰችን እንጂ እነምህረተአ ሲፈልጉ የሚቸሩን ካልፈለጉ ደግሞ የሚገፉን እርጥባን አይደለም ይላሉ ተሃድሶዎች) ወዘተ

2/ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ማህበር፡

 • ቤተ ክርስቲያናችን ከተመሰረተችበት የወንጌል ተልእኮ ወጥታለችና ወደ ቀደመ የወንጌል ቃል ትመለስ ይላሉ
 • የተሐድሶ ጥያቄ የቀደሙ የቤተ ክርስቲያኒቷ ሊቃውንትና መነኮሳት የጀመሩትና የሞቱለት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄ እንጂ ዛሬ የተጀመረ ጉዳይ አለመሆኑን ይናገራሉ
 • ሕዝባችን ሊማርና ሊሰበከው የሚገባው ሕይወት፣ ፍቅርና ሰላም ሰጪ የሆነው የክርስቶስ ወንጌል ብቻ እንጂ መርገምን የሚያስከትል ልዩ ወንጌል መሆን የለበትም በማለት ይሟገታሉ፣
 • ቤተ ክስቲያኒቷ ከመናፍስት ጠሪዎችና ከልዩ ወንጌል ሰባኪዎች በቃሉ ብርሃን ትጽዳ፣
 • ቤተ ክርስቲያኒቷ ንጹህ ወንጌል ባለመስበኳ ምክንያት የቃሉ ራሃብተኛ የሆኑት በርካታ ልጆቿ ወደ ሌላ ቤተ እምነት በመኮብለል የወላድ መካን የሆነችበትን ችግር የተመለከተ አምላካችን በመንፈሱ ያመጣውንና በራሷ ልጆች ትከሻ ላይ የጣለውን ሰማያዊ አደራ እስከ ነፍስ ህቅታ ድረስ ዋጋ በመክፈል ቤ/ክርስቲያናችን የሚገሰጸውን እየገሰጸች የሚባረከውን ደግሞ እየባረከች በምድራችን ላይ የጽድቅ ተጽእኖ የምታመጣ ታማኝ የሰማይና ያገር እንደራሴ እንድትሆን ሳንታክት እንሠራለን ይላሉ፣
 • በምድሪቱ ውስጥ ያለው ሁለንተናዊ የሕይወት ችግራችን ምንጩ መንፈሳዊ ሕይወታችን ከእግዚአብሔር ህያው ቃል በመራቃችን ስለሆነ ክርስቲያናዊ ታሪካችን ከማንም ሃገርና ሕዝብ በፊት እጃችን በገባው መጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ይመዘን ይላሉ፣
 • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እውነተኛ ወዳጅና ጠላት ማን እንደሆነ በሲኖዶሱ፣ በሊቃውንት ጉባኤውና በምእመኑ ፊት በግልጽነት ታውቆ ሁሉም አቋም እንዲኖረው ለማድረግ የሚያስችል መድረክ እንዲዘጋጅ ይፈልጋሉ፣
 • ባለው ሕግ መሰረት ፈቃድ አግኝተን ታሪክ የጣለብንን አደራ አሳድጎ ላስተማረን ወገናችን ለማበርከት በግልጽ በመንቀሳቀስ ላይ ሳለን የሥጋ ጉልበትና አቅም ያለው ሁሉ በተገኘው አጋጣሚ የበሬ ወለደ መርዝ በየዋህ ወገናችን መካከል በመርጨት ለጦርነት የማነሳሳቱን ኢሕጋዊ ሥራ መንግሥት ተከታትሎ ሕጋዊ እርምጃ ካልወሰደ አደጋው ለሁሉም ስለሚሆን የሰላም ሰዎች ሁሉ ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጡት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በአጽንዖት ያሳስባል!!! (የሚከተለውን ሊንክ ለመረጃ ይመልከቱ፡)

ጥብቅ ማሳሰቢያ

ይህን ጽሑፍ የምታነቡ ወገኖች እባካችሁ ለዚህ እውነተኛ መነፈሳዊ መሪና አስተማሪ ለሌለውና በአስመሳዮች ትክሻው ለጎበጠው ሕዝባችን መትረፍና ማረፍ ለእውነት በእውነት በዚህ ጉዳይ ላይ ላልሰማ እያሰማን በጋራ እንነሳ???

የእውነት አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ሃገራችንን/ሕዝባችንን ይጠብቅ

እውነቱ ይነገር:  eunethiwot@gmail.com

ከዝግጅት ክፍሉ፣ ይህ ጽሁፍ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለውና የግለሰብን ስም የሚጠቅስ በመሆኑ ጎልጉል የየትኛውንም ወገን የሚደግፍ ወይም የሚቃወም አለመሆኑ እንዲታወቅ ይሁን። በጠየቅነው መሠረት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ይህንን ጽሁፋቸውን ለመምህር ምህረተአብ በፌስቡክ ገጻቸው በኩል መላካቸውን ለጎልጉል አረጋግጠዋል። መምህር ምህረተአብ ለዚህ ጽሁፍ ምላሽ ካላቸው የምናስተናግድ መሆኑን እንገልጻለን።

goolgule

Share and Enjoy !

0Shares
0

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *