“በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል” ይባላል፡፡ “ቅርብ ባለ ጠበል ልጥ ይነከርበታል” የሚለውም ተመሳሳይ ሀሳብን ለመግለጽ የሚነገር ነው፡፡ አንድ ነገር የመኖሩን ጥቅም የምናውቀው ያን ነገር ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ስናጣው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ነገር ብናነሣ በዘመናችን በካህናት ጉዳይ እየሆነ ያለው ነገርም ተመሳሳይ ነው፡፡ አሁን ችግሩ አይሰማንም፤ ቀደም ሲል በነበሩት ጉባኤ ቤቶች የተማሩት ካህናት እያገለገሉን ነው፤ ብንወልድ ክርስትና ያነሡልናል፤ ብንሞት ይፈቱናል፡፡ ብንበድል ይናዝዙናል፤ ቀድሰውም ያቆርቡናል፡፡ እነርሱ የወጡባቸው ትምህርት ቤቶች ግን ተማሪ በማጣት ድርቅ ተመትተዋል፡፡ በሀገራችን የተከሰተው ድርቅ አዝርእትን እንዳይበቅሉና ፍሬ እንዳይሰጡ ብቻ አላደረገም፡፡ ድርቁ ትምህርት ቤቶችም ተማሪ እንዳያወጡ እያደረገ ነው፡፡ ነገሮች እንዲህ ከቀጠሉ ደግሞ አሁን ያለውን አገልግሎት ወደፊት የምናገኝ አይመስልም፤ ተተኪ እያፈራን አይደለምና፡፡

የተማሩ ካህናትንና መነኮሳትን በውጭ በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ ሰዎች እየወሰዷቸው ነው፡፡ ምእመናንም ልጆቻቸውን መንፈሳዊ ትምህርት እያስተማሩ አይደለም፡፡ ነገ ቀድሰው የሚያቆርቡ፣ ናዘው ኃጢአት የሚያስተሰርዩ የዛሬ የአብነት ተማሪዎች መሆናቸውን ዘንግተናል፡፡ ዛሬ የሚማር ከሌለ ነገ ዲያቆን ሊኖር አይችልም፡፡ ነገ ዲያቆን የለም ማለትም ከነገ ወዲያ ቄስ የለም ማለት ነው፡፡ ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ በየቤቱ የካህን ሚስት የሚሆኑ ሴቶችም እየተዘጋጁ አይደለም፡፡ ካህንንም ሆነ የካህንን ሚስት በሃይማኖት ቢሉ በምግባር ቀርጾ የሚያወጣ ማኅበረ ሰብ እየጠፋ ነው፡፡ “ቤተሰብ ትንሿ ቤተ ክርስቲያን ናት” የሚለው አስተሳሰብ ከሁላችንም ከተዘነጋ ዘመን የለውም፡፡

አንድ ዲያቆን ቄስ ለመሆን በሕግ መወሰን ወይም መመንኮስ ያስፈልገዋል፡፡ በሕግ ለመወሰን ሕጉን የምትጠብቅለት፣ ሕይወቱን የምታጸናለት መንፈሳዊት ሴት ታስፈልገዋለች፡፡ አንድ ደቀ መዝሙር ከካህናት ጋር ወደምእመናን ቤት ሲሄድ ወይም በዘመናዊ ትምህርት ቤት የሚያያቸው የክፍል ጓደኞቹ አስተዳደግ ግን ቄስ ለመሆን የሚያስመኘው አይሆንም፡፡ እንዳይመነኩስ ፆሩን ይፈራል፤ እኛም ደግሞ ለመነኮሳት የሚሆን የአኗኗር ዘይቤ የለንም፡፡ እንኳን ለማስተማር የመጣ መነኩሴ አብሮን ሲጸይና ሲያስተምር ሊውልና ሊያድር ወደገዳማት ስንሄድ እንኳ ሕይወቱ አጓጉቶን በዚያው የምንቀር ሳንሆን አባቶቻችንን ወደተድላ ዓለም የሚያመጣ አካሄድን የመረጥን ያመስልብናል፡፡ ወደገዳማት ስንሄድ የምንወስደው ምግብ የቀን መንገድ ርቆ የሚሸት፣ የምንወስደው መተኛ ምንጣፍ ለእንቅልፍ የሚመች፣ የምንቀባው ሽቱ ፍትወት የሚቀሰቅስ፣ ወዘተ ነው፡፡ ከዚያም በላይ ለአባቶቻችን የምናወጋቸው ስለኃጢአታችን ሳይሆን ስለገንዘባችንና ሀብታችን ይሆናል፡፡ በእኛ ምክንያት ከገዳም የወጡ አባቶቻችንን ደግሞ ዞረን እናማቸዋለን፡፡

Related stories   የመረጃ መንታፊዎች ዋትሳፕን እንደ ጥቃት ማድረሻ መሳሪያ እየተጠቀሙ መሆኑ ተገለጸ

ስለዚህም በዘመናችን አብዛኛውን ጊዜ ዲያቆን መመንኮስ አይፈልግም፡፡ የማይመነኩሰው ደግሞ ምንኩስናውን ስለጠላው ወይም ስለናቀው አይደለም፡፡ የማይመነኩሰው ዓለማዊ አስተሳሰባችን ወደሚኖርበት ገዳም ድረስ ሄዶ ስለሚረብሸውም ነው፡፡ በከተማ ያሉ ገዳሞቻችን ስማቸው እንጂ ግብራቸው የገዳማውያንን ስለማይመስል መንኩሶ በከተማ ከሚቀመጥ በሕግ ተወስኖ ቢያገለግል ይመርጣል፡፡ ይህም ግን ባለንበት ዘመን አስቸጋሪ እየሆነ ነው፡፡ ከምንኩስና በተለየ ባለሕግ ካህን ለመሆን ሕግን የምታጸና፣ መንፈሳዊነቷ የተረጋገጠ ረዳት ሴት ታስፈልገዋለችና፡፡ እርሷን ለማግኘትም እንዲሁ ፍለጋው መከራ ነው፡፡

ፍለጋውን አድካሚ የሚያደርጉትም ደግሞ “ቃና”ን የመሳሰሉ የውጭ ፊልም የሞላባቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ በየፌስ ቡኩ የሚተላለፈው የወሲብ ፊልምና ፋሽንማ ምኑ ተነሥቶ! ሴቶቻችን ሁልጊዜም ፊልም ላይ ናቸው፤ ሁል ጊዜ ድራማ ላይ ናቸው፡፡ ሴቶችን አልን እንጂ ወንዶችም እንዲሁ ናቸው፤ እነሱም ፊልምና ኳስ ላይ ናቸው፡፡ ዛሬ ዛሬ የኳስ ዜናነና ፊልም እንዳያመልጣቸው ተከናንበው የሚያስቀድሱ ወንዶች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ሲከናነቡ በጆሯቸው የሰኩት ማዳመጫ ከመታየት ይሸፈናልና፡፡ ለዜና የከፈቱት ጆሯቸውም “ቅዱስ …” ሲባል ሳይሰማ ይቀራል፡፡

በዚህ ጽሑፌ ማተኮር የፈለግሁትና ዘመናችንን ለካህን ያልተመቸ የሚያደርገው የዓለማዊ ነገሮች ማማለል ብቻ አይደለም፡፡ ወይም ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችን የገንዘብ ሳይሆን የአስተዳደር ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ወደፊት ዲያቆንም ሆነ ቄስ እንዳይኖረን የሚደርገውና ጉባኤ ቤቶቻችንን ባዶ እያስቀረ ያለው በሕግ ተወስኖ ለመኖር ጠንካራ አጋር ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑም ነው፡፡ ዛሬ በጉባኤ ቤት ያለ ተማሪ ትምህርቱን ሲያጠናቅቅ በቅስና ወይም በምንኩስና ሊያገለግል ነው፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ ዘመናዊ ትምህርት የተማሩ የምእመናን ልጆች በሚያሳዩት የሚያባብል ዓለማዊ አኗኗር መንፈሱ ይማረካል፡፡ ብዙዎቻችን የቆሎ ተማሪዎች ባሉበት እንዲጸኑ የምናደርግ ሳንሆን እንደኋላ ቀር እየቆጠርን ከበአታቸው የምናስኮበልል ነን፡፡

Related stories   እኛ የምንመርጠው አባትና አያቶቻችን የመረጡትን ነው።

ይህን ሁሉ ተቋቁመው ተምረው በሕግ መወሰን ለሚፈልጉት ግን ሚስት የማግኘት ታላቅ ፈተና ይገጥማቸዋል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በየደጃችን የተከፈቱ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ናቸው ብየ አምናለሁ፡፡ መብራት ጠፍቶ ቴሌቪዥን ሳይኖር የምናወራው ወሬም እንዲሁ ቴሌቪዥናዊ ነው፡፡ በየስልካችን የተጫኑት ፕሮግራሞችም የቅዳሴ ተሰጥዎ፣ ዜማና መዝሙራት ሳይሆኑ፣ ፊልሞችና ዘፈኖች መሆናቸውን ስልኮቻችን ይመሰክራሉ፡፡ ይህ ደግሞ የካህናት ሚስቶች ይሆኑ ዘንድ ያላቸው እኅቶቻችንንም ይጨምራል፡፡ እግዚአብሔር እመቤታችንን ለተዋሕዶ ሲመርጥ “ሰሜንና ደቡቡን፣ ምዕራብና ምሥራቁን አየ፤ ፈለገ፤ አሻተተ፤ ሻ፤ መረመረ፤ እንደእርሷ ያለ አላገኘም” ያለው በዓለማዊ ግብር ያልተማረከች ስለሆነች ነው፡፡ (ቅዳሴ ማርም)፡፡ ዛሬስ?

የካህን ሚስት አለባበስ፣ አነጋገር፣ አመጋገብ፣ ሰላምታ አሰጣጥ፣ አረማመድ፣ አተያይ፣ ወዘተ ከሌሎች የተለየ መሆን አለበት፡፡ እንዲህ እንዲሆን ደግሞ ምእመናን ትልቁን ድርሻ መውሰድ ይገባቸው ነበር፡፡ በግድየለሽ ማኅበረ ሰብ የሚያድጉ ልጆች ግድ የለሽ እንደማይሆኑ መጠበቅ ሞኝነት ነው፡፡ ሚስት የሚሆኑ ልጆችን በሥርዓት ሳያሳድጉ ካህን ጠፋ፣ ቀዳሽ አነሰ ብሎ ማማረር ሞኝነት ነው፡፡ ወደፊት ማነስ ሳይሆን ከነአካቴውም ይጠፋል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት እንደዋዛ ፈዛዛ እያዩ ልጅን ክርስትና የሚያነሣ ሲጠፋ መጮህ ዋጋ የለውም፡፡ ዲቁናና ቅስና የሚሾም ጳጳስ ሲጠፋ ለምን እያሉ መደንፋት ዋጋ የለውም፡፡ ስንሞት የሚፈቱን፣ ስንበድል የሚናዝዙን፣ ስንወልድ ክርስትና የሚያነሡልን፣ ወዘተ ዛሬ በቻልነው አጋጣሚ እያገዝን የምናስተምራቸው የዛሬ የአብነት ተማሪዎች ናቸው፡፡

Related stories   እኛ የምንመርጠው አባትና አያቶቻችን የመረጡትን ነው።

አንዳንድ ጊዜም ማኅበረ ቅዱሳን በየአጥቢያዎች ባሉ ግቢ ጉባኤያት እያስተማረ ዲቁና የሚያሰጣቸውን ተማሪዎች ተቀብሎ በመንከባከብና ወደቅስና ደረጃ እንዲደርሱ እንደመደገፍ በአንዳንድ ቦታ የሚሰማው ንቀት አጋዥን አለማወቅ ይመስለኛል፡፡ “በአብነት ትምህርት እድሜ ልኬን ኖሬያለሁ፤ በቅኔ ተራቅቄያለሁ” እያለ በዓለማዊ ሥራ ምክንያት ዲቁናውንም ሆነ ቅስናውን ችላ ካለ አገልጋይ ይልቅ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ወጣቶች ተቀብላ ብትንከባከባቸው ለቤተ ክርስቲያን ተስፋ ለምእመናንም ደገፋ ይሆናሉ፡፡ የካህናት ሚስቶችን ለማሠልጠንም እንዲህ ያሉ ማኅበራት የማይተካ ሚና ያላቸው ይመስለኛል፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ብዙውን ጊዜ በሌሎች አገልግሎት ደስተኞች አይደለንም፡፡ ጳጳሱን እንተቻለን፤ ጳጳሱን የሚደግፍ ሀሳብ ግን የለንም፡፡ ቄሱን እናማለን፤ ቄሱን ስንደግፍ ግን አንታይም፡፡ በመነኮሳት ምግባር መጥፋት እንማረራለን፤ ለመነኮሳት አኗኗር የሚመች አካባቢ ግን የለንም፡፡ ካህኑን እስኪሰክር አጠጥተን በመስከሩ የምንስቅ እኛው ነን፡፡ ዋዛ ፈዛዛ ተጨዋውተን ተራ ነገር እናናግራቸውና መልሰን እንቀልድባቸዋለን፡፡ እናስገርማለን’ኮ! ቀድሶ የሚያቆርበን ቄስ ትዳሩ ሲፈርስ ምንም እንደሚጎድልብን አናስብም፤ በትዳሯ ያልጸናችው ሴት እኛ ቤተሰብም ጎረቤትም ሆነን ያሳደግናት ልጅ እንደሆነች እንዘነጋለን፡፡ በአጠቃላይ የሌሎች ጥፋት እንጂ የእኛ ንዝህላልነት አይታየንም፡፡ ለካህን ሚስት ፍለጋ የሁላችንም ትብብር አስፈላጊ ነው፡፡ ሴቶችን ማስተማር፣ የሴቶችን መብት ማስጠበቅ፣ ስለሴቶች እኩልነት መትጋትም የካህናት ሚስቶች ይሆኑ ዘንድ በጭምትነት እንዲያድጉ ማድረግ ነው፡፡

እንዲህ ሲሆን ሀገራችን መልካም ዜጋ ይኖራታል፡፡ እንዲህ ሲሆን ሀገራችን ተተኪ ታገኛለች፡፡ የካህናት ሚስቶች ሲበዙ ልጆች በሥርዓት ያድጋሉ፤ ሥጋዊም ሆነ መንፈሳዊ ልማትም ይፋጠናል፡፡ ታዲያ ለምን መመሪያችንን “ሴትን የካህን ሚስት እንድትሆን ማስተማር ማኅበረሰብን ማስተማር ነው!” የሚል አናደርገውም?

ደግ ደጉን ያስመልክተን፤ አሜን!
የካቲት 10/2009 ዓ.ም

Minwagaw Temesgen FB.

Share and Enjoy !

Shares

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *